0

ይድረስ ለኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ !! መቅደላ ቁጥር 10 ፣ april 15, 2018

                                                                                                                                                                                                                                    ቅጽ 1 ቁጥር 10  ሚያዝያ 4/10,  2010

                           ይድረስ ለኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ!

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥፈርት መሠረት፣ «ወጣት» ማለት ዕድሜአቸው ከ15 እስከ 30 ዓመት የሆኑት የኅብረተሰብ አባሎች እንደሆነ ይገልጻል። ኢትዮጵያ የሕዝባቸው ቁጥር በከፍተኛ መጠን በማደግ ላይ ካሉት አገሮች አንዷ ከመሆኗም በላይ፣ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ትገኛለች። የሕዝባችን ቁጥርም ከመቶ ሚሊዮን በላይ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ ቁጥር ውስጥ ከመቶው 65ቱ ወጣት እንደሆነ ይታመናል። ይህም ከሕዝባችን ቁጥር ከፍተኛ መጠን ያለው ወጣቱ እንደሆነ ይታመናል። ወጣትነት ለሥራ ፣ ለትግል፣ ለለውጥ፣ ለአዲስ ነገር ተነሳሽነት ጎልቶ የሚታይበት የዕድሜ ገደብ እንደመሆኑ፣ የአንዲት አገር ዕድገት፣ ለውጥና መሻሻል ወይም ለዚህ ተቃራኒ ውጤት በየዘመኑ ባለው የወጣት ትውልድ እንቅስቃሴ የሚወሰን መሆኑ ዕውነት ነው።

ወጣቱ፣ የነገዪቱ ኢትዮጵያ ተረካቢና መሪ እንደመሆኑ መጠን፣ ይህን ኃላፊነቱን ለመወጣት መማር፣ መማር መማር እና ማወቅ ከቀደምት ተግባሮቹ ዋናው እንደሆነ ግልጽ ነው። ለመማር ደርግሞ በቅድሚ ለመማር የሚያስችሉ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሰላሞችና ደኅንነቶች መረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ከነዚህ ማኅበራዊ ደኅንነቶች መረጋገጥ በተጓዳኝ፣ ለመማር ማስተማሩ ተግባር ቀናነትና ውጤታማነት ከአድልዖ የፀዳ ሥርዓት መዘረጋት የግድ ይላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ በትምህርት ሥርጭትና ሥርፀት ውስጥ ቁልፉ መምህሩ እንደመሆኑ፣ የመምህራን ሙያ ብቃት፣ ሥነሥርዓት አክባሪነት፣ ኢትዮጵያዊ ማንነት የማያወላውል መሆን፣ በማኅበረሰቡና በተማሪዎቻቸው ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅና ተከባሪ የመሆን ባሕሪዎች ባለቤቶች ሊሆኑ ይገባል።

ከመምህራኑ ዝግጅት ተከትሎ ሥርዓተ ትምህርቱ ትውልዱ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከዘመኑ ማኅበረሰብ የዕድገት ደረጃ ጋር ለንቅጦ ያዋሐደ ሆኖ መዘጋጀት ለመማር ማስተማሩ ሂደት መቃናት የበኩሉን መልካም ድርሻ እንደሚወጣ ይታመናል።

ከዚህ አንፃር ባለፉት 27 ዓመታት የትግሬ ወያኔ ዘረኛ ቡድን የዘረጋው የትምህርት ፖሊሲ ኢትዮጵያን በሚንድና መልካም ዕሴቶቿን በሚያጠፋ መልኩ የተዘጋጀ በመሆኑ ፣ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በወጣቱ አእምሮ ውስጥ ሁነኛ ቦታ እንዳይዝ መደረጉን የትምህርት ፖሊሲው  በግልጽ ያሳያል።

ወጣቱ በአንድነት ምትክ የተሰበከው ብሔርተኝነት እና ልዩነት ነው። አገራዊ አንድነትን ሳይሆን፣ ነገዳዊ ማንነት ነው። ካለፉት መካም ተመክሮዎች ተነስቶ የወዲፊቱን የበለጠ የተሻለ ከማድረግ ይልቅ፣ የኋላ ታሪኮችን በሀሰት በማባዛት ትውልዱ ሆድና ጀርባ ማድረግ ነው። ያለፉ ድንቅና ተዓምራዊ ሊሰኙ የሚችሉ ታሪኮቻችን በማጣጣል ወፍ ዘራሽ የሆነውን ማንገሥ ነው። ትውልዱን የጋራ አገር ተረካቢ ከማድረግ ይልቅ፣ በወርቅና በመዳብነት በመከፋፈል አንዳንዶቹ፣ የወርቆቹ ዘሮች ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁ ትምህርት ተቋሞች ዕውቀት እንዲገበዩ ሲደረግ፣ ብዙኃኑ በዛፍ ጥላ  ፊደል እንዲቆጥቱ መደረጉን ስናስተውል ዘረኛው ወያኔ የዘረጋው የትምህርት ሥርዓት የቱን ያህል አግላይና አድላዊ እንደሆነ እንረዳለን።

ሥርዓተ-ትምህርቱ አግላይ በመሆኑም፣በርካታ የአገሪቱ ወጣቶች ከወቅቱ ጋር ተዛማጅ የሆነ ሙያ ለመቅሰም አልቻሉም። ይህም በመሆኑ ካገሪቱ ሥራ አጥ ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው ወጣቱ ነው። ራሱን ችሎ ወላጆቹን መጦር የነበረበት ወጣት ትውልድ፣ ለራሱ ያለመብቃቱ ዋናው ምክንያት አገዛዙ የተከተለው የትምህርት ፖሊሲ አድላዊና አግላይ መሆን ነው። ዛሬ የጫት ቤቶችንና የተጠቃሚውን ሰው ማንነትና ብዛት፣የሲጋራ አጫሹን፣ የተለያዩ ዕፆች ተጠቃሚው ማን እንደሆነ ስናስተውል፣ በርካታው ቁጥር በትምህር ፖሊሲው አድላዊነት ምክንያት ከትምህርት ገበታዎች የተገለለው ወጣት እንደሆነ እንረዳለን። በየትኛውም መልኩ ይሁን፣ ይህ አገዛዝ ካልተለወጠ የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ታሪካዊ ሚናውን ሊወጣበት የሚችልበት ሁኔታ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም።

ወጣቱ ሊያገኝ የሚገባውን የመማር፣ የማወቅ፣ የመዝናናት፣ የመጠየቅ፣ የመሳተፍ፣ የመደራጀት መብቱን ገፎ፣ የወጣት ጡረተኛ ያደረገውን አገዛዝ፣ ከሁሉም በላይ አገሩንና ማንነቱን ያሳጣውን ይህን አረመኔ ዘረኛ አገዛዝ ለማስወገድ ሕዝቡ በቆራጥነት የተያያዘውን ሕዝባዊ አመጽ በማጠናከር ፣ወያኔ አጥፍቶን ሳይጠፋ ሕልሙን ቅዠት ለማድረግ የተቀጣጠለውን ትግል ማጠናከር ለነገ የሚለውን እንዳይሆን አደራ ለማለት እንወዳለን።

ወጣቱ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹን የዚያን ጊዜዎቹን ወጣቶች፣ የአምስት አመቱን አርበኞች ተጋድሎ ታሪክ በማደስ፣ የነርሱ ልጅ መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል። ነፃነት፣ አንድነት፣ ዕኩልነት፣ ማንነት በዋዛ አይገኝምና ለነፃነት መከፈል ያለበትን ዋጋ ለመክፈል ምክንያቶችን ሊኖሩን አይገባም። የምንፈልገውን ለማግኘት የሚጠይቀውን ዋጋ መክፈል ግዴታ ነው። ግዴታውን ያልተወጣ፣ የመብቱ ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችልም መገንዘብ ተገቢ ነው።

በመሆኑም ወጣቱ፣ ከሁሉም በላይ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ሰለባ የሆንከው የዐማራ ወጣት፣የአባቶችህን ወኔ በመላበስ፣ ነፃነቴ ወይ ሞቴ! ማንነቴ ወይ ሞቴ ! ብለው ዱር ቤቴ ያሉትን ወጣቶች አርኣያ በመከተል ትግሉን መቀላቀል ይጠበቅብሃል። ዛሬ ትግሉ ካልተቀላቀልን ነገ ይመሽብንና የዘወትር ተገዥ እንሆናለን። ፕሌቶ«ራሳችን ከፖለቲካ ባገለልን ቁጥር፣ በምንበልጣቸው ሰዎች በመገዛት እንቀጣለን!» ሲላ ከክርስቶስ ልደት አሥር ሺ ዓመታት በፊት የተናገረው ቃል ዛሬ፣ የዐማራው ምሑራንና ወጣቶች፣ ራሳቸውን ከፖለቲካው በማግለላቸው፣ በሚንቋቸውና በአናሳዎቹ የወያኔ ቡድኖች እየተገዙ አይቀጡ ቅጣት እየቀጧቸው መሆኑን እያየን ነው። ይህ በምንበልጣቸው ሰዎች እየተገዛን መቀጣታችን ካንድ ቦታ ላይ ማስቆም አለብን። ይህም ነገ ሳይሆን ፣ዛሬ ነው። ለዚህ ትግል ግንባር ቀደም መሆን ያለበት ደግሞ የዛሬዪቱም ሆነ የነገዋ ኢትዮጵያ ባለቤት የሆነው ወጣቱ ትውልድ ነው።

የዐማራው ኅልውና መጠበቅ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!

ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን አደራ ይወጣል!

 

 

 

 

 

Filed in: Amharic News, News, መቅደላ

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.