0

ከ192 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት መንገድ በከፊል ሊፈርስ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ምክንያት ከዚህ ቀደም ከፈረሱት ሁለት አዳዲስ መንገዶች በተጨማሪ፣ ከ192 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ከሾላ ገበያ ለም ሆቴልን የሚሻገረው አዲስ መንገድ በከፊል ሊፈርስ ነው፡፡

ለቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ ግንባታ ከዚህ ቀደም እንዲፈርሱ የተደረጉት ሁለቱ አዳዲስ መንገዶች፣ ከመስቀል አደባባይ ቃሊቲ የሚዘልቀው መንገድ የመሀል ክፍልና ከደሴ ሆቴል ወደ ፑሽኪን አደባባይ  የተዘረጋው አዲስ ከፊል የአስፓልት መንገድ ናቸው፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከ192 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጐበት ከሾላ ገበያ በለም ሆቴል እስከ አንበሳ ጋራዥ የተገነባው መንገድ የተወሰነ ክፍሉ በቅርቡ ይፈርሳል፡፡

ከ20 ዓመታት በላይ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የተገነባውና በ2002 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ መንገድ በከፊል እንዲፈርስ የተወሰነው፣ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ለሚዘረጋው የባቡር መስመር ለም ሆቴል አካባቢ ሐዲዱን ለሚሻገሩ ተሽከርካሪዎች ማስተላለፊያ መንገድ ለመገንባት ነው፡፡

ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚዘረጋው የባቡር መስመር ላይ ይሠራሉ ከተባሉት የተሽከርካሪ ማስተላለፊያ መንገዶች ውስጥ አንዱ የሆነውና ለም ሆቴል አካባቢ ለሚገነባው ተላላፊ መንገድ ተብሎ የሚፈርሰው የአስፓልት መንገድ፣ አንድ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝመት እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

ይህም የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ካደረጋቸውና ከባቡር መስመሩ ግንባታ ጋር ተያይዞ ያፈረሳቸውንና የሚያፈርሳቸውን አዳዲስ መንገዶች ቁጥር ሦስት አድርሶታል፡፡ ለሦስቱ መንገዶች ግንባታ በአጠቃላይ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ አዳዲስ መንገዶች በተጨማሪ ከባቡር መስመሩ ጐን ለጐን ከአያት አካባቢ ተነስቶ እስከ ኮኮ ኮላ ፋብሪካ (ጦር ኃይሎች) ድረስ ያለው መንገድም ሙሉ ለሙሉ ፈርሶ እንደ አዲስ የሚገነባ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የከተማውን ነዋሪዎች አስደምሞ የነበረው ከመስቀል አደባባይ ቃሊቲ የሚዘልቀው የመሀል የመንገድ ክፍል ለዚሁ የባቡር መስመር ግንባታ ተብሎ መፍረሱ የሚታወስ ሲሆን፣ የመንገድ ፕሮጀክቱ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ነበር፡፡

በተመሳሳይም ከልደታ አካባቢ ከደሴ ሆቴል ወደ ፑሽኪን አደባባይ የተሠራውና ለባቡሩ መስመር ግንባታ ተብሎ እንዲፈረስ የተደረገው አዲስ መንገድ ከ400 ሜትር በላይ ርዝመት አለው፡፡ ለአገልግሎት ክፍት ከሆነ ገና ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው ይህ መንገድ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ መፍጀቱ ይታወሳል፡፡

ከእነዚህ መንገዶች መፍረስ ጋር ተያይዞ ለመንገዶች ግንባታ ከዚህ ቀደም የተወሰነ ይዞታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች በድጋሚ እንዲፈርስባቸው መደረጉ ታውቋል፡፡ ይህም ድርጊት ከነዋሪዎች ትችት እያስነሳ ይገኛል፡፡ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች ከነዋሪዎቹ የሚቀርበው ጥያቄ ትክክል ቢሆንም፣ ግንባታዎቹ የፈረሱት አስገዳጅ ሁኔታ በመፈጠሩ ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ መንገዶች የባቡር መስመሩ የሚያልፍባቸው መሆኑ ከታወቀ ለምን ይህንን ያህል ገንዘብ ቀድሞ ማውጣት አስፈለገ የሚለው ጥያቄም በተደጋጋሚ ተነስቷል፡፡

በባለሥልጣኑ የመንገድ ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ዋና የሥራ ሒደት መሪ ኢንጂነር ሙሉጌታ አብርሃም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለባቡር መስመሩ ግንባታ ሲባል የፈረሱትና በቅርቡም ይፈርሳሉ የተባሉት መንገዶች ባልተጠበቀው የባቡር ፕሮጀክት ምክንያት ነው፡፡

ከመስቀል አደባባይ ወደ ቃሊቲ የሚዘልቀው የመሀል መንገድ፣ በልደታና በለም ሆቴል አካባቢ የተገነቡ አዳዲስ መንገዶች አገልግሎት በጀመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍረሳቸው ተጠያቂው ማነው? የሚል ጥያቄም አስነስቷል፡፡

ኢንጂነር ሙሉጌታ ግን ለመንገዶቹ መፍረስ ተጠያቂው  ማነው ለሚለው ጥያቄ መልሱ አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹መንገዶቹ ገና በአዲስነታቸው የመፍረሳቸው ዋና ምክንያት ልማቱ ከምንጠብቀው ጊዜ በላይ ፈጥኖ የመጣ በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

በባለሥልጣኑ ዘንድ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቱ በቅርብ ጊዜ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ እንዳልታሰበ የጠቆሙት ኢንጂነር ሙሉጌታ፣ እስከ 20 ዓመት ድረስ የባቡር አገልግሎት ይጀመራል ተብሎ እንዳልታሰበም አስረድተዋል፡፡

ወደፊት የባቡር አገልግሎት እንደሚጀመር ታሳቢ በማድረግ ግን ለዚሁ አገልግሎት ሊውል የሚችል ቦታ እንዲተው የተደረገበት አሠራር ባለሥልጣኑ ሲከተል እንደነበረ አስረድተው፣ በምሳሌነት ከመስቀል አደባባይ ቃሊቲ በተዘረጋው መንገድ አካፋይ ላይ የተተወውንና አሁን የፈረሰውን መንገድ አውስተዋል፡፡

‹‹ለዚህም ነው ከቃሊቲ መስቀል አደባባይ የተገነባው መንገድ ላይ የባቡር መስመሩ ዝርጋታ እስኪጀመር በመንገዱ መሀል የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት እንዲሰጥ ተብሎ መንገዱ የተሠራው፤›› ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በፌዴራል መንግሥት ጥረት የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ ከተጠበቀው በፊት ማስጀመር በመቻሉ መንገዱ አዲስም ቢሆን እንዲፈርስ ተደርጓል ብለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ያልታሰቡ ለውጦች ሲመጡ ደግሞ አዲስም ቢሆኑ የተለያዩ ግንባታዎችን ማፍረስ የግድ ስለሚል ይኼው ታሳቢ ተደርጐ የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ወደዚህ ውሳኔ ሲገባ ሁለት ምርጫዎች እንደነበሩ የሚያስታውሱት ኢንጅነር ሙሉጌታ፣ አንደኛው ግንባታዎቹ አይፈርሱም ብሎ 20 ዓመት መጠበቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው የባቡር መስመሩን በቶሎ በማስጀመር ግንባታዎቹን ማፋጠን ነበር፡፡ የተመረጠውም የቱንም ያህል ወጪ የወጣባቸው ቢሆኑ ግንባታዎቹን አፍርሶ የበለጠ ጠቃሚ የሚሆነውን የባቡር መስመር ግንባታ ማስቀጠል የሚለው ተደግፏል ብለዋል፡፡ ይህ ዕርምጃ ሁሉንም የሚያስማማ መሆኑን የገለጹት ኢንጅነር ሙሉጌታ፣ ወደፊትም እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

http://www.ethiopianreporter.com

Filed in: Amharic News, News

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.