0

ከፖለቲካው በስተጀርባ ያሉት እውነታዎች – ከተማ ዋቅጅራ ክፍል ፫

ከፖለቲካው በስተጀርባ ያሉት እውነታዎች – ከተማ ዋቅጅራ

TPLF leaders

ክፍል

በክፍል ሁለት በደርግ አገዛዝ ዘመን እና በወያኔ አገዛዝ ዘመን ያሉትን እውነታዎች ከብዙ በጥቂቱ ተመልክተናል ክፍል ሦስት እንሆ:-

ወያኔዎች በኃይል ስልጣን ከያዙበት ግዜ ጀምሮ በሁሉም ረገድ እነሱ ብቻ የበላይ የሚሆኑበትን ስራ በመስራት ሌላው ኢትዮጵያዊ እውቀት ያለውን ችሎታ ያለውን ከሚሰራበት ከፍተኛ ቦታ እየተባረረ እውቀት እና ችሎታ በሌላቸው በወያኔ ሰዎች እየተተካ በመባረር የበዪ ተመልካች መሆን ከተጀመረ ሰናባብቷል። በተለይ ደግሞ ከዘጠና ሰባት ምርጫ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ሃገር ዘረፋ በቀጥታ በመግባት የኢትዮጵያን ጠቅላላ ኢኮኖሚ በማን አለብኝነት በመቆጣጠር ዛሬ የድርጅት ባለቤት እነሱ፣ የትልልቅ ህንጻ ባለቤት እነሱ፣ አስመጪና ላኪዎች እነሱ፣ ባጠቃላይ ከህዝቡ በስተቀር የኢትዮጵያ ሃብትና ንብረት የነሱ ብቻ እንደሆነ አውጀው በህዝባችን ላይ መቀለድ ከጀመሩ ቆይተዋል። ወያኔዎች በዘረፉት ንብረት የፈለጉትን ገዝተው መብላት ስለቻሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ርሃብ የለም ብለው የሚያወሩ፣ እነርሱ ሃብት ስላካበቱ ደሃ ጠፍቷል ብለው የሚሳለቁ፣ እነርሱ ባለ ብዙ ህንጻ እና ባለሞዴል መኪና ባለቤት ስለሆኑ ኢትዮጵያ አድጋለች ተለውጣለች ብለው የሚደሰኩሩ ባአጠቃላይ ኢትዮጵያ ማለት ወያኔ ወያኔ ማለት ኢትዮጵያ አድርገው በመሳል የዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ስቃይና ችግር መታየት ያልቻላቸው የ21ኛው ክፍለ ዘመን አውሬ በመሆን የተቀመጡ መቼም ከስተታቸው የማይማሩ የክፍለ ዘመኑ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ያላቸው ፍጡሮች ናቸው። ኢትዮጵያዊ የሚመስሉ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ለህዝቡም ሆነ ለአገሪቷ መጥፋት የማይጨነቁ ኢትዮጵያን በግዞት ይዘዋል።

በወያኔ ዘመን መምህር ማለት የማስተማር እውቀት ኖሮት የመምህርነትን ድርሻ ይዞ የሚያስተምር ማለት አይደለም። አንድ መምህር ለመምህርነት ሊያበቃው የሚችለው ያለው እውቀት እና የማስተማር ብቃት መሆን ነበረበት። መምህሩም ተማሪዎቹን ልክ እንደ ልጆቹ በማየት ነገ የአገር ተረካቢ እንደሆኑ ስለሚታወቅ ተቆጣጥሮ እና ተንከባክቦ እውቀት አስጨብጦ በማስተማር ለፍሬ ማብቃት ነው። እድሜ ለወያኔ ዛሬ…. ዛሬ የሚበዙት መምህራኖች የወሬ ጥርቅም የያዙ ሆኖ ሳለ በከፍተኛ ስልጣን የመማር ማስተማሩን ስራ እንዲቆጣጠሩት በማርደግ የእውቀት ባለቤት እና የማስተማር ችሎታ ያላቸውን ኢትዮጵያዊ መምህራንን በሙሉ አባሯል። ሌላው ደግሞ ተማሪ መምህርን እንዲገመግሙ ተደርጓል በዚህም እውነተኛ መምህራኖቹ ተማሪውን እንዲፈሩት አድርገዋቸዋል። በነገራችን ላይ ግምገማው በአግባቡ ቢሆን ችግር ላይኖረው ይችል ይሆናል ነገር ግን ይሄ አሰራር የመጣው ለአገር ፍቅር ኖሯቸው ዜጋን በማፍራት በትክክል የማስተማር ሙያ ላይ ያሉትን መምህራኖች ለመምታት ታቅዶ የተደረገ ሴራ ነው። ይሄ ደግሞ በአገር የመጣ ጥፋት ነው። ወያኔ መቼ ነው እውነት የሚናገረ? መቼስ ይሆን ክፋትን የሚተወው?

ሙህራኖች ኽረ ወዴት ናችሁ?።

የኢትዮጵያ ሙህራኖች ለአገር መስራት ከሁሉም በላይ ክብር አለው። ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉ ገና 43 አመት ጎልማሳ ሆኖ ነው ለአገሬ መስራት አለብኝ ብሎ የተነሳው። ሌሎችም ሙህራኖች የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳስቧቸው ወደ እውነተኛ ትግል ውስጥ የገቡት። ነገር ግን ኢትዮጵያ በአለም ዙሪያ ካሏት የተማረ ኃይል በመቶኛ ብናስቀምጠው 5% እንኳን አይሞላም። ሙህራኑ በአገር ቀልድ እንደሌለ ከናንተ በላይ ሊረዳው የሚችል አለ ብዬ ማሰብ ይከብደኛል። ወያኔ ኢትዮጵያን የምትባለውን አገር አጥፍቶ ህዝቦቿን እርስ በራስ አጣልቶ የደም መሬት ለማድረግ ባለ በሌለ ኃይሉ እየሰራ ባለበት ሰዓት የሙህራኑ ዝምታ አስገርሞኛል። አሁን አጭር መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለው ሙህራኑ ሁሉ አገር ወደማዳኑ ስራ በመግባት ህብረት ፈጥራችሁ ኢትዮጵያን ከጥፋት በመታደግ ስራ ውስጥ ትሳተፉ ዘንድ ኢትዮጵያ ጥሪ አድርጋላችኋለች። የኢትዮጵያ ባላደራዎች ናችሁና ኢትዮጵያንም የምትጠብቁም ናችሁና ስለ አገራችሁ ብላችሁ ስራችሁን በተቀናጀ እና በተጠናከረ መልኩ ታሳዩን ዘንድ የኢትዮጵያ ህዝብ ይጠይቃችኋል።

ሌላው ወያኔ በፈጠረው የዘር ፖለቲካ ተጠላልፈን ነገሮችን ወደ ኋላ ተጉዘን ለማየት ግድ ሆኖብናል። በዚህ የተነሳ ብዙ ያልተገቡ ነገሮችን ባልሰራው ህዝብ ላይ የሰላ ትችት በመሰጣጠት አንዱ ጎጂ ሌላው ደግሞ ተጎጂ አድርጎ በማቅረብ የታሪክ መልካምነትን ሆነ መጥፎ ክንውኖችን ወደ አንድ ጎን በማዘንበል የሚሰጠው ትችት ከእውነት የራቀ ጉዳይ ነው። ምንም የጽሁፍም ሆነ የአርኬሎጂ ማስረጃ ሳይኖር የሚደረገው የታሪክ ዝርጠጣ ተቀባይነት የለውም። ይሄ አካሄድ ወያኔን እና የአረብ አብዬት ናፋቂዎችን ሊያስደስት ይችል ይሆን ይሆናል እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅመው አንዳች ነገር የለውም። የኢትዮጵያ ታሪክ መልካሙም መጥፎውም በሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የተሰራው እንጂ የእገሌ ጎሳ ነው ተብሎ የሚመዘዝ ታሪክ የለንም። ይሄንን አብዮት የሚያካሂዱ አካሎች በኢትዮጵያ ህዝብ ሌላ አጀንዳ ያላቸው መሆናቸውን ልናውቅባቸው ይገባል። ወያኔ ባመጣው የዘር ፖለቲካ ሁሉም ብሄሮች የራሳቸውን ግዛት ለማስመር ችለዋል። ያሰመሩትንም የግዛቴ አካል ነው ያሉትንም ይዘው ብቅ ብለዋል። ትግሬው፡- ትግሬ ትግሪኛን ለመመስረት፣ አማራው፡- በታሪክ የነበረው የአማራ መሬት በማለት፣ ኦሮሞው፡- ኦሮሚያ መሬት በሚል፣ ኦጋዴኖች፡- ታላቋን ሱማሌ ለመመስረት ኦጋዴን ነጻ መሬት ብለው መጥተዋል። ካርታውም እንደሚከተለው ነው።

እንኳን አገርን ወረረ ለተባለው ጠላት ይቅርና አብሮ ላደገው ጎረቤቱ እንዲሁም ለገዛ ቤተሰቡ ድንበሬን ገፋህ ተባብለው የሚፈሰውን ደም እናውቀው የለ ታዲያ አገርን የሚያክል ተወስዶበት ያውም ጠላት በተባለ አካል ዝም የሚል አለ እንዴ? እየሄድንበት ያለው አካሄድ በጣም አደገኛ ነውና የኔ ግዛት ይሄ ነው የሚለውን አካሄዳችንን በአፋጣኝ ልናቆመው ይገባል። <> ይባላል። አንዱ አንዱም በማጥፋት በይገባኛል ጥያቄ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዳንገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ያስፈልጋል። ካለበለዛ ዶሮን በአግባቡ ማርባት ሲጠበቅበት የበለጠ ያገኘ መስሎት ቆቅን ይዞ እንዳመጣ እና ሁለቱንም እንዳጣው ሰነፍ ገበሬ እንዳንሆን ልናስብበት የሚያስፈልገን ጉዳይ እንደሆነ ይሰማኛል።

ጥቂት ስለ ኦነግ እና ኦብነግ ጠቀስ አድርጌ ልለፍ፡-

ኦነግ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ በኦርቶዶክስ እምነት ላይ እና በአማርኛ ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ አለው። ይህንን የምልበት ያለምክንያት አይደለም ብዙ ማስረጃ እና መረጃዎችም አሉ ይሄ ጉዳይ ደግሞ በዝምታ አልያም በቸለተኝነት የሚታለፍም ጉዳይ አይደለም። እና በትንሹ ጠቀስ አድርጎ ማለፉ አውቀው ለሚሰሩት የማስጠንቀቂያ ደውል ለማያውቁት ደግሞ የማንቂያ ደውል ነውና አንባቢው ልብ ይሉት ዘንድ አስፈላጊ ነው። ኦርቶዶዶክስ እምነት ማለት የአማራ እምነት ነው ብለው እስከማስተማር የደረሱበት አካሄድ አለ። የፓርቲው አባል የሚሆነው ሰው በሁለቱም ማለትም በናቱም በአባቱም ኦሮሞ የሆነ ሰው አልያም ወይ በአባቱ አልያም በእናቱ ኦሮሞ የሆነ ሰው አባል መሆን ቢችልም ቅሉ አማርኛ ተናጋሪ ማለትም ኦሮምኛ የማይችል ከሆነ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ከሆነ የፓርቲው አባል መሆን አይችልም። ከኦነግ ፖለቲካ በስተጀርባ ያለው እውነት ይሄ ነው።

ፖለቲከኞች ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ብቻ ይዞ መሄድ እና መጓዝ ሲገባቸው የግል ህይወት ውስጥ በመግባት በፖለቲካ ሽፋን ሃይማኖትን ማስለወጥ የሚወገዝ ጉዳይ ነው። 40% ኦርቶዶክስ የሆነውን የኦሮሞ ህዝብ የምታምኑትን እምነት የአማራ ነውና ተዉትና ወደተለያየ እምነት መግባት አለባችሁ ማለት የኦሮሞ ህዝብን መናቅ፣ መድፈር እና ማዋረድ ነው። ኦርቶዶክስ የአማራ ነው ማለት መንግስተ ሰማያት የአማራ ነው ብለው መናገራቸው እንደሆነ አልተረዱት ይሆንን? ስለዚህ በሚሊዮን የሚቆጠር አማርኛ ተናጋሪ ኦሮሞ እና በሚሊዮን የሚቆጠር የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ኦሮሞ እንዳለን እየታወቀ በድብቅ ፖለቲካ አጀንዳነት መንቀሳቀስ የፖለቲካ ሂደታችሁ በከፍተኛ ሁኔታ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደገባ ልነግራችሁ እወዳለው። ለአንድ ሰው መገኘት ምክንያት እናቱ እና አባቱ ቢሆኑም እግዚአብሔር ግን የሁሉም አስገኒ እንዲሁም ፈጣሪ ነው። ከቤተሰቡ በላይ የኦርቶዶክስ አማኝ ለሃይማኖቱ ትልቅ መሰዋትነት እንደሚከፍል አታውቁ ይሆንን? ሃይማኖት ማለት የህይወት መሰረት ነውና ኦነግ በኦርቶዶክስ እምነት ያለውን የጥላቻ አመለካከት ከፖለቲካው ጋር አያይዞ መሄድ ተገቢ አይደለም። ኦርቶዶክስን የመጥላት ፖለቲካዊ አመለካከት እና አካሄድ በፍጥነት መቀየር ያለበት ጉዳይ ነው። የኦርቶዶክስን እምነት አጣጥሎ እና ንቆ የሌሎች እምነቶችን በፓርቲው ውስጥ ማቀፍ የሚደረገው ፖለቲካዊ ጉዞ የሃይማኖት ትግል እንዳያስመስልባቹ መጠንቀቅ ተገቢ ነው። ከፖለቲካው በስተጀርባ ሆኖ ግልጽ ያልሆነ እና የተደበቁ አጀንዳዎችን መስራት ከህብረተሰቡ የሚሰወር ስላልሆነ በጥልቀት ይታሰብበት ህብረተሰቡም ይሄንን ጉዳይ በጥልቀት ይከታተለው። በዚህ ጉዳይ እና በሌሎች ተያያዝነት ባላቸው አስፈላጊ ሆኖ ካገኘሁት ሰፋ ባለ መልኩ እመለስበታለው።

ሌላው ኦጋዴኖች የራሳቸውን መንግስት ለማቋቋም እየታገሉ ነው። ሊሰመርበት የሚያስፈልገው ጉዳይ ከላይ ከላይ የሚካሄደውን ትግል ሳይሆን ከዛ በኋላ የሚያስከትለውን አደጋ ነው። ለግዜው እስኪሳካላቸው ኦጋዴን ነጻ አውጪ በመባል ይጠሩ ይሆናል። በኋላ ላይ ግን ማለቂያ የሌለው መከራ ውስጥ እና ጦርነት ውስጥ እንደምንገባ ከፖለቲካው በስተጀርባ ያለው እውነታዎች ይነግሩናል። በካርታው ላይ እንደተመለከትነው ከኦሮሚያ ብዙ መሬቶችን በመውሰድ የቦረናንን፣ የሸዋን መሬቶችን በመከለል የሱማሌ መሬት እንደሆነ አስቀምጠውታል። እንግዲህ ልብ ያለው ልብ ይበል የሚባለው እዚህ ጋር ነው በተናጠል የሚደረገው ጉዞ ወይንም የዘር ፖለቲካ ወዴት ሊያመራን እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው። መጀመሪያ ነው እንጂ መጥኖ መደቆስ ኋላ ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ የሚለው ተረት ሊሰማ የሚገባው ዘመን አሁን ነው።

እኔስ እላለው ኢትዮጵያ ውስጥ ተገንጥዬ በሰላም እኖራለው የሚል አካል ካለ ማስተዋል ያልቻለ ሰው ብቻ ነው። ከእህል መሃል ረዝማ የወጣች የእህል ዛላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ ነው እንደሚባል ሁሉ ከኢትዮጵያ ተለይቼ እወጣለው የሚል አካል ካለ እራሱን ለወንጭፍ እንዳዘጋጀ መቁጠር አለበት። በኢትዮጵያ ካለው ነባራዊ እውነታ መገንጠል መቼም የማይሆን ሊሆንም የማይችል ጉዳይ ነው። ትክክለኛው መንገድ የፖለቲካ የበላይነት ፈጥሮ ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ መምራት ብቻ ነው። አንባ ገነን የሆነውን ወያኔን ጥሎ ዲሞክራሲ አገር ሁሉም በእኩል እና በሰላም የሚኖሩባት ስርዓትን ማምጣት ነው እንጂ ሌላ አጀንዳዎችን ከሃሳባችን ማስወጣት ያስፈልገናል።

ከተማ ዋቅጅራ

06.11.2015

Email- waqjirak@yahoo.com

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.