0

በተቀየረው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የዐኅኢአድ ሚና !

በተቀየረው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የዐኅኢአድ ሚና!                                                          ቅጽ ፪  ቁጥር ፬  ሀምሌ ፭ ቀን ፪ሺ፲

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ)፣ የዐማራውን ኅልውና በአስተማማኝ አስጠብቆ፣ የኢትዮጵያ አንድነትን ማረጋገጥ የሚሉ ጣምራና ላይለያዩ የተጋመዱ ጉዳዮችን አጣጥሞ የያዘ፣ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አንድነት የሆኑ አስተሳሰቦችና አመለካከቶችን በመዋጋት፣ የኢትዮጵያን ዳግም ትንሣዔ ለማብሰር የተደራጀ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።

ዐኅኢአድ ለዚህ ዓላማው ዕውን መሆን፣ ዐማራነትና ኢትዮጵያዊነት የተጋመዱባቸውን ዘመን ጠገብ የሆኑ ዕሴቶችን በማዳበርና ወቅቱ ከሚጠይቃቸው ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እያዛመድ ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር እንዲቻል ኢትዮጵያዊነት ማተቡ፣ ማንነቱ፣ መገለጫውና ለዚህም ዳብሮ መቀጠል ከሚሹ ሌሎች ነገዶችና ጎሣዎች ጋር በተለያዩ መስተጋብሮች ውስጥ ራሱን አስገብቶ የአያያዥነት/የአንድነቱን ሚና የተጫወተውን የዐማራ ነገድ፣ በዘመነ የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ ቡድን የተፈጸመበትን የዘር ጥቃትና መገለል በጽናት እየመከተ ታሪካዊ የማሰባሰብ ሚናውን እንዲጫዎት የበኩሉን አስተዋጽዖ እያደረገ የሚገኝ ድርጅት ነው።
በመሆኑም በእስካሁኑ ጉዞው፣ ዐኅኢአድ የዐማራው ነገድ ሆን ተብሎ በትግሬ-ወያኔ የተፈጸመበትን የዘር ዕልቂት በመቋቋም ኅልውናውን ለማስጠበቅ ራሱን ከማናቸው አደጋ መከላከል የሚችልበትን ሁኔታ እንዲያዳብርና ማንነቱን እንዲያስጠብቅ በሚያስችሉ ስልቶች ዙሪያ እንዲደራጅ አጥብቆ ሠርቷል። የዐማራው ማንነትና ኅልውና መሠረቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት በመሆኑ፣ ማንነቱን ከሠፊዋ ኢትዮጵያ ጋር በጥብቅ የተጋመደ መሆኑን አውቆ፣ ለኢትዮጵያዊነት ዳብሮ መቀጠል ከሚሹ ሌሎች ነገድና ጎሣዎች ጋር የነበረውን በዘመናት የተገነባ የአብሮነትና የአንድነት ስሜት በማዳበር ወደ ተሻለ የዕድገት ጎዳና እንዲያመራ የሚያመላክቱ ሀሳቦችንና የአሠራር ግንኑነቶችን ሲያመላክት ቆይቷል።

ይህ ቆይታም ከሌሎች መሰል ተግባሮች ጋር ተዳምሮ፣ በአገራችን ኢትዮጵያ የአፋኙን ሥርዓት በነበረ መልኩ ሊቀጥል እንዳይችል በማድረጉ፣ የአመራር ለውጥ እንዲያደርግ መገደዱን አይተናል።
የአመራር ለውጡ እና የለውጡ ፊታውራሪ የሆኑት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ ባለፈው የተፈጸሙ ክፉ ድርጊቶች፣ ነጣጣይና ከፋፋይ ፖሊሲዎችን ሁሉ «በይቅርታ፣ በፍቅር እና በመደመር» ረስተን፣ ወደፊት በመመልከት ሰላም፣ ነፃነት፣ ዕኩልነትና በአንድነት እንኑር የሚል መርሕ አንግበው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ በግልጽ ይታያል።

ይህን መርሕ ደግሞ፣ ከትግሬ-ወያኔ ዘረኛ ቡድን አባላት በስተቀር፣ ምዕላተ ሕዝቡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከከተማ እስከ ገጠር፣ ከሕፃን እስከ አዛውንት ከሙሉ ልቡ የተቀበለው/ሉት መሆኑን በተለያዩ ከተሞች፣ በተለይም በአዲስ አበባ፣ በባሕርዳር፣ በጎንደር፣ በአርባ ምንጭ እንዲሁም ከአገር ዉጭ ጭምር ወዘተ በተደረጉ የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፎችና የአዳራሽ ዉስጥ ዉይይቶች የታደመው ሕዝብ ብዛትና ያነገባቸው መፈክሮች ተጠቃሾች ናቸው።
የለውጡ አመራር፣ ባለፉት መቶ ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሕዋር ውስጥ የተስተጋቡ ሀሳቦችና በተግባር የተስተዋሉ አመለካከቶችና ድርጊቶች አጥፊዎች እንደሆኑ ያምናል። በፀረ-ዐማራነት የተራመዱ ሀሳቦች ከፀረ-ኢትዮጵያዊነት ዕሳቤ የመነጨ እንደሆን ግንዛቤ አለው።

ማንነቶች ተፈጥሮአዊ በመሆናቸው፣ ማንነትን መሠረት አድርገው የሚነሱ ጥያቄዎች ነባራዊ ሁኔታዎች በፈቀዱት መጠን በውይይትና ሰጥቶ በመቀበል መልስ ማግኘት ያለባቸው እንደሆነ ያምናል። የማንነት ጥያቄዎች ግን፣ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን በሚንድ መልኩ መሆን እንደማይገባው በጽኑ ያምናል። ኢትዮጵያዊነትን ለመናድ፣ አንድነትን ለማላላት የተራመዱ ሀሳቦችና አሠራሮች መታረም እንዳለባቸው ያምናል። እነዚህ ደግሞ በተወሰኑ ቡድኖችና አካሎች ብቸኛ እንቅስቃሴ ዕውን ሊሆኑ እንደማይችሉ ግንዛቤ አለው።

የለውጡ ዓላማዎች ዕውን እንዲሆኑ፣ የሁሉንም የባለድርሻ አካላት፣ ከሁሉም በላይ የሕዝቡን ሙሉና ቀጥተኛ ተስትፎ የሚጠይቅ እንደሆነ የለውጥ አራማጁ ክፍል የፀና እምነት እንዳለው እያከናወናቸው ያሉት የተግባር እንቅስቃሴዎች ያሳያሉ።
ከዚህ አጠቃላይ የአገራችንና የሕዝባችን ፍላጎት በመነሳት፣ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አመራር ሁኔታዎችን በጥሞና መርምሮ፣ የለውጥ አራማጁ ኃይል፣ ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክና መሰል ማኅበራትና ታዋቂ ግለሰቦች ላቀረበው የአገር ግቡ እና ሀሳባችሁን በሕዝባችሁ መሀል ሆናችሁ አራምዱ ጥያቄን በመቀበል፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር አገር ቤት ገብቶ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቶ እና ሁኔታዎችን አጢኖ እንዲመለስ በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት፣ ተልዕኮውን ተወጥቶ ተመልሷል።

በተልዕኮም የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ እስካሁን በአገር ቤት በኅቡዕ ይንቀሳቀስ የነበረው ድርጅት በይፋ መንቀሳቀስ እንደሚችል፣ ውጭ ያለው የድርጅቱ አካላትና አባላት ገብተው ከሕዝባቸው ጋር ያመኑበትን፣ የዐማራውን ኅልውና አስጠብቆ፣ የኢትዮጵያን አንድነት የማረጋገጥ ሀሳብ በነፃነት ማራመድ እንደሚችሉ እና ለዚህም መንግሥት በሕግ በኩል ለሁሉም ዜጎች የሚደረገው ጥበቃ ለድርጅታችንም የተጠበቀ እንደሚሆን ያረጋገጡለት እንደሆነ አሳውቋል። ይህም ማለት የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የለውጡ እንቅስቃሴ አካል በመሆን፣ የለውጡ ሂደት በተገቢው መንገድ እንዲጓዝና አገራችንና ሕዝባችን የሚሹት አብሮነትና ኢትዮጵያዊነት ዳብሮ እንዲቀጥል የበኩሉን ሚና መጫዎት እንዳለበት በማመን፣ የጀመረውን የዐማራን ኅልውና አስጠብቆ፣ የኢትዮጵያን አንድነት የማረጋገጥ ትግል ለግብ እንዲበቃ፣ ከሕዝቡ መሀል ሆኖ፣ የሕዝቡን ኖሮ እየኖረ፣ የሕዝቡን ጥያቄ በራሱ በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ዕውን እንዲሆን፣ መንገድ የማመላከትና አቅጣጫ የማሳየት ተግባሩን ለመወጣት ውጭ ያለው አመራር አገር ቤት ለመግባት ቁርጠኛ ውሣኔ አድርጓል።
ይህ ውሳኔ በድርጅቱ የአደረጃጀት፣ የትግል ሥልትና እና እስካሁን ያራምዳቸው ከነበሩ አቋሞች የተለየ ሁኔታን መከተል ግድ እንደሚያደርገው ታምኗል። በዚህም መሠረት፣ ምንም እንኳን የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መሠረቱ አገር ቤት ይሁን እንጂ፣ የአገር ቤቱ እንቅስቃሴ በኅቡዕ በመሆኑ እንቅስቃሴው በሚፈለገው ደረጃ ተራምዶ ነበር ለማለት በሁለት ምክንያቶች አያስደፍርም። አንደኛው ድርጅቱ ከተመሠረተ ያስቆጠረው ጊዜ ረጅም አለመሆን፣ ዓላማውን ለማሰራጨት ጊዜ፣ ዕውቀት፣ የሰው ኃይልና መሰል ጉዳዮች በተሟላ መልኩ ማቅረብ አለመቻሉ ሲሆን፣ ሁለተኛው እንቅስቃሴው በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚራመድ ኅቡዕ መሆኑ ናቸው። ይህም ስለሆነ የድርጅቱ ሞተር ያለው ውጪ ነበር።   ይህም ማለት ወሳኝ የድርጅቱ አመራር፣ የሰው ኃይል፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ምንጭ ያለው ከአገር ውጭ ነው ።

በአደረጃጀት ደረጃ ለውጥ አለ ስንልም፣ የድርጅቱ ወሣኝ አካል የሆነውና ውጭ የቆየው አመራር ወደ አገር ቤት ገብቶ፣ ቀደም ሲል በኅቡዕ ከተመሠረተው አመራር ጋር ተቀላቅሎ ጠንካራ አመራር በመፍጠር አሁን አገሪቱና ሕዝቡ ለሚጠይቁት ጥያቄ ተገቢ መልስ እንዲያገኙ በማድረግ፣ የድርጅቱ ወሳኝ አካል ሙሉ ኃይሉን ከውጭ ወደ ውስጥ የማዛወሩ ነው። ውጭ የሚቀረው የድርጅቱ አካል ከወሳኝነት ወደ ድጋፍ ሰጭነት በመለወጥ የአደረጃጀት ለውጥ ማድረግ አስፈላጊና ተገቢ እንደሆነ ታምኖበታል።
በዚህ መሠረት፣ የውጭው የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አመራር አካላትና አባላት ቀደም ሲል ከነበረው የሠፋ አደረጃጀት በመውጣት፣ ሰብሰብና ምጥን ወዳለ የድጋፍ ሰጭነት አወቃቀር በመለወጥ፣ ለድርጅቱ የገንዘብ፣ የዲፕሎማሲ፣ የመረጃ እና የቅስቀሳ ሥራዎች ላይ በማተኮር የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዓላማ የሰመረ እንዲሆን የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ለዚህ ዕውን መሆንም ድርጅቱ አስፈጊውን የአደረጃጀት ለውጥ በምክር ቤቱ አስወስኖ ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጋል።

በሌላ በኩል የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የትግል ሥልት፣ ዘረኛውን የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ መንጭቆ ለመጣል ይከተል የነበረው የትግል ሥልት፣ የወያኔ «እህትና አጋር» ድርጅቶች የሚባሉትን ከወያኔ እኩል ተጠያቂ በሚያደርግ ደረጃ ላይ ያነጣጠረ ሁሉንም በጠላትነት የመፈረጅ ሥልት የሚያቀነቅን ነበር። ይህ ሁሉንም በአንድ ዓይነት የጠላትነት ደረጃ ፈርጆ የመታገል ሥልት የጠላትን ኃይል ከማሳሳት ይልቅ በተቃራኒው የማጎልበትን አቅም የሚፈጥር፣ የጠላትን ኃይል ማዳከምና ከጠላት ውስጥ ወዳጅ የሚሆን የማፍራትን ቋሚ የትግል ዘዴን የሚቃረን በመሆኑ፣ ከዚህ አመለካከት ወጥተን፣ የወያኔን አቅም የሚያዳክም፣ አጋሮቼ ናቸው ያላቸውን ጠላቶቹ እንዲሆኑ የማድረግ ሥልት መከተሉ ለትግሉ ዘመን ማጠር ከመርዳቱም በላይ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት የሚቀንስ ሆኖ በመታየቱ፣ የስልት ለውጥ ማድረጉ ተገቢ መሆኑ ታምኖበታል። በሌላ በኩል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምንማረው ሙሴ ከፈርዖኖች ጉያ አድጎ ለእስራኤላውያን ነፃነት እንደቆመ ሁሉ፣ ሚካኤል ጎርባቾቭም ከሶቭየት ኅብረት ኮሙኒስት ፓርቲ ማሕፀን ውስጥ አድጎ “ግላስኖስትና ፕሮስቶሪካ በሚሉ መርሆቹ” የተጫወተውን ወሣኝ ሚና አይተናል። 

በዚሁ ዕይታ፣ ወያኔ የኔ ያላቸው፣ «እህትና አጋር» ድርጅቶች ከሚላቸው መካከልም ዕውነተኛ የሕዝብ ልጆች እንዳሉ መጠራጠር አይቻልም።  በሕዝቡ እንቢተኝነትና የአመጽ ግፊት ወደ አደባባይ የወጡት የለውጥ አቀንቃኝ ቡድኖች እና አሁን በዶ/ር ዐቢይ መሪነት የሚዘመረው «የመደመር» መዝሙር የዚህ አባባል ማሳያ ነው። ይህም በመሆኑ፣ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የዐማራው ኅልውና ተጠብቆ የኢትዮጵያ አንድነት መረጋገጥ ፍላጎት ካላቸው ኃይሎችና ስብስቦች ጋር ተባብሮ መሥራትን ዓላማ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው።

አሁን በአገር ቤት የተፈጠረው የለውጥ እንቅስቃሴም ያስከተለው የእንደመር ጥሪ፣ ከዐኅኢአድ ዓላማ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ፣ የዐማራውን ኅልውና ቅድሚያ ትኩረት ሰጠዉ፣ ግን ደግሞ ለኢትዮጵያ አንድነት ዳብሮና ጠንክሮ መቀጠል ቁርጠኛ ፍላጎት ካላቸው ድርጅቶችና ቡድኖች ጋር ከትብብር እስከ ውኅደት ባሉት የአንድነት ቅርጾች ውስጥ በመሰለፍ አሁን የተጀመረዉ ለውጥ መሠረታዊ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማድረግ ቆርጦ፣ የትግል ማዕከሉን አገር ቤት ለማድረግ ወስኗል። የዐማራውም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት አገራችንና ሕዝባችን ላሉበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ችግሮች የዳረገው፣ የትግሬ-ወያኔ የዘረኛዉ የፖለቲካ ሥርዓትና እያራመደ ያለው የዘር አመለካከት እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል።  የዚህ ችግር ብቸኛ መወገጃውም መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል።

ከትግራይ ክ/ሀገር በስተቀር በሁሉም አካባቢዎች ባካሄደው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ባስተጋባቸው መፈክሮች እና ይዞት በወጣው ሰንደቅ ዓላማ ፍላጎቱንና መሆን የሚሻውን አሳይቷል። ይህም ከመሠረታዊ ለውጥ ባሻገር፣ በጥገናዊ ለውጥ የሚመለስ ጥያቄ አይሆንም። ይህ የመሠረታዊ ለውጥ ጥያቄ ደግሞ ዕውን ሊሆን የሚችለው፣ የዚህ ዓላማ አራማጅ የሆኑ ወገኖች የተከፈተውን የለውጥ እንቅስቃሴ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እንዲጓዝ የበኩላችን አስተዋጽዖ ማድረግ ስንችል ነው።

በእስካሁኑ ጉዞ፣ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት፣ የሚከተሉት መከናወን እንዳለባቸው አምኖ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወሳል። ለአብነት ያህል፦

1) የሕዝባዊ አመጹ እንቅስቃሴው ስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው አስፈላጊውን ሁሉ ማድረጉ፣

2) የትግሬ-ወያኔን አገዛዝ በሕዝብ ትግል መጣልና ሁሉን አሳታፊ የሽግግር ሥርዓት ሊፈጠርበት የሚችልበትን መንገድ
ማመቻቸትና ለዚሁ መነሻ የሚሆን የሽግግር ጊዜ ሰነድ ማዘጋጀቱ፣

3) የሽግግር ሥርዓቱም ሁለት ደረጃዎች ወይም እርከኖች ያሉት እንዲሆኑ እና፤ አንደኛው እርከን ወደ ሕዝባዊ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ሊያመራን የሚችል «የባላደራ ወይም የመሰላል» መንግሥት ማቋቋም።

4) የዚህ የባላደራ መንግሥት የሥልጣን ቆይታ ጊዜ፣ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ሆኖ፣ በነዚህ ጊዜአቶች ውስጥ፣ ያለው መንግሥታዊ መዋቅርና ቢሮክራሲ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሰላምና አገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ ሲሆን፤ ሁለተኛው የፖለቲካ ውክልና የሌላቸው በሕዝብ ብዛት መጠን በሚሠራ ቀመር ላይ ተመሥርቶ እያንዳንዱ ወረዳ የራሱን ወኪል መርጦ በመላክ ጊዜአዊ ብሔራዊ ሸንጎ ማቋቋም።

5) ይህ በሕዝብ ፈቃድና ይሁንታ የተመረጠው ብሔራዊ ሸንጎ የራሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩን መርጦ፣ በተመረጠው ጠቅላይ ሚኒስትር አማካኝነት የሽግግር መንግሥት በአዋጅ በማቋቋም ከሦስት ዓመት እስከ አራት ዓመት በሚቆይ ጊዜ ውስጥ ወደ ቋሚ መንግሥትነት ሊያሸጋጋሩ የሚችሉ የዲሞክራሲያዊ ተቋሞችን ማቋቋም፣ የተቋሞቹን አሠራርና ግንኙነት የሚወስኑ ሕጎችን፣ ከሁሉም በላይ አገሪቱ ልትመራበት የምትችልበትን ሕገመንግሥት፣ በማዘጋጀት በሕዝብ ድምፅ ማጸደቅ፣

6) ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት መፍጠር፣

7) ባለፉት 28 ዓመታት ሆን ተብሎ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ዜጎች ተመጣጣኝ ካሳ የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት፣

8) ኢትዮጵያ ልትከተለው ስለሚገባት የመንግሥት አደረጃጀት ቅርጽ፣ ጥቅምና ጉዳታቸውን ለሕዝብ በማሳየት በሕዝበ ውሳኔ ማጸደቅ የሚሉትን ደረጃ በደረጃ ማከናወን፤

9) ኢትዮጵያ ልትከተለው የሚገባትን የፖለቲካ ሥርዓት የሚወስን የፓርቲዎች ሕግ በማውጣት፣ ፓርቲዎች ተወዳድረው ባገኙት የሕዝብ ድምፅ መሠረት ሥልጣን የሚረከቡበትን ሥርዓት በማመቻቸት፣ የሽግግር መንግሥቱ በምርጫ ላሸነፈው አካል ሥልጣኑን ማስረከብ የሚሉት የእስካሁኑ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የመታጋያ አጀንዳዎች
ነበሩ። በእስካሁኑ ጉዞው የእነዚህ መፈጸም ለመሠረታዊ ለውጥ የማዕዘን ድንጋዮች ናቸው ብሎ ሲያራምዳቸው መቆየቱ ዕውነት ነው።

አሁን በተጀመረው የውስጥ እንቅስቃሴ ምክንያት እነዚህን እስከሁን ዐኅኢአድ የታገለላቸው ዓላማዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሁኔታውች ስለመፍቀዳቸው በሂደት የሚታይ ይሆናል። በድርጅታችን እምነት እኛ ከላይ በገለጥነው መንገድም ይጓዝ ወይም በሌላ አንድ የማይታለፍ እውነት አለ። ይህም በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ዲሞክራሲያዊ የሆነ ማጠናቀቂያውን ያገኝ ዘንድ ሁሉን አሳታፊ የሽግግር መንግስት መሰየም የግድ ማለቱ ነው። የዐኅኢአድ የማይለወጥ ዓላማ ፣ የዐማራው ኅልውና መጠበቅና የኢትዮጵያ አንድነት መረጋገጥ ጉዳይ ነው። ይህ ዓላማ ደግሞ ካለመሠረታዊ ለውጥ የሚታሰብ አይሆንም። የመሠረታዊ ለውጡ አንኳር መገለጫ የተግባር ማሳያውም የዜግነት መብት የገፈፈው፣ የሰዎችን በአገራቸው ምድር ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ የመሥራትና ባሻቸው አካባቢ የመኖር መብትን ያሳጠው የትህነግ ሕገመንግሥት ሲለወጥና ሕገመንግሥቱ ለግለሰብ መብት፣ ነፃነት፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ዕውቅና ሊሰጥ ይገባል። ይህ ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ ብዙ መንገዶች ስላሉት፣ ካሉት መንገዶች አንዱ፣ አሁን በዶ/ር ዐቢይ አማካኝነት የሚቀነቀነውን በይቅርታ የታጀበ የለውጥ ሂደት ወደ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ እንዲያመራ፣ አስፈላጊውን አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ትግሉን ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ማጣጣም በመሆኑ፣ የዐኅኢአድ የወደፊት ሚና በዚህ ዙሪያ የሚያጠነጥን መሆኑን አባላትና ደጋፊዎች ተገንዝበው አስፈላጊውን የተግባር እርምጃ እንዲወስዱ ለማሳሰብ ይወዳል።

የዐማራው ኅልውና መጠበቅ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ አንድነቷ ጸንቶ ይኖራል!

 

Filed in: Amharic News, News, Politics & Openion, Social & Culture, መቅደላ Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.