0

ሽግግር – ከጥገናዊ ወደ መሰረታዊ ለውጥ!!

 መቅደላ ቅጽ ፪ ቁጥር ፫ በየሁለት ሳምንቱ የሚወጣ ጋዜጣ

 

በዶ/ር አብይ እየተወሰዱ ያሉት የጥገናዊ ለዉጦች ይበልጥ ግልጽ ያደረጉት ጉዳይ ቢኖር “የሽግግሩን መድረክ” 

አይቀሬነት ነዉና የዐኅኢአድ ይህን ይበልጥ ተንተን አድርጎ ለማሳየት ሞክሯልና አባሪዉን በጽሞና ይመልከቱት።

 

ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ/ም በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረማርቆስና ኮምቦልቻ እንዲሁም ሌሎች ከተሞች ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ ሥልጣን በያዙ ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ላከናወኑት ሕዝብን የማረጋጋትና ላቀረቡት አብሮነትና ኢትዮጵያዊነት ዳብሮ የመቀጠል
ጉዳይ «ምሥጋና ለማቅረብና ከጎንህ ነን፣ በጀመርከው የመደመር እሳቤ ግፋበት» የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እጅግ ደማቅ የሆነ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል። እነዚህ ሕዝባዊ ሰልፎች፣ «ተሸፋፍኖ ቢተኙ፣ ገላልጦ የሚያይ አምላክ አለ»፣ እንደሚባለው፣ የትግሬ-ወያኔ
የአራት አስርተ ዓመታት በላቀ ጊዜ ያናፈሰው ኢትዮጵያን የማፍረስና ዐማራን የማጥፋት የተቀነባበረ ዘመቻ ሥር ያልሰደደ፣ «በአሸዋ ላይ የተገነባ ቤት» እንዳደረገው ሕዝቡ ይዟቸው በወጣቸው መፍክሮችና ባቀረባቸው ጥያቄዎች አረጋግጧል። የሕዝቡ ዕውነተኛ ፍላጎት
አንድነት፣ አብሮነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ሰላምና ወንድማማችነት እንደሆነ አሳይቷል። በቋንቋ መከፋፈል፣ ወያኔ አመጣሽ ክልል፣ ዘርን ከዘር ማጋጨት፣ መለያየትና ማበጣበጥ፣ እንዲሁም ስርቆትና ሙሰኝነት የትግሬ-ወያኔ የአገዛዝ ዕድሜ ማራዘሚያ ዘዴዎች እንጂ፣
የሕዝቡ ፍላጎትና ምኞት አለመሆኑን እጅ ለእጅ ከመያያዝ አልፎ በድምፁ አብሮነትና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳበር ቃል ገብቷል።

ሕዝቡ ባለፉት 28 ዓመታት የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ፣ ዘረኛ፣ ከፋፋይ፣ ዘራፊና ፀረ-ኢትዮጵያ ነው ከማለት አልፎ፣ አሸባሪ መሆኑን ከተጨባጭ ድርጊቱ በመነሳት መፈረጁ ይታወቃል። አገዛዙ በሕዝብ ላይ፣ ሆን ብሎ፣ ፈንጅ እያፈነዳ፣ «አሸባሪ» የሚል ቅጽል ለጥፎ፣
ንፁሐን ዜጎችን የሚገድል፣ የሚያስርና የሚያሰቃይ በመሆኑ፣ ሕዝቡ አሸባሪው ሌሎች ሳይሆኑ፣ የትግሬ-ወያኔ ቡድን እንደሆነ በግልጽ በያደባባዩ ሲናገር መኖሩን አንዘነጋውም። በትክክልም አሸባሪው የትግሬ-ወያኔ እንደሆነ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የትግሬ-ወያኔ አባል
ከሆኑ የፓርላማ አባሎች ከእስር የተፈቱት ሰዎች አግባብነት እንደሌለው አድርገው ላቀረቡላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ፣ «አሸባሪው ማነው?» ብለው በመጠየቅ፣ “ሰዎችን ጨለማ ቤት ማሰር፣ አካል ማጉደል፤ ማሰቃየት ሕገመንግሥታዊ አይደለም። የመከላከያ፣
የደኅንነቱና የፍትሕ አካሎቹ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው፣ ሕገመንግሥቱን ማስከበርና የአገሪቱን ዳር ድርንበር መጠበቅ ኃላፊነታቸውና ግዴታቸው ሆኖ ሳለ፣ እየገነባናቸው የመጡት ተቋሞች ግን ከዚህ በተለየ መልኩ መሆን ሕገመንግሥታዊ አለመሆኑን”
አስረግጠው፣ ሰዎች ሲፈቱ ዓይናቸው የሚቀላ ሰዎች መኖሩ ማስገረሙን አጽንዖት ሰጥተው ማስረዳታቸውን እናስታውሳለን።

ይህን የዶ/ር ዐብይን ምሥክርነት ከጥርጣሬ አልፎ፣ የሚክዱ የትግሬ-ወያኔ አባሎችና ደጋፊዎች እንዳሉ ቢታመንም፣ «ተሸፋፍነው ቢተኙ፣ ገላልጦ የሚያይ አምላክ አለ» የሚሉት የአባቶቻችን አባባል ዘመን የተሻገረ ሐቅ በመሆኑ፣ አሸባሪነታቸውን ከአራት ሚሊዮን
በላይ የሆነ ሕዝብ እጅግ ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ አንድነትን፣ አብሮነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ ሰላምን፣ መቻቻልና ይቅርባይነትን እያስተጋባ በሚዘምርበት አደባባይ ላይ ሕዝብን ለማጫረስ፣ ዶ/ር ዐብይንም ገድሎ ወታደራዊ አገዛዝ ለማስፈንና ሕዝቡን አባልቶ የቆየ
እቅዳቸዉን ተግባራዊ ለማድረግ አገሪቱን ለመበታተን ያመቸናል ብለው አስበውና አቅደው ያፈነዱት ቦንብ አሸባሪነታቸውንና ማንነታቸውን ለዓም ማኅረሰብ በይፋ አሳይተዋል።

ይህ ሕዝባዊ ሰልፍ፣ ሦስት ጣምራ ተግባሮችን ያሳየ ነበር። አንዱ ለዶ/ር ዐብይ እያቀነቀኑት ስላለው ከትግሬ-ወያኔ መሥመር የወጣ፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን፣ ይቅርታንና አብሮነትን ማዕከል ላደረጉት ብሩኅ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴዎች የይግፉበት፣ ከጎነዎት ነን
የሚል ድጋፍ ነበር። ሁለተኛ ሕዝቡ ያስተጋባቸው መፈክሮችና ብዛቱ፣ ያሳየው ሥነ-ሥርዓትና ድፍረት የኢትዮጵያን አንድነት ዳግም ትንሣዔ አይቀሬነት ያመላከተ ማሳያ ሆኖ መታየቱ ሌላዉ ነው። ሦስተኛው የሕዝብ ሰላም፣ አንድነትና ዴሞክራሲ ፀር የሆነው የትግሬወያኔ
ዘረኛ አገዛዝ፣ ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-መቻቻልና የይቅርታ አውራ ጠላትና አሸባሪ መሆኑን ሕዝብን ለመጨረስ ባፈነዳው ፈንጂ፣ አሸባሪነቱን በገሐድ ያሳየበት ሌላው ጥምረት ነው። በዚህም አሸባሪ ድርጊቱ የንፁሐን ዜጎች ሕይዎት እንዲቀጠፍ፣ የአካል ጉዳት
እንዲደርስባቸው በማድረጉ፣ ቀኑ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ልዩ ቦታና ትዝታ የሚይዝ መሆኑ ናቸው።   ለቀኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ እንዲይዝ የሚያደርገው፣ ሰልፉ የተጠራውና የተዘጋጀው እንዳለፉት ሁሉ በፖለቲካ ድርጅት
ካድሬዎች ጉትጎታ፣ ዛቻና ማስፈራራት፣ በቀበሌዎች አስገዳጅነት ሳይሆን፣ በራሱ የሕዝቡ አካል በሆኑ፣ ከሁሉም በላይ ለበርካታ ዓመታት ድምፃችሁን ለምን ታሰማላችሁ ተብለው የመከራ ሥቃይን በየእስር ቤቱ በተቀበሉት ሰዎች ባጭር ጊዜ ውስጥ ተጠርቶ፣
ከአራት ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድበው፣ በሌሊት እንቅልፉን ሳይጠግብ በገፍ ገንፍሎ ወጥቶ፣ ሁሉም ያመነበትንና የመሰለውን ሀሳብ በአደባባይ ማሰማቱ ከድሮዎቹ ሕዝባዊ ሰልፎች የተለየ መሆኑ ነው።
ከሁሉም በላይ ዕለቱን ልዩ የሚያደርገው ወያኔ ሀርነት ትግራይ በህዝብ በይፋ የተተፋበትና የተዋረደበት ቀን መሆኑ ነው።

ወያኔ ሀርነት ትግራይ በህዝባዊው ትግል ተገፍታ አመራሯ በመቀሌ ተሰባስቦ ለሌላ ዙር ጦርነት ዱለታ የትግል ደረጃ ውስጥ የወደቀበትን የተመለከትንበት ጊዜ ነው። ወያኔ የረጅም ጊዜ ህልሟ ተሰናክሏል። የረጅም ጊዜ ህልሟ እስከቻለችበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያን በመከፋፈል ሀብቷን መዝረፍና ትግራይን መገንባት፥ በሂደትም በኢሳያስ የምትመራ ኤርትራን አዳክሞ ከኢሳያስ ሞት በኋላ መሀሏ ባዶ በምትሆን ኤርትራ ላይ የትግሬን የበላይነት እውን የሚያደረግ የትግራይ-ትግርኝ መንግስት ጥንሥን ማዋቀር ነበር። ይህ ስሌት ደግሞ አዲስ ሳይሆን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በⷅኝ ግዛት ሙከራ ዉድቀታቸዉ ወቅት አቅደዉት የነበረዉና ወያኔ ተግባራዊ ሊያደርገዉ የተመሰረተበት ቀዳሚዉ ሴራው ነበር።

ከኢትዮጵያ የበላይነቷ ሲያከትም የትግራይን የበላይነት የሚቀበል የትግራይ ሪፑብሊክን እውን በማድረግ ከኢትዮጵያ መገንጠል ነበር።
ሆኖም ግን ክብር ለሰማዕታት ይሁንና የሰማዕታት ትግሉ ወያኔን ቀደማት። ትግሉ ኢትዮጵያን መታደግ ብቻም ሳይሆን ኢሳያስንም ሳይሞት ቀድሞ ደረሰለት።  እናም ኤርትራም ሳትበትን እንደ ሀገር ኮርታ ከኢትዮያ ጋር እንድትደራደር አደረጋት። በዚህም የወያኔ
የትግራይ-ትግርኝ ታላቅ እቅድ ውኃ በላው። የትግራይ የመገንጠል ህልምም ወደ ቅዠት ተለወጠ። ወያኔ ሀርነት ትግራይ አብይ በሚመራው መንግስት ላይ ቀጥታ ወታደራዊ ጥቃጥ ፈጽማ ስልጣን ላይ እንደገና ለመውጣት ያለ እድሏ በየቀኑ እየተሸረሸረ ሂዷል።
በጦር የምትወስደው ሙከራ ቢኖር በህዝቡ ከሚነሳ መቋቋም ባሻገር በቀሉን ለመመለስ ምክንያት ለሚፈልግ ኢሳያስ ወያኔን በጦር ለመምታት መልካም አጋጣሚ ይሆንለታልና ወያኔ ከኢትዮጵያ ህዝብና ከሸአብያ የበቀል በትር መሀል ገብታ ክፉኛ መመታት መሆኑንም
ተረድታለች።  በዚህ ምክንያት የቀራት ጥቃቅን የኢኮኖሚ ቀውስ መፍጠር፣ ህዝቡን በጎሳ እንዲተራመስ ማድረግ፣ አመርራሩን በተለይም አብይን ለመግደል መሞከርና በኢኮኖሚው ውስጥ ባሏት አባላቷ ታላላቅ ተቋሞችን ማሰናከልና ማቃጠል ድረስ የሚሄድ ጥፋት ላይ
ማተኮሯ አይቀሬ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ሰሞኑን በግልገል ጊቤ የኃይል ማመንጫ ላይ የተከሰተዉ ቃጠሎን መገመት አይከፋም። ለትርምሱም እነ ዓባይና ሌሎች የትግሬ-ወያኔ ከፍተኛ አመራሮችና እነበረከት በየስርቻዉ የፍጅት መመሪያ ለመስጠት በያቅጣጫዉ
ተሰማርተዋል።
አዲሱ ትውልድ በምክንያት ሞጋች፣ ደፋርና ኃላፊነትን ለመረከብ ቁርጠኝነቱን በሂደት እያሳየ ነው። ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ያለፉት መቶ ዓመታት የመጣንባቸው የጠላትነት ስሜት ስሕተት እንደሆነ ፣ የኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ባለቤትነት፣ የሰው ዘር ምንጭነት፣ የጥቁር
ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲልነት፣ የቅኝ ገዥዎች ቅስም ሰባሪ መሆኗን፤ ከትግሬ-ወያኔ አመለካከት በተፃራሪ መቆማቸውና ይህ ሕዝብ ከጎናቸው እንዲቆም ያቀረቡት ጥሪና ከሕዝቡ በተለይም ከወጣቱ ያገኙት አዎንታዊ ምላሽ፣ ትግሉ በዚህ እንደማይቆም አመላካች ነበር።
ሽግግሩ ከጥገናዊ ወደ መሰረታዊ ለውጥ ጉዞ ላይ መሆኑን ብዙ አመላካች ሁኔታዎች እየታዩ ነው። ከነዚህ አማላካቾች ውስጥ በጥገና ለውጥ ፍላጎቱ የማይረካው የህብረተሰቡ ብዙሀን የሆነው በጠዋቱ ነቅሎ መነሳት ነው። ይህ የወጣቱ ለመሰረታዊ ለውጥ መነሳሳት
ከዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) ለእዉነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ ቆራጥ አቋም ጋር መገጣጠም የአገራችን ትልቁ ተስፋ ነዉ። በመሆኑም ለምንወዳት ሀገራችንም የወደፊቱ ጉዞዋ ብሩህ ነው።

በሰልፉ ቀን ዐብይ ሕዝቡ ከጎኑ ያለውን በማቀፍና በመያያዝ ይቅር እንዲባባልና አንድነታቸውን እንዲያሳዩ በጠየቁት መሰረት የታየው መተቃቀፍና መጨባበጥ የተለየ ስሜት የፈጠረ ነበር። የተበደለ ሲካስ፣ በዳይ ሲክስ ባይታይም በስሜት ደረጃ ብሔራዊ ዕርቅ እንደወረደ
ያህል ሕዝቡ ደስታውን ሲገልጽ ተስተውሏል። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብ «ግዝ እንደንጉሡ፣ አውድማ እንደ አግማሱ» ወይም  «ተመልከት ዓላማህን ተከተል አለቃህን» የሚለው መርሕ ቁራኛ እንደሆነ ያሳያል። ሕዝቡን ክፉም ደግም የሚያደርጉት ገዥዎቹ እንደሆኑ
ባለፉት 40 ዓመታት በተለዋወጡ መሪዎች ሕዝባችን ያከናወናቸው ተግባሮች የአባባሉ ማሳያዎች ናቸው። በሌላ በኩል፣ ባንድ ወገን የትግሬ-ወያኔ ሕዝቡን ለማጫረስና መሪውን በመግደል ወታደራዊ አገዛዙን ለማስፈን አቅዶ ባፈነዳው ፈንጅና በፈጸመው የአሸባሪነት
ተግባር፣ በአያሌ ንፁሐን ዜጎች ላይ የሕይዎትና የአካል ጉዳት ያደረሰ አሳዛኝ ክስተት ሲፈጸም፣ ይህ ክስተት ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ፣ ለአብሮነት፣ ለይቅርታና ለመቻቻል፣ ለዴሞክራሲና ለኢትዮጵያዊነት ዳብሮ መቀጠል፣ የተዘራ ውድ የመስዋዕትነት ዘር መዘራቱን
ሲያሳይ፣ በሌላ በኩል የተዘራው የአብሮነትና የኢትዮጵያዊነት የደም ዘር፤ የዘረኛው አገዛዝ ማክተምን፣ የዶ/ር ዐብይን ከትግሬ-ወያኔ አመለካከት ፈጽመው እንዲርቁ የደም፣ የሕይዎትና የአካል ግብር የተገበረበት የወደፊት ግፋ የሕይዎት ሥንቅ ነው። ይህም በመሆኑ ይህ
ቀን በአገራችን የወደፊት ጉዞ ልዩ ቦታ ይዞ ሲዘከርና ሲወሳ ይኖራል። ቀኑ ዳግማዊ ዐድዋ በአዲስ አበባ ዓይነት ነው። ሰላማዊ ሰልፉ፤ ኢትዮጵያውያን ምንጊዜም አንድ ሊሆኑ የማይችሉ የተፈጥሮ እና የአመለካከት ልዩነቶችን በመቻቻል አቅፈው፣ ልዩነቶቹ
ውበቶቻቸውና ጌጦቻቸው እንደሆኑ አምነው በአንድነት ጥላ ሥር ለዘመናት የኖሩና ለወደፊቱም ካለፈው በተሻለና ዘመንን በዋጀ ሁኔታ በአንድነቱ መቀጠል እንዳለባቸው ያመላከተ መንደርደሪያ ወይም ማኮብኮቢያ ሆኖ ተቆጥሯል። የሀሳብ ልዩነቶችን በውይይት፣
በመቻቻልና ሰጥቶ በመቀበል መንገድ መፍታት የሥልጣኔና የዕድገት ማሳያ ዋና መሥፈርት ነው። በሌላ በኩል የሓሳብ ልዩነት ለወደፊት ጉዞ የተሻለ አመለካከት፣ ከልዩነቱ እንዲፈጠር የሚረዳ እንጅ፣ ነባር አንድነትን በሚንድ መልኩ መቀንቀን ትክክል እንዳልሆነ ህዝብ
ተረድቶታል። ይህም ሰላማዊ ሰልፍ አሉ የሚባሉት የሀሳብና የአመለካካት ልዩነቶች ለተሻለች ኢትዮጵያ ተጠናክሮ መውጣት የሚበጅ የወል አመለካከት ነጥሮ እንዲወጣ መሠረት የጣለ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ራሳቸው ወያኔዎች ላለፉት 27 ዓመታት በመድረኩ
ከተሰበኩት በጥላቻና በእናውድመው፣ በመገንጠልና ሌሎችን ማዋረድን ይሰማበት የነበረው አደባባይ አንድነት፣ ሰላም፣ መተሳሰብና ይቅርታ መሰበኩ፣ ያለፈውን የሻረ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያን ተንሣሄ በግልጽ ያሳዬ ነበር። ይህንም ላለፉት መቶ ዓመታት የተሰበከው
የጥላቻና የመነጣጠል ፕሮፓጋንዳ ላለንበት ችግር የዳረገንና ይህን ዘመን በይቅርታ መሻገር እንዳለብን ጥሪ ያቀረበ ነበር።

ዶ/ር ዐብይ ባለፉት መቶ ዓመታት የተነዛው የጠላትነትና የመነጣጠል ፖለቲካ እንዳልጠቀመ፣ ከዚያ አዟሪት መውጣት እንዳለብን የገለጹበት መንገድ፣ በአመለካከት ካሳደጋቸው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማዕከላዊነት አስተሳሰብ የወጡና ራሳቸውን ጨምሮ የኢትዮጵያን
ሕዝብ አስሮ ከያዘው የአመለካከት ማዕቀፍ ነፃ አውጥተው ሕዝቡ ነፃ እንዲሆንና ለአመለካከታቸው ሥር መስደድ ሕዝቡ ከጎናቸው እንዲቆም ያቀረቡት ጥሪ፣ ከትግሬ-ወያኔ በብዙ እርቀት የተለዩ መሆኑን ገላጭ ነው። ዶ/ር ዐብይ ያቀረቡት የእንደምርና የዕርቅ ጥሪ
እንደተጠበቀ ሆኖ፣ «ብልጥ ወይም ብልኅ ልጅ፣ የሰጡትን ይዞ ያለቅሳል» እንዲሉ፣ የዐማራው ሕዝብ ባለፉት 43 ዓመታት በትግሬወያኔ ድርጅታዊ መርሃግብር ተቀርጾ፣ ታቅዶና ሆን ተብሎ፣ ስለተፈጸመበት የዘር ፍጅት ይህ ነው ያሉት ነገር ባይኖርም፣ እያቀነቀኑት
ያለው የአብሮትና የኢትዮጵያዊነትን ሀሳብ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የሚመለከተው በአዎንታዊነት መሆኑን ደጋግሞ ገልጿል። ከሁሉም በላይ የዐማራውን የነቁ ልጆች አሳዶ ለመግደልና ለማሰቃየት ተጨባጭ ምክንያቶች ሲያጡ፣ ራሳቸው ፈንጅዎችን ቀብረው፣
እንዲፈነዱና በተቀነባበረ ሤራ በአሸባሪነት እየከሰሱ በሕዝባችን ላይ ያደረሱት ጥቃት እጅግ ዘግናኝና መሪር በመሆኑ ምንጊዜም የዐማራው ትውልድ የሚዘነጋው አይሆንም። «የወጋ ቢረሳ፣ የተወጋ አይረሳምና!» ስለሆነም እኛ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት
ድርጅት አባላትና ደጋፊዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደባባይ ንግግሮች ከጥገናዊ ለውጥ የወጡ መሆናቸውን ጠቋሚ ናቸው ብለን እናምናለን።   አስከትለውም እነዚህን በንግግር የጥገና ለውጦችን የሻሩ መልክትዎትን ወደ ተጨባጭ የመሰረታዊ ለውጥ ጉዞ
የሚያስኬዱንን እርምጃዎች እንዲወስዱ ዐኅኢአድ በአንክሮ ማሳየት ይወዳል። እንዚህም፦

1) ዐማራው ባልተሳተፈበትና ሆን ተብሎ በተገለለበት ሁኔታ የሕገመንግሥት ተብዮዉ መርቀቅና መጽደቅ፣ የሻዕቢያ፣ የትግሬ-ወያኔና የኦነግ ስምምነት በመባል የሚታወቀው የተሰኔ ማንፌስቶ(መግለጫ) ውጤት የሆነው ሕገመንግሥት
ዐማራን አገር አልባ ያደረገና ለሚደርስበት የዘር ፍጅትና ጥቃት እንደ ሕጋዊ መነሻ ሰነድ ሆኖ እያገለገለ ያለ ስለሆነ፣ ይህ ሕገመንግሥት ፀረ-ዐማራ ብቻ ሳይሆን፣ የዜግነት መብትንና የግለሰብ ነፃነት የማያውቅና የገፈፈ ስለሆነ፣ በዜግነት
ማንነትና የግለሰብ ነፃነትን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ሥልጣን የሕዝብ መሆኑን በሚያረጋግጥ ሕገመንግሥት እንዲተካ እርምጃ ይዉሰዱ፣

2) የእስካሁኑ የአገራችን ችግሮች ምንጩ ሕዝቡ የሥልጣን ባለቤት ሳይሆን የሚቀረጹ ሕጎች፣ አመለካከቶች፣ ግንኙነቶችና አሠራሮች ከቡድን እና ከግለሰቦች ፍላጎት የሚመነጩ መሆናቸውና የሕዝቡን ዕውነተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ
ፍልጎቶች ተፃራሪ መሆን አንዱ ነው። ከዚህ ኢ-ዴሞክራሲያዊና ፀረ-ሕዝብ ሁኔታ ወጥቶ፣ ሥልጣን በባለቤቱ በሕዝብ እጅ እንዲገባ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ድርጅቶች፣ ማኅበሮች፣ ስብስቦች፣ የሃይማኖት ተቋሞች፣ ታዋቂ
ግለሰቦችና ተቋሞች በቀጥታ ተካፋይ የሆኑበት፣ ማንንም ያላገለለ “ሁሉ አቀፍ የሽግግር መንግሥት”የሚመሠረትበትንና ኢትዮጵያ ወደ ዕውነተኛ ዴሞካራሲያዊ ሂደት ሊያስገባ የሚችል መደላድል እንዲፈጠር
የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎችን ይፍጠሩ፥

3) በትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ዐማራው በጠላትነት ተፈርጆ፣ «ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ፣ ገዥ መደብ፣ ጨቋኝ ብሔር ወዘተ–» ተብሎ ተፈርጆ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል የተፈጸመበት ስለሆነ፣ ይህን ዓለም አቀፍ ወንጀል
የፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ለፍትሕ የሚቀርቡበትን ሁኔታ የሚያመቻች የአሠራር ሂደትን ያመላክቱ፤

4) በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል መፈናቀል፣ መሳደድና መሰቃየት ለተፈጸመባቸው ወገኖች ተመጣጣኝ ካሣ የሚያገኙበት ሁኔታ አመላከች መንገድ ያሳዩ፣

5) ቀለም ቀመስ የሆነው ትውልድ ግራ ዘመም የዓለም አመለካከት ቁራኛ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ ደም የተቃባና ፊትና ጀርባ ሆኖ የቆመ ስለሆነ፣ ይህ የታሪክ አጋጣሚ በይቅርታና በመቻቻል መንገድ ለማስታረቅና ወደፊት በአንድነት ለመጓዝ
የሚያስችል የብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ሊፈጠርበት የሚችልበትን ሁኔታ የሚያመቻች ተግባር በተጨባጭ እንዲያሳዩ ማመላከት እንወዳለን።

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) ዶ/ር ዐብይ እስካሁን ላሳዩዋቸው ከትግሬ-ወያኔ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አመለካከት መውጣት፤ ለኢትዮጵያዊነት አንድነት መቀጠል፣ ለይቅርታና ለመቻቻል ላቀረቡት ጥሪ፣ ድጋፉን እየገለጸ፣ የሁላችን የሆነች
ኢትዮጵያን ለመገንባት ጽኑ መሠረት ለሚሆኑት ከላይ በዝርዝር የተገለጹትን ከዕለት ተዕለት ሥራዎችዉ መካከል ቀዳሚዎቹ እንዲያደርጓቸው ጥሪያችን በድጋሜ እናቀርባለን። እነዚህ ጥያቄዎች ሕዝባችን መሥዋዕተነት የከፈለባቸዉ የሕዝብ ጥያቄዎች ናቸውና
ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጧቸዉ ተስፋ አለን። ሆኖም ግን እነዚህ የሕዝብ ቀጥተኛ ጥያቄዎቹ ካልተመለሱ ወይም ቢሸራረፉ ደግሞ የዐማራው የተጋድሎ እንቅስቃሴ አይቆምም። ስለሆነም፣ ዐማራው የአገሩ፣ የታሪኩ እና የማንነቱ ባለቤት የሚሆነው በራሱ መራራ ትግል
እንደሆነ ስለሚታወቅ፣ እነዚህ ጥያቄዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሁነኛ መልስ እንደምናገኝ ተስፋችን አሁንም ከፍተኛ ነው። ዶ/ር ዐብይ ለእነዚህ ጥያቄቆች መልስ በመስጠትም በአደባባይ ለብሰውት የወጡት ማንዴላን ፎቶግራፍ እንደሚሆኑ መጠን ዕምነታችን ጽኑ
ነው።  ይህን ሲያደርጉ ቃልን ከግባር ያዋሐዱ ቆራጥና ዕውነተኛ ታሪካዊ ሰው የሚለውን ስም እንደሚያጎናጽፋቸው እምነታችን ነው። ታሪክ መሥራት ማለትም ከዚህ የበለጠ ሌላ ምንስ ከፍተኛ ኃላፊነት ይኖራል!!

የዐማራው ኅልውና መጠበቅ፣ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ አንድነቷ ጸንቶ ይኖራል

Filed in: News Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.