0

የሕዝብና የቤት ቆጠራ አሁን ለምን?

                         የሕዝብ  ቆጠራ  ለሚዛናዊ የሀብት ሥርጭትና ክፍፍል  ሚዛን ለጠበቀ  የተፋጠነ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ዕድገቱን በታቀደና  በተቀናጄ መንገድ ለመምራት  እጅግ አስፈላጊ  መሆኑ አጠያያቂ አይደለም:: የሕዝብ  ቆጠራው ለተፈላጊው ግልጋሎት የሚውለው ግን ቆጠራውን የሚመራውና የሚቆጣጠረው መንግሥታዊ ተቁዋም በምላተ ሕዝቡ ታማኒና ቅቡል ሲሆን; ፖለቲካው ከአካባቢያዊነት  ከዘር;  ከሃይማኖት  እና ከጎሣ የፀዳ  ሆኖ ውጤቱን ሁሉም አምኖ ሲቀበለው እንደሆነ ይታመናል::  እንደ አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ነገድና ጎሣዎች በሆኑ አገሮች ; በተለይም ለበርካታ ዓመታት ከአንድነትና አብሮነት በተቃራኒው ልዩነት ሆን ተብሎ በተራገበባት; የነገድ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አሸን በፈሉባት ኢትዮጵያ; የሕዝብ ቆጠራው በትክክል ይካሄዳል ; ውጤቱንም አብዛኛው ሕዝብ ይቀበለዋል ለማለት ያስቸግራል:: በአሁኑ ጊዜ ቆጠራውን አስቸጋሪና ኢታማኒ የሚያደርገውም  ለዘመናት በፀረ ኢትዮጵያና በፀረ ዐማራነት የተደራጁ የነገድ ድርጅቶች የፈለጉትን ለመሆን በመራጩ ሕዝብ ላይ የሚነዙት ፕሮፓጋንዳና የሚያሰራጩት መልዕክት የቆጠራው ውጤት እነርሱን ጠቅም ወደሆነ አቅጣጫ ሊመሩት የመቻላቸው ሁኔታ በግልጽ የሚታይ ስለሆነ ነው:: ዛሬ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የዘር ድርጅቶች ከመንግሥት አቻ የሚያደርጋቸው የመገናኛ ብዙኃን የገነቡ ከመሆኑም በላይ : ከማናቸው በላይ በብርሃን ፍጥነት በእያንዳንዱ መራጭ እጅ የሚገባው የማኅበራ ሚዲያ በቆጠራው ውጤት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል ነው የሚባል አይደለም:: የአገራችን ፖለቲካ የተቃኘው አንዱን ደፍቆ የራስን የበላይነት በማንገሥና ሌሎችን በማግለል ላይ ያነጣጠረ ከመሆኑም በላይ ; አጠቃላይ ቅኝቱ

  የመሬትና የሌሎች የተፈጥሮ ኃብቶችን  ሽሚያና ነጠቃ ላይ ያተኮረ ስለሆነ ; የሕዝብ ቆጠራው ለታለመለት መልካም ተግባር ከመዋል ይልቅ ለብጥብጥና  መሰል ተፈላጊ ላልሆኑ ድጊቶች እንዳያጋልጠን ብርቱ ጥንቃቄ ሊወሰድበት ይገባል:: ለዚህ አባባላችን መነሻ የሆነንም ባለፉት 27 ዓመታት  በዐማራው ነገድ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል ; መፈናቀል ; መሳደድና  መዋረድ ዓለም የመሠከረለት በመሆኑ ነው:: ይህም ብቻ አይደለም :: በሶማሊና በኦሮሞ ነገዶች መካከል የታየው መፈናቀልና መሳደድ በወላይታና በሲዳማ ; በቀቤና እና በጉራጌ ነገዶች መካከል የተፈጸመው አሰቃቂ ዕልቂት ; በጠለምት ;ራያ ;ወልቃይት ;ጠገዴ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ የዘርና የማነት ጥቃት ሥጋቻችን መሬት የያዘ መሆኑ ማሳያችን ነው::

በአገራችን ታሪክ የሕዝብና የቤት ቆጠራ ሦስት  ጊዜ  መደረጉ ይታወሳል:: የመጀመሪያው በ1976ዓም እንደነበር እናስታውሳለን:: ይህ የኢትዮጵያ  “አብዮታውያን” ቡድኖች ለሥልጣን ሲሉ ባካሄዱት ግብግብ ወታደራዊ  ደርግ የበላይነቱን የያዘበትና አይበገሬ የመሰለበት ወቅት ስለነበር; አገሪቱን በእቅድ ኢኮኖሚ  ለመምራት እንዲያስችለው በወቅቱ በነበሩ ዐማራ ጠል አብዮታውያን አቀናባሪነት የተደረገና የዐማራን ቁጥር ከነበረው ዕውነታ ዝቅ በሚያደርግ  መልኩ ውጤቱ  መጠናቀቁ ይታወሳል:: በዚህ ቆጠራ  የተለያዩ  የቁጥር  ጨዋታዎች  ተሠርተው ዐማራው በኦሮሞው ይበልጣል የተባለው በ342 000 ገደማ ነበር:: ሁለተኛውና ሦስተኛው ቆጠራ የተደረገው በ1987  እና በ1999ዓም ነበር:: በነዚህ  ቆጠራዎች ወቅት የሥልጣኑ ባለቤት  የትግራይ ሕዝብ ነፃአውጪ (ሕወሓት) ስለነበር  ዐማራው በጥቂት መቶ ሽዎች ሳይሆን በሚሊዮኖች በኦሮሞው እንደሚበለጥ የሚያሳይ ከዕውነት  የራቀ ውጤት  ይፋ  አደረገ::  ከሁሉም  በላይ ሦስተኛው  ቆጠራ በተቀነባበረ  ሁኔታ  የዐማራው ቁጥር ከሁለተኛው ቆጠራ ተነስቶ  ሊደርስ ይችልበታል ተብሎ ከሚጠበቀው ቁጥር 2 ሚሊዮን አራት መቶ ሽ  የቀነሰ እንደሆነ ተገለጸ:: የዐማራው ቁጥር በዚህ መጠን  ያህል የቀነሰው ሆን ተብለው በተሠሩ የቁጥር ጨዋታዎች ብቻ ሳይሆን; በዐማራው ላይ በተከፈተው የዘር ጥቃት በመገደሉ ; እንዳይዋለድ በመደረጉና  በገፍ በመፈናቀሉ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ:: ይህም ዐማራውን   ሆን ተብሎ  በሁለንተናዊ  መልኩ አናሳ ; ተዋራጅ ; ተጠቂና ዝቅተኛ ለማድረግ  የተሠራ  እንደሆነ በዐማራው ላይ የተነዛው ፕሮፖጋንዳና የወጣው ዕቅድ በግልጽ ያሳያል:; የፖለቲካ ሥርዓቱ መሣሪያ የሆነው በዘር ላይ የተመሠረተው ሕገ መንግሥት ሳይሻሻል ወይም ሳይለወጥ በሕገመንግሥቱ መሠረት የተቁዋቁሙት ተቁዋሞች መሻሻል ሳይደረግባቸው ; በመንግሥታዊ ተቁዋሞችና በባለሥልጣኖቹ አመራረጥና አመዳደብ ሕዝቡ አመኔታውን ሳይሰጥ የሕዝብ ቆጠራ ለማድረግ መዘጋጀት ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን እንደሆነ መናገር ነቢይነትን አይጠይቅም::  

ባለፉት 27 ዓመታት  ዐማራው ለትምህርት ለጤና ለመንገድ ለኃይል ግንባታ  ለጥናትና ምርምር ወዘተ ሊያውል የሚችለውን በጄት እንዲያጣ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የተፈጸመበት የዘር እልቂትና መፈናቀል በተጨማሪ;  በሁለቱ ተከታታይ ምርጫዎች  በተፈጸመበት የዘር ልቂት ምክንያት የታየው የቁጥር ቅነሳ መሆኑ ግልጽ ነው:: ይህን ዐማራው   ለከፋ  ድህነትና ርሃብ ተጋላጭ እንዳደረገው በግልጽ ይስተዋላል:: ይህም ዐማራውን ሆን ተብሎ ከሚደረግበት  የቁጥር  ቅነሳ በተጨማሪ በድህነትና በበሽታ ተጠቂ እንዲሆን በማድረግ በተራዘመና በረቀቀ መንገድ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ  እንዲሆን የተደረገ የፀረ ዐማራ  እንቅስቃሴ አንዱ ፈርጅ እንደሆነ እንረዳለን::

 ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶር ዐብይ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ  ወዲህ በይፋ የሚነገረውና ዓለም ያደነቀው አባባል (narrative) ; እኒህ ወጣት መሪ ለፍትህ፤ ለእውነተኛ የዜጎች እኩልነት፤ ለሰላምና ለእርጋታ፤ ለዘላቂና ፍትሃዊ እድገት የቆምኩ ነኝ ብለው የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ በማስተጋባታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው:: ዓለም የቸራቸው አድናቆት ቀጣይ የሚሆነው ግን ; በኢትዮጵያ የሚደረገው ይህ አራተኛው  የሕዝብ ቆጠራ በተመቻቸና በተረጋጋ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ከባቢ;  ታማኒነት ባላቸው የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ; ታማኒነት ባላቸው ጋዜጠኞች የየለቱን ሁኔታ ለሕዝብ ጆሮ ሲደርሱ ;  ከሁሉም በላይ ለሐቅ  የቆሙ ምርጫ ታዛቢዎች ምርጫውን ሲታዘቡና ሁሉም የየድርሻው ባለቤት መሆን ሲችል ነው:: ከሁሉም በላይ የዐማራው ሕዝብና ሌሎች ታዛቢዎች ባለፉት የሕዝብ ቆጠራዎች  በግልጽ የደረሱበት አይታወቅም ተብለው በፓላማ ሪፖርት የቀረበባቸው የዐማ ነገድ አባላት የት እንደገቡና ወይም  የት እንደደረሱ እውነቱን የዶር ዐቢይ አመራር ሲያሳውቅ ነው::የተለያዩ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ከአምስት ሚሊዮን (5,000,000) በላይ ዐማራ ጠፍቱዋል::  ይህ ከፍተኛ ቁጥር የዐማራ ሕዝብ ለምን ኅልውናው እንደጠፋ መታወቅ አለበት እንላለን።

ባለፉ ቆጠራዎች ሆን ተብለው የተሠሩ  የቁጥር ጨዋታዎች ሳይስተካከሉ የማንነት  ፖለቲካው ሳይሰክን ፀረ ዐማራ የሆኑ ኦነግና የጡት ወይም  የጉዲፍቻ ልጆቹ  እጄ ረጅም ከመሆን አልፈው በአገሪቱ  ፖለቲካ የወሣኝነት ቦታ በያዙበት ጊዜ ውስጥ; ሕወሓት የፖለቲካ የበላይነቴን ተነጠኩ ብሎ ከትግራይ ሕዝብ እምብርት ውስጥ አንገቱን ቀብሮ ለዳግም ዘመቻ ነጋሪት እየጎሰመ ባለበትና እሱ ያደራጃቸው የጥቅም ተካፋዮቹ  በየክልሉ  ጦር አውርድ እያሉ ሕዝቡን ሰላምና  መረጋጋት እንዳኖር ባለ በሌለ ኃይላቸው እየተንቀሳቀሱ ባለበት ሰዓት ; ዐማራው  ሁነኛ  እና የእኔ  የሚለው ጠንካራ ተጠሪ በሌለበት  ወቅት ; ከሁሉም በላይ የአገሪቱ ፖለቲካዊና  ማኅበራዊ  ሁኔታ ባልተረጋጋበትና ሁኔታዎች  ወደየት እንደሚጉዋዙ ግልጽ ባልሆነበት ሁኔታ የሕዝብ  ቆጠራ ለማድረግ መዘጋጀት ዐማራውን ሆን  ተብሎ አናሳ ለማድረግ የታለመ እንደሆነ ዝግጅቱና  ዝግጅቱን ለማስፈጸም የተዘጋጁት መመሪያዎችና አስፈጻሚ  አካላት ማንነት በግልጽ ያሳያል::

የሕዝብ ቆጠራ ዝም ተብሎ የሕዝቡን ቁጥር ለማወቅ የሚደረግ አይደለም:: ቁጥሩ የበጄት መደልደያ የቀመር መነሻ ነው:; የዕድገት አቅጣጫ መመልከቻ ነው::  የአንድ ሕዝብ ወይም ማኅበረሰብ የኃይል ማሳያያ ከሆኑት መሥፈርቶች አንዱ ነው:: የትምህርት  የጤና የቤቶች እና የመንገዶችና የግንባታ  ሥራዎች ቅደም ተከተል መያዣ ሁነኛ  ሰነድ ነው:: ባንድ ቃል የሕዝብ ቆጠራ የአንዲት  ሀገር  ሁለንተናዊ ማንነት ማሳያ የቁጥር ቀመር ነው:: በመሆኑም ቆጠራው በአግባቡ እንዲሆን ሕዝቡ የቆጠራውን ፋይዳ ተረድቶ አስፈላጊ  መረጃዎችን እንዲሰጥ የኅሊና ዝግጅት እንዲያደርግ ከማሳወቅ ጀምሮ ለቆጠራ ስኬታማ መሆን የሚረዱ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን  ከማሙዋላት በተጨማሪ ቆጠራውን የሚያደርጉት ሰዎች በሙያ የታገዙ የማንም ፖለቲካ ድርጅት ዓላማ አራማጅ  ያልሆኑ የቆጠራው  ውጤት ለአገሪቱ ዕድገትና ሰላም  መረጋገጥ ዋና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን  የተረዱ  ሰዎች መሆናቸው በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የታመነባቸው ሊሆኑ ይገባል::

በዛሬዪቱ  ኢትዮጵያ የማንነት  ፖለቲካ በነገሠበት : በተለያዩ የአገሪቱ  ክፍሎች ሰላም ከሰማይ  በራቀበት ባንኮች  በሚዘረፉበት ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ መንግሥት ባልቻለበትና “ ወንጀለኞች በመንግሥት እሥር  ቤት ባይገቡም የኅሊና እስረኞች” ናቸው ተብሎ ወንጀለኞች ኅሊናቸው ፈቅዶ በሠሩት ወንጀል መልሰው እስረኞች ናቸው ተብለው  ተደራራቢ  ወንጀሎችን  እንዲሠሩ ሠፊ በር በተከፈተበት ወቅት ይህን ለአገራችን የወደፊት ዕድገትና ብልፅግና መነሻ የሚሆን ትክክለኛ ቆጠራ ለማካሄድ ሁኔታውች  እንደማይፈቅዱ የዐማራ ሕልውና  ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ያምናል::

ስለሆነም የሕዝብ ቆጠራው እንዲደረግ ገፊ ምክንያት  ሆኖ  የሚቀርበው አገራዊና አካባቢያዊ የሕዝብ ተወካዮችን ለመምረጥ  የሕዝቡ መቆጠር አስፈላጊና የማይታለፍ ነው የሚለው ነው:: አዎ! ለትክክለኝ የሕዝብ ውክልና የሕዝብ ቆጠራው መደረግ ያለበት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም:: የእኛም ጥያቄ የሚነሳው ትክክለኛውን የሕዝብ ቁጥር ለማግኘት  በቂ ዝግጅትና የተረጋጋ ሰላም መኖር ከሁሉም በላይ የመንግሥት የማስፈጸም አቅም መጎልበትን ይጠይቃል:: ይህ በሌበት ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ ቆጠራ ውጤቱ ለተፈላጊው ግብ አያበቃምና ለቆጠራው መደረግ ገፊ ጉዳይ የሆነው ምርጫም በታቀደለት መሠረት ማከናዎን አይቻልም:; መረጋጋትና  ሰላም የለም:: የመንግሥት የማስፈጸም አቅም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ውሱን ነው:: በመሆኑም የለውጥ አራማጁ ቡድን  እውነት  ኢትዮጵያን  ወደ ዲሞክራሲ የማሸጋገር ዓላማ ካለው ለምርጫና ለሕዝብ ቆጠራ ተጣድፎ መግባት ያለበት አይመስለንም:; ከዚያ  በፊት ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ይጠበቅበታል:: የለውጡን አራማጅ ኃይል ማጎልበትና  ለውጡ መሬት እንዲይዝ ማድረግ ይኖርበታል:: ለዚህም ወንጀለኞችን ራሳቸውን በራሳቸው አስረዋል ሳይሆን ; ሕዝብና መንግሥት በሚያውቀው ለወንጀለኞች በተዘጋጀ ቦታ መጠበቅ  ይጠበቅበታል:: እነዚህን ሳያከናውን ምርጫና ሕዝብ ቆጠራ ላርግ ቢል ውጤቱ  “ከባል በፊት ልጅ “እንደማለት ነው:: በመሆኑም ዐኅኢአድ በጥድፊያ ሊደረግ የታቀደውን ምርጫና ቤት ቆጠራ ዐማራው አጠንክሮ በሰላማዊ መንገድ እንዲቃወም ጥሪው ያቀርባል::

የሕዝብ ቆጠራ በትክክል፤ በሃቅኛነትና ተቀባይነት በሚኖረው መልኩ ለማካሄድ   ከሚያስፈልጉት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ሰላምና እርጋታ ወሳኙ ሲሆን፤ በተጨማሪ በየአካባቢው የተፈናቀሉና ከአገራቸው የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ

አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አለን። በአሁኑ ወቅት እጅግ በጣም አሳሳቢ ሆኖ የምናገኘው ክስተት በጎንደር ሕዝብ ላይ የተካሄደውና የሚካሄደው ጭካኔ ወደ መቶ ሽህ የሚገምቱ ወገኖቻችን ከቤት ንብረታቸው  እንዲፈናቀሉ ማድረጉና ለሰላማዊ ኑር አስተማማኝ ሁኔታ አለመፈጠሩ ነው። በጎንደርና በሌሎች የዐማራ ክልል ተብሎ በሚጠራው አካባቢና በኦሮሚያ በደቡብ ;በኦጋዴን፤ በአዲስ አበባ ወዘተ  ከቤት፤ ከመሬትና ከንብረታቸው እንዲሰደዱ የተገፉት ኢትዮጵያዊያን በሕዝብ ቆጠራው የመሳተፍ መብታቸው አሁንም አስተማምኝ አይደለም።

መጭው ምርጫ ነፃና  ፍትሓዊ እንዲሆን እንመኛለን። የሕዝብ ቆጠራው ለምርጫው መሠረትም  መሆኑንም እንቀበላለን። ሆኖም፤የሕዝብ አመኔታ መሠረት ያላደረገ የሕዝብ ቆጠራና ምርጫ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እንገምታለን። ስለዚህ፤ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይስተካከሉ የሚደረግ የሕዝብ ቆጠራ አከራካሪ ብቻ ሳይሆን እንደ ፖለቲካ ውሳኔ እንደሚቆጠር አስቀድሞ መናገር ይቻላል።

 

የዐማራ ኅልውና መጠበቅ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው !

Filed in: Amharic News, News, Politics & Economics, Politics & Openion, Social & Culture, መቅደላ Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.