0

አዲስ አበባችን የሁላችንም ካልሆነች የማንም አትሆንም !

አዲስ አበባ የሁላችንም ካልሆነች የማንም አትሆንም!

“ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”  ያሉን አቶ ለማ መገርሳ አዲስ አበባን የኦሮሞ የግል ሀብት ለማድረግ ጠንክረው  እየሠሩ  እንደሆነ  የካቲት 28 ቀን 2011ዓም በወጣው የክልሉን መንግሥት አቋም በሚገልጸው መግለጫ አረጋርጠዋል:: መግለጫውም እንዲህ ይላል “በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር የወሰን ጉዳይ እልባት ሳይሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ መተላለፋቸው ተገቢ አይደለም::” ይላል::  መግለጫው አያይዞም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በሁሉም አቅጣጫ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ደረጃ በደረጃ እየሠራ መሆኑን  አጽንዖት ሰጥቱዋል:: በዚህም ትላልቅ ስኬቶች እየተመዘገቡ እንደሆነ መግለጫው በኩራት  ያብራራል:: የአዲስ አበባ ጉዳይ በተመለከተ እና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ስላላቸው  ጉዳዮች በሙሉ በቅደም ተከተላቸው መልስ እንዲያገኙ በተሃድሶ ከስምምነት ላይ የተደረሰበት እንደሆነ በማውሳት  ይህ ዕውን እንዲሆንም  አበክረው እየሠሩ እንደሆን መግለጫው አልሸሸገም:: ከሁሉም  በላይ መግለጫው በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር የወሰን ጉዳይ አልባት እስከሚያገኝ የኦሮሚያ ክልል ጥያቄ እያነሳባቸው ባሉ የአዲስ አበባ አዋሳኝ ቀበሌዎች ከክልሉ ወሰን አልፈው የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች በዕጣ  ማስተላለፍ ትክክል እንዳልሆነ በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ዕምነት እንደሆነ ያስረዳል::

በዚህ አቋሙም መሠረት ይህ ውሳኔ ሥራ ላይ እንዳይውል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጠንካራ አቋም መያዙን ይገልጻል:: “ዶሮን ሲያታልሉዋት በመጫኛ ጣሉዋት” እንደሚባለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት  ይህን አቋም የያዘው  በቀዳሚነት የኦሮሞን ሕዝብ  ተጠቃሚነት ከማስጠበቅ የመነጨ እንጂ የሀገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች  አብሮ የመኖር ዕሴትን  ከመጥላት የመነጨ አለመሆኑ ከግንዛቤ ሊገባ ይገባልም በማለት ሌሎች ነገዶችን ለማሞኘት ሞክሩዋል:: ሞኝ ከተገኘ! በሌላ በኩል መግለጫው በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ተያይዘው የሚከናወኑ ሥራዎች ከክልሉ መንግሥትና ሕዝብ እውቅና ውጪ ለመሥራት መታቀዳቸው ሕጋዊነት አላቸው ብሎ እንደማያምን ያስጠነቅቃል:: ይህንም ማስጠንቀቂያ እንዲህ በማለት ያጠብቀዋል፦

“ትናንት ከህዝብ ጋር የታገልነው የህዝቡን ችግሮች ለመቅረፍ እና ህዝቡን ወደ ተሻለ ብልፅግና ለማሸጋገር ነው:: ዛሬም ቢሆን ትናንት ለህዝቡ ቃል የገባናቸውን ድሎች እያስመዘገብን መተናል፤ ይህንንም በማስቀጠል ማንኛውንም የህዝብ ጥያቄ በትግል ለማስመለስ አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን” ብሏል:: አያይዞም የኦሮሞ እና የኦሮሚያ መብትና ጥቅምን በማስከበር ወደተሻለ ብልፅግና ለማሸጋገር እንሠራለን በማለት ኢትዮጵያዊነትን የሁዋሊት አሽቀንጥሮ መጣሉን በማያሻማ መንገድ ነግረውናል::  ይህን መግለጫ የቄሮው መሪ ነኝ ከሚለው ጀዋር መሐመድ “አዲስ አበባን በጡጫም በእርግጫም” ብለን የኦሮሚያ እናደርጋታለን “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” ከሚሉት  ኦነጋዊ ንግግር  እና “የፌደራል ሥርዓቱን ለድርድር አናቀርብም” ከሚለው የኦዴፓ መግለጫ ጋር አያይዘን በወያኔ ተይዘው የነበሩ ቁልፍ መንግሥታዊ መዋቅሮች በነማን እንደተያዙ ስናጤንና የአቶ ለማን የሚኒሶታ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ከፋችነትን ስናገናዝብ ኢትዮጵያዊነት “ሱስ ነው” የሚለው የአቶ ለማ ንግግር እውነትም ሱስነቱ ይፋ መሆኑን እንርዳለን::  ምክንያቱም ሱስ መጥፎ ልማድ በመሆኑ ይተዋል:: ይጣላል እና! ኢትዮጵያዊነት ቅር ቢሉት የማይቀር የቀትር ጥላ ነው::  ልጣልህ ቢሉት የማይጣል ከኅሊና ጋር ተጣብቆ የሚኖር የማንነት መንፈስ እንጂ ሲሹ የሚያነሱት ሳይሹ ሲቀሩ የሚጥሉት ሱስ አይደለም:: ለነለማ ቡድን ግን ኢትዮጵያዊነት ማንነት ሳይሆን ሱስ በመሆኑ ይኸውና አሽቀንጥረው ለመጣል የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ሲናገሩና ሲፈጽሙ እያየን ነው።

አዲስ አበባ የአንድ ነገድ አንጡራ ሀብት ናት ብለን በማመን ሌሎቹን “ሠፋሪዎች” ናቸው እያልን አብሮነትና ኢትዮጵያዊነትን አልፎም  ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንገነባለን የምንለው እንዴት  ተብሎ ነው? ዲሞክራሲ መቻቻል እንጂ አንዱ ነገድ በሌሎች ላይ በማነሳሳት  በሌሎች ላይ የሚጭን አይደለም:: የሁሉንም ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንጂ የእንዱ ብቸኛ ተጠቃሚነት ማርጋገጫ አይደለም::  ሰጥቶ በመቀበል እንጂ የእኔ ብቻ የሚል አይደለም:: በሀሳብ የበላይነት የሚያምን እንጂ ያልበሰሉ ጮርቃዎችን አሰባስቦ የመንጋ ፍርድ የሚሰጥ አይደለም:: ለብዙኃን ወሳኔ ተገዥነትና  የጥቂቶችን መብት አስከባሪ  መርሕ እንጂ  እኛ ያልነው ካልሆነ የሚል ሃይማኖታዊ ቃል አይደለም::   በሕግ የበላይነት በጽኑ የሚያምን ሥርዓት እንጂ በቡድኖች አመጽና ሁሉንም ለእኔ በሚሉ የሚመራ እይደለም:: እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በቅድሚያ መሪዎች የሥርዓቱን ባሕሪይ ጠንቅቀው ሊያውቁ ይገባል:: ያለበለዚያ ያላዋቂ ሳሚ…. ነው የሚኮነው::  ኢትዮጵያውነት የልዩነቶች ውኅደት የፈጠረው የወል ማንነት መገለጫ የሆነ እኛነት ነው:: ይህ እኛነት ዘመን ተሻጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ሃይማኖት ለመሆን የበቃ ነው:: በደቡብ አፍሪካ ተመሥርቶ የነበረውንና  ኒዮርክ ከተማ ያለውን የአቢሲኒያ ቤተ እምነት (Abyssinian Baptist Church) ልብ ይሉዋል::

ኢትዮጵያዊነት ታላቅ የስበት ኃይል ነው:: የታላቁ ዮሐንስ ግዛትን ለማወቅ ከዓለም ዙሪያ የጎረፉትን ሰዎችና የጻፉዋቸውን ገድሎች ላገላበጠ ሰው የስበት ኃይሉዋ ምን ያህል እንደሆነ ይረዳል:: ኢትዮጵያዊነት የነፃነት ቀንዲልነት ነው :: ኢትዮጵያዊነት ነፃነት ነው:: የነፃነት ሚስጥሩም ልዩነታችን ሳይሆን በልዩነታችን ውስጥ ያለው አንድነት፣ የጋራ እሳቤ፣ የጋራ ዓላማ መያዝ ነው። የሃይማኖት ልዩነትም ሆነ የቋንቋ ልዩነት የመለያዬት ምክንያት ሆኖ የኢትዮጵያን ነፃነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቶ አያውቅም ነበር።   ለጥቁር ዓለም ሕዝቦችና በቅኝ ግዛት ተጠፍረው ተይዘው ለነበሩ የአፍሪካ የእስያና የላቲን አሜሪካ ሕዝቦችም የነፃነትን ዋጋ ያሳየ ነው:: ኢትዮጵያዊነት የዓለምን የፖለቲካ አሰላለፍ የቀየረ አስደናቂነትና አይበገሬነት ነው::  በ1896 ዐድዋ ላይ በጣሊያ ላይ ያስመዘገበችው ድል የዚህ ሁሉ ማሳያ ቁዋሚ ሰሌዳ ነው::

እነዚህ ሁሉ ድንቅ ጉዳዮች በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት የተገነቡ የሁላችንም መኩሪያና መመኪያ የወል ዕሴቶቻችን ናቸው:: እነዚህን ላንዱ ነገድ ልስጥ ወይም ልውሰድ ማለት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነውን አንዱን አካል ከጠቅላላው መነጠል ማለት ነው:: ይህ መነጠል ደግሞ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ማንነትን አያመለክትም::  ስለሆነም የኦሮሚያ መንግሥት የያዘው ኦሮሞን ብቸኛ የኢትዮጵያ ሀብት ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘ አቁዋም ኢትዮጵያዊነትን በጽኑ የሚፃረር ነው:: ሲጠብ  አዲስ አበባ ከሁሉ ቀድማ የነዋሪዎቹዋ መኖሪያ ከተማ ናት:: ስለከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገትም ሆነ የኑሮ ዘይቤ ወሳኞቹ ነዋሪዎቹዋ እንጂ ኦዴፓ ሊሆን አይገባም:: ሲሰፋ ደግሞ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መዲና ናት:: የፌደራል መንግሥት ተቋማትና የመሳሰሉት ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚሰበሰብ ግብር የተገነባች፣ ሁሉም ዜጎቿ ዋና ከተማችን የሚሏት፣ በዙሪያዋ ያሉትም በሩቅ ካሉት በተሻለ ሁኔታ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተጠቃሚ የሚሆኑባት ከተማ ናት። ይህ ደግሞ በማንኛውም ከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች እነደየሁኔታው ተጠቃሚ እንደሚሆኑት ማለት ነው። ከዚያ ባለፈ ግን የኢትዮጵያዊነት ባህል ሃይማኖት ኢኮኖሚ የኑሮ ዘዴና ቋንቋ ተለውሶ የተቦካባት ገበቴ ስለሆነች የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ሙዚዬም ናት:: በመሆኑም አዲስ አበባ የሁላችንም እንጂ የኦሮሞ የግል ሀብት አይደለችም:: እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ በየትኛውም ዓለም ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም። አዲስ አበባ የሁላችንም ካልሆነች የማናችንም አትሆንም:: “የማን ቤት ጠፍቶ የማን ይበጅ የአውሬ መውለጃ ይሆናል እንጂ!” እንደሚባለው:   ይህ ግን ለማንም አይጠቅምም:: የሚጠቅመን እንደአባቶቻችን ተቻችለን ይቺን ውብ ድንቅና በሁለመናዊ ሀብት የደለበች ግን አስተዋይ የፖለቲካ ተወናዋዮች ያጠጡዋት ሀገር  እያላት ከመቸገሩዋ በላይ ቆራርሰን ለበዮች እንዳናስረክባት የቄሮ መሪዎችና ኦነጋውያን ሀግ ሊባሉ ይገባል:: ወደ ሁዋላ እንይ ከተባለ ዛሬ “ ሠፋሪ” የሚሉ ሰዎች ወራሪና መጤ ሊባሉ እንድሚችሉ ልናስገነዝባቸው እንውዳለን::

 

አዲስ አበባ የነዋሪዎቹዋ እንጂ የኦሮሞ አደለችም!

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Economics, Politics & Openion, Social & Culture, መቅደላ Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.