0

ከታሪክ መዝገብ፣ ለመሆኑ ዐማራ ማነው? በዶር ኃይሌ ላሬቦ

ከታሪክ መዝገብ

haile-lareboለመሆኑ አማራ ማነው

በኃይሌ ላሬቦ

ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ መንግሥት ዐማራ በተባለው ኅብረተ-ሰብ ላይ ብዙ ግፍና ዐመፅ እንደፈጸመና እንዳስፈጸመ በገፍ ይነገራል። በኅብረተሰቡ ላይ ተፈጸሙ ከተባሉት ድርጊቶች አብዛኞቹ በሥዕል የተቀረጹ፣ ለሰው መብት በቆሙ ባስተማማኝ ብሔራዊና ዓለም-ዐቀፍ ድርጅቶች ከነማስረጃቸው የተጠናቀሩ፣ እሙን በሆኑ ያይን ምስክሮች የተደገፉ ስለሆኑ ማስተባበሉ ከመደናቈርና የአተካራ ግብግብ ከመግጠም ውጭ ሌላ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። የግፎቹ ኢሰብኣዊነትና የፈጻሚዎቻቸውም አውሬነት ለሚሰማ ሁሉ ከመዘግነን አልፎ፣ ሰው ሁኖ መፈጠሩን ራሱን የሚያስጠላ ከመሆኑ የተነሣ፣ ልቦና ያለው ተመልካችም ሆነ ሰሚ፣ መንግሥት ነን ባዮቹ የወያኔ ገዢዎች በጀርመንና በኢጣሊያን ምድር ከታዩት ከናዚና ከፋሽስት መንግሥታት መሪዎች በምን ይለያሉ ብሎ ለመጠየቅ ይገደዳል። በበኩሌ ጥላቻው ከየት መጣ ብዬ አውጥቼ አውርጄ ማሰላሰል ከጀመርሁ ዓመታት ቈጥሬአለሁ። ዕድል ቀንቶኝ ከብዙ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጋር ኑሬአለሁ፤ አድጌአለሁም። ስለዚህ ፍንጭ ይሰጠኝ ይሆናል ስል ወደልጅነት ሕይወቴ ወደኋላ ተመልሼ በዐይነ-መነጽሬ ሳይና ሳሰላስል፡ ሁሌዬ ተመላልሰው እፊቴ የሚደቀኑብኝ ሁለት ገጠመኞች ናቸው። አንደኛው በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ከምትባል ከተማ በሠላሳ ኪሎሜትር ያህል ርቀት የሚገኝ መንዲዳ የተባለ መንደር አለ። ባንድ የኢጣሊያን መሐንዲስ ለሕንፃ ሥራ ተቀጥረው ከሰሜን የመጡ ሠራተኞች ባካባቢው ዘመናዊ ምግብ ቤት ስለሌለ፣ ሁሌዬ የሚበሉት ከተማሪዎቹ ጋር አብረው ነበር። የቀረውን ምግብ ሁሉ በልተው፣ ጠላዉን ብቻ መተው ልማዳቸው ሁኖ ስለነበር፣ አስተናጋጁ ገርሞት አንድ ቀን ምክንያቱን ሲጠይቃቸው አላንዳች ማፈር “ዐማሮች ናችሁ አሉን፤ ዐማራ ቂጥኝ አለውና እንዳይተላለፍባችሁ ምንም ዐይነት መጠጥ ቢሰጣችሁ እንዳትጠጡ ተብለን ስለተመከርን ፈርተን ነው” ብለው በጨዋነት መልስ ሰጡ። ሌላው በአሥመራ ከተማ በአንዳንድ አስተማሪዎች አነሣሽነት፣ ተማሪዎቹ እነዚህን ዐማሮች አታናግሯቸው ተብለው ስለተመከሩ፣ ከደቡብ የመጣነው በመጀመርያው ዓመት ምንም ብንጥር ጓደኛ ማፍራት ከባድ ሆነብን። እምብዛም ባይሆን ጥቂት ከምንቀርባቸው ጋር ችግሩ ምን እንደሆነ ለማወቅ ተሰባሰብን። መልሱ እውነትም ‘ዐማሮች’ ስለሆነን እንደነበር ለማወቅ ብዙም አልፈጀንም። ከሁሉም የከፋብን ግን ዐማሮች አይደለንም ስንል፣ ቀጥሎ የመጣው ልውውጥ ነበር። “ዐማሮች ካልሆናችሁ፣ ታዲያ ጋላ ናችሁ እንዴ!” ተባልን። ለዚህም በአሉታ ስንመልስ፣ “ታዲያ ከጋላ በታች ሰው አለ እንዴ!” ሲሉን ክው አልን። እንግዴህ እነዚህ የልባቸውን የሚናገሩ ላቅመ አዳም እንኳን ያልደረሱ ልጆች ናቸው፤ በጭንቅላታቸው ውስጥ የሚያንሸራሽሩት አሳቦች ግን የአካባቢውን ስሜት የሚያንፀባርቁ ሊሆኑ አይችሉም ብዬ መከራከሩ የሚያዋጣ ስለማይመስለኝ አልፈዋለሁ። ሁኖም የገጠመኙ ወቅት የወያኔ መሪዎች ልክ ወደጫካ ያመሩበት ጊዜ ስለነበር፣ የዛሬውን ሥራቸውን እያየሁ የለም እነሱ በዚህ ዐይነት አስተሳሰብ የተበረዙ ሰዎች አልነበሩም ብዬ ማሰቡ ያዳግተኛል። በአፍሪቃ ቅኝ ገዢዎችና በፋሽስቶች እጅ ባካባቢዎቻቸው ይካሄድ የነበረው ኀይለኛ ስብከት፣ በዐማራ ላይ ጥላቻ፣ በተቀረው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ላይ ደግሞ ከፍተኛ ንቀት እንዳሳደረባቸው አይጠረጠርም ብል በሐሰት የምወነጀል መስሎ አይታየኝም። 8-12-2016 Who Are The Amhara……..read in .pdf

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.