0

የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት በክብር ተገለጠ

-የሜክሲኮ አደባባይ የራስ ቅርጽ ሙዚየም ገባ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት በክብር ተገለጠ

ፒያሳ አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ቆሞ የነበረውና በምድር ባቡር ግንባታ ምክንያት ብሔራዊ ሙዚየም የገባው የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት በሙዚየሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ በክብር ተገለጠ፡፡

በቀላል ባቡር ፕሮጀክት ምክንያት ከሦስት ወር በፊት ተነስቶና ታሽጎ በብሔራዊ ሙዚየም ግቢ ውስጥ ተቀምጦ የነበረው የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት፣ ሰሞኑን ሕዝብ ማየት በሚችልበት መልኩ በክብር ተገልጧል፡፡ በሐውልቱ ግርጌ ዙርያ የሰማዕቱን ጳጳስ ታሪክ የሚያወሳው ጽሑፍም በወርቃማ ቀለም ደምቆ ይታይበታል፡፡

በ1875 ዓ.ም. ፍቼ የተወለዱትና ከኢትዮጵያ የመጀመርያ አራት ጳጳሳት አንዱና የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ፋሺስት የኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሣ ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር የዘመቱ ሲሆን፣ ከማይጨው መልስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን  ለአርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡

አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች ከሰሜናዊ ምዕራብና በደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺስት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፣ እምቢ ለአገሬና ለሃይማኖቴ ብለው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ በመቀበላቸው ለመታሰቢያቸው ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም. ሐውልት እንደቆመላቸው ይታወቃል።

ብሔራዊ ሙዚየም የቆመው  የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሁለተኛው ሐውልታቸው ሲሆን፣ የመጀመሪያው ሐውልት የኢትዮጵያ ጳጳሳት የአለባበስ ትውፊት ያልተከተለ በመሆኑ ተነቅሎ በመናገሻ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አፀድ እንዲገባ መደረጉ ይታወቃል፡፡

የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ያረፈበት ብሔራዊ ሙዚየም ቅጥር ግቢ በውስጡ ከሚገኙት ልዩ ልዩ ሐውልቶች መካከል ሲኒማ አምፒር ፊት ለፊትና ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ግቢ ተተክለው የነበሩት የቀድሞው ንጉሠ ነገሥት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) ሐውልቶች፣ እንዲሁም የልዕልት ፀሐይ፣ የልዑል መኰንን እና የአሌክሳንደር ፑሽኪን ሐውልቶች ይገኙበታል፡፡

ሚያዝያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ከስፍራው ለጊዜው የተነቀለው ሐውልት የቀላል ምድር ባቡር ግንባታ ሥራው በተያዘለት ጊዜ ሲፈጸም አዲስ በሚገነባው አደባባይ ላይ ሳይለወጥ በ2006 ዓ.ም. እንደሚመለስ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል ሜክሲኮ አደባባይ ቅጥር ውስጥ የነበረው የጥንታዊው ሜክሲኮ ሥልጣኔ መገለጫ የድንጋይ ራስ ቅርጽ፣ ሰሞኑን በምድር ባቡር ግንባታ ምክንያት ከቦታው ተነሥቶ ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ገብቷል፡፡ የኦልሜክ የራስ ቅርጽ በደቡብ ማዕከላዊ ሜክሲኮ ከ3,600 ዓመታት በፊት የነበረው የኦልሜክ ሥልጣኔ መገለጫ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

Filed in: Amharic News, News, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.