0

ትልቅነት የመከራን ጊዜ በመወጣት ይመዘናል !

ዛሬ የዐማራው ሕዝብ ከምንጊዜውም በላይ የኅልውና አደጋ የተጋረጠበት እንደሆነ ተደጋግሞ ተገልጹዋል:: ዐማራው በጥቃቅን ማንነቶች ችግሮችና እኔ ያልኩት ካልሆነ  በሚሉ ልዩነቶች ኅብረቱንና አንድነቱን ማላላት ለከፍተኛ ጥቃት የሚዳርገው መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይሆንም:: ይህን አደጋ መመከት የሚቻለው በአንድነት ነው:: አንድነት የማድረግ ብቃት ማረጋገጫው ብቸኛ መንገድ ነው:: ዐማራው አንድ አንገት እንጅ ብዙ አንገቶች የሉትም:: አንዱ አንገት ከተቆረጠት የሁሉም ዐማራ አንገት ተቆረጠ ማለት ነው:: ይህ እንዳይሆን በአካባቢና በጎጥ ከመለያየት መቆጠብና ወደዚህ ልዩነት የሚያመሩ ንግግሮችን ቀልዶችን ስላቆችን አሽሙሮችን ላለመናገር እርግጠኛ መሆን አለብን::

በዐማራው ክልል አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያና ማቁሰል ራስን በራስ ከመግደልና ከማቁሰል አይለይም:: እጄን በእጄ የምንለው ዓይነት ነው:: ይህ ድርጊት ለዐማራው ትውልድ የወደፊት ጉዞ ጥቁር ነጥብ የጣለ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ መሆኑ ግልጽ ነው::

ችግሩ ታስቦም ሆነ በድንገት ተፈጥሩዋል:: የፈሰሰ ወተት አይታፈስምና ከስሕተቱ በመማር የዐማራ ልጆች በድርጊቱ ሳንደናገጥና ሳንሸበር ሁኔታዎችን ለማረጋጋት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል:: የእኛ ትልቅነት አስተዋይነት አርቆ ተመልካችነት የሚፈተነው በሰላም ጊዜ በምናደርገው ሳይሆን በእንደዚህ ያለው ወቅት በምናሳየው ትብብርና ለችግሮች በምንሰጠው የመፍትሔ ሀሳብ አሻጋሪነት ነው::

ስለሆነም የተፈጠረውን ችግር በልዩ ልዩ መልክ በመቅረብ እገሌ እንዲህ አለ እነገሌ እንዲህ ብለው ነበር ከማለት በመቆጠብ ችግሩ ዘመን ተሻጋሪ እንዳይሆንና እንዳይስፋፋ ነገን ተመልካች የሆነ ሀሳብን በማፍለቅ አንድነታችን ማጎልበት በይደር የምንይዘው ጉዳይ አይሆንም:: “ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን” የምንለው መፈክር እውን የሚሆነው ለዚህ ችግር በምንስጠው ጥበብ ትግሥት ቆራጥነትና አስተዋይነት የተመላበት የመፍትሔ እርምጃ ነው:: ብልኅነት ለሚገጥሙ ችግሮች አለመርበትበት ለሚያጋጥሙ መልካም ነገሮችም ባለመቦረቅ እንደሁኔታው በረጋ መንፈስ የማስተናገድ ጥበብ ነው:: የዐማራው ልዩ ባሕሪም ይህ ነው:: ችግሮችን አጎንብሶ የማሳለፍ ወድቆ የመነሳት ታጋሽና ነገን አሻግሮ የማየት ሥነ ልቦናው የዳበረ መሆን ነው::

በመሆኑም ይህን ችግርም ዐማራው እንደሌሎች ችግሮች ሁሉ በተለመደ ችግሮችን የመሻገር ባህሉ በማለፍ በዐማራው ላይ የተጋረጠውን የኅልውና አደጋ በጽናት በመጋፈጥ የማንነቱና የአገሩ ባለቤት የመሆንን  ተጋድሎ እጅ ለእጅ ተያይዞ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፎ ከግቡ ለመድረስ ተግቶ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል! ትልቅነት የመከራን ጊዜ በመወጣት ይመዘናልና ዐማራው ይህን የገጠመውን የኅልውና አደጋ ለመወጣት በሚወስደው የአሰባሳቢነትና የታሪካዊ ድርሻን የማበርከት ሚናው የሚለካ ይሆናል:: በዚህ አጋጣሚ በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ኤታማጆር ሹም እና በዐማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድርና በሥራ ባልደረቦቹ ላይ በተፈጸመው ግድያ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የተሰማውን ሐዘን ይገልጻል:: መገዳደል ለአገራችን ችግሮች መፍትሔ እንደማይሆንም ዐኅኢአድ ያምናል:: የአገራችን ችግሮች መፍቻ ቁልፉ ዉይይት ክርክርና በነዚህ ውይይቶችና  ክርክሮች ነጥረው የወጡ ሀሳቦች ገዥነት ብቻ እንደሆነ ዐኅኢአድ ጽኑ እምነቱ ነው::

 

የዐማራው ኅልውና ትግል በልጆቹ የተባበረ ትግል ዕውን ይሆናል!

 

Filed in: Amharic News, News, Politics & Economics, Politics & Openion, Social & Culture, መቅደላ Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.