1

የአገርን ዉጥረት በአገር መፍታት – ዶር ተስፋዬ ደምመላሽ

Tesfaye Demmelash

ተለዋዋጭ ሁኔታዎችንና ፈታኝ ችግሮችን ተቋቁመዉ ማንነታቸዉን፣ ቀጣይነታቸዉን፣ ማረጋገጥ የማይሳናቸዉ ጥልቅ የታሪክ ሥር ያላቸዉ አገሮች የታደሉ ናቸዉ። ዛሬ በዉጥረት የተያዘችዉ ኢትዮጵያ ከነዚህ እድላማ አገሮች አንዷ ናት። ተብትቦ የያዛትን የጭቆና ሥርዓት ሰባብራ ራሷን ነፃ ማዉጣት የሚያስችላት፣ የለዉጥና እድገት እምቅ ችሎታ ያላነሰዉ፣ ጽኑ ብሔራዊ ህልዉና አላት። ኢትዮጵያ የማህበረሰብ፣ የባህል፣ የቋንቋና የእምነት ብዙሃንነትን ያካተተች ብትሆንም ህልዉናዋን የተጠናወቱት የዛሬዎቹ ሞገደኛ ገዢዎቿ እንደሚያዩዋት “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” ጥርቅም ሳትሆን የተዋለደና የተሳሰረ አንድ ሕዝብ ተደጋግፎና ተከባብሮ በሰላም የሚኖርባትአንድ አገር ናት።

ይህን እዉነታ በእምነትም በተግባርም በመላ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ማረጋገጥ ከገዢዉ “የትግሬ ህዝብ ነፃ አዉጪ” ከተባለ ቡድን በስተቀር ለማንም ከማይበጅ አገር ከፋፋይ የአምባገነን አገዛዝ ለመላቀቅና ብሔራዊ ህልዉናችንን ለማደስ እኛ ነገደ ብዙ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መዉሰድ ያለብን ወሳኝ እርምጃ ነዉ። ዘረኛ “ነፃ አዉጪ” የአገዛዝም ሆነ የተቃዉሞ ፖለቲካ ጐዳና ለጊዜዉ ጠባብ አራማጆቹን የሚጠቅም ቢሆንም ለዘለቄታዉ የትም የማያስኬድ፣ መዉጫ የሌለዉና መዳረሻዉ ፍሬ ቢስ መንገድ እንደሆነ፣ ይልቅስ የጋራ ብሔራዊ ህይወታችንን በጋራ መወሰን የማናመልጠዉ እጣ ፈንታችን መሆኑ ዛሬ ብዙ የማያከራክር ሃቅ ነዉ። ይህን ሃቅ ሶስት አስርተ አመታት በፈጀ ጦርነት ያገኙት “ብሔራዊ ነፃነት” መራራም ጣፋጭም የሆነባቸው፣ የዚያ ሁሉ ትግልና መስዋዕትነት መጨረሻ ዉጤት በአስከፊ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ስር መማቀቅ ሆኖ ያገኙት ከመረብ ወንዝ በላይ ያሉ ኢትዮጵያዊነታቸዉን የጣሉ ብዙ ትግሬዎች ዛሬ በይፋ ባይገልጹትም በልባቸዉ የሚክዱት አይመስለኝም።

ኢትዮጵያ ከምሽት ወደ ንጋት እንዴት?

ኢትዮጵያ ዛሬ ጨልማለች። አለምላሚ ሳይሆን አጠዉላጊ በሆነ ብርሃን የራቀዉ የጐሳ ፖለቲካ ተሸንሽና፣ በጐጥ ተመትራ የምትገኝ አገር ናት። ለመረዳት አዳጋች በሆነ መንገድ በታዋቂ ንጉሧ የአፄ ዩሃንስ ዘሮች ሴረኛነትና አድራጊ ፈጣሪነት ከዉስጧ ተኖ የተነሳ አጨላሚ የመከፋፈል ደመና ያንዣብብባታል። ዘመኑ አገራዊ ሉዓላዊነታችን ያልተረጋገጠበት፣ አንድነታችን አስጊ ሁኔታ ዉስጥ የወደቀበት ጊዜ ነዉ። ዉጥረቱ ብዙ ሳይዉል ሳያድር ዘላቂ መቋጫ እንደሚያስፈልገዉ ግልጽ ነዉ፣ ምንም እንኳን ያቆጫጩ አኪያሄድ በቀላሉ ባይታየንም። የጋራ ብሔራዊ ህይወታችን፣ ኢትዮጵያዊነታችን፣ ወሳኝ መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሷል። የሞት ወይስ የሽረት አቅጣጫ፣ ለሁላችንም አደገኛ የሆነ ጠማማና ጠባብ የመለያየት መንገድ ወይስ ቀና፣ ሰፊ የአንድነት ሕዳሴ ጐዳና?

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ዉጥረት ዉስብስብ የሚያደርገዉ ከኤርትራ ጋር ያለን ማለቂያ የሌለዉ የተንዛዛ መፋጨት ነዉ። የኢትዮጵያና የኤርትራ “መለያየት” እድሜ ልክ ቀጣይ በሆነ መጥፎ፣ አጨቃጫቂ፣ የባልና ሚስት ፍቺ ይመሰላል። ከመረብ ወንዝ በታች ባሉ ወያኔ ትግሬዎች የተቋቋመዉና ዛሬ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ግራ በሚያጋባ መንገድ የሚያምስ ዘረኛ አምባገነናዊ አገዛዝ ራሱ ከጽንሱ የኤርትራ እጅ አለበት። ከዛሬ አመራሩ ዉስጥም የኤርትራ ትግሬዎች አሉበት። ሆኖም ከመረብ በላይ ባሉ የትግሬ ፖለቲካ ሊህቃንና ከመረብ በታች ባሉ የጐሳና የፖለቲካ አቻዎቻቸዉ መካከል ነባር፣ ባመዛኙ የጣሊያን ቅኝ አገዛዝ የፈጠረዉ ልዩነት፣ አለመጣጣምና መናናቅ አለ። እንዲሁም ሁለቱ ገዢ ወገኖች ጊዜዉ የፈጠራቸዉ፣ ሰሞኑን የኢሳያስ አፍወርቂ ቅጥረኞች የሚመስሉ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች “እናስታርቅ” ብለዉ የተነሱባቸዉ፣ የብሔርተኝነት ቅራኔዎችና “ልማት” ከሚሉት ከኢትዮጵያ የዉስጥና የዉጭ ብዝብዛ አጀንዳ ጋር የተያያዙ ስልታዊ ልየነቶችም አሏቸዉ። በተጨማሪ አንዱ ገዢ ወገን ሌላዉን ከሥልጣን በትጥቅ ትግል ለማዉረድ የተነሱ ተቃዋሚ ሃይሎችን በቁጥጥሩ ሥር “ደግፎ” በፖለቲካ መሣሪያነትና ወካይ ጦር ተዋጊነት ይዟል። ይህ ሁሉ ዘባዝንኬ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ዉጥረትና መፍቻዉን ዉስብስብ አድራጊ ነዉ።

የኤርትራ አምባገነናዊ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጥታ የጦር ግጭት ከማድረግ ቢቆጠብም (አቅም አንሶት ወይም በባድመ ዉጊያ የደረሰበትን አይነት ሽንፈት ፈርቶ) ብሔራዊ ጐናችን ዉስጥ በቋሚነት ተሰክቶ ቀሰ በቀስ የሚያደማን ጋሬጣ ከመሆን ጋብ የሚል አይመስልም። ብሔራዊ ነፃነት የተቀዳጀሁ፣ ራሴን የቻልኩ አገር ነኝ ባይ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጉያ የማዉጣት ወይም የማራቅ ፍላጐቱም ችሎታዉም የለዉም። ሆን ብሎም ይሁን ሳያሰላ ብሔራዊ ዉጥረታችን ዉስጥ የራሱን እኩይ ፀረ ኢትዮጵያ ሚና ይጫወታል፣ በተለይ አጋሮቹም ተቀናቃኞቹም የሆኑት ወያኔዎች ስልጣን ላይ እስከቆዩ ድረስ። ይህን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለኤርትራ ህዝብም የማይበጅ፣ ሲበዛ ጨቋኝ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ማስወገድ የተጨቋኙ ህዝብ ራሱ ሥራና ሃላፊነት ቢሆንም አገዛዙ የኢትዮጵያ ገዳዮች ላይ ያለዉን ቀጥታና ተዘዋዋሪ ጐጂ ተጽእኖ የብሔራዊ ህይወታችን ሕዳሴ ትግል በሚገባ መተንተን፣ መገንዘብና መቋቋምና ያለበት ነገር ነዉ። ይህ ካልሆነ ኢትዮጵያና ኤርትራ በሰላም ተለያይተዉም ሆነ ተዋህደዉ ሊኖሩ አይችሉም።

እንግዲህ ከተያዝንበት የተወሳሰበ ብሔራዊ ዉጥረት መዉጣት የምንጀምረዉ እንዴት ነዉ? ከየት ወይም እንዴት ነዉ የምንነሳዉ? ጥያቄዉ ይህ ነዉ። የገጠመን የመንግሥት ወይም የፖለቲካ ለዉጥ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ይህ አይነት ለዉጥ ለአገር ማዳን ትግሉ አሰፈላጊና ወሳኝ ቢሆንም በቂ አይደለም። ጥያቄዉን በዝች ጽሑፍ በቅጡ ለመመለስ የሚሞከርም ባይሆን ለመልሱ አስተዋጽዎ የሚሆኑ ጥቂት አወያይ ሃሳቦች መሰንዘር ይቻላል። “እንዴት” የሚለዉን ጉዳይ ሳነሳ የሚያስፈልገንና የሚበጀን ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የለዉጥ ዘመቻ ነዉ ወይስ የትጥቅ ትግል በሚል የተለመደ “የአማራጮች” አቀራረብ በመገታት አይደለም፣ በግሌ አነዱ ወይም ሌላዉ መንገድ ይበልጥ ያስፈልጋል የሚል እምነት ቢኖረኝም እንኳን።

ጉዳዩ በሰፊዉ ሲታይ በተለያዩ መስኮች፣ ረድፎችና ደረጃዎች የተለያዩ የትግል ዘዴዎችና አቅሞች (የነፍጥንም ጨምሮ) እየገነቡ በመጠቀም በጀግንነት የሚንቀሳቀሱ አገር ወዳድ ዜጐችና ተቃዋሚ ሃይሎች ዘንድ አግባብነት አለዉ። እንደ አገር ያለንበት ዉጥረት በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጉዳዮች፣ ለምሳሌ በዜግነትና አገራዊ ሉዓላዊነት፣ በኢኮኖሚና ማህበረሰባዊ ኑሮ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት፣ በትምህርትና ባህል መስክ፣ በመንግሥት ሥልጣን አያያዝ፣ አገሪቱ ከጐረቤት አገሮች፣ በተለይ ከሱዳንና ከኤርትራ (ኤርትራ ራሱን የቻለ ለኢትዮጵያ “የዉጭ” አገር ነዉ ከተባለ) ጋር በተከተተችባቸዉ ጐጂ፣ የተዛቡ ግንኝነቶች ይታያል። በተለይ ደግሞ ቀኖናዊ ለሆኑ አራማጆቹ የተወሰነ ስነልቦናዊ እርካታ ከመስጠቱ ባሻገር ምንም ያህል ገንቢ የሆነ አካባባዊም ሆነ አገራዊ ጐን በሌለዉ ጐሳ “ነፃ አዉጪ“ ፖለቲካ በአገሪቱ መስፋፋት ይከሰታል።

በነዚህ ሁሉ መስኮች በአንጻር ራሳቸዉን የቻሉ ግን የተያያዙ አገር አዳኝ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ ነገደ ብዙ የኢትዮጵያዊያን ስብስቦችና ወገኖች ሊኪያሄዱ ይችላሉ። አስፈላጊነታቸዉም አጠያያቂ አይደለም። ነገር ግን ከላይ ያነሳሁትን ጥያቄ በሚመለከት የማጐላዉ የታጋይ ወገኖችን የየብቻ ወይም የጋራ አድራጊ ፈጣሪነት ሳይሆን ትግላቸዉን በቅንብር የሚያነሳሳ፣ የሚያካትት፣ የሚደግፍና ከፍ የሚያደርግ፣ መልሶም በትግላቸዉ የሚጠናከር ጠቅላላ የኢትዮጵያ ራስን አዳኝ ብሔራዊ ተንቀሳቃሽነት ላይ የሚያተኩር ነዉ። ከዚህ ትኩረት ጀርባ ከአገራዊ ባህላችንና ልምዳችን እይታ ጋር የተያያዘ ቅድመ ግንዛቤ አለኝ። ይኸዉም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ልምድ የራሱ ሕይወትና ተጽእኖ የሌለዉ፣ ዝም ብሎ ሲገፉት የሚገፋ በደልና ጥቃት ተቀባይ፣ በቀላሉ የኛን (የዜጐችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የምሁራንን) መታደግ ጠባቂ ሆኖ የሚታይ ሳይሆን ለለዉጥና እድገት ክፍት የሆነ፣ ራሱ ተንቀሳቃሽ ሃይል መሆኑ ወይም ሊሆን መቻሉ ነዉ።

ይህ ግንዛቤ በመሠረቱ ትክክል ከሆነ (በዝርዝር ሊያከራክር ቢችልም) ከተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን ጀምሮ በተቃዋሚም ሆነ በገዢ አብዮተኞችና ፖለቲከኞች ዘንድ መንጸባረቅ አካቶ ያላቋረጠ የአገር እይታ ተለምዶን መክላትና በምትኩ የተሻለ፣ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተሐድሶ አስፈላጊና ተገቢ የሆነ አመለካከት ማዳበር ያሰችለናል። ተለምዶዉ የጋራ ብሔራዊ ህይወታችንን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ በጅምላ አሉታዊ በሆነ መንፈስና አቀራረብ “የችግሮች” ምንጭና ድምር ብቻ አድርጐ አይቶ፣ በእዉንም ሆነ በምናብ ለታዩ ችግሮች የአገራዊ ህልዉናችን ተቀናቃኝ የሆኑ የፖለቲካ “መፍትሔዎች” ያራባ ነዉ። ልምዱ ኢትዮጵያን ከሃያ አመት በላይ የገዛዉና ዛሬም በገዢነት ላይ እያለ ራሱን “የትግሬ ህዝብ ነፃ አዉጪ” እያለ የሚጠራ ወገን ኢትዮጵያዊነትን የሚያፍን አደገኛ ዘረኛነት ጨምሮ የሚከተለዉ ነዉ።

ስለዚህ ዛሬ ባለንበት የዉጥረት ሁኔታ የጋራ ብሔራዊ ህይወታችን የራሱ ተጽእኖ ያለዉ ተንቀሳቃሽ ሃይል ነዉ ማለት አጠያያቂ ሊሆን ይችላል። በመላ የአገሪቱ ጉዳዮች ዉስጥ ቦርቡሮ የገባና በላያቸዉ ላይም የተስፋፋ አምባገነናዊ የጐሳ ብሔርተኝነት አገዛዝ በሰፈነበት ባሁኑ ዘመን፣ የአገሪቱ ሰፊ ህዝብ ጥቅሞችና “ልማት” ከሥር እስከ ቅርንጫፋቸዉ ለተወሰኑ የዉስጥም የዉጭም ተቀራማቾች ተመቻችተዉ በቀረቡበት ጊዜ፣ እንዴት ብሎ ነዉ ሃቀኛ ኢትዮጵያዊነት የራሱ ተጽእኖ ሊኖረዉ የሚችል? ጥያቄዉ ተገቢ ነዉ፣ መልሱም ስላለንበት ብሔራዊ ዉጥረትና ስለ ፍችዉ ያለንን ግንዛቤ ያዳብርልናል። በይበልጥ ጠቃሚነትም ለዚህ ጥያቄ የምናበጀዉ መልስ ከዉጥረቱ ለመላቀቅ እንደ አገር የምናደርገዉን ጥረት ሊያበረታታና ሊያግዝ ይችላል።

ለጥያቄዉ የኔ ምላሽ የሚከተለዉ ነዉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ጠንካራ ታሪካዊ ሥር ባላቸዉ አገሮች ዉስጥ ብሔራዊ ዉዝግብና ሽብር፣ አብዮት የሚያመጣቸዉን ፖለቲካዊ፣ ህብረተሰባዊና ብሔራዊ ዉጥረቶች ጨምሮ፣ አገራዊ ህልዉናን ጨርሰዉ የሚያወድሙ ወይም እንዳልነበረ የሚያደርጉ አይደሉም። ለምሳሌ ቻይና በቀዳሚዉ የሃያኛዉ ክፍለ ዘመን ግማሽ የደረሰባትን፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ካለችበት አስጊ ሁኔታ የከፋ፣ ከባድ ብሔራዊ ዉጥረት መጥቀስ ይቻላል። እንደ ፈረንጆች ዘመን ቀመር 19ኛዉ ምእተ አመት እየተገባደደ 20ኛዉ ክፍለ ዘመን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 1940ዎቹ መጨረሻ ቻይና የሄደችበት የዉጥረት መንገድ ምን ይመስል ነበር? ጥንታዊ ንጉሠ ነገሥታዊ የአገዛዝ ሥርዓቷን መፍረስ፣ በአዉሮፓ አገሮች በቅርምት መያዝንና መበዝበዝን፣ በጃፓን መወረርንና በወረራዉ የህዝቧን  በአረመኔያዊ ጭፍጨፋ ማለቅንና መሰቃየትን (ናንኪንግ እሚባል ከተማዋ ብቻ ከ250,000 የሚበልጡ ሰላማዊ ዜጐቿ ተገለዋል)፣ እንዲሁም ከዉስጧ የጦርነት ባላባቶችን ዉዝግብና በብሔርተኞችና በኮሚንስቶች መካከል የተደረገ የእርስ በርስ ግጭትንና አብዮታዊ ትግልን ያካተተ ጐዳና ነበር። ቻይና እነዚህን ብሔራዊ ህልዉናዋን ከባድ አደጋ ላይ የጣሉ ከዉስጥም ከዉጭም የመነጩ ተፈራራቂና ተደራራቢ ዉጥረቶች ሁሉ አሸንፋ ነዉ ዛሬ ላለችበት ከፍተኛ የልማትና የሃየለኛ አገርነት ደረጃ የበቃችዉ።

እንግዲህ ኢትዮጵያ ከቻይና ባልተናነሰ ደረጃም ባይሆን የማንሰራራትና የሕዳሴ እምቅ ችሎታ አላት። አንድ የዘርፌ ከበደን መንፈሳዊ መዝሙር ቃላት ለመዋስ፣ ቢመሽም ለኢትዮጵያ ቀን አለ። እንደ ኢትዮጵያና ቻይና ያለ ጠንካራ ታሪካዊ መሠረት ያለዉ ብሔራዊ ልምድ ለተወሰነ ጊዜ ከዉስጥ ሊበጠበጥና ሊናወጥ ይችላል። የዉጭ ጠላት ሃይሎች ወይም በዝባዦች በዉስጥ ተባባሪዎች፣ በዉጨኞች መጠቀሚያዎችና ተጠቃሚዎች፣ እየተረዱ ልምዱን ሊያናጉትና ሊያዳክሙት ይችላሉ። በዚህ አይነት ጊዜያዊ ሄደት የአገር ሉዓላዊነት ከባድ ወጥረት ያጋጥመዉ ይሆናል። የሆነ ሆኖ ግን አገሩ ከገጠመዉ ዉጥረተ ለመዉጣት ተንገዳግዶም ቢሆን የሚነሳዉ አካቶ ካልወደመዉ ከራሱ ታሪካዊ ህልዉና ነዉ። ራሱን ለማዳን የሚንቀሳቀሰዉ፣ ከጨለማ ወጥቶ ብርሃን የሚላበሰዉ፣ ከደረሰበት ጥቃትና ጉዳት በተረፈ ብሔራዊ ህይወቱ ነዉ። የራሱን ብሔራዊ አቅሞችና ፀጋዎች አድሶ፣ አሰባስቦና አጠናክሮ ነዉ።

አገር በዚህ የሕዳሴ አነሳሱና እንቅስቃሴዉ ከሌሎች አገሮች ወይም ከዓለም አቀፍ ምንጮች እዉቀት፣ መረጃዎች፣ ሃሳቦችና ቴክኖሎጂዎች ቢያገኝም እነዚህን መሣሪያዎች በሚገባ ለመጠቀም ከራሱ ጋር ማዛመድና ማዋሃድ ይኖርበታል። መሣሪያዎቹ አገራዊ ባህልን በጅምላ መንቀፊያና ማፍረሺያ ወይም መተኪያ አይሆኑም፣ ይልቅስ ማደሻና ማሻሻያ ነዉ መሆን ያለባቸዉ ። ይህ ነጥብ በተለይ ዘመናዊ ፖለቲካ ሃሳብ የዛሬዉ የኢትዮጵያ ራስን አዳኝ ብሔራዊ ትግል ዉስጥ ያለዉን አገባብ ይመለከታል። ስለዚህ በወቅቱ የኢትዮጵያ የለዉጥ ትግል ሂደት ሃሳቦች ላይ የተመሰረተ ፖለቲካችንና ራሱ ተንቀሳቃሽ የሆነ ብሔራዊ ህልዉናችን ያላቸዉን ወይም ሊኖራቸዉ የሚገባን ግንኙነት ቀረብ ብሎ መቃኘቱ ይጠቅማል።

የፖለቲካ ሃሳብና ብሔራዊ ባህል በትግል ትስስር

ይህ ንዑስ ርእስ የሚነሳበትን ግንዛቤ ከጅምሩ ግልጽ ላድርግ። ዘመናዊ የሚባሉ የፖለቲካ ሃሳቦች (ለምሳሌ “ዲሞክራሲ”፣ የማህበረሰቦች ወይም ያካባቢዎች “ራስ ገዝነት”) እና ባህላዊ ብሔርተኝነታችን ወይም አገር ወዳድነታችን በተናጠል የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ህልዉና ለዘለቄታዉ በብቃት አያካትቱም፣ አያረጋግጡም። ትስስራቸዉ አስፈላጊ ነዉ። ጉዳዩ በዛሬዉ የለዉጥ ትግል ዉስጥ ግንኙነት አላቸዉ ወይስ የላቸዉም ሳይሆን የግንኙነታቸዉ ቅርጽና ይዘት ነዉ። ለምሳሌ ዛሬ በአገራችን ያሉ የተለያዩ እምነታዊና ባህላዊ ማንነቶችን እኩልነት በመርህ ስንደግፍ ለዚህ መርህ ወያኔዎች የሰጡትን በመሠረቱ ስታልናዊ የሆነ የአምባገነን ፖለቲካ ቅርጽና ትርጉም ዉዳቂነት ተገንዝበንና አስገንዝበን ነዉ የሚሆነዉ። ለመርሁ በኢትዮጵያ ህዝብ ይበልጥ ተቀባይነት ያለዉ የተሻለ አማራጭ ፍቺ፣ መዋቅርና አፈጻጸም ሰጥተን ነዉ።

ሆኖም ፖለቲካ ሃሳባችንና ብሔራዊ ልምዳችን ስላላቸዉ ትስስር በቅጡ ለመወያየት መጀመሪያ አንጻራዊ ልዩነታቸዉን በግልጽ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።ፖለቲካ ሃሳብ ስል የአገርና የህዝብ ጉዳዮችን ሆን ብለንና አትኩረን የምናስተዉልባቸዉንና የምንቀርጽባቸዉን ፈርጆች፣ መርሆች፣ እምነቶችና ጽንሰ ሃሳቦች፣ እንዲሁም ዲስኩራዊ የትንተና፣ የክርክርና የትችት እንቅስቃሴዎች በመመልከት ነዉ። እነዚህን ዘመናዊ የፖለቲካ ንቃተ ህሊናችን ፈጠራዎች ወይም ዉጤቶች ራሳቸዉንም ሆነ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ገዳዮች ዉስጥ ያላቸዉን እዉን አገባብ መፈተሽ፣ መገምገም፣ መለወጥና ማሻሻል እንችላለን። ብሔራዊ ባህል የምለዉ በታሪክ ሂደትም አጋጣሚም  ሥርና ቅርጽ የያዘ፣ የተፈተነ፣ በዝግመት እያደገና እየዳበረ የመጣዉን የኢትዮጵያን ማንነት ወይም አገርነት ልምድ ለመለየት ነዉ። ባህሉ ከጊዜ ወደጊዜ ተቋማዊና ቴክኖሎጂያዊ ዘመናዊነትን በጨረፍታ ያስተጋባ ቢሆንም በመሠረቱ ታሪካዊ ሂደት ያፈራዉ፣ የምንኖረዉ ልምድ እንጂ ትናንት የመጣ የፖለቲካ ሃሳብ የፈጠረዉ አይደለም። የማህበረሰብ፣ የባህልና የቋንቋ ብዙሃንነት የተመላበት ብሔራዊ ህልዉናችንን “መሥራች አባቶች” ሆን ብለዉ በረቂቅ ሃሳቦች አልነደፉትም።

ፖለቲካ ሃሳብ ሥር ነቀል ቅርጽና ይዘት ቢኖረዉም፣ ተራማጅ ቢባልም፣ የግድ ብሔራዊ ህልዉናን ተጻራሪና አፍራሽ አይደለም። ለምሳሌ የ18ኛዉን ምእተ አመት የፈረንሳይ አብዮትና የ20ኛዉን ክፍለ ዘመን የቻይና አብዮት መጥቀስ ይቻላል። አብዮት አንድን አገር ወይም ህዝብ አንድነቱንና ሉዓላዊነቱን ጠብቆ የራሱን መሠረታዊ ለዉጥና እድገት ማኪያሄድ የሚያስችል ሃይል ሊሆን ይችላል ማለት ነዉ። ነገር ግን አገራችን ዉስጥ ፈሩን በለቀቀ የተማሪዎች ግራ ክንፈኛ ንቅናቄ ተጀምሮ በወያኔዎች ጐሳዎችን “ነፃ አዉጪ” ነኝ ባይ አገር ከፋፋይ አምባገነናዊ አገዛዝ የተገባደደዉ አብዮታዊ ሂደት የኢትዮጵያ የራሷ የለዉጥ ትግል ሳይሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአመዛኙ የአገሪቱን ህልዉና ተጠናዉቷል፣ ምንም እንኳን ትግሉ እህብረተሰቡ ዉስጥ አጀማመሩ አገራዊ የነበረ ቢሆንም።

ይሁን እንጂ የፖለቲካ ሂደቱ በጅምላ “የኢትዮጵያ አብዮት” ተብሎ ተፈርጇል። የዚህን ፍረጃ አጠያያቂነት አጉልቶ የሚያሳይ አንድ ከጥቂት አመታት በፊት ገብሩ ታረቀ በተባለ ደራሲ በእንግሊዝኛ የተጻፈ መጽሐፍ አለ። መጽሐፉ ባመዛኙ ያጠነጠነባቸዉ ጉዳዮች የኤርትራና የትግሬ ጐሰኛ ብሔርተኞች በትጥቅ ትግል እንዴት የኢትዮጵያን “አብዮታዊ ጦር ሠራዊት” አሸንፈዉ ራሳቸዉን ነፃ እንዳወጡ የሚያትቱ ናቸዉ። የመጽሐፉ ርዕስ ግን The Ethiopian Revolution ነዉ። እዚህ ብዙዉን ጊዜ የማይነሳ አወያይ ጥያቄ አለ። ይኸዉም አብዮታዊ የተባሉ የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች የተሸነፉበት ብቻ ሳይሆን አካተዉ የወደሙበትና በመጨረሻም አገሪቱ ከዉስጧ ለተነሱ ግን ከፋፋይ የቅኝ ገዢነት መንፈስ ላላቸዉ ደመኞቿ ተገዥ የሆነችበት አኪያሄድ የኢትዮጵያ  አብዮት የተባለዉ፣ የአገሪቱ የራሷ ለዉጥ የሆነዉ እንዴት ነዉ?

ይህን ሰፊ ታሪካዊና ጽንሰ ሃሳባዊ ትንተና የሚጠይቅ ጉዳይ እዚህ ልሄድበት አልሞክርም። ያነሳሁት ዘመናዊ፣ አገር ለዋጭ፣ ፖለቲካ ሃሳብና በታሪክ ዝግመት የዳበረ ብሔራዊ ህልዉና ያላቸዉን ወይም ሊኖራቸዉ የሚችልን ግንኙነት በሚመለከት የተራማጅነት ባህላችን የፈጠረዉን፣ በርዝራዥ ዛሬም ያልተለየንን፣ መሠረታዊ ዉዝግብ ለመጠቆም ነዉ። አክሎም ከዛሬዉ የለዉጥ ትግል አኳያ አበዮታዊ ልምዳችንን ለተሟላ መልሶ ማስተዋልና ማመዛዘን ከፍተን ከልምዱ ጋር ያለንን የርዕዩት አለምና የፖለቲካ ሂሳብ መዝጋት የሚያስፈልገን መሆኑን ለማመልከት ነዉ።

እንግዲህ በዛሬዉ የኢትዮጵያ የለዉጥ ትግል፣ ሃሳቦች ላይ የተመሠረተ ስልታዊ የፖለቲካ ሥራን ከጋራ ብሔራዊ ህይወታችንና እንቅስቃሴያችን ጋር የምናዛምደዉ እንዴት ነዉ? በኔ ግምት ጉዳዩ በአንድ በኩል የብሔራዊ ልምዳችንን ተገቢ ግንዛቤ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሃሳቦችን አቀራረባችንና አያያዛችን ይመለከታል። የማዛመዱ ሥራ መነሻችን አገራዊ ህልዉናችን እንጂ ረቂቅ ርዕዩተ ዓለም አይደለም። የተለያዩ የዘር ብሔርተኝነት እቅዶች ወይም ጐሳ “ነፃ አዉጪ” የፖለቲካ ዉጥኖችም አይደሉም። የነፃነትና የዲሞክራሲ ጉዳዮች፣ የአካባቢ፣ የባህልና የእምነት እኩልነት ጥያቄዎች፣ የኢኮኖሚ ልማትና የማህበረሰባዊ ኑሮ እንቅስቃሴዎችና የሌሎችም ጉዳዮቻችን መነሻና መዳረሻ የምንጋራዉ ብሔራዊነታችን፣ ኢትዮጵያዊነታችን ነዉ።

የጋራ ብሔራዊ ባህላችንን ከዘመናዊ ሃሳቦች ተነስቶ መመዘን፣ መተንተንና መገምገም፣ ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚጠቅም መልክ የሚለወጥበትንና የሚሻሻልበትን መንገድ መፈለግ አንድ ነገር ሲሆን፣ ባህሉን ከሥር እስከ ቅርንጫፉ በጅምላ ተቃርኖ በጥላቻ በተዋጠ ተራ ዘረኛነትም ሆነ በከፊል የረቂቅ ርዕዩተ ዓለም ፈጠራ በሆነ ጐሰኛ ብሔርተኝነት አማካኝነት እንዳልነበረ ለማድረግ መሞከር ግን ጨርሶ ሌላ ነገር ነዉ። የኋለኛዉን አደገኛ፣ በእምቁ አገር አፍራሽ፣ አዝማሚያ የዛሬዉ የለዉጥ ትግል በቆራጥነትና በዘዴ ሊቋቋመዉና ቢያንስ ጥግ ሊያስይዘዉ ይገባል።

አገራዊ ልምዳችንን በሚመለከት “ተራማጅ” የፖለቲካ ሃሳባችን ሳይጨብጠዉ የቀረ ወይም ሊረዳዉ ያልቻለ አንድ ዋና ነገር አለ። ይኸዉም ልምዱ ለትችትም ሆነ ለተጨባጭ ምርምርና የእዉቀት ክትትል ክፍት የሆነ እዉነታ ቢሆንም እንደማንኛዉም ከታሪካዊ ማንነት ጋር የተሳሰረ ብሔራዊ ልምድ ስለራሱ አግባብ ያለዉ የራሱ ግንዛቤ፣ አመኔታና ያነጋገር ዘይቤ አለዉ። ለተመዘገቡ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁነቶች፣ ክንዉኖችና የታላላቅ መሪዎች ድርጊቶች (ለምሳሌ የአፄ ምኒልክ) የራሱ ፍቺና እሴት ሰጪ ትረካ፣ የራሱ አተረጓጐም፣ እምነትና የአነጋገር ዘይቤ አለዉ። ቁም ነገሩ ይህን የብሔራዊ ባህላችን ህያዉ ቅርጽ አስተዉሏችንና አቀራረባችን ነዉ።

በዚህ አገራዊ ማንነትና እመነት ገንቢ በሆነ ጐኑ ብሔራዊ  ባህላችን ተጨባጭ ታሪካዊ እዉነታዎችን ዝም ብሎ ቃል በቃል ዘጋቢና ገላጭ ስላልሆነ አብዮተኞቻችን ያለማመዛዘን እንዳደረጉት ባህሉን ላይ ላዩን የሳይንስ ቋንቋ በሚናገር ዘመናዊ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና አይን አይተን እዉነት አይደለም፣ ዉሸት “የአፈታሪክ” ፈጠራ ነዉ ብለን የምናጣጥለዉ አይደለም። አለበለዚያ አንድን የእምነት ባህል፣ ለምሳሌ የክርስትናን ወይም የእስልምናን አመኔታ ከነአለም አፈጣጠር ትረካ ልምዱ፣ በተመሳሳይ ጥራዝ ነጠቅ “ሳይንሳዊ” እይታ ዝቅ አድርጐ እንደመገመት ይሆናል። ቅኔን ወይም ግጥምን እንደ ተራ ድርሰት ማንበብ ይቆጠራል።

ብሔራዊ ባህላችን አላግባብ በእዉነታ ዘጋቢነት ብቻ ታይቶ አፈታሪክ ነዉ ቢባልም እንኳን በዚህ ሁኔታዉ  በአበዮቱ ሳቢያና በድህረ አብዮቱ ዘመን በአገራችን ከሰፈነዉ ተራማጅ የተሰኘ የፖለቲካ አስተሳሰብ ባህል አይለይም። ዘመናዊዉ አብዮታዊ ተብዬ የፖለቲካ አስተሳሰባችን ራሱ በተራ አፈታሪክ የተሞላ ነዉና። ይህን ለማየት ብዙ ሐታታ ዉስጥ ሳንገባ በድህረ አብዮቱ ዘመን የተፈለፈሉ፣ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ያልተገናኙ ብቻ ሳይሆኑ ምንም ያህል ጽንሰሃሳባዊ ይዘትም የሌላቸዉ የርዕዩተ አለማዊ ቃላትን ጥርቅም፣ ለምሳሌ “ዲሞክራሲን” እና “የህግ የበላይነትን”፣ ከደርግና ከወያኔ አምባገነናዊ አገዛዞች ጋር ማነጻጸር ይበቃል። አብዮታዊም ተባለ ልማታዊ ከወያኔ “ዲሞክራሲ” የበለጠ እዉን ሁኔታን ገላጭና ጨባጭ ነኝ ባይ ግን ጨርሶ ከእዉነታ የራቀ ግልብ አፈታሪክ የት አለ?

በዛሬዉ አገር አዳኝ ትግል እንግዲህ የጋራ ብሔራዊ ልምዳችን ያለዉን የራስ ግንዛቤና አመኔታ በተገቢ ቦታዉ የምንቀበለዉና በተሳትፎ የምናንጸባርቀዉ ዉስጣዊ የማንነታችን ገጽታ ነዉ፣ ህያዉ አነሳሽና አንቀሳቃሽ ሃይላችን ነዉ። ከዉጩ ሆነን ባልተመዛዘነ ረቂቅ ሃሳባዊና ፖለቲካዊ አቀራረብ ልንተነትነዉና ልንተቸዉ ስንሞክር ከግጥም ወደ ስድ ንባብ ዝቅ እናደርገዋለን፣ ህያዉነቱን፣ አነሳሽ ሃይሉን እናሳጣዋለን። በዚህ መንገድ ራሳችንንም ለገዛ ብሔራዊ ባህላችን ባይታወር በማድረግ፣ ራሳችንን በማዳከም፣ በቀላሉ የዉስጥና የዉጭ ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ግፊትና በደል ተቀባይ ሆነን እንቀጥላለን። በዚህ ሁኔታ የምናጠነጥነዉ የፖለቲካ ሃሳብ ደግሞ ለተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ስብስቦች በመለስተኛ ደረጃ እንቅስቃሴ ማሰላሰያ፣ ማደራጂያና መምሪያና ከመሆን አልፎ የሚኖረዉ ሕዝብ አነሳሽ፣ አወያይና አታጋይ ሰፊ አገራዊ ትርጉም ወይም ራዕይ ዉስን ሆኖ ነዉ የሚቀረዉ። ተቃዋሚ ወገኖች ራሳቸዉ ብሔራዊ ልምዳችን የሚሰጠዉን አነሳሽ መንፈስና አንቀሳቃሽ ሃይል ጠልቀዉ ሳያካትቱ በፖለቲካ ሃሳቦችና ግቦች (ፍትህ፣ ድሞክራሲ ወ.ዘ.ተ) ዙሪያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እነሱንም ሆነ አገራዊ ትግሉን ሩቅ አይወስድም። የትግል ጉዟቸዉ አገር ነፃ ማዉጣት የሚያደርስ ለዘለቄታዉ በቂ “ነዳጅ” አይኖረዉም።

ይችን መጣጥፍ ከማገባደዴ በፊት በዛሬዉ የለዉጥ ትግል ብሔራዊ ልምዳችንን በሚመለከት ሊኖረን ስለሚገባ ግንዛቤ የምለዉን እዚህ አቁሜ በትግሉ ዉስጥ ሃሳቦችንና መርሆችን በአግባብ ከማካተት ወይም ከመከታተል አኳያ መወጣት ያለብንን ተግዳሮቶችና ችግሮችም ባጭሩ ልሂድባቸዉ። በቅድሚያ መጨበጥ ያለብን ነገር የዛሬዉ የሃሳብ ክትትል እንቅስቃሴያችን ከየት እንደሚነሳ ነዉ። ለአገር የሚበጅ፣ በመላ የኢትዮጵያ ዜጐችና ማህበረሰቦች ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት ሊኖረዉ የሚችል ወደ ፊት ተራማጅ የፖለቲካ ሃሳብ በአዲስ መንፈስና ሁኔታ ለማዳበር በአስተሳሰብ ልምዳችን የት እንደነበርንና ዛሬ የት እንዳለን ማስተዋል ግድ ይላል። እዚህ ላይ ጉዳዩ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ በጻፈዉ መጽሐፉ (ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ) እንደሚያየዉ ወደ ኃላ ተመልሶ ርዕዩተ አለማዊ ክርክር ለማድረግ መፈለግ ወይም አለመፈለግ አይደለም። ብርሃኑ ራሱ እንደሚረዳዉ ዛሬ የገጠመን ከባድ ተግዳሮት ያለፈዉን፣ ግን በወያኔ አገዛዝ ከሞላ ጐደል ቀጣይነት ያገኘዉን፣ አምባገነናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና አሠራር ሥርዓት መቋቋምና መስበር፣ ከሥሩ መመንገል ነዉ። አያይዞም ሥርዓቱ ዛሬ የጋራ ብሔራዊነታችንን ተጠናዉቶ አገራዊ አንድነታችን ላይ ብቻ ሳይሆን አካባቢያዊና ማህበረሰባዊ ራስ ገዝነታችን ላይ ያሳረፈዉን ጐጂ ተጽእኖ ለማስወገድ ነዉ። ይህ ሥራ ርዕዩተ አለማዊ ክርክር ቢያስነሳም ክርክሩ አስፈላጊ ነዉ።

ከዚህ በፊት በሌላ ጽሑፍ እንዳልኩት፣ በአብዮቱ ጊዜና በድህረ አብዮቱ ዘመን፣ በተለይ በወያኔ አገዛዝ፣ በአገሪቱ የተስፋፋዉን በጥልቅ እንከናማ የሆነ ግራ ክንፈኛ የፖለቲካ አስተሳሰብና እምነት ባህል መልሰን ሳንፈትሽና ሳናርም አዲስ “እዉነተኛ” ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማቋቋም መሞከር ሙጃ የዋጠዉ ያልተጐለጐለ እርሻ መሬት ላይ ዘር በትኖ ሰብል ለማምራት እንደመጣር የሚቆጠር ነዉ። የወያኔ አገዛዝ ነገ ቢወገድም አስተሳሰቡ በቀላሉ ባንዴ አብሮ የሚወገድ አይደለም። እምነቱ ከአገዛዙ ዉጭ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጐሰኛ ብሔርተኞች፣ መልሰዉ ባልታነጹ “ተራማጆች” እና አልፎ አልፎም ጉዳዩን ጠለቅ ብለዉ በሂሳዊ አይን ባላዩ ገራገር ዜጐች ዘንድ ከሞላ ጐደል የሰፈነ ነዉ።

እንግዲህ በዉጥረት ዉስጥ የሚገኘዉን ብሔራዊ ህይወታችንን ለማዳን በፖለቲካ ሃሳብ መስክ ላይ ስንታገል መስኩን ራሱን አዙረን እያየንና የአረም ማጽዳት ዘመቻ እያኪያሄድን ነዉ የሚሆነዉ። ምክንያቱም ዛሬ  ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ የፖለቲካ ቋንቋ ሙስና መረን ለቆ የተስፋፋበት ነዉ። ጊዜዉ ህዝብን አደንዝዞና አፍዝዞ መግዣ የሆኑ፣ ምንም ተጨባጭ አወንታዊ ትርጉም ወይም ዋጋ የሌላቸዉ የተደጋጋሚ ቃላት ጥርቅም (“ነፃነት”፣ “ዲሞክራሲ”፣ “እኩልነት”፣ “ህገ መንግስት”፣ “የራስን ዕድል በራስ መወሰን” ወ.ዘ.ተ) በመሠረቱ አስቀያሚ የሆነ ጐሰኛ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን ተገቢና ህጋዊ አስመስሎ ማስጌጫ እርካሽ ጌጣ ጌጦች ሆነዉ የሚያገለግሉበት ዘመን ነዉ። ገዢዎቻችን አንዴ ብቻ እንኳን ቢሉት እዉን ዲሞክራሲያዊ ትርጉም ወይም ፌደራላዊ ይዘት የሌለዉን ስታልናዊ “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነፃነትና እኩልነት” ዲስኩር ከሃያ አመት በላይ ሌት ተቀን እየደጋገሙ ሲያሰሙን የዘመኑን የፖለቲካ ቋንቋ ሙስና እያስፋፉ ነዉ። ይህ አይምሮ አደንዛዥ ዲስኩር ከጅምሩ (በተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን) የረባ ፍቺ ነበረዉም አልነበረዉም ዛሬ ከመጠን በላይ ከመደጋገሙ ብዛት ለዛዉን ጨርሶ ያጣ፣ ትርጉሙ ተሟጦበት ብቅት ያለዉ፣ የቸከ አፈትረካ አባባል እንጂ ከአገዛዝ መሣሪያነቱ ባሻገር ምንም ያህል ሃሳባዊና መርሃዊም ሆነ ተግባራዊ ፋይዳ ያለዉ አይደለም።

ባጭሩ፣ ያለንበት ጊዜ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ሃቀኝነት በራቃቸዉ አስመሳይ ርዕዩተ አለማዊ፣ ባህላዊና ተቋማዊ ማንሜናዎች፣ በተልካሻ የላይ ላይ እምነቶችና የታይታ ድርጊቶች፣ ገዢዉ ወግን እንዳሻዉ ለራሱ ጥቅም መጠበቂያ በፈጠራቸዉ አገር ከፋፋይ የጐሳ ማንነቶችና ክልሎች፣ እንዲሁም ረክሰዉ የጋራ ብሔራዊ ባህላችንን ያረከሱ ሌሎች የፖለቲካ ፍጆታ ሸቀጦች የተጥለቀለቀበት ዘመን ነዉ። በአገር ተሐድሶ ትግሉ የሃሳብና ባህል ማጥራት ዘመችዉ ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል።

የፖለቲካ ሃሳብ በቋንቋ ሙስና ሳይጣመምና ሳይረክስ፣ የቃል በቃል አቀራረቡ በተግባራዊ ትርጉሙ ሳይሰረዝ፣ ያለዉን ወይም ሊኖረዉ የሚችለዉን በጐ ፍቺ እንኳን በዛሬዉ አገር አዳኝ ትግል ዉስጥ በቅጡ መጨበጥና ተፈጻሚ ማድረግ ቀላል አይደለም። አብዛኛዉን ጊዜ ሃሳባዊ ይዘቱም ሆነ ተግባራዊ የሚሆንባቸዉ እዉን ሁኔታዎች ተገቢ ትንተና፣ ግንዛቤና አስተዳደር ያስፈልጋቸዋል። ትርጉማቸዉ በአግባብ ሳይስተዋልና ሳይጨበጥ በቃል መደጋገም የተለመዱ፣ በአመዛኙ ህይወት የሌሽ ቀኖና ወይም ያነጋገር ዘይቤ ብቻ ሆነዉ የቀሩ የፖለቲካ ሃሳቦች (በተለይ “ዲሞክራሲ”) የተሻለ፣ ከብሔራዊ ህልዉናችን ጋር የሚግባባ፣ ህያዉ አተረጓጐምና አፈጻጸም ይፈልጋሉ። ባጭሩ የአገሪቱን ብሔራዊ ጉዳዮች በዉስጠ ሁኔታቸዉና በአካባቢያቸዉም ሆነ በአገራዊ ትስስራቸዉ በአማራጭ መንገድ ለመጨበጥና ለማስተዳደር ምን አይነት ጠቅላላ የአስተሳሰብ፣ የስልትና የእንቅስቃሴ ሂድት ተፈላጊና ተመራጭ ነዉ የሚል መሠረታዊ ጥያቄ በዛሬዉ የለዉጥ ትግል ዉስጥ መነሳትና መመለስ ያለበት ይመስለኛል። ይህ ሁሉ ሥራ ደግሞ በተለያዩ መስኮችና ደረጃዎች የተቀናበሩ ምሁራዊ፣ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ አቅሞች ይጠይቃል።

አገርን ከአደገኛ ዉጥረት ለማዉጣት እንደ አገር መነሳትና መታገል ስንል የፖለቲካ ሃሳብ ወይም እንቅስቃሴ ራሱ በጠቅላላ የጋራ ብሔራዊ ህይወታችን ዉስጥ የሚኖረዉን ተገቢ ቦታ እግምት በማስገባት ነዉ። ግምቱ የሚያስፈልገን ከተማሪዎች ተራማጅ ንቅናቄ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ የወያኔ አገዛዝ ዘመን ድረስ አብዮታዊ ልምዳችን በሚያሳዝን መልክ ከአሳየን የተዛባ አገር ጐጂ የፖለቲካ አኪያሄድ አሉታዊ ትምህርት ስለወሰድን፣ ማለትም ምን ማድረግ እንደሌለብን  ስለተረዳን ነዉ። እንደምናዉቀዉ አኪያሄዱ የተወሰነ ርዕዩተ አለምን እንደ ጣኦት አምልኮ ከአገርና ከህዝብ በላይ የቀረጸና ያዋቀረ፣ ለዚሁ አምባገነናዊ የርዕዩተ አለም “አምላክ” ያለማመዛዘን፣ በጭፍኑ፣ የሰገደና የታዘዘ ነበር። ወያኔዎች የራሳቸዉን ጠባብ የዘረኛነት አምልኮ ያክሉበት እንጂ ከሞላ ጐደል በዚሁ “የተራማጅነት” አኪያሄድ ነዉ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የበቁት።

እንግዲህ የዛሬዉ አገር አዳኝ ፖለቲካ ዋና ሥራ ከራሱ ዉስጣዊ እምነቶች፣ ግቦችና ክርክሮችና የመነጩ አንድ ወጥ የሆኑ ወይም የተለያዩ ሃሳቦችንና ፖሊሲዎችን በቅድሚያ መፍትሔዎች አድርጐ ማንደርደር ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ብሶትና ፍላጐት በጥሞና ተገንዝቦ፣ ብሔራዊ ልምዳችን ካለበት አስጊ ሁኔታ መዉጣት የሚያስችሉት የራሱ ሃይሎችና አቅሞች የሚታደሱበትንና የሚጠናከሩበትን መንገድ ማመቻቸት ነዉ። እዚህ ላይ አገር ፈዋሽ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሰዎች ጤና ጥበቃ ሥራ ይመሰላል። ሕመም የያዘዉን ሰዉ ሰዉነቱ በዉስጡ ያለዉን ራስ አዳኝ አቅም ቀድሞና ችላ ብሎ በዘመን አመጣሽ የመድኃኒቶች፣ የስቃይ ማስታገሻዎችና የተክኖሎጂ መሣሪያዎች ብዛት በሽታዉን መቆጣጠር ለታማሚዉ ዘላቂ ፈዉስና ጤንነት የማያስገኝ መሆኑ በጤና ባለሙያዎችና አዋቂዎች ዘንድ እያደገ የመጣ ግንዛቤ ነዉ። በማመሳሰል የኢትዮጵያን “ሕመም” ከአገሪቱ ከራሷ የማንሰራራት፣ የማገገምና የመጠናከር አቅሞች አርቀዉ የሚቀርቡ ዘመናዊ  የፖለቲካ “መፍትሔዎች”፣ ጐሰኛ ብሔርተኝነትንም ጨምሮ፣ ለዘለቄታዉ የጋራ ሕመማችንን የማይፈዉሱ ብቻ ሳይሆኑ ለማንኛዉም የአገሪቱ ማህበረሰብ አይበጁም። አገር በጠቅላላ ጤና አጥቶና ተጐድቶ፣ የአገር አካላት የሆኑ ማህበረሰቦች በርቀት ሂደት ጤናማ አይሆኑም፣ አይጠቀሙም። የማን አገር ፈርሶ የማን ክልል ሊለማ?

ይህን ዉይይት ለመደምደም፣ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁኔታ አስጊነት፣ የምትሄድበት የፖለቲካ አቅጣጫም አደገኛነት፣ በእርግጥ አሳሳቢ ነዉ። ይሁን እንጂ አገርን እንደ አገር ተነስቶ ለማዳን ከመታገል አኳያ ስጋታችን ራሱ (ሲጋነን) የማይበጅ ጐን አለዉ። በአገር ወዳድ ዜጐችና ተቃዋሚ ድርጅቶች ዘንድ አንዳንዴ የሚታይ ችግር አለ። ይኸዉም የመለያየት ስቃይ ፍራቻ  ከመለያየት ሕመም ራሱ ማየሉና ይህም ፍራቻ ብሔራዊ ተነሳሽነታችንን፣ እንደ ኢትዮጵያዊያን በራሳችን መተማመንን የሚያዳክም መሆኑ ነዉ። አገራዊ ልምዳችንን እያደስን እያጠናከርንና እያሰፋን በሙሉ ልብ በመንቀሳቀስ የተለያዩ የአገር ወገኖችና ክፍሎችን በቅንብር ከመሳብና ከማሰባሰብ ይልቅ ከኢትዮጵያ ጥቅምና ከኢተዮጵያዊነት ጋር ሲያንስ አጠያያቂ ግንኙነት፣ ሲበዛ ደግሞ ተጻራሪነት ካላቸዉ ስብስቦችና ሃይሎች ድጋፍ ወይም ትብብር መፈለግ በራሳችን ያለመተማመን መገለጫ ይመስላል። የተወሰነ ድርጅታዊና ታክቲካዊ የትግል ቀመር ቢኖረዉም የሩቅ ሂደት ብሔራዊ ራዕይና ስልታዊ አስተዉሎ ይጐለዋል።

ይህን ያመኔታ፣ የራዕይና የስልት ጉድለት በዛሬዉ የለዉጥ ትግል ለማሟላት በብሔራዊ ልምዳችን የሚኖረን እዉን ተሳትፎ ወሳኝ ነዉ። ልምዱ ወደ ፊት ተመልካች ፖለቲካ ሃሳባችን ተቀባይነት የማይነፍገዉና በተለያዩ ግን የተሳሰሩ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ረድፎች (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ምሁራዊ፣ ኪነጥበባዊ፣ ወ.ዘ.ተ) ተገቢ ቦታ ያለዉ ስለሆነ ተሳትፏችንም እንዲሁ ልዩ ልዩ ቅርጾች አስተባብሮ ሊይዝ ይችላል። በዚህ ሁለንተናዊ አገር መልሶ ገንቢ ትግል የፖለቲካ እንቅስቃሴያችንና ብሔራዊ ህይወታችን አይጋለሉም። አንጻራዊ ረድፋቸዉን ወይም ነፃነታቸዉን ጠብቀዉ እርስ በርስ ይመጋገባሉ፣ ተደጋግፈዉ ወደ ፊት ይሄዳሉ። በድግግፍ ሂደታቸዉም ኢትዮጵያ ትታደሳለች። እንደ አገር ከምሽት ወደ ንጋት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንሻገራለን።

 

Email: tdemmellash@comcast.net

 

 

 

 

 

 

 

 

Filed in: Amharic News, News, Politics & Openion

Recent Posts

One Response to "የአገርን ዉጥረት በአገር መፍታት – ዶር ተስፋዬ ደምመላሽ"

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.