0

የእኔ ባዮች እንዴት የእኛ የሚሉትን ለሌሎች አሳልፈው እንዲሰጡ ይጠበቃል?

የእኔ ባዮች እንዴት የእኛ የሚሉትን ለሌሎች አሳልፈው እንዲሰጡ ይጠበቃል?

አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች አዲስ አበባ በእነርሱ አጠራር “ፊንፊኔ” የእኛ ናት ብለው ራሳቸውን ካሳመኑ ቆይተዋል:: የዚህ እምነታቸው መነሻም  በ1830ዎቹ ጀርመን የመካከለኛውን አፍሪካ በቅኝ ግዛቱዋ ሥር ለማዋል ያላትን ዓላማ ለማስፈጸም የሠራችው የስለላ ሥራ ውጤት መሆኑ ነው::  ጀርመን ይህን  ዓላማዋን ተግባራዊ ለማድረግ ጥናት እንዲያጠና ዮሓን ክራፍ የተባለ ሚሽነሪ በሃይማኖት ማስፋፋት ስም ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ አደረገች:: ክራፍ ኢትዮጵያን ተዘዋውሮ በማጥናት ከሸዋ በስተደቡብ ያለው አካባቢ በዚያን ጊዜው አጠራር “ጋላ” ዛሬ ኦሮሞ የሚባለው ነገድ በሥፋት የሠፈረባቸው አካባቢዎች አንድ ዓይነት ቁዋንቁዋ እና አንድ ዓይነት የአስተዳደር ግዛት ቢሰጣቸውና በጀርመን ቀጥጥር ሥር ቢውሉ በነርሱ መረማመጃነት መካከለኛውን አፍሪካ የጀርመን ቅኝ ተገዥ ማድረግ ይቻላል ከሚል ድምዳሜ ይደርሳል:: ለዚህ ዓላማው ተፈጻሚነትም ግዛቱን “ኦሮሚያ” ብለን ነገዱን “ኦሮሞ” ብንልና ቁዋንቁዋውን “ኦሮሚኛ” ብንለው ነገዱ በአንድ እንዲቆም  ተመሳሳይ ሥነልቦና እና ወጥ ትርክት ለመሥራት ያስችላል የሚል ሀሳብ ለጀርመን መንግሥት የጥናቱን ውጤት አቀረበ:: ይህ ሀሳብ በጀርመን መንግሥትና በተለያዩ አገር አሳሾች የተለያየ ትርጉምና እንደምታ ተሰጥቶት የጀርመን ፍላጎት ዕውን ባይሆንም  ክራፍ በደንቢ ደሎ መሥርቶት በሄደው የካቶሊክ ቤተ እምነት ቀስ በቀስ እንቁላሉ እየተፈለፈለና እየተራባ ለግራው ዘመም ትውልድ ደረሰ::

ግራ ዘመሙ ትውልድ ለውጥ ለማምጣት ከውስጥ ወደ ውጭ ከማዬት ይልቅ  ከውጭ ወደ ውስጥ ያነጣጠረ ስለነበር የኢትዮጵያዊነት የወል እሴቶች የነበሩትን እንደ እርካሽ ነገር በመጠየፍ ውጭ አምላኪ ሆነ:: ትውልዱ ውጭ ማምለክ ብቻ ሳይሆን  የተወሰነው የኢትዮጵያ ችግር “የመደብ ጭቆና እና ብሔራዊ ጭቆና” ነው ሲል ሻዕቢያ እና ኦነግ “በዐማራ ቅኝ የተያዝን ነን” በማለት የመገንጠል ዓላማ ይዘው ተንቀሳቀሱ:: ሁሉም ግን ባንድ ነገር ይስማማሉ:: “ገዥው መደብም  ጨቁዋኙ ብሔርና ቅኝ  ገዥውም ዐማራ” የተሰኘው ነገድ ነው ብለው ያምናሉ::

ኦነግ በዚህ እምነቱ በመግፋት የዓላማው ማስፈጽሚያና  የጥያቄው ትክክለኛነት ማሳያ የዮሓን ክራፍን ሀሳብ በሙሉ ልብ በመቀበል የጀርመን መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፉን እንዲሰጠው በማድረግ የነገዱን ስም ኦሮሞ  ቁዋንቁዋውን ኦሮሚኛ በማለት  ኦሮሚያ የምትባል ሀገር ከኢትዮጵያ ቆርሶ ለመመሥረት ግቡ አድርጎ ተንቀሳቀሰ:: ለዚሁ ዓላማው ስምረትም “ገዳ መልባ” የተሰኘ የሀሰት ድርሳን ደርሶ ትውልዱን ኢትዮጵያና ዐማራ ጠል አድርጎ ቀረጸው:: ዘመዶቻችን “ገንፎ ሲያምርበት ተንከባሎ ቅቤ ማሰሮ ይገባል” እንደሚባለው የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት ሲፈነዳ  በኃይሌ ፊዳ የሚመራው “መኢሶን” ለደርግ “ድጋፍ ከሂስ ጋር” በሚል እሳቤ በፖለቲካው ቁንጮ ላይ መውጣት ያላንዳች ችግርና ውዝግብ “ጋላ” የሚለው መጠሪያ ትክክል አይደለም:: መባል ያለብን “ኦሮሞ” ነው በማለት ነገዱን “ ኦሮሞ” ብለው ቁዋንቁዋውን “ኦሮሚኛ “ ለማሰኘት በቁ:: ከመኢሶን በተጉዋዳኝ ኢጭአት(የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል) በሚል ድርጅት ሽፋን ኦነግ የተሰኘውን ድርጅት እንዲደራጅ ዕድል አገኘ:: መኢሶን “አብዮት ልጁዋን ትበላለች” በሚለው የራሱ መፈክር በአብዮቱ ተበልቶ ከፖለቲካው መድረክ ተገፍቶ ወጣ::

ኦነግ ከኢትዮጵያ በትጥቅ ትግል የመገንጠ ዓላማውን በወለጋ እና በሐረርጌ ክፍለ ሀገሮች በማካሄድ እስከ ደርግ ውድቀት 1983 ግንቦት 20 ቀን ቆየ:: በሻዕቢያ በሕወሓትና በኦነግ እርዳ ተራዳ ትግል የአንድነት ኃይሉ ተበታትኖ ማዕከላዊው መንግሥት ሲወድቅ ሻዕቢያ ኤርትራን ገንጥሎ አሥመራ ላይ መንግሥት ሲመሠርት ወያኔና ኦነግ ሌሎች የወያኔ ፍጡሮች የሆኑ የነገድ ድርጅቶችን አካተው የሽግግር መንግሥት መመሥረታቸው ይታወቃል:: የሽግግር መንግሥት የተሰኘውም የሚመራበት ቻርተር ሲያጸድቅ ዐማራን የሚወክል አካል እንዲካተት ባለመፈለጉ ብቻ ሳይሆን እንዲጠፋ ቁርጥ ዓላማ የተያዘበት ስለነበር አልተገኘም:: ዐማራው ባልተገኘበት ጉባዔም አገሪቱን በቁዋንቁዋ በመከፋፈል በመጀመሪያ በ14 ክልሎች ቀጥሎም በ9 ክልሎች እና  በሁለት የከተማ አስተዳደሮች በበሸንሸን አጥፊና ጠፊ ሆነው እንዲደራጁ ተደረገ::  በፈለጉ ጊዜ መገንጠል የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ተሰጠ:: ከዚህ የቁዋንቁዋ ክፍፍል ክልሎች ውስጥ ያገሪቱ ለምና ሠፊ ግዛት የሆነውን “ኦሮሚያ” በማለት ለኦነግና ለወያኔ ፍጡር ለሆነው ኦሕዴድ/ኦዴፓ አስረከቡት:: ይህም  “የጠሉት ይወርሳል የፈሩት ይደርሳል” የሚሉት የአባቶቻችን ብሂል እውነት ሆኖ የዮሓን ክራፍ  ለጀርመን ቅኝ ግዛትነት ያዘጋጀው መነሻ ሀሳብ በሻዕቢያ በሕወሓትና በኦነግ የጋራ ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ ዐማራ ትግል እውን ሆነ:: ኢትዮጵያም በምዕራባውያን ቅኝ ገዥ ኃይሎች ኅልውናዋ ሳይደፈር በገዛ ልጆቹዋ ለክፍፍልና ለውርደት በቃች::

የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኞች ከሻዕቢያ እና ከሕወሓት ጋር በማበር ከ1981 እስከዚህ ጊዜ ድረስ በወለጋ በኢሉባቡር በሐረርጌ በአርሲ ማለትም በአሰቦት ገዳም በገለምሶ በመቻሬ በአርባጉጉ ወዘተ በዐማራው ላይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል እንዲፈጸም አደረጉ:: ይህ በዐማራ ላይ የተፈጸመ የዘር ዕልቂትና ጥቃት የዐማራውን ልጆች አስቆጥቶ የትግሬ ወያኔን አገዛዝ አምሮ መታገል ሲጀምር  በ1987 በወያኔ ተገፍቶ ከፖለቲካው ዕምብርት የወጣው ኦነግ ውስጣዊ ሥራውን መለስ ዜናዊ እንዳለው “እንደፈጣን ሎተሪ ሲፋቅ ኦነግ በሚሆነው ኦሕዴድ” አማካኝት የማደራጀት ሥራውን አከናውኖ ባደራጀው “ቄሮ” በተሰኘ የነውጥ ቡድን ከሌሎች  ለውጥ ፈላጊ ኃይሎች  ጋር  እንደ “ፋኖ” እና “ዘርማ” በመሳሰሉት ቡድኖች በተደረገ ግፊት ጋር ተዳምሮ በሕወሓት አመራር ላይ በፈጠረው ጫና በዶር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የለውጥ ቡድን የፖለቲካ መዘውሩን እንዲጨብጥ ማስቻሉ ይታወቃል::

የለውጥ ቡድኑ ባለፉት 27 ዓመታት አገዛዙ ሆን ብሎ እንዲጠፉ የበየነባቸውን የኢትዮጵያዊነት ዕሴቶችን ማለትም ኢትዮጵያዊነት አንድነት ዕኩልነት  ሃይማኖት  መቻቻል አብሮነት ይቅርታና ፍቅር የተሰኙትን በመስበኩ ምላተ ሕዝቡና ተቃዋሚ የተሰኘው ኃይል ሁሉ እስቲ አድሮ እንዬው  “አስቀድሞ ማመስገን ለሜት ያስቸግራል” ወዘተ ሳይል ሙሉ ድጋፉን ሰጠው::  ይህ ድጋፍ ግን  ወርድና ቁመት ከመጨመር ይልቅ ወደ ሁዋላ የመመለስ  አጋጣሚው እየጎላ መታየት ጀምሩዋል::  የዚህም ማሳያዎቹ:-

  • ኦነግ በወለጋ በሐረርጌና መሰል ክፍለሀገሮች ጦርነት ከፍቶ ሕይዎት ሲቀጥፍ እና 18 ባንኮችን ሲዘርፍ
  • ሻሸመኔ ላይ የሰው ልጅ በ21ኛው ክፍለዘመን ላይ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ ተቀጥቅጦ ሲገደል
  • በአዋሳ የሲዳማ ብሔርተኞች በወላይታ ነገድ ተወላጆች ላይ የመንጋ ፍርድ በመስጠት አያሌ ሕይዎት ሲጠፋና ንብረት ሲዘረፍ
  • ውልቂጤ ውስጥ በጉራጌና ቀቤናዎች መካከል ብጥብጥ ሲፈጠር
  • በአዲስ አበባ ቡራዩ ነዋሪዎች ላይ ግድያና ዘረፋ ሲካሄድ
  • በቡሮ ሆራ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበሩ የዐማራ ልጆች በማንነታቸው ምክንያት ሴቶቹ በቡድን ተደፍረው በግፍ እንዲባረሩ ሲደረግ
  • በወያኔ ትብብር የቅማንት ኮሚቴ የሚባለው ነገዱን አደራጅቶ በጎንደር ላይ ሽብር ሲያካሂድ
  • ከሁሉም በላይ ከፍተኛ የሆነ ኢሰብአዊ ድርጊት የፈጸሙት የሕወሓት አባሎች መቀሌ መሽገው ለሕግ አንገዛም ሲሉ የለውጡ ኃይል የመንግሥትን ሚና መጫወት ባለመቻሉ የሕዝቡ ማኅበራዊ ሕይዎት በሽብር እና በስጋቻ እንዲዋጥ አድርጎታል::

 ከሁሉም በላይ የለውጡ ግንባር ቀደም ነው የሚባለው በለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አዲስ አበባን በሚመለከት ያውጣው ያቁዋም መግለጫና ይህኑ በሚመለከት ኦዴፓ የሰጠው መግለጫና “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” ከሚለው የዶር ዐቢይ አነጋገር ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ የቆመ መሆኑን ማስተባበል አይቻልም::

በሌላ በኩል የለወጥ ኃይሉ በተለይም የቲም ለማ ቡድን በአክራሪ የኦነግ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር የወደቀ በሚያስመስል ሁኔታ የለውጥ ኃይሉ እመራበታለሁ የሚለውን ሕገ መንግሥትና ለሁላችንም የምትሆን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንገነባለን ከሚሉት ሀሳብ በፍጹም ተፃራሪ የሆነ ድርጊት በኦዴፓ አመራር ሲፈጸም እና  “ፌደራላዊ ሥርዓቱን ለድርድርሽ አናቀርብም  በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄና በኦሮምኛ ቁዋንቁዋ ላይ እየሠራን ነው” የሚል መግለጫ ሲያወጣ  በታከለ ኡማ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ለገጣፎ በሚባለው አካባቢ ከሥርዓቱ ጋር በተቆራኘ ብልሹ አሠራር ቦታ ገዝተው ቤት ቀልሰው የሚኖሩ ዜጎችን ካለበቂ ማስጠንቀቂያ በማንነታቸው  እየተለዩ  በላያቸው ላይ  ቤታቸው እንዲፈርስ መደረግና ከጉሮሮአቸው እየቆጠቡ የጋራ መኖሪያ ቤት የሠሩ ወገኖች ቤቱ ለነሱ አይገባም!  መሰጠት ያለበት ለኦሮሞ ወጣት ነው! በማለት አስተዳደሩ የወሰደው አቁዋምና የኦሮሚያ ክልላዊ  መንግሥት ይህኑ ደግፎ የሰጠው መግለጫ ለሁላችንም የምትበቃ አገር አለችን በማለት ዶር ዐቢይ በተደጋጋሚ ከሚነግሩን የተቃረነ መሆኑ ግልጽ ነው:: ይህ  ከኦሮሞ ውጭ ያለውን ዜጋ  በተለይም በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የሚኖረውን ከኦሮሞ ውጭ ያለውን ዜጋ ሕይዎት ሥጋቻ ላይ የጣለ ብቻ ሳይሆን በለገጣፎና በሰበታ ነዋሪ በሆኑ ዜጎች ላይ የታዬው የቤቶች ማፍረስ ዘመቻ የተሰበከለት አብሮነት “አያ በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” ሲሉ ዶር ዐቢይ “በእርካብና መንበር” መጽሐፋቸው ያስነበቡን ሀሳብ በገሀድ መገለጡን ያሳያል::

ይህን ሀሳብ የሚያጠናክረው ሌላው ገጠመኝ አቶ ሌንጮ ለታ(ዮሐንስ ለታ) እና  ዶር ዲማ ነገዎ(ዮሐንስ ነገዎ) በአዋሳ ከተማ የሲዳማ ነገድ ያቀረበውን የክልል ጥያቄ ተገቢነት ለመመሥከር ባደረጉት ንግግር ለውጡ የአገሪቱ የፖለቲካ ሥልጣ ከሸዋ ወደ ደቡብ የተሸጋገረበት መሆኑን ገልጸዋል:: ይህም ማለት ሥልጣን ከትግሬና ከዐማራ ነጥቀን ከኦሮሞ እጅ እንዲገባ አድርገናል ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው:: ቢሸፍጡ እንጂ ዐማራ ብቻውን ሥልጣ ላይ የቆየበት ጊዜ የለም:: ሁለቱ የኦነግ ነባር አመራሮች  ይህን ለውጥ እንዳይቀለበስ በደቡብ ክልል የሚገኙ ነገዶች በማንነታቸው ተደራጅተው ከኦሮሞ ጎን እንዲቆሙ ከማስገንዘባቸውም በላይ አዲሲቱዋ ኢትዮጵያ ካለፉት በተሻለ ለምስራቅ አፍሪካ ትምህርት ሊሰጥ በሚያስችለው በገዳ ሥርዓት በመመራት የነገዶች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በሚያረጋግጥ መልኩ መከወን እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተዋል:: ያለው ሕገ መንግሥት እነርሱ እንዳዘጋጁትና ወሎ አዲስ አበባና ጎጃም የኦሮሞ አካል አድርገው አካተውት እንደነበር ሆኖም በነበረው ሕወሓት ጉዳዩ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ተገፍተው እነዚያን ማጣታቸውን በቁጭት ሲናገሩ ተደምጠዋል:: ደቡቡን በተመለከተም እያንዳንዱ ነገድ በክልል እንዲደራጅ አድርገው እንደነበር ሲዳማና ጌዲዮ አንድ ክልል እንደነበር አውስተው ሁሉም የየራሱን ክልል መመሥረት እንዳለበት በማስረዳት የሲዳማ ነገድ ለክልል መብቱ መከበር እስካሁን ከጎኑ ቆመው እንደረዱት ሁሉ አሁንም ከጎናቸው እንደሚቆሙ ቃል ገብተዋል:: ይህም ኢትዮጵያን የመከፋፈልና የማዳከም እንጂ የማጠናከርና የአብሮነት ዓላማን የሚቃረን መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም::

በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄን ተንተርሶ እያወዛገበ ያለውን ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመራር ለችግሩ መፍትሔ የሚያጠና ስምንት ኣባላት ያሉት ኮሚቴ ማቁቁሞን አሳውቁዋል::  ከስምንቱ አባላት አምስቱ የኦነግና የኦዴፓ አመራር አባላት መሆናቸው ደግሞ ያደባባይ ሚስጢር ነው:: ከሐሰት ተነስቶ እውነት ላይ መድረስ ስለማይቻል በኮሚቴው ውስጥ የተካተቱት ግለሰቦች ማንነት ሲታይ “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ” የሚባለው ዓይነት በመሆኑ ሕዝቡ የዐቢይን አመረር ከጥርጣሬ በዘለለ እንዲመለከተው እያደረገ ነው::

ማንም እንደሚገነዘበው የአገሪቱ ፖለቲካ ገዥ ሀሳብ የማንነት ጉዳይ ነው:: ሁሉም ለእኔ ለእኔ ባይ በሆነበት የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ከሁሉም በላይ “ፊንፊኔ የእኛ ናት” “የኦሮሚያ ማዕከል ናት” የሚል አቁዋም ያላቸውንና ለዚህም ዕውን መሆን አምረው የሚሠሩትን የኦነግና የኦዴፓ አመራር ሰጭዎችን በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ማስገባት “ተጨፈኑ ላሞኛችሁ” ከሚባለው አባባል የተለየ ነገር የለውም::

የዚህ ኮሚቴ አመሠራረት በራሱ በዐቢይ አመራር ላይ ወጥ አመለካከት የጎደለው እንደሆነ ያሳያል:: የአዲስ አበባ ወሰን ጉዳይ እንደዚህ አጨቃጫቂ ከሆነ ቀደም ሲል በምክር ቤቱ እውቅና ተሰጥቶት ለተቁዋቁዋመው የወሰንና የማንነት ኮሚሽ ጉዳዩ መመራት ነበረበት:: ይህ ካልሆነ ደግሞ አዲስ አበባ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 መሠረት ራሱን የቻለ አስተዳደር የመመሥረት መብት ያለው በመሆኑ ነዋሪዎቹ ጉዳዩን አውቀው ለችግሩ እልባት እንዲሰጡ መብቱ ሊሰጣቸው በተገባ ነበር:: ይህም ካልሆነ በከተማው የሚኖሩት የነገዶች ስብጥር ሚዛን ውስጥ ገብቶ ሙያና መልካም ሥነምግባር ያላቸው ሰዎች ተጠንተው አጥንተው እንዲያቀርቡ መደረግ ነበረበት:: ከዚህ ውጭ የተሰየመው ኮሚቴ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፍላጎት ጋር የሚጣጣም የጥናት ውጤት እንኩዋን የማያመጣውን ቢያመጣም ታማኒነት ይኖረዋል ለማለት አይችልም:: ምክንያቱም  አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት  ብለው ለዘመናት በሀሰት ድርሳንና ትርክት ራሳቸውን ያሳመኑ ሰዎች በአጋጣሚዎች መገጣጠም ከመሐል እጃቸው ሥልጣን የገባላቸው  ቡድኖች ለእኩል ተጠቃሚነት የሚበጅ ሀሳብ ያቀርባሉ ብሎ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትም ሆነ ሌሎች አካላት ለማመን ይቸራሉ::  በመሆኑም የዐማራው ነገድ ልጆች አዲስ አበባ የነዋሪዎቹዋ እንጂ  የማንም  አንጡራ ሀብት አይደለችምና ይህ መብት እስኪረጋገጥ ድረስ በቆራጥነት መታገል የኅልውና ጉዳይ ነውና በንቃት ትግሉን  መቀላቀል  ቀጠሮ የሚሠጠው አደለም::የእኔ  ባዮች እንዴት የእኛ የሚሉትን ለሌሎች አሳልፈው እንዲሰጡ ይጠበቃል?

ከዚህ በተጉዋዳኝ የለውጡ ዓላማ በታሰበው መልኩ እየቀጠለ ነው ከማለት ይልቅ ለውጡ ተቀልብሱዋል የሚለው የድርጊትና የሀሳብ መገጣጠም በግልጽ ያሳያል:: ማሳያዎቹም ከፍ ሲልን የተጠቀሱት መረጃዎችና ከለውጡ መሪዎች አንዱ የሆነው ለማ መገርሳ  “የታገልነው ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ነው !” “በፌደራል ሥርዓቱ አንደራደርም”  በፖለቲካ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ከተሜ ነው:: ከዚህ አንፃር አዲስ አበባንና ሌሎች ከተሞችን ኦሮሞ ጠቀም ለማድረግ ማኅበራዊ ሥብጥሩ እንዱለወጥ አጥበን እየሠራን ነው:: ለዚህም ከአምስት መቶ ሽ በላይ ከሶማሊያ የተፈናቀሉ ኦሮሞዎችን ከፍላጎታቸው ወጭ በአዲስ አበባ እንዱሠፍሩ አድርገናል   ሲሉ የሰጡዋቸው መግለጫዎች እና በለገጣፎና በሰበታ ቀበሌዎች  ከኦሮሞ ውጭ ያሉትን ዜጎች ቤቶች ለይተው እንዲፈርሱ ከማድረጋቸው ሌላ ከአምስት ሽህ በላይ የሆነ የኦነግ እና የኦዴፓ ታጣቂ በአዲስ አበባ ዙሪያ ጥበቃ እንዲሠማራ ማድረጋቸው ሰላማዊ ለውጡን ወደ ደም አፋሳሽ ሁኔታ እየገፉት እንደሆነ ግልጽ አመላካች ነው::

በዚህ ደም አፋሳሽ ሁኔታ የቅድሚያ ተጠቂ እንዲሆን የታቀደውም ዐማራው እንደሆነ ላለፉት አርባ ምናምን ዓመታት የተሰበከው ፀረ ዐማራ ፕሮፓጋንዳ ግልጽ ማሳያ ነው:: ዐማራው የዚህ የዘመናት የጥፋት ዕቅድ ሰለባ ላለመሆን በማንነቱ ዙሪያ ተደራጅቶ ኅልውናውን ለማስቀጠል የመከላከል አቅሙን ማጎልበት ለነገ ይደር የሚለው ጉዳይ አለመሆኑን ሊገነዘብ ይገባል:: ለዚህም ራስን ከጥፋት የመታደግ ዓላማ  ዕውን መሆን በዐማራ ስም የተደራጁ ድርጅቶች ወደ አንድነት መጥተው ዐማራውን ከተጋረጠበት የጥፋት አደጋ ሊታደጉት እንደሚገባ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ጥርውን ያቀርባል::

 

የዐማራው ኅልውና በልጆቹ ቆራጥ ተጋድሎ ይከበራል!

 

 አዲስ  አበባ  የነዋሪውቹዋና የመላው ኢትዮጵያ  መዲና ናት!

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Openion, መቅደላ Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.