0

የሕዝብ ጥያቄ መሰረታዊ ለውጥ ነው !!

3/30/2018 ልዩ እትም

                                                       

የሕዝቡ ጥያቄ መሰረታዊ ለውጥ ነው

 

የሰሞኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካና ፖለቲከኞች የመወያያ ርዕስ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የትግሬ-ወያኔው ጭምብል «ኢሕዴግ» ሊቀመንበር መሆንና፣ አይቀሬው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የመሆን ጉዳይ ነው። በተወሰነ  የሀገራችን  ሕዝብ  ዘንድ የማይጨበጥ  ተስፋ ማጫሩም የሚታይ ነው።  ይሁንና  ግን  የዶ/አብይ  ወደ ስልጣን  መምጣት መታየት ያለበት ኢሀዲግ ከገባበት ማጥ ውስጥ ቢያወጣኝ ብሎ ያደረገው ውስጠ ሹም ሽር አንጻር ነው። ይህ ውስጠ ሹም ሽር ይበልጥ የሚያተኩረው  ኢሀዲግን ከማጡ ውስጥ ለማውጣት ድርጂታዊ የጥገና ለውጥን ማካሄድ ላይ ይሆናል።  ይህንን ለማድረግ ከዚህ በፊት ድርጂቱ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የጣላቸውን የአፋኝ ድንጋጌዎችን  ሊያነሳ ይችላል።  እራሱን ያደሰ አስመስለው ሊያሳዩኝ  ይችላሉ ብሎ የሚያስባቸውን የመቀባባት እርምጃዎችን  ሊያደርግ ይችላል። ከነዚህም ወስጥ  ያለጥፋታቸው ያሰራቸውን መፍታት፣ ወታደሩ ከግድያው እንዲታቀብ የማድረግ፣ ለወጣቱ የተወሰነ ጊዜያዊ የስራ ፈጠራ የማድረግ፣ እሱ በፈጠራቸው የጎሳ ግጭት የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው የመመለስ ውዘተ ተግባሮችን  ሊያካሄድ ይችላል።   ይሁንና   እነዚህ መለስተኛ የሆኑ የጥገና መሰል ለውጦች ድርጂቱ ባለፉት 27 ዓመታት የፈጸማቸው ወንጀሎች ናቸው። ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደ መልካም ስራ ተቆጥረው የሚሰጡት ከቶም ሊሆኑ አይችሉም። ህዝቡ በወሰደው ትግሉ በግዴታ እራሱን ተመልሶ እንዲፈትሽ  መደረጉ ነው እውነቱ። ይህ መቀባባት  ህዝቡ ከሚጠይቀው መሰረታዊ ለውጥ ጋር ምንም የሚያደራርሳቸው ነገር የለም።
አኢሀዲግ መለስም መራው አብይ ድርጂታዊ ቁመናውና የሚከተለው ረእዮተ ዓለም ዲሞክራሲያዊ እርምጃን እንዲወስድ አይፈቅድለትም።ከላይ ወደታች በማእከላዊ እዝ የተገነባ ወታደር መሰል ድርጂት ነው። በድርጂቱ ውስጥ የግለሰቦች ነጻነትና የፈጠራ ችሎታና ሚና  ቦታ የላቸውም።  በነዚህ ድርጅቶች የውስጥ አሠራርም ሆነ፣ በግለሰቦች ላይ የመወሰን ሙሉ መብትና ሥልጣን ያለው ሁሉንም የመለመላቸውና ያደራጃቸው ሕወሓት ነው።  የግለሰቦችም ቦታና ሚና የሚወሰን በድርጂት ውሳኔ ነው። ኢሀዲግ የኮሚኒስት ድርጂት በካፒታሊዝም ጭንብል ውስጥ ያለ ድርጂት መሆኑ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል።

አብይን ማየት ያለብን በኢሀዲግ ውስጥ ያደገ፣ የተማረና ለሹመት የበቃ ማደጎው  መሁኑን ነው።  በርግጥ ድርጂቱ በመጥፊያው  ወቅት ውስጥ በመግባቱና  በተለይም ከመለስ ሞት በኋላ አመራር የለሽ ሁኖ መቆየቱ በወያኔ ጥርነፋ ውስጥ ለነበሩት የኢሀዲግ አባል ድርጂቶች በድርጂቱ ውስጥ እኩልነትን ለማግኘት አጋጣሚው ተፈጥሯል። 

አብይ የሚመጣበት የኦህዴድ የእኩልነት ጥያቄም መልስ የሚያገኝበት ጊዜም ዛሬ ሁኗል።  በመሁኑም ለአብይ ሁለት የቤት ስራዎች ቀርበውለታል።  የመጀመሪያው በኢሀዲግ ውስጥ የቆየውን የህወሀትን የበላይነት አስተንፍሶ  በመሀከላቸው እኩልነትን መፍጠር ነው።  ሌላው ስራው  የኢሀዲግን የወንጀል ገጽታውን በማሰማመር ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደ  ስጦታ ያንን አሳምሮ በማቅረብ  የኢሀዲግን የውድቀት ጊዜን ማራዝም  ነው።   ይህ ጎዳና  ባጭር  ጊዜ ውስጥ የአብይንን ማንነት  ፍንትው  አድርገው የሚያሱ ይሆናሉ።  የህልም ተስፋ የጫረባቸው ዜጎችም  ወደ እውነተኛው  የትግል ዓለም ይመለሳሉ።

አብይ መጪውን  አስፈሪ ጊዜ የሚገነዘብ ከሆነ፣  ድርጂቱንም ከመጥፋት ሀገራችንንም  ከማያስፈልግ አደጋ ለመታደግ  የሚያስችል አመለካከት ባለቤት ከሆነ ሌላ አማራጭ ጎዳናን ሊከተል እንደሚችል የአማራ ህልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጂት ሊጠቁመው ይወዳል። የሚከተለው ጎዳና  መልካሙ አማራጭ ነው። የሚወስደውን  ኢሀዲግን ለማሻሻል የሚያደርገውን ዘመቻ ይግፋበት። ይህም  መሻሻል  ማካተት ያለበት በድርጂቱ ውስጥ ያሉ በዘር ፍጂት ፣ በሀገር ክህደት ወንጀል፣በጦር ወንጀል፥ በህዝብ ሀብት ዘረፋ፣ በሙስናና በቅሚያ የሚጠየቁ አባላቱን የማጥራት እርምጃ  ድርጂቱ ወደ ሀገራዊ ድርጂትነት ለያደርግ  ለሚገባ ጉዞው የሚረዱት ተግባሮች ይሆናሉ።   ይህንን ውስጠ መሻሻል  ካደረገ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ የተቃዋሚ ድርጂቶች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በሀገር የወደፊት እጣ ፈነታ ላይ ለመነጋገር ያስችለዋል።   በሕዝባዊ  የሽግግር መንግስት አመሰራረት ላይም የማይናቅ ሚና ሊጫወት ይችላል።   አብይ  ይህንን ጎዞ ከተከተለ ያለምንም ጥርጥር  የጥገናዊ ለውጥ ፊታውራሪ  ሳይሆን  የመሰረታዊ ለውጥ አጋርነቱን አወጀ ማለት ይሆናል። ይህንን ዘመቻ እያደረገ እሱን ገፍቶ ካላበት የስልጣን ማማ ላይ ያወጣውን የህዝብ ትግል ሳይቋረጥ የመቀጠሉን አይቀሬነት ለሱ የውስጥ ትግል እንደአጋር  አድርጎ ሊቆጥረው ይገባል።

በሂደትም በሀገሪቱ  እጣ ፈንታ ያገባናል ለሚሉት ሁሉ ለሽግግር መንግስት ምስረታ እውን መሆን እንዲሰባሰቡ ጥሪ ሊያደርግ የግድ ይላል።እነዚህ ሁለት መሰረታዊ  የሆኑ  ድርጊቶች እውን  ሲሆኑ  ብቻ  ነው  የአማራን ህዝብ ጥያቄን ለመመለስ ከጎዳናው ውስጥ ገብተናል   የምንል። ከዚያ መለስ ያለ መቀባባት ኢሀዲግን ከማይቀርው ውድመቱ ለማዳን የሚደረግ ያልሞት ባይ ተጋዳይ  መፍጨርጨር  ይሆናል።

ይሁንና  ዐቢይ አሕመድ ኮትኩቶ ካሳደገው እና አሁን ለደረሰበት ደረጃ ላበቃው የትግሬ ወያኔ ዓላማና ፍላጎት ተፃራሪ ሆኖ ይቆማል ማለት «ገለባ ያብባል» ከማለት የዘለለ አይሆንም።  ከወያኔ ፍልጎት ውጭ ሊንቀሳቀስ የማይችል መሆኑ ማሳያው፣ ኃላፊነቱን የሰጠው ወያኔ፣የራሱ ሰው መሆኑን በሚገባ አጥንቶና አምኖ ከመሆኑም ባሻገር፣ ሕገመንግሥቱ የሚፈቅድለትን፣የራሱን የካቢኔ አባላት እንኳ መምረጥ እንደማይችልና ኢሕአዴግ መርጦ የሰጠውን ብቻ እንደሚቀበል አምኖና ተማምኖ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህም ዐቢይ ሕገመንግሥቱ የሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት፣ ልክ መለስ ያደርግ እንደነበረው የማድረግ መብቱን ከመጀመሪያው ተገፏል ማለት ነው።

  ዐቢይ ሥልጣኑን እንደተረከበ፣ ቢያንስ  በራሱ ውሳኔ  የራሱን አዲስ ካቢኔ ካላቋቋመ፣ የራሱን ፀሐፊ፣ ጠባቂዎች እና ረዳቶች ካልመረጠና ካልሾመ፣ የአስቸኳይ አዋጁን ካላነሳ፣ የታሰሩትን ሰዎች ካላንዳች ቅድመ ሁኔታ ካልፈታ፣ማናቸውንም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶችና በአገራችን ያገባናል የሚሉ ወገኖችን ያላገለለ፣ አስቸኳይ አገራዊ መግባባትና የሽግግር መንግሥት ምሥረታ የሚያመራ የእንተባበርና የአንድነት ጥሪ ካላቀረበ፣ዐቢይ የኃይለማርያም ደሣለኝን ቦታ የወሰደ ሌላው የድርጂቱ ማደጎ ዐቢይ  ማለት ነው። ራሱን ካልሆነና፣ የህልም ተስፋውን ለጣለበት  ደጋፊው  በትንሹ እንኳ በሕገመንግሥቱ የተሰጡትን የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ኃላፊነቶች ለመወጣት ካልጣረ፣እስካሁን የዘመራቸው የኢትዮጵያዊነትና የአንድነን መዝሙሮች፣ ወያኔ አንጋሎ የጋተው የጊዜ መግዣና ጠላቶቼ ናቸው ብሎ የፈረጃቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች አድኖ ማስጠፊያ ፣የተጋጋለ የሕዝባዊ እንቅስቃሴ ማዳፈኛ መሣሪያ ሮቦት እንደሆነ ማሳያ ነው። ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ ብዙ ጊዜ አይፈጅም። ኃላፊነቱን በተረከበ ማግሥት የምናውቀው ጉዳይ ነው።

 ከዐቢይ መሠረታዊ ለውጥ የሚጠበቅ አይደለም። ይህን ለማድረግ የመጣበት መንገድና ለዚህ ኃላፊነት ያበቃው አደረጃጀት አይፈቅድም። ዐቢይ ብዙ የተዘመረለትን ያህል ሆኖ ለመገኘት ማድረግ የሚችለው፣ሥርዓቱን ተከራክሮ ማሸነፍ የሚያስችለው፣ ሕዝቡንም ከጎኑ ማሰለፍ የሚረዳው የትግሬ-ወያኔ፣ ታግየ፣ «ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች» ዕኩልነት ማረጋገጫ የሆነ ሕገመንግሥት በሕዝብ አጸድቄአለሁ እያለ የሚመካበትን መነሻና መድረሻ አድርጎ፣ ሕጉ በሚሰጠው ሥልጣን ተጠቅሞ፣ ከፍ ሲል ከተጠቀሱት በተጨማሪ፣በግፍ የተፈናቀሉ ዐማራ፣ ኦሮሞ፣ ሱማሌና አኙዋኮችን ወደ ነበሩበት ቦታ ከተመጣጣኛ ካሳ ጋር እንዲመለሱ ካደረገ፣ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖችን ለፍትሕ የሚያቀርብ ኮሚሽን እንዲቋቋም ያደረገ እንደሆነ፣ የዘመረው ኢትዮጵያዊነትና አንድነት ከመስቀልኛ መንገድ ለማውጣት አንድ እርምጃ ወደፊት እንደተራመደ ሊታይለት ይችላል።

ሕዝባችን ላለፉት 27 ዓመታ የታገለው ለመሠረታዊ ለውጥ ነው። የመሠረታዊ ለውጡም መገለጫው፣ የትግሬ-ወያኔ የዘረጋውን በዘር ላይ የተመሠረተ ሥርዓት አፍርሶ፣በምትኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመከረበትና ፍላጎቱን የገለጸመት ፣የሕዝቡ የዜግነት መብቱና የግለሰብ ነፃነቱ የተረጋገጠባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት ነው። በቋንቋ ልዩነት ላይ የተመሠረተው ፌዴሬሽን መሰል አሃዳዊነት የመንግሥት አደረጃጀት ተለውጦ፣ሕዝቡ ለአንድነታችን፣ ለአብሮነታችን፣ ለሰላማችንና ለዕድገታችን ይበጀናል ብሎ በድምፁ ያጸደቀው የመንግሥት አደረጃጀትና የዚሁ ማስፈጸሚያ የሆነ ሕገመንግሥት ባለቤት ሲሆን ነው። የዘመናት ማንነቱ መታወቂያና የነጩ ዓለም የአይደፈሬነት ምልክት የሆነችው አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓለላማችን የክብር ቦታዋን ስትይዝና በዓለም አደባባይ አየር ላይ መውለብለብ ስትችል ነው። ለነዚህ ሁሉ መሟላት ሕዝቡ በተወካዮቹ አማካኝነት የሚመክርበትና የሚወስንበት የሽግግር ሥርዓት ሲመቻች ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ሲሟሉ የሕዝቡ መሠረታዊ የለውጥ ጥያቄ  ደረጃ በደረጃ እየተሟላ መሄዱን ለማየት እንችላለን።

የዐማራው ነገድና የዐማራው ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በዐቢይ መመረጥ የዐማራው የኅልውና ችግር መፍትሔ ያገኛል ብለው  ያምናሉ፣ በዚህም ከትግላቸው ይዘናጋሉ ለማለት አይቻልም። የዐቢይ በዐማራው ላይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል እንዲፈጸም ፕሮግራም ቀርጾ የተንቀሳቀሰው ሥርዓት ዋና አስፈጻሚ ሆኖ የቆመ እንደመሆኑ፣ ለዐማራው የኅልውና ጥያቄ ይቆማል አይባልም። በዚህም የተነሳ ዐቢይ ተመረጠ ከተባለበት ሰዓት ጀምሮ የተቃውሞ ድምፅ እየተሰማ ያለው፣ ያው ወያኔና እህት ድርጅቶቹ በአውራ ጠላትነት የፈረጁት በዐማራው ልጆች አካባቢ ነው። የዚህ ተቃውሞ መቀጠል ዋና ምክንያቱም፣ አንደኛ የዐማራውን የማንነት ጥያቄ የዐቢይ መመረጥ ሁነኛ መልስ ያስገኝለታል ተብሎ አለመታመኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምክንያት በሕዝቡ ተቃውሞና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ከእስር ለቀኳቸው ያላቸውን ከሌሎች ነገድ ልጆች ነጥሎ መልሶ ማሰሩና ሌሎችን የዐማራ ወጣት ንቁ ልጆች በገፍ እያሰረ ማሰቃየቱን በማብዛቱ ነው። ይህም በመሆኑ የተዋቅሞው ድምፅ ቀጥሏል። መቀጠልም የግድ ነው።

የዐማራው የኅልውና ጥያቄ የተሟላ መልስ የሚያገኘው በዐማራው ሕዝብ ትግል ነው።የኃይለማርያም በዐቢይ መተካት፣ የሕዝቡ የተቃውሞ ትግል ያስገኘው መሆኑ ዕውነት ነው። ሕዝባዊ እንቅስቃሴው የወያኔን ፖለቲካዊ መርሕ ከማናጋት አልፎ፣ የስለላና የአፈና መዋቅሩን ከሥር መሠረቱ አናግቶታል። ከስለላ መዋቅሩ መናጋት በተጨማሪ፣ የወያኔ ባሕር የሆነው የትግራይን ሕዝብ ማዕበል ሆኖ እያናወጠው ነው። የትግሬ ሕዝብ እንደ ትናንቱ የወያኔ ቱባ ባለሥልጣኖች አድርግ ያሉትን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። ለምን? እንዴ? ከሁሉም ጋር ደም አቃብታችሁ የት ልታስገቡን አስባችኋል? የሚሉ ጥያቄዎችን እያቀረበ ፊት ለፊት እየተጋፈጣቸው ነው። ይህም የሕዝቡ አመጽ የመግፋት ውጤት ነው።

ዐማራው መብቱንና ነፃነቱን የሚያረጋግጠው፣ በስጦታ፣ ወይም በችሮታ ከዐቢይ በሚቸር ቁርስራሽ መብት ሳይሆን፣ በራሱ ልጆች ትግል የሚያገኘው ተፈጥሮአዊ መብቱ ነው። ስለሆነም የዐማራው ተጋድሎ እንቅስቃሴ ኃይሎች፣ በዐማራ ስም የተደራጁ የፖለቲካ፣ የሲቪክ፣ የሙያና የዐማራ ማኅበራት ስብስቦች ኃይላቸውን አጠናክረውና አቀናጅተው በትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ላይ ሁለንተናዊ ጫናቸውን ማሳደር ይጠበቅባቸዋል። አቅማዳ፣ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ አቅማዳ ነውና፣ የኃይለማርያም በዐቢይ መተካት የሕዝባችን መሠረታዊ የለውጥ ጥያቄ መመለስ አይችልምና ሳናዘናጋ የዐማራው ወገናችን አንግቦት ለተነሳው የማንነትና የኅልውና ጥያቄ አእምሮአችን ሰብሰብ፤ ኅሊናችን ቆጣ፣ አንድነታችን ጠበቅ፣ ጽናታችን በርታ፣ በማድረግ ለትግሉ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንድንሆነ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ጥሪውን ያቀርባል።

የዐማራ ኅልውና መጠበቅ ፣ለኢትዮጵያ አንድነት ዋስትና ነው!

 

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Economics, Politics & Openion, መቅደላ Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.