1

ያዋረደን ማነው ? ? ? – መሰረት ቀለመወርቅ

ቅጥረኝነት፤ የስልጣን ልክፍት፤ ዝቅተኝነትና እብደት፤ ቡድነኝነትና ጎጠኝነት፤ ዘራፊነት፤ ነፍሰገዳይና ጨካኝነት አፋኝነትና አሸባሪነት፤ በታኝነትና ከፋፋይነት፤ ሗላቀርነትና ምቀኝነት፤ እምነት የለሺ የታሪክና አገር ካሐዲነት ወዘተ…የተሰኙት ቃላት ወያኔንና የሺፍታ ስርዓቱን በሚገባ ይገልፁታል። እኛ ኢትዮጵያውያን ውርደታችን የሚጀምረው በዚህ ጨካኘና ካሐዲ ቡድን መዳፍ ስር ከወደቅንበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ወያኔና መሰሎቹ በኢትዮጵያና በሕዝባችን ላይ ባለፉት 22አመታት የፈፀሙት ወንጀለኛ ተግባሮቻቸው ዋንኛ መለኪያና ማረጋገጫችን ነው።

በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ እንደተመዘገበው መንግስትን ገልብጦ መንግሰት ማቋቋም ያለና የነበረ አለማቀፋዊ ክስተት ነው። ነገርግን ወያኔንና የሺፍታ ስርዓቱን ከዓለማችን ታሪካዊ መዘውር ውስጥ ልዩ የሚያደርገውውና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ምስቅልቅል ስርዓቱም የሚጠቁመው የገለበጠው አላፊውንና ጠፊወን ምድራዊ የኮሎኔል መንግስቱ ሐ/ማሪያምን መንግስት ሳይሆን ይልቁንም የነበረውንና ወደፊትም የሚኖረውን የጋራ አገር፤ የጋራ ሕዝብ የጋራ ታሪካችንና ባሕልላችን ሆኖ መገኘቱ ነው። ለዚሕም ነው ወያኔ ተፈጥሮዋዊ ውልደቱና እድገቱ መንግስት ተብሎ ለመጠራት መመዘኛውን የማያሟላው። ይሕ ጎደሎው የመንግስትነት ስነምግባርና ሺፍታዊ መታወቂያው በመሆኑ ብሔራዊ ሐላፊነት የማይሰማው ሐገርንና ሕዝብን ያዋረደ የጥቂት ሺፍቶች ማፍያ ቡድን ነው ብልን አፋችን ሞልተን እንድንናገር የምንገደደው። የብሔራዊ ውርደታችን ምንጭም እራሱ ወያኔና አጋሮቹ ለመሆናቸው ከተግባር የበለጠ ሌላ ገላጭ ቋንቋ ስለሌለ ማንንም የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም የወያኔውም አፈጣጠር ለዚሕ ጥፋት ታስቦና ተመቻችቶ ነው።

ቆምነገሩ ኢትዮጵያ ተብላ በምትታወቀው ምስራቅ አፍሪካዊት አገር ውስጥ ሐገሪቱን እንደሐገር ሕዝቡን እንደህዝብ የሚያስከብር መንግሰት አለን ወይ ብሎ ለሚጠይቅ ዜጋ መልሱ የለንም ማለታችን ብቻ ሳይሆን በዚሕ በኩል የነበረው እድል በ4ነጥብ መዘጋቱ ነው። ባንፃሩ ስናይ እኛን ኢትዮጵያንን ያዋረደን ማነው የሚለውን ሰሞነኛ ጥያቄ ለመመለስ ወያኔ ነውና ደረታችን ነፍተን ከመናገር ውጭ ከቶውንም ማነንም ቅን ዜጋ አያሳፍረውም። ሰሞኑን ደግሞ ያረጀ ጡርንባ እየተነፋ አየሩ ተበክሎል። በውጭና በውስጥ ለምንገኝ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ያረጀ ካርድ ተመዞ የተሰጠን አጀንዳ አለ። እሱም በዘመናዊ የባሪያ ፍንገላ ስልት በራሱ በወያኔው ተሺጠው በሳውዲ አረቢያ ውስጥ ስርተው በሚያድሩ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው አሰቃቂ እልቂትና ውርደት አንዱ ሲሆን ሁለተኛው የአማራውን ሕዝብ ከኦረሞው ጋር የማጋጨቱ የቆየው የወያኔ አጀንዳ በቴዲ አፍሮ ዘፈን ምክንያት እንደገና በአዲስ መልክ ተቀስቅሶ በውስጥም በውጭም በምንኖረው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ አቧራው ጨሰ የተሰኘውን ወያኔዊ የፕሮፓጋንዳ ሺብር አስከትሎ አጀንዳውን ጀባ ተብለናል።

 

ታዲያ የሰሞኑ አቧራው ጨሰ ወያኔዊ ሺብርተኛ ፕሮፖጋንዳ አጀንዳ ሚስጥሩ ምንድነው ብሎ መጠየቅ ብልሕነት ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔው የጥፋት ውሳኔ መሰረት ኢትዮጵያ የምትባል ሐገርና የዜግነት መብት የለህም ተብሎ በሕዋ ላይ መኖር ከጀመረ ይኸውና 22 ዓመታትን አስቆጥሮል።ኢትዮጵያዊነቱንና ሰው በመሆኑ ብቻ ነፃነቱን የጠየቀው ሕዝብ በወያኔና መሰሎቹ በገዛ ሐገሩ ይገደላል፤የደበደባል፤ይታሰራል፤ ይሰደዳል፤ሐብትና ንብረቱን ይነጠቃል፤ትውልድ ቦታውን በማስለቀቅ እንዲጋዝ ይፈረድበታል፤ በእምነቱ የማመን ነፃነቱ ይገፈፋል፤ ፍትህን ፍለጋ ወደሰማይ እያነባ ያንጋጥጣል፤እራሐብና እርዛት ለሱ የተሰጠ ፀጋ ሆኖበታል፤ አኩሪ ባሕሉ ቆሺሾል፤ መጋባቱ መዋለዱ ተገድቦ ፈጣሪው የቸረውን ነፃነት ተነጥቆል፤ እርስበርሱ የመደጋገፍ ተስፋው ተሟጧል፤ በየመንደሩ በተሰገሰጉ የወያኔ ጀሮ ጠቢውች እንዳይናገር ልሳኑ ተዘግቶል፤ የዘራፊወች የበይ ተመልካች ሆኖ በራሐብ አለንጋ ይጠበሳል፤ ቤተሰቡን ማስተዳደር ተስኖታል፤ ባልተለመደ መልክ ስብዕናን ለሚሸጡ የወያኔ ደላላወች ልጆቹን አሳልፎ እዲሰጥ ተገዷል፤ በየቀኑና በየደቂቃው ወያኔው ለራሱ ህልውና ይጠቅሙኛል ብሎ በሕዘቡ ውስጥ በሚቀሰቅሳቸው ግጭቶችና ሺብር የመኖር ዋስትናው ተናግቶ ተሰላችቶል፤ የወያኔው የውሸት ነፃ አውጭነት ፕሮፓጋንዳ ነጋ ጠባ ሆዱን ነፍቶ አቅለሺልሾታል።

 

በዚሕ አይነት የወያኔው የግፍ ቀንበር ተጭኖት ሕዝባዊ ብሶቱ ለአመታት ተጠራቅሞ ቆይቶ ዛሬ በሐገሪቱ የትኛውም ማእዘናት ሞልቶ እየፈሰሰ ነው። ታዲያ ይህ ብሶት የወለደው ሕዝባዊ ማዕበል ማንም ሊገታው በማችል መልኩ ሊከሰት እንደሚችል ማመላከቱ ብቻ ሳይሆን ወያኔንና መሰሎቹን መግቢያና መውጫ አሳጥቶ የሚጠራርግ ሕዝባዊ ማዕበል መሆኑ አይቀሬ ነው። ይሕ አይቀሬ የሆነው የታሪክ ሒደት ወያኔን አስጨንቆ አሳብዶ የራስምታት በሺታ ጥሎበታል አባኖታል አንቀዠቅዦታል የባህሩ ሞገድ ከድንጋይ ከቋጥኙ ጋር እያንከባለለ ያላትመዋል። የሕዝባዊ ብሶቱ የአደጋ ጥሪም በመረዋ ድምፁ ተንቆርቁሮ ተዋርደን አንቀርም የሚለው ጩኸቱ ከወያኔው ጀሮ በመድረሱ የሚጨብጠውን አሳጥቶታል። በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እዲሉ ወያኔው በራሱ ውስጠ ሕይወት የተፈጠረው ታሞ የማይድን አስተዳደራዊይ ግማቱ ታክሎበት አቀጣጣይ ክብሪቱን ለመለኮስ ተቀጣጣይ ቤንዚሉን አርከፍክፎ የህዝባዊ ብሶቱን ቦንብ የመፈንዳት ፍጥነት እዲጨምር የበለጠ እየገፋው ነው።

ታዲያ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንደሚባለው ዛሬ ብለጣብልጡ ውያኔ ከተፈጠረበት ከፍተኛ እራስ ምታት በሺታ የሚያድነው መዳሕኔት ባያገኝም ለጊዜውም ቢሆን ሊውጠው ሊሰለቅጠው የተቃረበውን ሕዝባዊ ማእብል ለመግታት ማስታገሻ ኪኒን ይሆነኛል ያለውን ወያኔ ሰራሺ ኬሚስትሪ ማፈላለጉ አልቀረም። ዘመድ ከዘመዱ አሕያ ካመዱ ሆነና አቅፈውና ደግፈው በቅጥረኝነት ያሰለፉትን አረቦች ተመልሶ እጅ መንሳቱ ግድ ስለሆነበት የሜንጫ ፖለቲካ አራማጅ የሆኑ ኤጀንቶችን ከሲያድባሬ አክራሪ እስላሚስት መኮንኖች ተውሶ ኦረሞ ፈርስት የተባለውን ቋንቋ ካረጁና ተስፋ ከቆረጡ ጥቂት የኦነግ ሚሺነሪወች በማዳቀል በጀት መድቦ ጮሌ ካድሬወችን ቀጥሮ በሚቆጣጠራቸውና አዳዲስ በፈጠራቸው ሚዲያወች በመጠቀም በውጭም በውስጥም እያተራመሰ ነው። ፈውስ ባያገኝም በጠና ከታመመበት የእራስ ምታት በሺታ ለጊዜውም ቢሆን ጊዜ ለመግዛት ማስታገሻ ኪኒን እየወሰደ ነው። ደሮውንም ወያኔ ሲወጠርና ሲጨነቅ ኮንዶሞቹን እንደደባል እቃ ማውጣትና ማግባት ዛሬ የተከሰተ ባለመሆኑ ለሐገር ወዳዱ ሕዝባችን አዲስ ነገር አይሆንበትም በወያኔ ላይ ያነሳውን ሕዝባዊ አመፅ የሚያስቆም አንዳችም ምድራዊ ሐይል የለም። የልቁንም የምስራቁ በረኛ የደጃዝማች ዑመር ሰመተርንና የደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶን የነራስ ጉብና ዳጨውንና የነ አፃ ምኔልክን የነ ራስ አበበ አረጋይንና የነ ጀኔራል ኤጃማ ኬሎን የነ ጀኔራል ታደሰ በሩንና የነ ጀኔራል ደምሴ ቡልቱን የመሳሰሉ ጀግኖቻችን ያቆዩንን ኢትዮጵያ አገራችን መዳፈር የዘመናት ታሪካችን አለማወቅ ይመስለኛል። ወያኔና ቅጥረኞቹ በአሁኑ ወቅት እየደረሰባቸው ካለው ሕዝባዊ ማዕበል ለማገገም የቻሉ እየመሰላቸው አቧራው ጨሰ የተሰኘውን የወያኔ ሰራሺ ሺብረተኛ ፕሮፖጋንዳ አጀነዳ አዲስ ግኝት አስመስለው በማራገብ ሕዝባዊ ጀግኖቻችን ማዋረድና ማንቓሸሺ የወያኔውን ግባተ መሬት መቃብሩን ቁፈራ ቢያፋጥነው እንጅ ከቶውንም ለጣረሞቱ ማስታገሻ ኪኒን ሆኖ አያገለግለውም። በውስጥም በውጭም የምንኖር ቀለም ቀመስ ኢትዮጵያውያን ሆይ!! ሕዝባቸህን ብሶቱ ገንፍሎ ወያኔንና ጀሌወቹን ከራሱ ላይ ለማውረድ እየታገለ መሆኑን እናውቃለን ስለዚህ ሳናመነታ ሞላች ጎደለች ሳንጫወት የወያኔ የጥፋት ፕሮፖጋንዳ ማራገፊያ ሳንሆን መከራ ተቀባይ የሆነውን ሕዝባችእንና ታሪካዊት ሕገራችን ከሺብርተኛ ቡድኖች ጥፋት እንከላከል፤ እናድን!!

አገራችን በጎሳ ስም ዳግም ስልጣን ከሚናፍቁ ሺብርተኞችና

ሚሺነሪወች ጥፋት እንጠብቅ !!

 

መሰረት ቀለመወርቅ

አውሰተራሊያ

Filed in: Amharic News

Recent Posts

One Response to "ያዋረደን ማነው ? ? ? – መሰረት ቀለመወርቅ"

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.