0

የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የመግባባት ኮሚቴ ፤ The Ethiopian Stakeholders Convention Seattel Declaration !!

 

የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የመግባባት ኮሚቴ

 

የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም.

ሲያትል ዋሽንግተን፤ ሰሜን አሜሪካ

 

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለ ብዙ አንፀባራቂ የታሪክ ባለቤት ሀገር ናት። ሕዝቦቿም ለብዙ ሺህ ዓመታት ተከባብረው፣ ተባብረውና ተዋደው የኖሩባት ታላቅ ሀገር መሆኗን ያህል በታሪኳ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን አስተናግዳ የማታውቅ፣ ሕዝቦቿ በጉልበት ሥልጣን ላይ ለወጣ አምባገነን ሁሉ ተገዢ ሆነው የኖሩባት ሀገር መሆኗንም ታሪክ ይመሰክራል።

እስከዛሬ ከታዩት አምባገነን ገዥዎች ሁሉ የዛሬው ህወሓት መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥት ደግሞ በክፋቱ በጨካኝነቱና በከፋፋይ ስልቱ ታይቶ የማይታወቅ አምባገነን ቡድን ነው።

ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሕዝባችን የነፃነት፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ጥሙን ለማርካት በርካታ ለውጥን ማዕከል ያደረጉ እንቅስቃሴዎችንና አመፆችን አድርጓል። በምትኩም ከነዚህ አገዛዞች የሚያገኘው ምላሽ ሞት፣ እስራት፣ ሰቆቃና ጭቆና ሆኖ እስከዛሬ ቀጥለናል።

የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ገና ከድርጅታዊ አፈጣጠሩ ጀምሮ ሕዝብን በጠላትነት ፈርጆ፣ ፀረ-ኢትዮጵያ ህልሙን አንግቦ በመሣሪያ ኃይል ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ፣ ሰቆቃ፣ እሥራት፣ ስደትና ሞት እየፈጸመ 27 ዓመታት አስቆጥሯል።

እንዲህ እየሆነ መቀጠል እንደሌለበት የተገነዘበው ገና ከጠዋቱ ቢሆንም በተደራጀ፣ በተቀነባበረ መልክ ትግሉን በከፍተኛ ደረጃ መርቶ ከግብ ለማድረስ ሳይቻል አሁን ያለንበት አስከፊ ሁኔታ ላይ እንድንገኝ ሆነናል። ሕዝቡ በዚህ አምባገነን ብሔርተኛነት በተለከፈ ከፋፋይ አገዛዝ ላይ አምጿል። በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎችም በተናጥል ከዚህ ብሔረተኛ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ፈጽሞ ከሌለው ጨካኝ ቡድን፤ ለሰው ልጆች ሕይወት ቅንጣት ታህል ደንታ ከሌለው አረመኔ አገዛዝ ጋር በባዶ እጁ ፊት ለፊት ገጥሞ በመታገል እንዳይድን፣ እንዳያገግምና መልሶም እንዳያንሰራራ አድርጎ ከመሠረቱ አናግቶታል።

ይህ በሀገሪቷ ዙሪያ ብልጭ ድርግም እያለ የሚሄደው የተበታተነ ትግል መሪ ድርጅትን ይሻል። እስከዛሬ ድረስ በተለያዩ መንገዶች የተለያዩ ድርጅቶች ሕዝቡን አደራጅተው ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸው ሀቅ ቢሆንም የምንፈልግበት ቦታ ላይ አልደረስንም። በጋራ ተቀናጅተንና ተባብረን የህዝባችን ጠላት ላይ የጋራ አጀንዳ ቀርጸን፣ የጋራ ራዕይ ሰንቀን ሕዝባችንን ነፃ የማውጣቱን ትግል በጋራ ልናካሂደው እንደሚገባ፤ ይህም የጠላትን ዕድሜ ለማሳጠር ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑን በመገንዘብና ሀገራችን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ በጥልቅ በመመርመር የዚህ ጉባኤ ተሳታፊ የፖለቲካ ድርጅቶች ዓበይት የሀገራችን የፖለቲካ ችግሮችንና ከነዚህ ችግሮችም ሊታደጉን በሚችሉ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት አካሂደናል።    

ይህንን ታሪካዊ ጉባኤ እንድናካሂድና በሀገራችን መፃሂ ዕድል ላይ እንድንወያይ፣ ብሎም ለሕዝባችን እንድንደርስለት ሁኔታዎችን በማመቻቸትና በማስተባበር ይህን ትልቅ ታሪካዊ ኃላፊነት ለተወጡ “የማህበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር (የትብብር)” አመራሮችንና አባል ድርጅቶችም ከልብ የሆነ ከፍተኛ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል እንላለን።

እነሆም የተጣለብንን ታሪካዊ ኃላፊነት ተቀብለን፣ የሀገራችንን ጥልቅና ሰፊ ችግሮች በጥልቅነትና በጥሞና መርምረን፡ ዘርፈ ብዙ ለሆኑት የሀገራችን ችግሮች ምንጩ ህወሓት/ኢሕአዴግ የሚያራምደው የሀገር አንድነትን የካደ ብሔረተኛ የከፋፋይ፣ ጨካኝ፣ ዘራፊና ገዳይ ስርዓት በመሆኑ ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ሉዓላዊነቷ ተከብሮ፣ የግዛት አንድነቷ ተጠብቆ የኖረች ክቡር ሀገር ሆና የመቆየቷን ያህል፤ የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ሲል ብቻ በሕዝቡ መካከል ጥላቻን በመንዛት የተከፋፈለችና የተዳከመች ኢትዮጵያ እንድትሆን አጥብቆ እየሠራ ያለውን ሥርዓት በማስወገድ አንድነቷ የፀና ሉዓላዊነቷ የተከበረ ኢትዮጵያን ዳግም ዕውን ለማድረግ እስካሁን የተጓዝንበትን አዝጋሚና የተበታተነ የትግል ሂደት በማረም እጅ ለእጅ ተያይዘን ቀን ከለሊት ትግላችንን ማጠናከር እንዳለብን በማያሻማ ሁኔታ መግባባት ላይ ደርሰናል።

ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ምትክ የሌለው መፍትሄ ስለሆነ የህወሓት አገዛዝ መወገድና ህወሓት በኢትዮጵያ ምድር የመጨረሻ አምባገነን እንዲሆን፤ በምትኩም ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የመላው ኢትዮጵያውያንን የዜግነት መብትና እኩልነት በሚያረጋግጥ ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት መተካት እንዳለበት ስምምነት ላይ ደርሰናል።

በሕዝባችን መካከል ፀንቶ የኖረውን የአንድነታችን መሠረቶች የሆኑትን የተለያዩ ብሔራዊ ዕሴቶቻችንን በመናድ፤ ይልቁንም ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት የመለያያ ምንጮች እንዲሆኑ የህወሓት አገዛዝ ሳያሰልስ እየሠራ ነው። ይህን አድሎአዊና በቀልተኛ ሥርዓት ከመሠረቱ ለመንቀልና በምትኩም ልዩነቶቻችን ውበቶቻችንና ጌጦቻችን የአንድነታችንም ፅኑ መሠረት መሆናቸውን ለማረጋገጥ እንደምንሠራ ሙሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል።                                                                           

 ለዘመናት በሀገራችን ሕዝብ ጀግንነትና መስዋዕትነት በቆራጥ መሪዎቿ ተጋድሎ ተከብሮ የኖረው የሀገራችን ሉዓላዊ ግዛት ተደፍሯል። ድንበራችን ተቆርሶ ለባዕዳን ተሰጥቷል። ገበሬው ከርስቱ ተፈናቅሎ ለም መሬታችን ለባዕዳን ተላልፎ ተሸጧል። ይህ በህንዲህ እንዳለም የመከላከያ ኃይል የሀገር ድንበርን የሚያስጠብቅና የሕዝብን ደህንነት የሚያረጋግጥ ብሔራዊ ኃይል መሆን ሲገባው፤ የመከላከያ ኃይል ጄነራሎች እና ከፍተኛ የአመራር ኃላፊዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የህወሓት አባላትና ጉዳይ አስፈፃሚዎች ሆነዋል። ከታች ያሉት የመከላከያ አባላት በገዛ ሕዝባቸው ላይ አልመው እንዲተኩሱና ወገናቸውን እንዲገድሉ እየተገደዱ እንደሆነ በሚገባ እንገነዘባለን። ይሁን እንጂ ይህ ወቅት ሕዝብ ለነፃነቱ ቆርጦ የተነሳበት በመሆኑ የሕዝብ ልጅ የሆነው የሠራዊት አባል ሕዝባዊነቱን የሚያስመሰክርበት ጊዜ አሁን መሆኑን እንዲረዳና ወገኖቹን ለዕልቂት ከመዳረግ ወንጀል እንዲታቀብ፤ ከወገን ጋርም እንዲቆምና የሕዝቡን ደህንነት የሚያረጋግጥ ኢትዮጵያዊ ኃይል መሆኑን እንዲያስመሰክር ተግተን የምንሠራ፣ ለዚህም የምንተባበር መሆናችንን ተስማምተንበታል።         

  ህወሓት መራሹ አገዛዝ በፈፀመው መርዘኛ የፖለቲካና ማህበረሰባዊ ተንኮል የተነሳም፤ አብሮ የኖረው ሕዝብ ዐይን ለዐይን እንዳይተያይ ይልቁንም በጠላትነት እየተፈራረጀ እንዲገዳደል፤ ለዘመናት የኖረበትን ቀዬ ለቆ እንዲሰደድ፣ በብዙ ዘመን ድካምና ልፋት ያፈራውን አንጡራ ሀብት እንዲበትንና መሬቱን ለቆ የትም እንዲሄድ ተደርጓል። ይህ በሕዝባችን መካከል የተረጨበት አደገኛ የፖለቲካ ሴራ የሚከሽፈው በማህበረሰቡ ውስጥ በሚፈጠር ሰላም፣ ብሔራዊ ዕርቅና ሀገራዊ መግባባት መሆኑን ጉባኤው አምኖበታል፤ ለዚህ አብሮነትና ፍቅርም በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ቃል ገብቷል።

የህወሓት አገዛዝ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ብቸኛው ሀብታም ቡድን ነው። ሀገሪቷን በጠመንጃ ኃይል ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱን ንብረት በብቸኝነት እየዘረፈ ዘልቋል። አንዳንዴ በጉልበቱ ሌላ ጊዜ በትግራይ ህዝብ ስም በተቋቋሙ ኤፈርትን በመሰሉ ድርጅቶቹ አማካኝነት ለከት ባጣ መልኩ የሀገሪቱን ሀብት ማጋበሱን ተያይዞታል። የሀገሪቱ ሕዝቦች የድህነት መጠን እጅግ በዘቀጠበት ሁኔታ ከዕርዳታ የሚገኝ ገንዘብ ሳይቀር የሚሰርቅ፣ ባንክ የሚዘርፍ፣ መሬት ነዋሪዎቹን አፈናቅሎ የሚሸጥ አገዛዝ በመመስረት የሀብት ክምችት መፍጠሩ ወንጀል መሆኑንም እንገነዘባለን። ስለሆነም ይህ ሕገ ወጥ የሀብት ዘረፋ እንዲቆም፣ ያለአግባብ የተዘረፈ ንብረት በሙሉ ለባለቤቱ የኢትይጵያ ሕዝብ እንዲመለስ ለማድረግ በትጋት እንሠራለን።

የጨቋኝ ተጨቋኝ የመከፋፈያ የፖለቲካ ስልቱን በማራገብ ታሪካችንን በማጉደፍ፣ ጀግኖቻችንን በማዋረድ፣ ቅርሶቻችንና ባህሎቻችን በማንቋሸሽና በማጥፋት፣ በሕዝባችን ላይ ስነልቡናዊና ማህበራዊ ቀውሶች እንዲፈጠሩ በማድረግ፤ ዜጎች በሀገራቸውና በማንነታቸው እንዳይኮሩ፣ ለስደት እንዲዳረጉ ማድረጉን በመገንዘብ፤ ለሁሉም ዜጎቿ የምትሆን፣ ለአዲሱ ትውልድ አዲስ ተስፋና አለኝታ የምናሻግራት ኢትዮጵያ እንድትኖር አጠንክረን እንደምንሠራ ቃል ተግባብተናል።

የህወሓት አገዛዝ የድርጅቱን ፕሮግራምና ማኒፌስቶ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት አድርጎ በሕዝብ ላይ በመጫንና አፋኝ ሕጎችን በየጊዜው በማውጣት የብዙ ዘመናት የመንግሥትነት ታሪክ ያላት ሀገር የመበተን ቋፍ ላይ እንድትደርስ አድርጓል። ይህንን በመገንዘብ፣ አብሮነታችን እንዲለመልም፣ ባህሎቻችን እንዲበለፅጉና የሁላችንም በሆነው ዐድዋን በመሰሉ አኩሪ ታሪኮቻችን ይበልጥ እንድንኮራ በህዝባችን መካከል ሠላምና ፍቅር ጎልቶ እንዲወጣ ተግተን መሥራት እንደሚገባን ተሰማርተናል።

ከዚህ በላይ በተዘረዘሩትና በዚህ ሠነድ ውስጥ ባልተካተቱ በጥልቅ በተነጋገረባቸው ቁም ነገሮች ላይ ተመሥርቶ ጉባኤው የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።

ውሳኔ

 1. የህወሓት አገዛዝ እንዲወገድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊና ሕዝባዊና መንግሥት እንዲቋቋም በብርቱ መስራት እንደሚገባ ወስነናል።

 2. በሀገሪቱ እየተቀጣጠለ ያለውን ሕዝባዊ ትግል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ማበረታታትና መደገፍ፤  ከኛ የሚጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር በመሆኑ ላይ አቋም ተወስዷል።

 3. ከዚህ አምባገነናዊ መንግስት ወደ ሕዝባዊ መንግስት የሚደረገው ሽግግር ሠላማዊ እንዲሆን መጣርና ሁሉን አቀፍ ሕዝባዊ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም መስራት የሥራ ሁሉ መጀመሪያ መሆን እንደሚገባ ተወስኗል።

 1. ባለፉ ሥርዓቶች የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ለማስወገድና የአንድነት ስነ ልቦና ለመመለስ የሚያስችል አጠቃላይ ብሔራዊ ዕርቅ እንዲወርድ ማድረግ ትኩረት ይሰጠዋል።

 2. ተቀራርበን እንድንሠራ ማድረግ የሚችል፣ መዋቅራዊ ያልሆነ አስተባባሪ ኮሚቴ ማቋቋም እንደሚገባ በመተማመን “የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የመግባባት ኮሚቴ” አቋቁመናል።

 3. በሀገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ አክቲቪስቶችን፣ ምሁራንን፣ የባህልና የሃይማኖት አባቶችን ያካተተ ብሔራዊ ዕርቅና ሽግግር ጉባኤ እንዲጠራ ለማገዝ ተስማምተናል።

 4. በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጭ የነፃነት ትግሉን ከሚረዱ ማንኛቸውም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር አብረን ልንሠራ እንደሚገባ ወስነናል።

 5. የህወሓት አገዛዝ የሀገራችንን ሕዝብ በሙሉ እስረኛ አድርጎ እየገዛ መሆኑን ብናውቅም አሁን እሥር ቤት ውስጥ ያሉ ሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ መጠየቅ ተገቢ ሆኖ አግኝንተነዋል።

 6. የህወሓት አገዛዝ በተከታታይ ለሦስተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ሕዝብን በመሣሪያ ኃይል ለመግዛት መወሰኑ ሊወገዝ የሚገባው በመሆኑ ላይ ውይይታችን አፅንዖት በመስጠት ይህ አዋጅ የህዝቡን የነፃነት ትግል ለማፈን ታስቦ እንደተደረገ ብናውቅም፤ በዚህ ምክንያት ትግሉ ለአፍታም እንደማይቆም ተረድቶ ህወሓት ይህን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያነሳ አጥብቀን እጠይቃለን።

ከዚህም በመነሳት ሁሉን አቀፍ የሀገራዊ መግባባት ጉባኤ እንዲጠራና ሂደቱም ሰላማዊ ሕዝባዊ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም እንዲረዳ በዚህ ጉባኤ የተሳተፍን ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ጥሪዎች አቅርበናል።

 

                           ሕዝባዊና ሀገራዊ ጥሪ

 

 1. ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!

በአምባገነን መንግሥት መዳፍ ሥር ሆነህ የዘመናት ጭቆናን ተሸክመህ ለምትኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በመንግስትነት በግድ የተሰየመብህ አምባገነን አገዛዝ እርስ በርስ እንድትገዳደል እያሤረብህ ፤

ነገር ግን ጨዋነትህና ታላቅ ሕዝብነትህ አይሎ በመከባበር ለምትኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤

ይህ የመከራና የግፍ ዘመን ተቋጭቶ ለክብርህና ለታላቅነትህ የሚመጥን መንግስት በራስህ ፈቃድ እንድትመሰርት እንቅፋት ሊሆንብህ የሚገባ ምድራዊ ኃይል ሊኖር እንደማይችል ህያው ታሪክህ ምስክር እንደሆነ እናውቃለን። ስለሆነም የህወሓት አገዛዝን አሽቀንጥረህ ለመጣል የጀመርከውን ትግል አበርትተህ እንድትቀጥል፤ በዚህም የትግል ጉዞ ውስጥ እኛ ልጆችህ ከጎንህ እንደተሰለፍን እንድትረዳ በክብር ለመግለጽና ቃላችንን ለመስጠት እንወዳለን።

2. መላው የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎች

 እጅግ አደገኛና ከፋፋይ የሆነውን የህወሓት ባህሪ በሚገባ ተረድታችሁ በመደራጀት የህዝባችሁን የነፃነትና እኩልነት ትግል ዕውን ለማድረግ፤ አንድነቷ የተጠበቀ፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረ፣ ዴሞክራሲያዊት፣ ፍትህ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በምታደርጉት ትግል የተባበረ ክንድ በጠላት ላይ ለማሳረፍ የትግሉን ዕድሜ እንደሚያሳጥረው ተረድታችሁ ከሚመስሏችሁ ጋር አብራችሁ በአንድነት እንድትታገሉ፤ እኛም ከጎናችሁ መሆናችንን እንድታውቁ ለመግለጽ እንወዳለን።

 1. ለመከላከያ ሠራዊት አባላት

የሀገር ዳር ድንበር በአንተ ጊዜ ተደፍሯል። ሉዓላዊነታችን ተሸርሽሯል። ዜጎች ያለአግባብ በአልሞ ተኳሽ የአጋዚ ሠራዊት አባላት ተጨፍጭፈዋል። ይህ በዓለም አቀፍ ሕግ የሚያስቀጣ ምህረት የማይደረግበት ወንጀል ነው። ህወሓት የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም አንተን በመሳሪያነት እየተጠቀመብህ ነው።

እናት፣ አባት፣ ወንድም፣ እህቶችህን እና ልጆችህን የሚገድል ስብዕና ልትላበስ አይገባህም። ነገ ዞሮ መግቢያህ ነውና በገዛ ወገንህ ላይ እጅህን አታንሳ። ይልቅስ ከወገንህ ጋር የሚያቆራርጥህ ይህ የወንበዴ ቡድን መሆኑን ተረድተህ ጠመንጃህን በአስገዳይ መኮንኖች ላይ እንዲዞር፣ የሕዝቡን የነፃነት ትግል እንድትቀላቀል እንጠራሃለን።

 

 1. ለመላው የኢትዮጵያ ወጣቶች

 

ነገ የምትኖርባት ሀገርህ የነፃነት ምድር እንድትሆን ያላሰለሰ ትግል እያደረግህ ላለኸው ጀግና ኢትዮጵያዊ ወጣት፡ 

በሥራ አጥነት፣ በድህነት፣ በአድሎ፣ በጭቆናና በግፍ ሠንሰለት ታስረህ ለምትባዝነው ኢትዮጵያዊ ወጣት፤  ከህወሓት ሴረኛ አገዛዝ በኋላ የምትረከባት ኢትዮጵያ ሁሉንም ዜጎቿን በእኩልነት የምታስተናግድ የነፃነት ፋና ወጊ አፍሪካዊት ምድር እንደነበረች ሁሉ፤ ዛሬም የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት፣ የፍትህና የአንድነት ምድር እንድትሆን የጀመርከውን የነፃነት ተጋድሎ ከምንጊዜውም በላይ አጠናክረህ እንድትቀጥል አደራ እንላለን። በማንኛውም መልኩ ከጎንህ ነን።                                                            

 1. ለመላው የትግራይ ሕዝብ

የህወሓት አገዛዝ ለአለፉት አሥርተ ዓመታት በስምህ ነግዷል፤ በስምህ በርካታ ንጹህ ኢትዮጵያውያንን ገድሏል፣ አሥሯል፣ አሰድዷል። ከዚህ መሠሪ መንግስት አንተ ያተረፍከው አንዳችም ጠቀሜታ እንደሌለ እናውቃለን። እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ወገንህ በደሉም፣ ግፉም ተፈጽሞብሃል። ህወሓት በስምህ መነገዱን እንዲያቆም ከቀረው ወገንህ ጋር አብረህ ፀረ-ህወሓት ትግሉን በይፋ ተቀላቀል። “ውሃው ሂያጁ፤ አለቱ ቀሪ” ነው። ይህ የሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ የታሪክ ጠባሳ እንዳይተው ከወገኖችህ ጋር ተባብረህ ተነሳ!

 

 1. ለሁሉም የፖለቲካ አክቲቪስቶች (ብሎገሮች) የግልና የመንግስት ሚድያዎች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪዎች፤

ለህሊናችሁ ተገዥዎች በመሆናችሁ ከፍተኛ የአካልና የሥነ ልቦና ዋጋ መክፈላችሁን በክብር የምንዘክረው መስዋዕትነት ነው። የናንተ ሥራ ለቀረው የህብረተሰብ ክፍል ፋና ወጊ፣ አቅጣጫ ጠቋሚና የወደፊቱን የተስፋ ጭላንጭል የሚያሳይ፤ እየበራችሁ የምትቀልጡ ነጸብራቆች መሆናችሁን እናውቃለን። ዴሞክራሲያዊት ነፃ ኢትዮጵያ የህዝቦቿ ትሆን ዘንድ የህሊናዎቻችሁ ተገዥዎች ሆናችሁ የዕውቀት ጠበቃ እንድትሆኑ እንጠራችኋለን።

 1. ለብአዴንና ኦህዴድና ለደሕዴድ አባለት

የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና ነፃነት የሁላችንም የትግል ውጤት ነው። ሕዝቦች በእኩልነትና በመከባበር የሚኖሩባት ሀገር እንድትኖረን የምታደርጉትን ጥረት እናከብራለን፣ እናደንቃለንም። ወደፊትም ለሁሉም ዜጎቿ ምቹና ፍትህ የተሞላባት ሀገር እውን ትሆን ዘንድ የሁላችንንም ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ ይጠይቃልና የበኩላችሁን የዜግነት ግዳጅ ትወጡ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።

 1. በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ

ወያኔ የጎርፍ ውሃ ነው። ነገ ያልፋል። ከህንግዲህ ብዙ ጉዳት ሳያደርስ እንዲያልፍ የሁላችንም ጥረት በጣም አስፈላጊ ነው። ትግሉ ብዙ መስዋዕትነት ይጠይቃል። ስለሆነም እንደተለመደው ሁሉ ከሕዝባችን ጐን በመቆም የኢትዮጵያን ሕዝብ የነጻነትና የፍትህ ትግል እንድታግዙ ከጐኑም እንድትቆሙ እንጠይቃለን።

 1. መላው የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች

የሕዝባችንን የትግል ጥሪ በሚገባ በመገንዘብ “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” የሚለውን ጥሪ ተቀብላችሁ ለብሔራዊ መግባባትና ለእርቅ ጉባኤ እንዲሁንም የሕዝቡን ትግል ለመደገፍ በአንድነት እንድንቆም ጥሪ እናቀርባለን።                                                                       

 1.  ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብና መንግስታት

የስልጣኔ መጀመሪያ ከሆኑት ሀገራት ተርታ የሚቆጠር ታሪክ ያላት ሀገራችን ለበርካታ የዓለማችን ጭቁን ሕዝቦችና ሀገራት ምሳሌና ድጋፍ ሰጪ ሆና ለበርካታ ሀገራት ነፃነት ጉልህ አስተዋጽዎ ማድረጓ ከማንም የተሰወረ እንዳልሆነ ይታወቃል።

በተለይም ከቅኝ ገዥዎች ለመላቀቅ ብርቱ ትግል ከአደረጋችሁት ሁሉ ጋር የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳልተለየ ታሪክ ምስክር ነው። የነፃነት ተምሳሌትና የሰው ዘር መገኛ የሆነች ሀገራችን ዛሬ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ አምባገነኑ የህወሓት አገዛዝ ለሦስተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ በር ዘግቶ ዜጐቻችንን እየገደለ ይገኛል። ስለሆነም ከዚህ ከህዝብ ከተነጠለ አገዛዝ ያላችሁን ግንኙነትና ፖሊሲ ዳግመኛ እንድትመረምሩ ጥሪ እናቀርባለን።

በመጨረሻም ጉባኤው ቀጥሎ ለተዘረዘሩት ምስጋናውን አቅርቧል።

 1. በአለፉት ሦስት አመታት በተደረገው ከፍተኛ መስዋዕትነት በሚጠይቅ ትግል ውድ ህይወታቸውን ተነጥቀው፣ ስቃያችንን ተሰቃይተው፣ ሞታችንን ሙተው ለተሰዉ ሰማዕታት ጀግኖቻችን ክብርና ምስጋና ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለዘለዓለም በልባችን ታትመው እንደሚኖሩም ለመግለጽ እንወዳለን። ጀግኖቻችን የዘመን ምልክት የታሪካችን ፈርጥ ሆነው ለዘላለም ሲታወሱ ይኖራሉ።

 2. መላው የሀገራችን ሕዝብ እያደረገው ያለውን ከፍተኛ ትግል በጽኑ የሚደገፍና ከእስከ ዛሬው በተሻለና የትግሉን ደረጃ በመጠነ ሁኔታ ትግላችንን የምናቀናጅ መሆኑን በማክበር እንገልጻለን። በተለይም በገዥዎች የሚደረግበትን ሤራ ተቋቁሞ ባህሉን እና ሃይማኖቱን ጠብቆ በጨዋነት ተከባብሮና ተዋዶ ለሚኖረው ህዝባችን ያለንን ታላቅ ክብርና አድናቆት ለመግለጽ እንወዳለን።

 3.  ለሀገራችን እና ለሕዝባችን ፍትህ እና ነፃነት ሲሉ የተንገላቱ፣ በግፍ አገዛዝ በወህኒ መከራ የተቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ብሎገሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሃይማኖት አባቶች ላደረጉት ተጋድሎ ከፍ ያለ አክብሮት ያለን መሆኑን እንገልጻለን።

 4. የህዝቡን ስቃይ፣ መከራና መሠርተታዊ ፍላጐት በመረዳት በተለይም ሀገሪቷ ያለችበትን የፖለቲካ ቀውስ በማጤን ከሕዝብ ጐን ለመቆም ተነሳሽነት ላሳዩት እና በሀገር አንድነት ዙሪያ ከብሔረተኛው የህወሓት ከፋፋይ ስርዓት የተለየ ግልጽ አቋም በይፋ በማንጸባረቅ ፋና ወጊ ለመሆን ለደፈሩት ለኦህዴድ አመራሮች በተለይም ለአቶ ለማ መገርሳ፣ ለዶክተር አብይ አሕመድና ለአቶ አዲሱ አረጋ ያለንን አክብሮት እና አድናቆት ሳንገልጽ አናልፍም። በዚህ እረገድ የብአዴንና የኦህዴድ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች ሞቅ በረድ፣ ሄድ መጣ በማለት ከሕዝብ ትግል ጋር ለመተባበር ያሳዩትን ተነሳሽነት ማንሳትና በማመስገን እንዲበረቱ ጥሪ ማቅረብም የሚገባ እንደሆነ እናምናለን።                                                                   

 1. እጅግ አደገኛ ዋጋ የሚያስከፍል ሁኔታም እንዳለ እያወቁም ቢሆን የህወሓት ኢሕአዴግ አገዛዝ የሚሰጠውን ትእዛዝ ወደጎን በመተው ወደ ሕዝባችን አንተኩስም ላሉ አንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልል የፀጥታ መዋቅር አመራርና አባላት አክብሮትና ምስጋናን መግለጽ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን።      

 2. የህወሓትን ከፋፋይ ብሔረተኛ ሥርዓት ከመሰረቱ ነቅሎ በመጣል የሁሉም ብሔረሰቦች ባህል ቋንቋ እና ፍላጐት የተከበረባት ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ትግል ውስጥ ግምባር ቀደም ሚና በመጫወት ትግሉን ለመምራት መላው የሀገራችን ሕዝብ ማንንም ሳይጠብቅ ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ መሆኑን በሀገራችን የበለጠ እንድንኮራ ያደረገን ከመሆኑ ባሻገር የሕዝብ ልጅ የሆኑት ወጣቶች ቄሮ፣ ፋኖ፣ ነብሮ፣ ዞርማ ወዘተ የሚል የተለያየ የህቡዕና የግልፅ አደረጃጀት እየፈጠሩና እያደረጉ ላለው ከፍተኛ ትግል በህዝባችን እና በራሳችን ስም አክብሮትና ምስጋናችንን እንገልፃለን።

 3.  ትላንትም ሆነ ዛሬ ህዝባችን በሚያደርገው የትግል ሂደት ውስጥ የሃይማኖት አባቶች ሚና የማይተካ አስተዋጽዎ እንዳለው በሚገባ እንገነዘባለን። በዚህ እረገድ ከሀገር ውጭ በስደት ያሉ ብፁሃን ጳጳሳት ካህናት እና ሰባኪያን ወንጌል እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ብፁሃን ጳጳሳትና በእስር እየተሰቃዩ ያሉ መነኮሳት፣ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ ከሀገር ውጭ ፈርስት ሂጅራና የተባበሩት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ፣ የፕሮቴስታንት፣ የካቶሊክና ሌሎች ሀገር በቀል የሃይማኖት መሪዎች እያደረጉ ያለው አስተዋጽዎ በኢትዮጵያ ታሪክ በደማቅ ቀለም የሚፃፍ እንደሆነ እንገነዘባለን።

 4. ዋነኛ ሀብታቸው ህዝብና የሀገር ፍቅር እንደሆነ የወሰኑ አንዳንድ የሀገራችን አርቲስቶች በሙዚቃ፣ በቲያትር፣ በግጥም፣ በፊልም፣ በሥዕል ወዘተ ወቅታዊ የሀገራችንን ችግር የህዝባችንን ስቃይና መሰረታዊ ፍላጐት በመግለጽ ለሕዝብና ለሀገር አንድነት እያደረጉ ያለውን አስተዋጽዖ ሳናደንቅ አናልፍም።

 5. የህወሓት ኢሕአዴግን ከፋፋይ ጫፍ የረገጠ የብሔረተኝነት ፖለቲካ ለማምከን በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ወንድማዊ ትብብር እንዲጐለብት ከፍተኛ አስተዋጾዖ ላበረከቱ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ከፍ ያለ አክብሮትና ምስጋና ማቅረብ እንደሚገባ በጽኑ እናምናለን።

 6.  በመገናኛ ብዙሃን እረገድ የህዝብን ትግል ወደ ከፍታው ለማምጣት ኢሳት (Eth SAT)፣ ኦኤምኤን (OMN)፣ ዶቼ ቪለ (Doche Wille)፣ ቪኦኤ (VOA)፣ ቢቢኤን (BBN)፣ አባይ ሚድያ (Abbay Media)፣ ኤስቢኤስ (SBS) እንዲሁም የተለያዩ ሬድዮና ዌብሳይቶች፣ ምስለ ገጽ (Face Book) ብሎጐች የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው እንገነዘባለን።                                                                  

 7. HR 128 ፦ Freedom act in Ethiopia የአሜሪካ ምክር ቤት የቀረበ ሠነድ ያዘጋጁትንና ኃላፊነት የወሰዱትን የአሜሪካ ኮንግሬስና ሴኔት አባላት በተለይ በዚህ ሂደት ግምባር ቀደም የሆኑትን ኮንግሬስ ማን ክሪስ እስሚዝና ኮንግሬስ ማን ማይክ ኮፍማን እንዲሁም ዘመቻውን የሚያስተባብሩትን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሳናመሰግንና ሳናደንቅ አናልፍም።

 

“ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ከልዩነታችን በላይ ነው !”

ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!!!

የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም.

February 18, 2018

Filed in: Amharic News, News, Politics & Economics Tags: ,

Related Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.