0

የዐማራው የኅልውና ትግል ከሌሎች የጎሰኛነት ትግሎች የሚለየው በምንድን ነው?

   ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት : ዐርብ ጥቅምት ፴ ቀን ፪ሺህ፲፩ዓ.ም.  ቅጽ ፮ቁጥር፲፰         

ድርጅት ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ወይንም ስብስቦች በዓላማቸው ወይንም በእምነታቸው ዙሪያ የሚሰባሰቡ የሰዎች ማኅበር ወይንም የወል ማዕከል ነው። የየአንዳንዱ ድርጅት ኅልውና የሚወሰነው ደግሞ ድርጅቱ በቆመለት አላማና ግብ ስለሆነ ኅልውናው ጊዜያዊ ወይንም ቋሚ ሊሆን ይችላል። ድርጅት የሕዝብ ችግር ለመፍታት ወይም ለአባላቱ የተሻለን ለማድረግ በፍላጎት የሚቋቋም አጭርና ረጅም ራዕዮችን ለማሳካት የሚያስችል ተቋምና አሰባሳቢ ማእድም ነው። ድርጅት ኅልውና የሚኖረው የሕዝብ ችግር ለመፍታት ከሕዝብ ችግር ሲፈጠር ብቻ ነው። የሕዝብን የተፈጠረ ችግር ለመፍታት ከሕዝብ ችግር የማይፈጠር ድርጅት ሕይዎት የለውም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ባለፉት አርባ አራት አመታት የተፈጠሩት የጎሳ ድርጅቶች የጭቆና ታሪክ ፈብርከው ከሕዝብ ችግር ጋር ግንኙነት የሌላቸው የፖለቲካ ትርክቶች ፈጥረው ሕይወት አልባ በመሆን የራስ መንግሥት ለመፍጠር ከመሰባሰባቸው በፊት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበረ ስለሚባለው ጭቆና መርምሮ ጥናት ያቀረበ ሰው የለም። ከየካቲት ወር 1966 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያነሳቸው ጥያቄዎች መብት ይጨመርልን የሚል እንጂ አንዳቸውም ተጨቆንን የሚል ሕዝባዊ ጥያቄ አልነበረም። መብት ይጨመርልን የሚለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ በመቀማት የጭቆና ትርክት የፈጠሩበትና የራስ መንግሥት ለመፍጠር ማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮተ ዓለም የተጎናጸፉበት ጎሰኛ የግራ ፖለቲከኞች ናቸው።

በአንድ አገር ውስጥ የነገድም ሆነ የመደብ ጭቆና አለ የሚባለው ቢያንስ የሚከተሉት ሶስት ነገሮች ተፈጻሚ ከሆኑ ነው፤

1. በቋንቋ፣ በዘር ወይንም በመደብ ላይ ተመስርቶ የሚያዳላ መንግሥታዊ ፖሊሲ ሲኖር፤
2. በቋንቋ፣ በዘር ወይንም በመደብ ላይ የተመሰረተው የአድሎ ፖሊሲ ከታወጀና ተቋማዊ ከሆነ፤
3. በቋንቋ፣ በዘር ወይንም በመደብ ላይ ተመስርቶ የታወጀውንና ተቋማዊ የሆነውን የአድሎ ፖሊሲ የማስፈጸሚያ መሳሪያዎች [implementation tools] ለምሳሌ በቋንቋ፣ በዘር ወይንም በመደብ ላይ የተመሠረተውን ፖሊሲ ለማስፈጸም እየተከታተለ የሚያስፈጽም አካል፣ ፖሊሲውን የጣሱትን እያሳደደ የሚያስር ፖሊስና አጥፊ የተባሉትን የሚቀጡ ፍርድ ቤቶች የተዘጋጁለት ከሆነ የነገድ ወይንም የመደብ ጭቆና አለ ሊባል ይችላል።
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በመንግሥትነት ተሰይሞ በቋንቋ፣ በዘር ወይንም በመደብ ላይ የተመሰረተ የሚያዳላ መንግሥታዊ ፖሊሲ የቀረጸ፤ ፖሊሲውን ያወጀና ተቋማዊ ያደረገ፤ ከዚያም አልፎ ፖሊሲው ለመተግበር የማስፈጸሚያ መሳሪያዎች [implementation tools] ያዘጋጀ አካል ኖሮ አያውቅም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ነበረ የሚባለው ጭቆና በተለምዶ በጎሰኛ ልሒቃን ሲነገር የምንሰማው እንጂ ጭቆና ስለመኖሩ አንዳች ማስረጃ ሊቀርብ አይችልም። የነገድ ጭቆና ነበረ የሚለውን የጎሰኞች ትርክት እንደማይቀበሉ የሚናገሩ አንዳንዶች ኢትዮጵያ ውስጥ የመደብ ጭቆና እንደነበረ አድርገው ሲሟገቱ ይታያል። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ የነበረው የገዢ መደብ ከኤርትራ እስከ ቦረና፤ ከጅጅጋ እስከ ጋምቤላ የሚወለዱ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ያቀፈ፤ እየሰፋ እንዲሄድ ሆኖ የተዘረጋ ድንኳን እንጂ በፖሊሲ የታጠረ፤ በተቋም የተከነቸረና ሌላውን ለማግለል የአድሎ ማስፈጸሚያ መሳሪያዎችን የዘረጋ አልነበረም። ባጭሩ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ተደረገ ተብሎ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የሚቀርብ
ጭቆናን የሚያሟላ መንግሥት ኖሮ አያውቅም።   በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ አንድን ነገድ ለማጥፋት የጭቆናና የዘር ማጥፋት ፖሊሲን በማውጣት
ተቋማዊ ያደረገው ወያኔ ነው። ወያኔ ዐማራውን ለመጨቆንና በዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት ለማካሄድ ያዘጋጀው ፖሊሲው አብዮታዊ ፕሮግራም ይባላል።

አብዮታዊ ዲሞክራሲና ዐማራን መጨቆን፤ ብሎም በዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት ማድረግ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚነሳው “ዐማራ የሚባል በዳይ የነበረና መብት የማይገባው ሕዝብ አለ” ከሚል ነው።  አብዮታዊ ዲሞክራሲ እስለ ፍልስፍና የሚነሳው በአንድ አገር ውስጥ ዲሞክራሲ የሚገባውና የማይገባው ነገድ አለ ከሚል የማዳላት እሳቤ ነው። በወያኔ የአገዛዝ ዘመን ዐማራን መጨቆንና በዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት ማካሄድ ተቋማዊ ስለመደረጉ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በመንግሥትነት ከመሰየሙ በላይ ማስረጃ ማቅረብ አይጠይቅም። እንደውም ዐማራን ያፈናቀሉ፣ ያንገላቱና በዐማራ ላይ እጃቸውን የሰነዘሩ ሁሉ በኢህአዴግ ሲሾሙና ሲወደሱ በአይናችን ያየነው አስከፊና አሳፋሪው የዘረኝነት ታሪክ በመሆን ታሪክ
ይመዘግበዋል።
ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ እንደሚገባ ሲያውቅ የመሰረተውና በመንግሥትነት የተሰየመበት ግንባር ኢሕአዴግ ይባላል። ኢሕአዴግ ማለት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርኅ የሚመሩ የድርጅቶች ግንባር ማለት ነው።
በመንግሥትነት የተሰየሙት የኢሕአዴግ ግንባሮች የሚያወጧቸው አገራዊ ፖሊሲዎች፣ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማለትም ዐማራን በመጨቆንና ዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት በመፈጸም የተቃኙ ናቸው።
በዐማራ ላይ ጭቆና የማይፈጽምና በዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት የማያካሂድ የኢሕአዴግ ፖሊሲ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አይደለም። በዘመነ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ዐማራን በአገሩ አገርህ ሂድ ተብሎ ከተራራ ላይ መወርወር፣ ቤት ተዘግቶበት በእሳት እንዲቃጠል ማድረግ፤ ከነነፍሱ በማይሞላ ገደል ውስጥ መጨመር፤ ዘሩን እንዳይተካ የዐማራ ሴቶች የሚያመክን መርፌ መወጋት፤ የሕግ ጥበቃ ማሳጣት፣ ስራ የማግኘት ዕድልና የትምህርት እድል እንዳያገኝ መደረግ፤ የንብረት ማፍራት መብት፣ ያለመፈናቀልና የመኖር መብቱ በግላጭ በአገዛዙ ተቋማት መገፈፍ፣ በአጠቃላይ በዐማራ ኅልውና ላይ አደጋ መጣል ሁሉ ህጋዊነት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የወለደው ዐማራን መጨቆንና በዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት ማካሄድ የሕግ ከለላ በማግኘቱ ወያኔ ባመነው እንኳ 2.40 ሚሊዮን ዐማራ እንዲጠፋ ተደርጓል። በኢትዮጵያ ውስጥ የጭቆናን ምንነት የሚያሟላና በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚታገዝ የመጨቆንና ዘርን ለማጥፋት ታስቦና ታቅዶ በመላው ኢትዮጵያ የተዘረጋው የጭቆናና የዘር ማጥፋት ፖሊሲ ቢኖር በዐማራ ላይ ባለፉት 27 የወያኔ አገዛዝ የተካሄደው ብቻ ነው።   በአጭሩ የዐማራው ትግል ከሌላው ትግል የሚለየው ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ጭቆናና የዘር ማጥፋት
እየተካሄደበት የሚገኝ ብቸኛ ሕዝብ መሆኑ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ከዐማራው በስተቀር በማንነቱ የሚፈጸምበትን ጭቆና በማንነቱ ተደራጅቶ ለመመከት የሚያስችል የትግል ስንቅ [material foundation] ያለው ሕዝብ የለም። በወያኔዋ ኢትዮጵያ ዐማራው ለሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶች ለይስሙላ የተሰጣቸው መብት እንኳ የለውም። በአገዛዙ ማስረጃ መሠረት «ኦሮምያ
ክልል» በሚባለው ክልል ውስጥ ብቻ ኢህአዴግ ራሱ ባመነው ቁጥር ብንሄድ እንኳን አስራ አንድ ሚሊዮን ዐማራ ይኖራል። ይህ አስራ አንድ ሚሊዮን ዐማራ ባለፉት ሀያ ሰባት የወያኔ የአገዛዝ አመታት ለሌሎች ለይስሙላም ቢሆን የተሰጠው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፤ የመመረጥ መብትና ሌሎች የዜግነት መብቶች የተነፈገ ህዝብ ነው።
በወያኔ የምርጫ ቦርድ ሕግ መሠረት አንድ የምርጫ ወረዳ የሚዋቀረው በምርጫ ወረዳው እስከ መቶ ሺህ ሕዝብ ( ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ አዋቂ በሙሉ) ሲኖር ነው። በዚህ ስሌት መሠረት ኦሮምያ ክልል በሚባለው ክልል ውስጥ ይኖራሉ ለተባሉት አስራ አንድ ሚሊዮን ዐማሮች አንድ መቶ አስር ሺህ የምርጫ ወረዳ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው። አንድ መቶ አስር የምርጫ ወረዳ ማለት አንድ መቶ አስር የፓርላማ አባል ጋር እኩል ነው። ይህ ማለት የዐማራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቁጥር በአንድ መቶ አስር ጎድሏል ማለት ነው። በአለም ላይ ካሉ 197 አገሮች መካከል 160ዎቹ አገሮች የሕዝብ ቁጥራቸው ከአስራ አንድ ሚሊዮን አይበልጥም። ይህ ማለት በአለም ላይ ያሉ 160 አገራት ቁጥር ያለው ዐማራ፣ ዐማራ በመሆኑ ብቻ ተወካዩን እንዳይመርጥ ተደርጓል ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት ግፍ፣ በደል፣ ጭቆናና የዘር ማጥፋት እየተካሄደበት ያለው ዐማራ ብቻ ነው። ስለሆነም በዚህ መልኩ በልዩ ሁኔታ ጭቆና እየተካሄበት ያለው ዐማራ ለኅልውና የሚያደርገው ትግል ከሌሎች ትግል ጋር አንድ አይደለም።   የኢትዮጵያ ተቋማት አገዛዙ የተዋቀረበት ርዕዮተ ዓለም ወይንም መስመር ውጤት ወይንም ነጸብራቆች ናቸው። የአገዛዙ ርዕዮተ ዓለም ወያኔ ዐማራን ለማጥፋት ኢሕአዴግ የሚባለው ግንባር ሲመሰርት የግንባሩ መሥመር ያደረገው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው። ሕገ መንግሥት ተብዮው የተወለደው ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር እንደሆነ በመግቢያው ላይ በግልጽ አስቀምጧል። ስለዚህ የዐማራ ጭቆና ሕገ መንግሥታዊና ተቋማዊ እንደሆነ ግልፅ ነው ማለት ነው።  ይህ ተቋማዊና ሕጋዊ ጭቆና ደግሞ በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍና በደል የዘር ማጥፋት አድርጎታል።

የዘር ማጥፋት የሚካሄድበት ሕዝብ ደግሞ የሚያካሂደው ትግል የኅልውና ትግል ነው። አብዮታዊ ዲሞክራሲ የአገዛዙ ርዕዮተ ዓለምና የኢትዮጵያ ፖሊሲዎቹ ማሕደር የሆነው የዐማራን ጭቆና ተቋማዊ ለማድረግና የዘር ማጥፋቱን ሕጋዊነት ለማላበስ ነው።
ባጠቃላይ “እናቱ የሞተችበትና እናቱ ገበያ የሄደችበት ሕጻን እኩል ያለቅሳሉ” የተባለው ካልሆነ በስተቀር በርዕዮት ዓለም የታገዘ ዐማራን የመጨቆንና በዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት ማካሄድ ተቋማዊና አገራዊ በሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ የዐማራ የኅልውና ትግል መብት ይጨመርልን ብለው ለፖለቲካ ሥልጣን ከሚታገሉ ጎሰኞች ትግል ጋር በእኩል አይን ሊታዩ አይችልም። የዐማራ የኅልውና ትግል ከሌሎች በነገዳቸው ተደራጅተው ለሥልጣን ከሚታገሉ ቡድኖች ጋር በእኩል ሊታይ የሚችለው፣ ዛሬ የሚሰራበት ዐማራን የመጨቆን ፖሊሲ ተወግዶ ለሁሉም እኩል የሚሆን የጋራ የመጨዎቻ ሜዳ ከተዘረጋ ብቻ ነው። እኛ በተደጋጋሚ ስንለው እንደነበረው አሁንም አስረግጠን የምንደግመው የዐማራው ትግል የኅልውና ተጋድሎ ነው። ስለሆነም መዋቅራዊ መሆነ መልኩ በአገዛዙ ርዕዮተ ዓለም የታገዘ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበት ኅልውናውን ለመታደግ ጥረት የሚያደርገው የዐማራ የኅልውና ትግልና ለፖለቲካ ስልጣን በነገዳቸው ተደራጅነት ጎሰኛነት ከሚያራምዱ ቡድኖች ጋር አንድ አይነት አይደለምና የዐማራው የኅልውና ትግል ከሌላው የፖለቲካ ትግል የሚለይ መሆኑን መጀመሪያ በመላ የዐማራ ልጆች ቀጥሎም በዐማራ ደጋፊዎች፤ ወዳጆችና አንጡራ ኢትዮጵያኖች ዘንድ በሚገባና በውል እንዲታወቅ ሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት በአክብሮት ያሳስባል፡፡

ኢትዮጵያ በቆራጥና ጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘለዓለም ጸንታ ትኖራለች!
ፈለገ አሥራት የትውልድ ቃል ኪዳናችን ነው!
የዐማራው ሕልውና መጠበቅ ለእትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

Filed in: Amharic News, News, Politics & Economics, Politics & Openion, Social & Culture, የሞረሽ ወገኔ መግለጫ Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.