0

ካሰቡት ግብ ለመድረስ ፣ያመኑበትን ዓላማ አንግቦ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ!

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ቅዳሜ ጥር ፲፫ ቀን ፪ሺህ ፱ ዓ.. ቅፅ፭፣ ቁጥር ፲

ካሰቡት ግብ ለመድረስ ፣ያመኑበትን ዓላማ አንግቦ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ!

የዛሬ አራት ዓመት ዐማራ ነኝ ብሎ ደፍሮ ለመናገር ብዙ ማሰብና ማውጠንጠን ይጠይቅ ነበር። ምክንያቱም ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት በዐማራው ነገድ ላይ የተነዛው ፕሮፓጋንዳ በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ዐማራ ነኝ እንዳይሉ ገደብ የጣሉ ነበሩ። የመጀመሪያው ምክንያት ዐማራው ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምን በመሆኑ፣ ራሱን ወደ ነገድ ደረጃ ማውረድ ውርደት ወይም ከኢትዮጵያዊነት የሚያፋታው አድርጎ መቁጠሩ አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት ነው። ሁለተኛው በኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ የሩቅና የቅርብ፣ የውጭና የውስጥ ጠላቶች የተራገበው ኢትዮጵያን የማጥፋት የተቀነባበረ ዘመቻ ዋነኛው ዒላማ ዐማራው በመሆኑ፣ የዐማራውን ማንነት ጥላሸት የቀባ፣ መልካም ስሙንና ዝናውን ያጎደፈ፣ «በጡት ቆራጭነት፣ በወራሪነት፣ በገዥ መደብነት፣ በጨቋኝ ብሔርነት፣ በነፍጠኝነትና በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጠሩ ለተባሉ ችግሮች ሁሉ ፈጣሪ» ተደርጎ በመወንጀሉ ምክንያት የዐማራው ልጆች ራሳቸውን ዐማራ ነኝ እንዳይሉ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑ ነው።

በነዚህና በሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች የዐማራው ልጆች፣ በመሰል የሌሎች ነገድ ልጆች ተክደውና ተገድፈው በነገዱ ላይ፣ በተለያዩ ፖለቲካዊ ቡድኖችና ስብስቦች ከስም ማጥፋት እስከ ዘር ማጥፋትና ዘር ማጽዳት ወንጀል ሲፈጸምበት፣ ለምን? እንዴት?ያሉት እምብዛም እንደነበሩ በነገዱ ላይ የደረሰው ዕልቂትና የዕልቂቱ አለማቋረጥ ጉልህ ማሳያ ነው። ይህን የዐማራው ነገድ ልጆች፣ በኢትዮጵያዊነት ራሱን ደብቆ የወገኑን ዕልቂት እያየ እንዳላየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ የሆነውን፣ ወደራሱ ኅሊና ተመልሶ ዘሩን ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ እንዲችል፣ ዐማራው በማንነቱ ዙሪያ ተደራጅቶ፣ ማንነቱን አስጠብቆ፣ የኢትዮጵያን አንድነት እንዲያስጠብቅ ጥሪ ያቀረቡት ክቡር ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ እንደነበሩ እናስታውሳለን።

ሆኖም ዐማራው፣ ለቀረበው ኅልውናውን የማስጠበቅ ጥሪ የሰጠው ምላሽ፣ ከተደገሰለት ጥፋት ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ፣ ፕሮፌሰር አሥራት በዘረኛው ወያኔ አገዛዝ ታስረው እንዲገደሉ መደረጉን የምናስታውሰው በቁጭት ነው። የአሥራት መገደል በተወሰነ ደረጃ ተነሳስቶ የነበረው የዐማራዊነት ማንነት እንቅስቃሴ ከመዳከም አልፎ፣ እንዲከስም አደረገ። ይህም ዐማራን ለማጥፋት የዘመናት ዝግጅት ያደረገው ወያኔ፣ የዐማራውን ልጆች፣ ያለይሉኝታና እሳ፣ በተገኘበት እንደክፉ አውሬ እያደኑ ጨረሱት። ዐማራውን በገፍና በግፍ እያደኑ ሲጨርሱ፣ ከዐማራው ወገን ኧረ ለምን? የሚል ድምፅ ባለመሰማቱ፣ ወያኔ በመሀል፣ በምሥራቅ፣ በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ ለዘመናት የኖረውን ዐማራ አገርህ አይደለም፣ ካገር ለቀህ ውጣ በማለት ሀብት ንብረቱን ዘርፈው አባረሩት። ዐማራው በአያት እና ባባቶቹ ሕይዎት፣ አጥንትና ደም ተጠብቃ በኖረችው አገር የመኖር መብቱን ተነጠቀ።

ይህስ በዛ! ያሉ ወገኖች፣ ከተሸፈኑበት ኢትዮጵያዊ ካባ ራሳቸውን ገልጠው፣ ለወገናቸው ድምፅ መሆንን መረጡ። እነዚህ ለወገናቸው ራሳቸውን ቤዛ ለማድረግ የቆረጡ ወገኖች« ዐማራውን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደግበሚል መፈክር ጥፋት ለታወጀበት የዐማራ ነገድ ድምፅ ለመሆንና ዐማራው ራሱን አደራጅቶ ኅልውናውን እንዲያስጠብቅ ሲንቀሳቀሱ፣ ከማኅበረሰቡ የተገኘው መልስ ቀና አልነበረም። በማንነት ዙሪያ መደራጀት፣« ወያኔን መሆን ነው»« ወያኔ በቀደደው ቦይ ገብቶ መፍሰስ ነው»«ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው» ከማለት አልፎ፣« ዐማራ የሚባል ነገር የለም»«ዐማራ ማነውየሚሉ ጭፍን ሀሳቦችን በመርጨት ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት፣ ለዐማራው ድምፅ የመሆን እንቅስቃሴውን በለጋው ለመቅጨት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።

ይሁን እንጂ፣ካሰቡት ግብ ለመድረስ ፤ያመኑበትን ዓላማ አንግቦ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ለድል እንደሚያቃርብ ከልብ የሚያምኑት፣ በቁጥር እጅግ ትንሽ፣ በዓላማ እጅግ ግዙፍ የሆኑት የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት መሥራች አባሎች፣ ሳይሰለቹና ሳይታክቱ ባደረጉት የዐማራውን ነገድ የማሳወቅ፣ የማንቃት፣ የማደራጀትና መረጃዎችን የማሰራጨት ትግል፣ ይኸውና ዛሬ እንደ ተርብ የሚናደፉ፣ እለፈ

አዕላፍ የዐማራ ልጆች ዝምታቸውን ሰብረው፣ በማንነታቸው ኮርተው ወገናቸውን ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግና የኢትዮጵያን አንድነት ዳግም ትንሣዔ ዕውን ለማድረግ ሌት ተቀን ከሳይበር እስከ አካላዊ ጦርነት ገጥመው ወያኔንና አጋሮቹን የተፉትን ምራቅ እንዲልሱ እያስገደዱት ይገኛሉ። ይህ የጽናትና የቁርጠኝነት ውጤት ነው። ያለቁርጠኝነት ለድል መብቃት አይቻልምና፣ ሞረሽ ወገኔ ባለፉት አራት ዓመታት በቁርጠኝነት ያካሄደው ዐማራውን የማንቃትና የማደራጀት ትግል ፣ ትግሉን ወደ ትጥቅ ትግል ያሸጋገረው ስለሆነ፣ ይህንም በድል አድራጊነት ለመወጣት ቁርጠኝነቱን በእጥፍ ድርብ ማሳደግ ይጠበቃል።

ስለሆነም፣ የዐማራው ልጆች፣ የተፋፋመው የዐማራው የመደራጀትና ማንነትን የማስከበር ትግል ለድል እንዲበቃ፣ ሁሉም የዐማራ ልጅ፣ በሀሳብ፣ በቁሳቁስ፣ በገንዘብ፣ በምክር፣ በሰው ኃይል ወዘተ ሊተባበር ይገባል። «ድር ቢያብር አንበሳ ያስር» ነውና ብሂሉ፣ ሊያጠፋን የዘመተውን አጥፊ ቡድን ጨርሶ ሳያጠፋን፣ አጥፊውን ለማጥፋት ድጋፋችሁን ከምንጊዜውም በበለጠ ዛሬ እንሻለን። ብረትን መቀጥቀጥና ተፈላጊውን ቅርጽ ማስያዝ የሚቻለው ሲግል ሲቀጠቅጡት ነውና፣ ወያኔውም የሚወድቀው ራሱን በፈጠረው ሁለንተናዊ ችግር ተማሮ አደባባይ የወጣው የሕዝብ ቁጣ ሳይበርድ፣ቁጣውን ማጋጋል ለነገ የሚባል ተግባር ሳይሆን አሁኑኑ ልንያያዘው የሚገባን ነው። በመሆኑም በውስጥና በውጭ ለሚደረገው ትግል ገንዘብ ወሳኝ ድርሻ ያለው ስለሆነ፣ ጀግኖቻችን ከእኛ ድጋፍ ማነስ የተነሳ ትግላቸው እንዳይጓተት የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ጥሪውን እያቀረበ ሳይውሉ ሳያድሩ በሚችሉት መጠን የወገናችንን ትግል በገንዘብ ለመርዳት የሞረሽ ወገኔ አማራ ድርጅት ድሕረገጽን (http://www.moreshwegenie.org/) በመጎብኘት፡ የጎፈንድሚ (GoFundMe)፤ የፔይፓል (Paypal)፤ ወይም የባንክ አካውንታችንን ቁጥር ተጥቅመው የዚህ ታሪካዊ ትግል አካል በመሆን የማያቋርጥ ድጋፍዎን በአንክሮና በትሀትና ያሳስባል።

ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!

ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!

Filed in: News

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.