0

ቅድሚያ ትኩረትና ፍትህ ለወልቃይት፤ለራያ እና መተከል አውራጃ ወገኖቻችን!

 

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ቅዳሜ ጥቅምት ፳፬ ቀን ፪ሺህ፲፩ዓ.ም.  ቅጽ ፮ቁጥር፲፯

 

 ዐማራ ወኪል አልባ ሆኖ በፀደቀ ህገመንግስት የዐማራ ህዝብ ያለማቋረጥ በመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ በደል እየደረሰበት ይገኛል።  ይህ ለ 27 ዓመት የዘለቀው ዐማራን ከመጫን አልፎ የሚደፈጥጥው አገዛዝ ሸክሙ እጅግ ከባድ ቢሆንም ዐማራ በየአቅጣጫው የሚሰነዘርበትን ጥቃት ሁሉ ኢትዮጵያን እያሰበ በትዕግስት እዚህ ደርሷል።

ሰላም ፈላጊው ኢትዮጵያዊ ዐማራ በተደጋጋሚ የጥቃት ኢላማ የሆነው በነገዱ ዐማራ በመሆኑና ኢትዮጵያዊነትን የሙጥኝ በማለቱ ብቻ እንጅ ሌላ ጥፋት ተገኝቶበት እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ዐማራ ሲጀመር ጎሳዊ አስተሳሰብ ያልተጠናወተው በመሆኑ ዶ/ር አብይ ወደስልጣን ሲመጡና ለ27 አመት ሲወገዝ የነበረውን ኢትዮጵያዊነትን በአንደበታቸው በማቀንቀናቸው እንዲሁም
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በመፍቀዳቸው ብቻ የነፃነት ጭላንጭል የታየ ሲመስለው ከማንም ቀድሞ እጁን ዘርግቶ እንደተቀበላቸው እሙን ነው። የዐማራ ህዝብ ዶ/ር አብይን ሲደግፍ እሳቸው የኦሮሞ ህዝብን ወክለው ለስልጣን እንደበቁና ሲጨቁነው የኖረው የኢ ህ አ ዲ ግ አባል መሆናቸውን አጥቶት አይደለም። ነገር ግን ስለሰው ልጅ መብት መጠበቅና
ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገደው መሪ ከየትኛውም ነገድ ቢመጣ በዐማራ ህዝብ መቸም ቢሆን ተቀባይነትን እንደሚያገኝ ለዶ/ር አብይ የተደረገው ድጋፍ ማሳያ ነው።

ዐማራ ዛሬም የለውጡ አራማጆች የሚያቀነቅኑትን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ደግፎ ቁርጠኝነቱን ሲያሳይም የዐማራ ህዝብ ሰቆቃና መከራው ጨመረ እንጅ አልቀነሰለትም። ጭቆናው ቅጥ ያጣና ጭካኔ የተሞላበት ስለሆነ ካለወያኔ ፈቃድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ የህይወት ዋጋ ያስከፍላል። እንደምሳሌ የፋሲል ከነማ አርማ ያለበትንና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ምስል
ያለበትን ቲሸርት መልበስ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ይዞ መገኘት ሁሉ እንደወንጀል ተቆጥሮ በወያኔ ህግ አልባ ፍርድ እስከሞት ያስቀጣል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ ራሱን የቻለ ተጨማሪ መንግስትና የአስተዳደር ህግጋት ያለ እስኪመስል ድረስ ዛሬም እንደትናንቱ የዐማራ ህዝብ በህውሀት ልዩ ሀይል ማንነቱ ተደፍጥጦ፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ግድያ፣ እንግልትና መፈናቀል እየተደረሰበት እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ዐማራ በዋጃና ጥሙጋ፣ በኮረም፣ በአላማጣ፣ በወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት፣ እንዳ መሓሪ፣ በራያ፣ በወፍላና በአላማጣ ልጆቹን በአማርኛ እንዳያስተምር በህውሀት ተከልክሏል። ዐማራ በቀድሞው ጎጃም ክፍለሀገር መተከል አውራጃ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተባለው ክልል ያለምንም ጥፋት ይሰለባል፣ ይገደላል።  ስጋውም የገዳዮቹ ማእድ ሁኖ በቁርጥ ስጋ/ በብርንዶ መልክ ይበላል።

የሚገርመው ነገር ብዙ ህገ አራዊት የሆነ ከሰብአዊነት የወረደ አሰቃቂ ወንጀል ሲፈፀም አሁንም ዐማራ በማያውቀው ነገር ያለአግባብ ህይወቱ እንዳይጠፋ፣ እንዳይፈናቀልና ሌላ አደጋ እንዳይደርስበት ጥበቃ አይደረግለትም። ይህ ያለ ተከላካይና ተጠያቂነት በግፍ ህይወትን ማጣት ደግሞ ጎጅነቱ ለሟቾቹ ብቻ ሳይሆን የቋሚም ሰቀቀን በመሆኑ የሚያሳድረው የስነልቦና
ጦርነት ጭምር እጅግ አሳዛኝ ነው።

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ዐማራ ሲሞት ገዳዩን ሁሉ ”ተሸናፊ” ብሎ ንቆ መተው የሚያዋጣ የሚሆነው ገዳይ መግደል መሸነፍ መሆኑን ሲያምንና ወንጀለኞች በህግ ሲዳኙ ብቻ እንጅ የሰው ህይወት እንደቅጠል የሚቀጥፉትን ወንበዴዎች ተሸናፊዎች ናቸው ብሎ መተው ትዕግስት ሳይሆን ሞኝነት ነው ብሎ ያምናል።  ዐማራ ዛሬም እንደትናንቱ በአገሩ ኢትዮጵያ፣ በአባቶቹ ርስት ወልቃይት፣ ራያና መተከል ተወልዶ ካደገበት፣ ወልዶ ከከበደበት ቀየው ”ክልልህ አይደለም” ተብሎ ወይም ”ዐማራ አይደለህም፣ ትግሬ ነህ ብለናልና አምነህ ተቀበልና ፀጥ ረጭ ብለህ ተገዛ፣ ካልሆነም እንዴት እንደምናጠፋህ እናውቃለን” ተብሎ፣ ልጆቹን በአፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ ማስተማር ጭምር ወንጀል ሆኖበት ሞትና ግዞት ሲወሰንበት
ህገመንግስት ተብየው ለተበዳዩ ከለላ እንዳይሰጥ ተደርጎ ስለተፃፈ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ የትም ወድቆ ይቀራል።

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ዐማራ ወኪል አልባ ሆኖ በፀደቀ ህገመንግስት ከለላ ሲበደል ለ27 ዓመት መኖሩ አንሶ ዛሬም በህገመንግስቱ መሰረት ትዳኛለህ ማለት ፍትሀዊ ነው ብሎ አያምንም። ስለዚህ የአዲሱ የዶ/ር አብይ የፌደራል መንግስት በሰላማዊ የዐማራ ህዝብ ላይ ጦርነት ታውጆ፣ የሰውነትና የማንነት መብቱ ተገፎና ህዝብ በጠራራ ፀሃይ እንደወጣ ሲቀር
ዝምታን መምረጥ ማለት የወንጀሉ ተባባሪ ከመሆን የማይተናነስ ወንጀል መሆኑን ተገንዝቦ ወገኖቻችን ለጠየቁት የመብት ጥያቄ አፋጣኝ ፍትሀዊ ውሳኔ በመስጠት አስተዳደራዊ ግዴታውን ይወጣ ዘንድ ይጠይቃል።

ኢትዮጵያ በቆራጥና ጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘለዓለም ጸንታ ትኖራለች!
ፈለገ አሥራት የትውልድ ቃል ኪዳናችን ነው!

የዐማራው ሕልውና መጠበቅ ለእትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

Filed in: News, የሞረሽ ወገኔ መግለጫ Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.