0

የልዩነታችን መሰረቱ ሕገመንግስቱና የፌዴራል ሥራዓቱ !!

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) ልሳን መቅደላ ልዩ ዕትም ቁጥር ፳፰ መስከረም ፲፩ ፳፻፲፩ ዓ.ም “የዴሞክራሲ መነሻ መሰረቱ ሕገመንግስቱ ነው”   በሚል

ለሕዝብ በተዘረጋ ትንታኔ  ዐማራው ላለፉት ፳፰ ዓመታት በገዛ ሀገሩ የዘር ፍጅት፣ ከእርስቱና ተወልዶ ካደገበት ቀየው መፈናቀልና ዘርፈ ብዙ ጥቃት እየተፈጸመበት ያለው ትህነግ/ወያኔና ኦነግ በተናጠል ያዘጋጁትን ሕገመንግስት ተብዮ ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል በመሆኑ ይህ የዘር ፍጅት ቆሞ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ እኩልነት፣ ሰላምና ብልጽግና ዕውን እንዲሆኑ ከተፈለገ የልዩነታችን መሰረት የሆነው ሕገመግስቱ የኢትዮጵያ ሕዝብና ጉዳዮ የሚመለከታቸውን አካሎች ሁሉ በቀጥታ ባሳተፈ መንገድ እንደገና ሊታይና ውይይት ሊደረገበት ይገባል በማለት ዐኅኢአድ አቋሙን ግልጽ አድርጓል።

የልዩነታችንም መሰረቱ ይሄው አደገኛውና የችግሮች ሁሉ ችግር ፈጣሪ ሆኖ ለትህነግ እያገለገለ ያለው ሕገመንግስት ተብዮው ሆኖ እያለ “የሽግግር ጊዜ/ወቅት አይኖርም፤ ሕገመንግስቱም ሊለወጥና ውይይት ሊደረግበት ይቅርና አንዲት ቃላት እንኳ አትቀየርም” ማለት ላለፉት ፳፰ ዓመታት በጽኑ ስንታገለው የቆየነውንና ሕዝባችን እየተገደለበት ያለውን የነሱን አግላይና ሕገአራዊት/ሕገመንግስት በኃይልና በእንግርግሪያ አሁንም ሊጭኑብን ከመዛት አልፈው የኃይል አሰላለፋቸውም ከማን ጋር እንዳደረጉት በግልጽና በአደባባይ እየነገሩን ነው!! ይህ በዕውነት እጅግ በጣም አሳዛኝና ታሪካዊ ዝቅጠት ብቻ ሳይሆን በሕዝባችን ላይ ለደረሰው የዘር ፍጅት፣ ማፈናቀል፣ ወከባና ማሳደድ የቱንም ያህል ደንታ እንደሌላቸውና በግብር እየታየ ያለው ያው “ድመት መልኩሳ አመሏን አትረሳ” የሚሉት ዓይነት መሆናቸውን ነው።

በሁሉም ጥረትና የሕይወት መሰዋዕትነት የተገኘውን የለውጥ ጅምር እየመሩ ያሉትን ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድን የዐማራው ነገድ በነቂስ ወጦ በየአደባባዩ ድምጹንና ድጋፉን የሰጠ መሆኑ እየታወቀ እነዚሁ ተንኳሽ ኃይሎች በለውጥ አደናቃፊነት መክሰሳቸውም “ሳይቀድሙኝ ልቅደም” ከመሆኑ ባሻገር ከላይ የተነሳውን የልዩነታችን መሰረት የሆነውን የትህነግና ኦነግ ሕገመንግስት አሁንም ተሸክመን እንድንሄድ ትንኮሳን፣ ግርግርንና ግጭትን ልክ እንደ ትግል ስልት አድርገው አቅርበውታል።

በአቦ አባባል “እንኳንስ ሲሸጡኝ ሲያስማሙኝ አውቃለሁ” እንደሚባለው ሁሉ የሰሞኑ መግለጫ ሕዝብ በየዋህነት ከሚገምተው ድርጅት አልፎ ጦሩ ለማን እንደተወረወረ በሚገባ እናውቃለን። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ግንቦት ፯ “በስልጣን ጉዳይ እንጅ” በትህነግና ኦነግ ሕገመንግስት ላይ የአቋም ችግር እንደሌለበት ሁሉም ያውቀዋል። ለዚህ ደግም የዓለማችን ትላልቅ ከተሞችና የውይይት መድረኮች አፍ አውጥተው ይመሰክራሉ፤ ግንቦት ፯ አሽሞንሙኖ በየአደባባዩ ይዟቸው ይዞር የነበር እነዚሁን ሕገመንግስት ተብዮው ሀ ብለው የቀረጹትን የኦነግ ጎምቱ ባለስልጣኖች ነውና/ነበርና። ሌላው ቀርቶ ከጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አመራር ከመምጣታቸው ጥቂት ቀደም ብሎም እንኳ ቢሆን በግንቦት ፯ አማካኝነት ለአውሮፓ ሕብረት ቀረበ የተባለው የሽግግር ሰንደ ያው የትህነግና ኦነግ ሕገመንግስት መሆኑን ማንም ያውቀዋል። ለዚህም ነው “የሽግግር ጊዜ/ወቅትና ሕዝብን በቀጥታ ያሳተፈ ዴሞክራሲያዊ ሕገመንግስት ከመቅረጽ” አስፈላጊነት ጋር በተያያዘ ይሄው ሕዝብ በየዋህነት ከሚገምተው ድርጅት ይልቅ “የሽግግር ጊዜ” ሰነድ አዘጋጅቶ ለሁሉም ድርጅቶችና ጉዳዮ ለሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በስፋት ዘርግቶ ሲያወያይ የቆየ ዐኅኢአድ መሆኑ እየታወቀ በእጅ አዙር ዛቻና እንግርግሪያ ማስተላለፍ የተፈልገ ለማን እንድሆን ይገባናልና ዙርያ ጥምጥም መሄድ አያስፈልግም!! እናም ይህን መልካም የታሪክ አጋጠሚ ከስሜትና ትንኮሳ ነፃ ሁኖ በአግባቡ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ “ዘላቂና ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ” ለመውሰድ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ የሽግግር መድረክ በመፍጠር የሕዝባችን የሥርዓት ለውጥ እውን እንዲሆንና የዴሞክራሲያዊ ሕገመንግስት ጥያቄ ተገቢ መልስ እንዲያገኝ ዐኅኢአድ አቋሙን ግልጽ እያደረገ ያለው።

አንዳንድ አክራሪና ጥንፈኛ ግለሰቦችንና ድርጅቶች የኃይል አሰላለፋቸውን ከትህነግ ጋር ያደረጉ እንደሚሉት “ቀጥሎ በሚኖረው ምርጫ በመሳተፍ አሸናፊ ከሆኑ ሕገመንግስቱን ማሻሻል ይሞክሩ፣ ይህን ካላደረጉ ግን ወዮላቸው አርፈው ይቀመጡ” ይሉናል። ዴሞክራሲያዊ ሕገመንግስት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊኖር እንደማይችል ሕሊናቸው በሚገባ እያወቀው!! ሌላው እነዚሁ ተንኳሽ ኃይሎች የትህነግና ኦነግ ሕገመንግስት ከተነካ “ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ እንደወደቀ ይቆጠራል” በማለት ብዙ ብዙ እየዛቱ ነው። ሲፈልጉም መገንጠልን ልክ እንደ ዴሞራሲያዊ መብት ቆጥረውና ላለፉት ፳፰ ዓመታት ከኢትዮጵያ ሕዝብ የዘረፉት ገንዘብ የማያልቅ መስሏቸው አንቀጽ ፴፱ ስራ ላይ ይውላል ብለው ያንገራግራሉ። በመሰረቱ በመሬት ወረራ ላይ የተፈጠረን አፓርታዳዊ መስተዳደር ልክ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የዘረጉ አስመስለው ሲናገሩ ደግሞ አያፍሩም። ከዚህም ስድብ ገፋ ብለው ይሄዱና የፌዴራላዊ ስርዓቱ አዘረጋግም ይሁን ሌላ አማራጭ ካለ ወደ ሕዝብ ለውይይት ሊወርድ ይገባል የሚል ሃሳብ ሲሰሙ ወዲያው ሮጠው “የድሮው ሥርዓት ናፋቂዎችና ትምክዕተኞች” ይላሉ። እነሱው ራሳቸው ቁሞ ቀር ሆነው ለዘመኑ የፖለቲካ ሥርዓት ሊመጥን የሚችል አስተሳሰብን መቀበልና መለወጥ ተስኗቸው መላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁም ስቅሉን እያሳዩት መሆኑን የዓለም ሕዝብ በግልጽ እያወቀ ፡ እናም ዐኅኢአድ ሕገመንግስቱ ለሕዝብ ውይይት መቅረብ አለበት ሲል በዚያው መጠን የትህነግና ኦነግ ፌዴራላዊ ሥርዓት ተብዮው ጭምር ማለቱ ግልጽ ሊሆን ይገባል።

ሕገመንግስትና ፌዴራላዊ ሥርዓት ተብዮዎች ሁለቱም የትህነግ ባለሁለት ስለት ማጥቂያና መግደያ መሳሪያዎቹ እንጂ የተለያዩ አይደሉምና ዐኅኢአድ ሕገመንግስትና ከፌዴራላዊ ሥርዓት አወቃቀሩ ነጣጥሎ አይመለከታቸውም። ለዚህ ደግሞ እነ አባይ ፀሓዬ በፌዴራል ጉዳዮች ሚ/ርነት ስም በመላ ሀገሪቱ እየዘረ በዐማራ ነገድ ላይ ሲፈጽም የኖረውን የዘር ፍጅት፣ ማፈናቀልና የመሬት ነጠቃ የምናውቀው ነው። ሃቁ ይህ ሆኖ እያለ የአፓርታይ ፌዴራሊዝን ተቀብሎ ማለት ተጨፈኑና ላሞኛችሁ እንደማለት ነውና በፍፁም የምንቀበለው አይደለም።

ሌላው ከሰሞኑ በቡራዩ ሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ በደረሰው ጥቃትና ግድያ አንገታችን ተሰብሮ ሳይቃና “አዲስ አበባ የእኛ ናት” የሚለው መግለጫ መዥጎድጎዱ እጅግ በጣም አስገራሚና ኃላፊነት የጎደልው ከመሆኑ ባሻገር ከእውነትና ከታሪካ ጋር ጭራሽ የሚጣረስ ጭምር መሆኑ ነው። ላለፉት ፳፰ ዓመታት ትህነግ የዐማራ ነገድን ያሰቃየውን ያህል የአዲስ አበባ ነዋሪንም ፍዳውን ሊያስቆጥረው እንደኖረ በሚገባ ይታወቃል። ለዚህም ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪ የራሱን የከተማ አስተዳር ነፃ ሆኖ ሊዘረጋና ሊያቋቁም ይቅርና ከአባቶቹ ባድማ በትህነግ ካድሬዎችና ተላላኪዎች እየተባረረ አምስት ሳንቲም ከኪሳቸው ሳያወጡ የሰው ባድማ በመቀማትና በውድ ዋጋ እየቸበቸቡ በሰበሰቡት ገንዘብ ዘመናዊ ፎቅ ለራሳቸው ገንብተውበታል። ከላይ ለማመላከት እንደሞከርነዉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሕዝብ የራሱን አስተዳድር ከትህነግ ነፃ ሆኖ ሊፈጥር ይቅርና በባሕላዊ ዕድርና ዕቁብ እንኳን ተሰባስቦ መገናኘት አይችልም።

ይህ ፀያፍ ድርጊት የሚቆምበት ጊዜ ይመጣል እየለ በነቂስ ወጥቶ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ በደገፈ ማግስት ዛሬ ደግሞ ለአዲስ አበባ ነዋሪ ሕዝብ የተሰጠው መብት “በጉዲፈቻና በሞጋሳ” የኦሮሞ ጽንፈኛ ድርጅቶችን መልካም ፈቃድ ተጠግቶ እንዲኖር የሚፈቀድለት መሆኑን መስማት እጅግ በጣም አደገኛ አካሄድ መሆኑ ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ ባላይ ሄዶ መነጋገር ከንቱ መጃጃል ነውና ምንም ይሁን ምንም የአዲስ አበባ ነዋሪ ሕዝብ በየደረጃው ላሉት የከተማ አስተዳድር መዋቅሮች ራሱን በራሱ እንዲመራ እንዲደረግ ዐኅኢአድ በጽኑ የሚታገልለት ጉዳይ መሆኑን መግለጽ የግድ ብሏል። በመጨረሻውም ብዙ ጊዜ ስለ ሁለተኛ ቋንቋ አስፈላጊነት ይነሳል። ይህን ሃሳይ ዐኅኢአድ በጽኑ የሚደግፈው ቢሆንም ቅሉ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ሁሉም ት/ቤቶች “የልዩነት ምልክት እንዲሆን ታስቦ” በታሪካዊ ጠላት ኃይሎችና በነሱ ተከታዮች በተቀረጸ ላቲን ፊደላት የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ሃሳብና ፍላጎት ቅድሚያ ስሜቱን ጠይቀው ሳያውቁ እንዲሁ በጅምላ ለማስተማር መሞከር እድምታው ቀላል አይደለምና ጉዳዮ የሚመለከታቸው አካሎች ጋር ሰከን ብለው በምሁራዊ መንፈስ ቢመለከቱት ይበጃል።   ምክንያቱም በሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋዕፆ ያደገውና የበለጸገው ሀገር በቀሉ የራሳችን የግዕዙ ፊደል እያለ የላቲኑን ፊደል መጠቀሙ በብዙዎች ዘንድ እያወዛገበ ያለ ነውና አላስፈላጊ ገንዝብ፣ ጉልበትና ጊዜ እንዳይባክን ማድረግ ተገቢ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በላቲን ቋንቁ ዜጎችን ማስተማር እንደ ግዴታ ሲወሰድ ዜጎች በራሳቸው ቋንቋ የመማር መብታቸውን መጠበቅም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው መሆኑን መቀበል ግዴታ ነውና ይህም ተገቢ እልባት ይሰጠው!!

የዐማራ ኅልዉና መጠበቅ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው !!!

Filed in: Amharic News, News, Politics & Economics, Politics & Openion, Social & Culture, መቅደላ Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.