0

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ማዕከላዊ ምክር ቤት ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባ የአቋም መግለጫ፦

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ማዕከላዊ ምክር ቤት ሦስተኛ መደበኛ 
ስብሰባ የአቋም መግለጫ፦ እኛ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) 
የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት እ.ኤ.አ ነሓሴ 18 ቀን 2018(ነሐሴ 12 ቀን 2010 ዓም)
ለአንድ ቀን ባደረግነው ስብሰባ፣ በድርጅቱ የስድስት ወራቶች እንቅስቃሴ፣ በአገራችን ተጨባጭ 
ሁኔታና በተለወጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ የዐኅኢአድ የአደረጃጀት ለውጥ አስፈላጊነት በሚሉት
ዐባይት ርዕሶች ላይ የቀረቡትን ሪፖርቶች አዳምጦ እና ተወያይቶ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

1. አገራችን እና ሕዝባችን የሚገኙበት ተጨባጭ ሁኔታ ወደ አዲስ የለውጥ እንቅስቃሴ የገቡበት ወቅት መሆኑን፣ ይህም ሕዝባችን ከፍተኛ የተስፋ ሰንቅ መሰነቁ፣ በአንፃሩም፣ የለውጡ እርማጃ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማችን ይነካብናል ብለው የሰጉ ቡድኖችና ኃይሎች የሕዝቡ ተስፋ እንዲጨልም የማይፈነቅሉት የተንኮ ሤራ ድርጊት ሊኖር እንደማይችል ያስገነዘበው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቱው ዘገባ፣ የለውጥ አራማጁ ኃይል ይቅር ተባባሉ ስላለ ብቻ፣ ፍፁም ይቅርታ ይወርዳል ለማለት እንደማይቻል ምክርቤቱ አስገንዝቧል። ምክንያቱም ይቅር በሉ በመባሉ፣ በደሉን በጫናቃቸው የተሸከሙ ወገኖች ልብ የሚሽር የመሰላቸው ብዙዎች እንደሆኑ የተስተዋለ መሆኑን ያጤነው ምክር ቤቱ፣ የትናንቷ ባሕረ ነጋሽ ወይም ኤርትራ “በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ተይዧለሁ፤ ቅኝ ያዥውም ዐማራ” ነው ብለው ለዐማራው የተለያዩ ማጥላያ ስሞች ሰጥተው፣ አያሌ ግፎችን ከፈጸሙ በኋላ፣ ጊዜ እና መቆየት ትክክለኛውን መንገድ ሲያሳያቸው፣ «ዐማራን በጠላትነት ፈርጀን ያልሆነውን እንደነበረ አድርገን ብዙ ማለታችን ትክክል አልነበረም»
በማለት « የይውጋህ ብሎ ይማርህ» ዓይነት አነጋገር በአደባባይ ሲነገር ስንሰማ፣ ዐማራው ምንጊዜም ከዕውነት ጋር የቆመ ሐቀኛ ሕዝብ እንደሆነ ዛሬ የመሰከረው የኢሳያስ አፈወርቂ አመራር፣ ነገም የመለስ ዜናዊ ቡድን ይህን
እንዲደግም ትግሉን አጠንክሮ መቀጠል ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ጭምር እንደሆነ አጢኗል ። ይህ እንዲሆንም፣ ይቅርታውና የወደፊት ምልከታው ሳይዛባ መቀጠል የሚችለው፣ ይቅርታው ሥራዓት ተበጅቶለት፣ ጥቃትና ጉዳት
የደረሰባቸው አካሎች የጉዳታቸው መጠን ታውቆ፣ የጥቃት እና የጉዳት አድራጊዎቹ ማንነት ተለይቶ፣ በሚዘከርበት መልኩ፣ «ይቅር ለእግዜርአብሔር» መባባሉ ሲፈጸም እንደሆነ ዐኅኢአድ ያምናል። ይህም ዕውን እንዲሆን የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አባላት፣ አካላትና ደጋፊዎች የበኩላቸውን ሚና ለመጫዎት እንዲችሉ አመራሩ ከምንጊዜውም በበለጠ ከሕዝቡ መሀል ሆኖ ኃላፊነቱን ለመወጣት ቃል ይገባል።

2. ምክር ቤቱ ባደረገው ሠፊ ውይይት፣ ይህ ዛሬ በአገራችን ምድር የሚቀነቀነው የይቅርታ፣ የሰላምና የመደመር መዝሙር ባለቤቱ ማንም ሳይሆን፣ ሕዝቡ ራሱ መሆኑን ግንዛቤ ወስዷል። የዚህ የጠነከረ አቋም መነሻ ምክንያቱም ባለፉት ከሦስት አሥርታት ዓመታት በላይ ባስቆጠረ ጊዜ ሕዝቡ መተኪያ የሌላት የልጆቹን ሕይዎት፣ አካል፣ ደምና ንብረት ገብሮ በትግሉ ያመጣው እንጂ፣ የተወሰኑ ቡድኖች ከሰማይ ያወረዱት አለመሆኑን ሂደቱ በማሳየቱ እንደሆነ ታምኖበታል።

ለውጡ፣ በእስር የተሰቃዩ፣ የተገረፉ፣ የተዋረዱ፣ በባሕር የሰመጡ፣ በሊቢያና በግብፅ ምድረ-በዳዎች የታረዱ፣ በዱር በገደሉ የቀሩ የሕዝብ ልጆች የደምና የሕይዎት ዋጋ እንደሆነ በማመን፣ ይህ ለውጥ እንዲመጣምአያሌ ዜጎች በግልና በቡድን ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ መሆናቸውና፣ ከነዚህ ወገኖች አንዱና ዋናው የዐማራ ሕዝብመሆኑ፣ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት በዐማራው ወገናችን ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋትና
የዘር ማጽዳት፣ ዘመቻ እንዲገታ፣ ዐማራው ኅልውናውን አስጠብቆ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ ለሚደረገው ትግል የበኩሉን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የተጀመረው የለውጥ ሂደት ተፈላጊውን ግብ ለመጨበጥ
እንዲቻል በአገር ቤት ገብቶ ሕዝቡን ታግሎ የማታገል ሚናውን እንዲጫዎት ቃላችን እንድሳለን ።

3. ተደጋግሞ እንደተነገረውና ነባራዊ ሁኔታዎችም እንደሚያሳዩት ለማናቸውም እንቅስቃሴዎች ለግብ መብቃት የሚወሰነው በውስጣዊ ሁኔታዎች እንደሆነ ይታወቃል። የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትም ምንም
እንኳን፣ ወሣኝ አካሉ ውጭ አገር ቢሆንም፣ አመራሩ በሚሰጣቸው የተግባር መመሪያዎችና የንቃተኅሊና ማጎልመሻ መሪና ቀስቃሽ መልዕክቶች በአገር ቤቱ እንቅስቃሴ ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ የፈጠረ እንደሆነ አሌ አይባልም። በዚህ ምክር ቤት የወል ውሣኔ እና ለውሣኔው መነሻ የሆነው የአገሪቱ ፖለቲካ ለተፎካካሪ ድርጅቶች ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ብንገነዘብም፣ አገራችን ኢትዮጵያ ወደዬት አቅጣጫ ልታመራ እንደምትችል በግልጽ የተቀመጠ ፍኖተ መንገድ ባይኖርም፣ በሕዝቡ በተለመደውና ባለፈው መንገድ አንገዛም የእንቢተኝነት ሁለንተናዊ ግፊትና የተግባር ተሳትፎ፣ የተገኘው የአመራር ለውጥ የተገኘው ተስፋ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ እንዲሁም የዐማራው የኅልውና ተጋድሎ ካስመዘገባቸው ድሎች በመነሳት፣ የውጭ አመራሩ አገር ቤት መግባት፣ ቀደም ሲል በእንቅስቃሴ ላይ ካለው የድርጅቱ የውስጥ አካል ጋር በመዋሐድ፣ ዓላማውን ወደ ተሻለና የላቀ ደረጃ በማሸጋገር ታግሎ የማታገል ኃላፊነቱን በጥራትና በቅልጥፍና ለመወጣት ለውጡ በር የከፈተለት እንደሆነ ይታያል። ይህም የውጭው አካል አመራሩን ከውስጥ እየተቀበለ፣ በድጋፍ ሰጭነት ማለትም በዲፕሎማሲ፣ በገንዘብ፣ በመረጃና በዕውቀት ዘርፎች ላይ ትኩረቱን አሳርፎ፣ ድርጅቱ የዐማራውን ኅልውና አስጠብቆ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ ለሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የሚጠበቅበትን ሚና ለመጫት ዝግጁነቱን ያረጋግጣል።

4. የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ምክር ቤት፣ በኅልውና ዘመኑ ያጋጠሙትን ችግሮችና በሂደቱ የተከሰቱ ድክመቶችን በማረም፣ ቃሉን ሆኖ፣ የውዴታ ግዴታውን ለመወጣት የምንችለውንና አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ቃላችን ከማደስ በተጓዳኝ፣ ሕዝቡ ለለውጥ ያለውን ተነሳሽነት አጎልብቶ እንዲቀጥል ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ከርቀት በማመላከት፣ ሕዝቡ የለውጡ ተጠቃሚና ባለቤት ሆኖ ለድል የሚበቃበትን ሁኔታዎች ከባለድርሻ አካላት ጎን በመሆን የድርሻችን ለመወጣት ቃል እንገባለን።

5. የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የዐማራውን ኅልውና በአስተማማኝ አስጠብቆ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት ዳብሮ መቀጠል ከሚሹ ወገኖች ጋር ከኅብረት እስከ
ውሕደት በሚደርሱ የትብብርና የአንድነት ቅርጾች ውስጥ በመሳተፍ ጣምራ ዓላማዎቹን ዕውን ለማድረግ እንዲቻል አባላቱና አካሎቹ የሚቻለንን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን።

6. የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት በዐማራ ኅልውና እና በኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄዎች ለድርድር የማይቀርቡ የጸኑ አቋሞቹ ናቸው። እነዚህ ጣምራ ዓላማዎቹ በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ዕውን ይሆኑ ዘንድ፣ የምላተሕዝቡን ፍላጎትና ጥቅም በሚወክል መልኩ፣ የተያያዘው የለውጥ እንቅስቃሴ ሕዝቡን ያሳተፈ እና ተቋማዊ እንዲሆን፣ የለውጡ እርምጃዎች የትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ሂደትን እንዲከተል እና ሂደቱ ተከታታይ እንዲሆን፣
የዲሞክራሲያዊ ተቋሞች ማለትም የምርጫ ሕግና የምርጫ ቦርድ፣ የፍትሕ አካሎች፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋሞች፣ የፓርቲዎች ሕግ፣ የባለሥልጣኖች ሥነምግባር ሕግ፣ እና የነዚህ ሁሉ እናት የሆነው በግለሰብ ነፃነትና በዜግነት
መብት ላይ የተመሠረተ ሕገመንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ተረቆ፣ በምላተ ሕዝቡ የሚጸድቅ እንዲሆን ይታገላል። 

የዐማራ ኅልውና መጠበቅ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!

Filed in: Amharic News, News, Politics & Economics, Politics & Openion, መቅደላ Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.