1

ጤፍ ሠለጠነች

ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ አንድ መልዕክት ደረሰኝ፡፡

መልዕክቱ ማክሰኞ ማለዳ ከአዲስ አበባ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቲቢላ ወረዳ በሚካሄድ አንድ ዝግጅት ላይ እንድሳተፍ የሚጋብዝ ነበር፡፡ ቲቢላ በምሥራቅ ሸዋ ዞን የምትገኝና በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የምትታወቅ ወረዳ ነች፡፡

በቲቢላ ስለሚካሔደው ዝግጅት ይዘት የተሰጠኝ ማብራሪያ ግን ትንሽ ግር የሚል ነበር፡፡ ጤፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮምባይነር መታጨድና መወቃት መጀመሩን የሚያመለክት ነው፡፡ ጤፍ በኮምባይነር መታጨዱና መወቃቱ ምን አዲስ ነገር አለው? ከሚለው መጠይቅ በፊት ግን እስከ ዛሬ ጤፍ በኮምባይነር አይታጨድም ወይ አይወቃም ነበር ወይ የሚለውን ጥያቄ አስቀድመን ነበር፡፡

ወደ ቲቢላ ከመጓዜ በፊትም የጤፍ አመራረት ሒደትን በተመለከተ የማውቃቸውን የግብርና ባለሙያዎች በማነጋገር የተወሰነ መረጃ ለማግኘት ሞከርኩ፡፡ ያገኘሁት መረጃ ጤፍና ኮምባይነር የማይተዋወቁ መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡ ሌሎች የምግብ ሰብሎች በኮምባይነር ሲታጨዱና ሲወቁ ጤፍ ግን ለዚህ ማዕረግ ሳይታደል መቆየቱን አስረዱኝ፡፡ የአገሪቱ የጤፍ አምራቾችም ለዘመናት የሚጠቀሙት ባህላዊና አድካሚ በሆነው የአመራረት ዘዴ መሆኑንም አረጋገጡልኝ፡፡  ይህ መረጃ ወደ ቲቢላ የመሔድ ጉጉቴን ጨመረ፡፡ በኮምባይነር ለመታጨድ የመጀመርያ ነው ወደተባለው የአፍሪካ ጁስ አክሲዮን ማኅበር የጤፍ ማሳ ላይ እረፋዱን ስንደርስ፣ ጀንዲር 1175H/616R በተባለው ኮምባይነር ጤፍ እየታጨደ ነበር፡፡ ይህ ኮምባይነር ለጤፍ ተብሎ የተመረተ ባይሆንም ለጤፍ አገልግሎት እንዲውል ተደርጐ ውስጣዊ ይዘቶቹ እንዲስተካከሉ የተደረጉበት ነው፡፡ ጤፍ ሠለጠነች

በዚህ ፕሮግራም ከኢትዮጵያ አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የተወከሉ  የግብርና ባለሙያዎችና ጤፍን በኮምባይነር እንዲታጨድና እንዲወቃ ለማድረግ በጋራ የሠሩት የአፍሪካ ጁስ አክሲዮን ማኅበር፣ የገደብ ኢንጂነሪንግ ኩባንያና የበለው መኮንን የመካይናይዜሽን አገልግሎት ሥራ አስኪያጆች ነበሩ፡፡

 በእርግጥም ጤፍ በኮምባይነር ሲታጨድና ሲወቃ ተመለከትን፡፡ በቦታው የነበሩ የግብርና ባለሙያዎችም በትክክል እየታጨደ መሆኑን ወደ ኮምባይነሩ ተጠግተው ጭምር አረጋገጡ፡፡ ይህ አዲስ ታሪክ ነውም አሉ፡፡

ዶ/ር አባይነህ ኢሳያስ የአፍሪካ ጁስ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የኩባንያቸው ዋነኛ ምርት አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት ነው፡፡ ዘመናዊ መጭመቂያ     አለው፡፡ ዋነኛ ኢንቨስትመንቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ቢሆንም በይዞታው ካለው መሬት የተወሰነውን ለተከታታይ ዓመታት ጤፍ ሲመረትበት መቆየቱን ይናገራሉ፡፡ አምና በ60 ሔክታር ዘንድሮ በ100 ሔክታር ላይ ጤፍ አምርተዋል፡፡ ሆኖም ጤፍ ምርትን ለመሰበሰብ፤ ዘርቶ አጭዶና ወቅቶ ለገበያ ለማውጣት እጅግ ከባድ እንደነበር ዶ/ር አባይነህ ይናገራሉ፡፡ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ የጤፍ አምራቾች ባህላዊ አመራረትን ይጠቀሙ ስለነበር፣ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ያዩት አድካሚ ጉዞ ወደ መፍትሔ ፍለጋ እንዲገቡ አደረጋቸው፡፡ የጤፍ ምርት እንደ ሌሎች የሰብል ምርቶች በኮምፖነር ለማጨድ የማይቻለው ለምንድነው የሚል ጥያቄ አጫረባቸው፡፡

ከዚህ ጥያቄ በመነሳት በዘንድሮ የምርት ዘመን ለአጨዳ የደረሰው በ100 ሔክታር መሬት ላይ ያለው ጤፍ እንደቀድሞ በጉልበት ሠራተኞች ከመሰብሰብ ይልቅ ለምን በኮምባይነር ለመሰብሰብ አይሞከርም በማለት ይነሳሉ፡፡ ሌሎች ሰብሎችን መውቃት የሚችሉ ኮምባይነሮች ለጤፍም እንዲያገለግሉ ለምን አይሞከርም ተብሎ ከባለው መኰንን ሜካናይዜሽን አገልግሎት ድርጅት ጋር ኮምባይነር ይከራያሉ፡፡ ይህ የኪራይ ስምምነት ግን የተለየ ነበር፡፡ ኮምባይነሩን ለጤፍ ማጨጃ ለመጠቀም እንዲቻል ለማድረግ ጭምር ነበር፡፡ በዚህ ስምምነት ውስጥ የጀንደር ኮምፖነር አስመጪ የሆነው ገደብ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ተሳታፊ ሆነ፡፡ ኮምባይነሩን ጤፍ ሊያጭድና ሊወቃ በሚችልበት ደረጃ የተለያዩ ማስተካካያዎች ተደረገ፡፡ የኮምባይነሩ የማጨድና የመውቂያ ክፍሎች ለጤፍ በሚመች ደረጃ ተዋቀሩ፡፡ የኮምባይነሩ የሙከራ ሥራ በዚሁ በአፍሪካ ጁስ የጤፍ ማሳ ላይ ተሞከረ፡፡ ያልተጠበቀ የተባለ ውጤትም ተገኘ፡፡ ጤፍ በኮምፖነር መታጨድና መወቃት የሚችል መሆኑን ለማገረጋገጥ የተለያዩ ፍተሻዎች ተደረጉ፡፡ ክፍተት የታየባቸው ታረሙ፡፡ የሙከራ ሥራው በተሳካ መንገድ እንደተረጋገጠም፤ የአፍሪካ ጁስ የዘራው 100 ሔክታር ጤፍ በዚሁ ኮምባይነር መታጨድ ጀመረ፡፡

ይህ ሙከራ መሳካቱ ለአንድ አፍሪካ ጁስ ኩባንያ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ጤፍ አምራቾች እንዲሆን በመታሰቡም ነው የማክሰኞ የመስክ ጉብኝት ፕሮግራም የተዘጋጀው፡፡

ከአገሪቱ በምግብ ሰብል ከተሸፈነ መሬት ውስጥ ወደ 27 በመቶው የተሸፈነው በጤፍ ሰብል ነው፡፡ ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአገሪቱ ውስጥ ከ2.7 ሚሊዮን ሔክታር በላይ የሚሆን መሬት በጤፍ ምርት የተሸፈነ ነው፡፡ የአገሪቱን ሰፊ የእርሻ መሬት የተቆጣጠረውን የጤፍ ምርት የሚያመርቱ የአርሶ አደሮች ቁጥር ከስድስት ሚሊዮን በላይ ይደርሳሉ፡፡

የጤፍ ፍላጐት ከዓመት ዓመት እየጨመረ የምርት መጠኑም እያደገ መምጣት በተለይም ከፍላጐት አንፃር የሚመረተው ምርት በቂ አለመሆኑም ተጠቀሷል፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያመለክቱት፣ የጤፍ የምርት ሒደት ከሌሎች በተለየ ፈታኝ፣ አድካሚና አሰልቺ ነው፡፡ የጤፍ ዋጋ እንዲወደድ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ በምርት ሒደቱ የሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡

የጤፍ የአመራረት ሒደት ባህላዊ በመሆኑ በምርት ሒደቱ የሚባክነው ጤፍ ከፍተኛ ነው፡፡ እስከ 20 በመቶ ብክነት እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ በኮምባይነር መታጨድና መውቃት መጀመሩ ግን ብክነቱ እንዲቀንስ ያስችላል፡፡

በባህላዊ መንገድ የሚደረገው የምርት ሒደት ጤፍን ለመውቃት ከብቶችን መጠቀም ግድ ነው የሚሉት የገደብ ኢንጂነሪንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቾምቤ ስዩም፣ በከብት እየተረገጠ የሚደረገው ውቂያ ደግሞ ለጥራት ጉድለት ምክንያት እንደሚሆንም ያስረዳሉ፡፡ የእስካሁኑ የአመራረት ሒደት ትልቅ ጉዳት ተደርጐ የሚታየው ሌላው ገጽታ ደግሞ ለአጨዳ የደረሰን ማንኛውም ምርት በቶሎ ለማንሳት ካለመቻል ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ነው፡፡ በባህላዊ አመራረት ዘዴ ምርትን ለመሰብሰብ ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ይህ በጤፍ ብቻ የሚታይ ሳይሆን በሌሎች ሰብሎች ላይ የሚገጥም ነው፡፡

እንደ ዶ/ር አባይነህ ገለጻ 100 ሔክታር ላይ ያለውን ጤፍ በኮምባይነር ማሳጨዳቸው ከወጪ አንፃር ብዙ ልዩነት ያለው መሆኑን ነው፡፡ አምና በባህላዊ መንገድ ለማሳጨድና ለመውቃት በአንድ ሔክታር 2800 ብር በላይ ወጪ አውጥተዋል፡፡ ዘንድሮ በኮምባይነር ማሳጨዳቸውንና ማስወቃታቸው ግን በአንድ ሔክታር ያወጡ የነበረውን ወጪ በአንድ ሺሕ ብር ቀንሶላቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ አምና በ60 ሔከታር ላይ የነበራቸውን ጤፍ ምርት ሰብሰቦ ለማስገባት ወደ ሦስት ወር ፈጀቷል፡፡ አሁን ግን 100 ሔክታሩን በአንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጨርሰው ጤፍ ለመሸጥ ጨረታ እስከማውጣት መድረሳቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ለውጡን ሌሎች ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ያስታውሳሉ፡፡ ጤፍን በኮምባይነር ማጨድና መውቃት ያለውን ጠቃሜታ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ቾምቤ፣ አንድ ሔክታር ጤፍ ለማጨድ፣ ለመከመርና ለመውቃት ከሁለት ሳምንት በላይ ይፈጅ ነበር፤ አሁን በኮምባይነሩ በቀን ከ15 እስከ 20 ሔክታር ማጨድና መውቃት ይቻላል ብለዋል፡፡

በዚህ ሥራ ውስጥ እንቅፋት የሆነው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መዝነቡ ነበር፡፡ ዝናቡ ጤፍን ስለሚያስተኛ ለማጨድ አስቸጋሪ ከመሆኑ ውጪ በተገኘው ውጤት መርካታቸውን ዶ/ር አባይነህ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

እንደዚህ ዓይነት ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የታየው ጅምር ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆኑን የጠቆሙት በሙከራ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙ የአግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የግብርና ባለሙያዎች ደግሞ በተለይ ምርትን በቶሎ ለመሰብሰብ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሰሞኑን የወጡ የሜትሮሎጂ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በጥቅምት መጨረሻና ህዳር ወር ዝናብ ሊኖር እንደሚችል መሆኑን ያስታወሱት ባለሙያዎች፣ ምርቱ በቶሎ ሳይሰበሰብ ዝናብ ቢመጣ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡

እንዲህ ዓይነት ችግር ሲመጣ የደረሱ ሰብሎችን በቶሎ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ እንዲህ ዓይነት ቴክኖሎጂዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ የወደፊት ተስፋን ያመላከተ ነው በማለት ከኢትዮጵያ  አግሪካልቸር ትራንስፎሜሽን ኤጀንሲ የመጡ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን ለማዳረስ ኤጀንሲው በጤፍ ዙሪያ እየሠራ ካለው ሥራ ጋር በማቀናጀት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን መሥራት አለበትም ተብሏል፡፡

የግብርና ባለሙያዎች የጤፍ ምርት ሒደትን በተመለከተ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ አርሶ አደሮች ማሳቸውን አሥርና አሥራ አምስት ጊዜ ያርሳሉ፡፡ ብዙ ጊዜና ጉልበት ይባክናል፡፡ ጤፍን ለማጨድ፣ የታጨደውን ወደ ውቂያ አውድማ ማጓጓዝ፣ አውድማ መለቅለቅና ተያያዥ ሥራዎች ረዥም የምርት ሰንሰለት ብክነት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ቴክኖሎጂ ይህን ሁሉ የሚያቃልል ነው፡፡ ለአርሶ አደሩ ከቀረበ የማምረቻ ወጪን ያወርዳል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ለውጥ ነው ተብሏል፡፡

አርሶ አደሮች ይህንን የሚጠብቁት ስለመሆኑም ተብራርቷል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ይህንን ቴክኖሎጂ እንዴት ለአርሶ አደሩ ማዳረስ ይቻላል የሚለው ነው፡፡  አቶ ቾምቤ ግን መላ  አለ ይላሉ፡፡

ድርጅታቸው ይህንን ኮምባይነርና ተያያዥ መሳሪያዎችን የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል፡፡ በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች በመጓዝ በሞባይል ሾው ፕሮግራም መሳሪያችንን በማስተዋወቅ ግንዛቤው እንዲፈጠር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

አሁንም ከፍተኛ ጤፍ በሚመረትባቸው ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ እንደ ሞጆና ሸንኮራ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች በዚህ መሳሪያ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል፡፡ በኮምባይነር ስንዴና ሌሎች ሰብሎቻቸውን የማሳጨድ ልምድ ያላቸው ገበሬዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ የጤፍ አምራቾች የጤፍ ማጨጃውና መውቂያው ተከራይተው እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡ በኮምባይነር ምርቶቻቸውን በማሳጨድ የባሌ ስንዴ አምራቾች ገበሬዎች በምሳሌነት ቀርበዋል፡፡

ለሙከራ የተጀመረው ሥራ በጤፍ ምርት ጥራት ደረጃ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ያሉት አቶ ቾምቤ፣ በሰው ኃይልና በኮምባይነር በመታገዝ በሚሠራው ሥራ መካከል ከፍተኛ የወጪ ልዩነት አለው ብለዋል፡፡

በኮምባይነር ማምረቻ መውቃት ጠቀሜታ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚገልጽ ሲሆን፣ ከወጪና ከድካሙ ባሻገር በፍጥነት ማሳው እንዲላቀቅ ይረዳል ተብሏል፡፡

የባለው መኰንን ሜካናይዜሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ባለው መኰንን በበኩላቸው ‹‹ቴክኖሎጂውን ሠርተነዋል፡፡ ውጤታማ መሆኑንም አይተናል፡፡ በሙከራ ወቅትም በአካባቢው ያሉ የጤፍ አምራች ገበሬዎች አይተው ተገርመዋል፡፡ እኛም በዚህ መንገድ እናሳጭድ፤›› ማለታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ጤፍ በዚህ መንገድ መታጨድ መቻሉን በመረጋገጡም ገደብ ኢንጂነሪንግ የጀንደር ኮምፓይነሮችን ለጤፍ ማጨጃ እንዲሆኑ ከጀንደር አምራች ኩባንያ ጋር በመነጋገር ኮምባይነሩ ለጤፍ በሚስማማ ደረጃ እንዲመረት የሚያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሞደፊክ የተደረጉትን የኮምባይነሩን ውስጣዊ ዕቃዎች በፋብሪካ ደረጃ    እንዲሠሩና በየጊዜውም የጤፍ ማጨጃው ኮምባይነር እየተሻሻለ እንዲቀርብ የሚደረግ መሆኑንም አቶ ቾምቤ ገልጸዋል፡፡

በሚቀጥለው የምርት ዘመን ይህ መሳሪያ እንደገና ተሻሽሎ እንደሚቀርብም እምነት አላቸው፡፡ በዚህ መሳሪያ የሚሠራው ሥራ የምርት ብክነትን የሚቀንስ ቢሆንም፣ አሁንም የበለጠ ብክነትን እየቀነሰ እንዲሄድ ጥረታችን ይቀጥላል ይላሉ፡፡ ይህንን ማሳያ ያለችግር ለመጠቀም ደግሞ የጤፍ ማሳዎች ድንጋይ የሌለባቸው ከጤፍ ባህሪ አንፃር ማጨጃው ወደ ታች ወርዶ የሚታጨድ በመሆኑ ድንጋያማ ቦታዎች ችግር ሊሆኑ ከመቻላቸው በቀር ጤፍን በኮምባይነር ማጨድ መውቃት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ይላሉ፡፡

ጤፍ በኮምባይነር እያጨድንና እየወቃን ነው ስንል ብዙዎች አላመኑንም ነበር ያሉት አቶ በለው፣ አምጥተን ስናሳያቸው በውጤቱ ተደስተዋል ብለዋል፡፡ ስለዚህ ሌሎች ሰዎችም የእኛን ጅምር ይከተላሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡ ይህን የጤፍ ማጨጃና መውቂያ ሌሎችም እንዲሠሩበት እንዲጠቀሙበት ለማድረግ ግን በጋራ መሠራት አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የኤጀንሲው ባለሙያ እንደገለጹት ደግሞ ኮምባይነር መጠቀሙ የሚያስገኘው ለውጥ ከፍተኛ ቢሆንም ቀድሞ መሠራት የሚገባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ይህም የማሳና የዘር ዝግጅትን የሚመለከት ነው፡፡ በተለይ ጤፍ ሲዘራ በመስመር እንዲሆን ማድረግ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ጤፍን በመስመር መዝራት የተሻለ መሆኑ በመታመኑ በኤጀንሲው በኩል ጤፍ አምራቾች ይህንን አሠራር እንዲለምዱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይኸው ቴክኖሎጂ ጤፍ በመሥመር መዝራት የዘር ፍጆታን እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ አረም እንዳይበረክትም ያግዛል፡፡ ይህ ደግሞ በኮምባይነር የሚሠራውን ሥራ ይበልጥ ውጤት እንዲኖረው በማድረግ አስተዋጽኦ ያበረከታል፡፡

ገደብ ኢንጂነሪንግ መካናይዜሽን ለማጠናከር ተጨማሪ ሥራዎችንም እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የጤፍ መዝሪያ መሳሪያ አስመጥቷል፡፡ ይህ መሳሪያ ለኢትዮጵያ ተብሎ የተመረተ ሳይሆን ከ40 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ለሳር መዝሪያ የሚመቀሙበት ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ ይህንን መሳሪያ እየተጠቀሙበት በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥም ይህንኑ መሳሪያ በማስመጣት ጤፍ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እዲዘራ ያስችላል ተብሏል፡፡

Filed in: Amharic News, News, Politics & Economics

Recent Posts

One Response to "ጤፍ ሠለጠነች"

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.