0

ከፖለቲካው በስተጀርባ ያሉት እውነቶች – ከተማ ዋቅጅራ ክፍል ፩

ከፖለቲካው በስተጀርባ ያሉት እውነቶች – ከተማ ዋቅጅራ

TPLF 2
ክፍል ፩

ወያኔ በመጀመሪያ እቅዱን ቀርጾ ሲንቀሳቀስ የነበረበት ትግራይን ነጻ ለማውጣት የሚል ነበረ። በዚህ ግልጽ ባልሆነ በተደበቀ አላማቸው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የሆኑትን የትግራይ ተወላጆችን አታለውበታል። ከዓላማቸው በስተጀርባ ተንኮላቸውን ደብቀው በቋንቋቸው የትግራይ ተወላጆችን በመቀስቀስ ወደ ትግሉ ጎራ በብዛት እንዲገቡ በማድረግ ህዝቡ የማያውቀውን አላማ በመጫን በህዝብ ላይ ታላቅ ደባ ሰርተውበታል። ህይወትን በሚያክል መሰዋትነትን በሚጠይቀው ትግል ውስጥ ሲገባ ታጋዩ የሚታገልበትን አላማ ሊያውቀው ይገባል አታጋዮችም የተነሱበትን አላም በግልጽ ለታጋዩ እና ለህዝብ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ወያኔዎች የትግላቸውን ዓላማ ከጥቂቶች በስተቀር በታጋዩም ሆነ በህዝቡ ዘንድ አይታወቅም በዚህ የተነሳ እርስ በራሳቸው ይበላሉ ነበረ። ሚስጢራቸውን ያወቀውንም ሆነ ለማወቅ የሚፈልገውን አልያም ክትትል የሚያደርጉት ታጋዮችን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን በረሃ ላይ አጥፍተዋቸዋል። አሁን የያዙትን ስልጣን ለመያዝ በሚያደርጉት ትግል ከደርግ ጋር በመዋጋት ከሞተው የትግራይ ተወላጅ በራሳቸው ሰዎች ምስጢራችንን አወቁብን ምስጢራችንን ሊያውቁ ነው ምስጢራችንን እንዳያወጡብን በማለት አላማችን ከሚጠፋ እነሱ ይጥፉ እያሉ በወያኔ ሰዎች የተገደሉት የትግራይ ታጋዮች ከደርግ ጋር በነበረው ጦርነት ከሞቱት በአስር ሺዎች የበለጠ እንደሚሆን ለወያኔ ቅርበት ያላቸው የትግል አጋሮቻቸው የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ይነግሩናል። ግዜው ሲደርስ ሁሉም እውነታዎች ፍንትው ብለው ይወጣሉ እንደታፈነ የሚቀር ምንም ነገር የለም። ታዲያ ወያኔ የታገለው ለማን ነው? የትግሉስ አላማ ምንድን ነበረ?

የወያኔ የትግል እና የደርግ ትግል ሌላኛው ገጹ የአሜሪካ እና የሩሲያ ጦርነት ሊባል ይችላል። ኃይሌ ገብረስላሴ እና ፖልቴርጋት ሲዲኒ ላይ በተደረገው የኦሎፒክ ውድድር የአስር ሺ ሜትር ሩጫ ሲያደርጉ ኬኒያዊው ፖልቴርጋት የናይክ ካንፓኒ ትጥቅ አድርጎ ኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገብረስላሴ የአዲዳስ ካንፓኒን ትጥቅ አድርገው ይሮጣሉ ፉክክሩም በጣም ከባድ ነበረ በመጨረሻውም ኃይሌ አንገት ላንገት ተናንቀው በመግባት ፖልቴርጋትን አሸንፎታል። እናም ሚዲያዎች በኢትዮጵያዊው ኃይሌ እና በኬንያዊው ፖልቴርጋት የተደረገ ውድድር ሳይሆን በናይክ እና በአዲዳስ ካንፓኒዎች ጭምር ውድድሩ እንደተደረገ አድርገው ያቀርቡ ነበረ። እንደዚሁ ሁሉ ከወያኔ ጀርባ አሜሪካ እና እንግሊዝ ከደርግ ጀርባ ደግሞ ሩሲያ ነበረች። በአሜሪካ እና በእንግሊዝ ከፍተኛ ድጋፍ ታግዘው በነዚሁ አገሮች የስለላ መረብ ተዘርግቶላቸው በለስ ቀንቷቸው ወያኔ ወደ ስልጣን ወንበር ወጡ። በሌላ አገላለጽ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አሜሪካ እና እንግሊዝ በሪሲያ ላይ የበላይነታቸውን አሳዩ እንደማለትም ሊሆን ይችላል።

የደርግ ወታደር በጦርነት ተሸንፎ ስልጣኑን አላስረከበም ይሄንን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያውቀዋል። አሁን እንኳን ሰራዊቱ የመሰባሰብ እድሉን ቢያገኝ ወያኔዎችን መግቢያ እና መውጫ ቀዳዳ እንደሚያሳጣቸው ይታወቃል ምክንያቱም ወያኔ ማለት አገር ሻጭ አገር ከፋፋይ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ስላወቃቸው በጽናት ስለሚታገላቸው የቀደመው አይነት ክፍተት አይፈጠርም። የደርግ ሽንፈት የእግዚአብሄር ጉዳይ ነው እንጂ የወያኔ የጦር የበላይነት አይደለም። ደርግ አንባ ገነን ቢሆንም ቅሉ ስርአቱ መለወጥ እንዳለበት ቢታወቅም ቅሉ እንደ ወያኔ በጥላቻ እና በዘር በሃይማኖት መከፋፈል የአንድ ብሄር የበላይነት አንግሶ የሚዘርፍና የሚጨቁን ሳይሆን ኢትዮጵያን ሁሉ እንደ አንድ የሚያይ በማንም ላይ የዘር ጥላቻ ስለሌለው ከዳር እስከዳር አንድ አድርጎ የሚገዛ ነበረ። ሰራዊቱ የህዝብ ፍቅር ስላለው መሳሪያችሁን ጥላችሁ ወደ ቤተሰቦቻችሁ ተቀላቀሉ ሲባሉ በየዋህነት ያንን አድርጎ ነው ወደ ቤተሰቡ የተቀላቀለው እንጂ በህዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም። ያ ባይሆን ኖሮ ግን ወያኔ እንደዚ አገር አፍራሽ እና አገር ሻጭ እንደሆነ ሰራዊቱ ቢያውቅ ኖሮ መቼም የአሁኑን ስልጣን አይዙም ነበረ። የደርግ ወታደር የኢትዮጵያ ወታደር ነበረ። የደርግ ስርአቱ ቢለወጥም ወታደራዊ ተቋሙ መፍረስ አልነበረበትም ምክንያቱም ያ ሰራዊት ወታደራዊ ስልጠናዎችን በኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት የተማሩ ትልልቅ የወታደር ተቋም ካላቸው አገር እንደ ሩሲያ፣ አሜሪካ እና እስራኤል ባሉ አገራት ወታደራዊ ትምህርታቸውን በብቃት የተከታተሉ የወታደ ኢንጅነሮች የነበሩበት ተቋም ስለነበር። ታዲያ ይህ ጠንካራ ወታደራዊ ተቋም አፍሪካን መግዛት ይችላል እየተባለ በሃያላን አገራት ጭምር ይነገርለት የነበረው ወታደራዊ ኃይል እንደት ወያኔ እና ሻቢያ የተባሉትን ማጥፋት አቃተው? ቢባል ደርግ በፈጠረው ከፍተኛ የሆነ አንባ ገነንነት አቋሙ ተጠቅመው ድብቅ የሆነውን አጀንዳቸውን መፈጸም በመቻላቸው ነው። ሌላው ደግሞ አሜሪካም ሆነች እንግሊዝ በአፍሪካ ጠንካራ የወታደር ተቋም ያውም የነሱን ፖሊሲ የማይደግፍ በአፍሪካ አገር እንዲቋቋም ያለመፈለጋቸው ነው። ወያኔዎች በነዚህ አገራት ከፍተኛ የሆነ የስለላ ስራ እና ትጥቅና ስንቅ እርዳታ ጭምር በከፍተኛ ድጋፍ የማግኘታቸው ጉዳይ ነው። ሌላው ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው እና ቁልፍ ቦታ የሚባለው ወታደራዊ ቦታዎችን የሚመሩትን የደርግ ባለስልጣን ለወያኔ መስራታቸው ነው። ትልቁም የደርግ ውድቀት ወያኔ ጀግና ሆኖ ሳይሆን የደርግ ባለስልጣን ወታደራዊ ሚስጢርን አሳልፈው በመስጠታቸው ነው።

ሽንፈቱም የራሱ በሆኑት በከፍተኛ ማእረግ እና ቁልፍ ወታደራዊ ቦታ በሃላፊነት ተሰጥቶአቸው የተሳሳተ ትህዛዝ እየሰጡ ምስኪኑን ለአገሩ የሚታገለውን ወታደር እያስፈጁ በተከበበ የጠላት ክልል ውስጥ መሃል እንዲገባ ትእዛዝ እየሰጡ ያስፈጁት ነበረ። ሌላው ቀርቶ የጦር ሄሊኮፕተር ጭምር አስልከው የወያኔ ምሽግ እና ወታደሮችን ሳይሆን የራሳቸውን ወታደር ሲጨፈጭፉ የነበሩት። የደርግ ወታደራዊ መዋቅር በብቃት የተመሰረተ ነው። መከላከያዉ በእዞች እዞች በክፍለ ጦሮች ክፍለ ጦሮች በሻለቆች ሻለቆች በሻንበሎች እያለ የተከፋፈለ እና በተዋረድ የሚወርድ ጠንካራ መዋቅር ነበረው።ጠንካራ አየር ኃይል ጠንካራ ባህር ኃይል ጠንካር ምድር ጦር የነበረው ያውም በዘመድ ሳይሆን በብቃት የተመለመሉ ብቃት ያላቸው ጀግና ወታደሮች የተሸነፈው በወያኔ ሳይሆኑ አምኖ በሾማቸው የራሱ ሰዋች ናቸው።

የደርግ ሃይል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር በኤርትራ ተቀምጦ ነበር። ይሄ የሆነበት ምክንያት ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ግንባር የሚለውን አዋጅ ተከትሎ ነው። ሰሜን የሰፈረውን ኃይል ድጋሜ ሌላ ትዕዛዝ በመስጠት ወደ ሸዋ እንዲንቀሳቀስ አድርገውታል። ይህ የሚደረገው ከአንድ ቦታ ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ግዜ በጠላት አስከብቦ ወታደሩን ለማስጨረስ ነው። በሁሉም ግንባር ላይ ቦታችሁን ለቃችሁ ሂዱ ጠላት በከፍተኛ ሁኔታ ያላው በዛኛው ግንባር ነው እያሉ የያዙትን ቦታ በበላይ አዛዞቻቸው ትዕዛዝ ወሳኝ የሚባሉትን ቦታዎች በቀላሉ ወያኔ እንዲይ ያደርጉ ነበረ የወያኔ ወታደሮችም ጫካ ውስጥ ጥይታቸውን እያንጣጡ በመንገድ ጠራጊዎች በደርግ ባለስልጠን እየተመሩ በፍጥነት ወደ መሃል አገር መጓዝ ጀመሩ። ቀድመው ለስብሰባ ተብለው ከአገር እንዲወጡ የተደረጉት መንግስቱ ኃይለማሪያም ከአገር በወጡ በጥቂት ቀናት ውስጥ አዲስ አበባን በመቆጣጠር ደርግ ሲቆጣጠርበት የነበረውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዝን እና ራዲዮ የኢህአዴግ ሰራዊት ተቆጣጥሮታል ብለው በቴሌቪዝንም በሬድዮም በመናገራቸው ሰራዊቱ መሳሪያውን በመጣል ወደ ቤተሰቡ ለመቀላቀል ችሏል። ጀግና ሳይሆኑ መጀገኑ ዋጋ የለውም አሸናፊ ሳይሆኑ አሸናፊ መባሉ እርባና አይኖረውም እድል ቀንቷት ቅል ድንጋይ ልትሰብር መጣሯን እያየን ነው። ቅል ድንጋይ መስበሯን ወደፊት እናየዋለን ወይ ቅልነቷን አውቃ ትቀመጣለች አልያም እራሷን ከድንጋይ ጋር አጋጭታ እራሷን በራሷ ትሰብራለች።

ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኃላ ድብቅ ማንነቱን ያየንበት ነው። ይሄ ማንነቱ ምን ይመስላል ለሚለው እና ሌሎች ተያዝነት ያላቸውን እውነታዎችን በክፍል ሁለት ይቀጥላል።
ከተማ ዋቅጅራ
22.10.2015
Email-waqjirak@yahoo.com

Filed in: Amharic News, eMedia, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.