0

(የላጲሶና የተክሌ ጉዳይ) ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ ፤ ወይ ጣፍጠው ወይ መረው ታገኟቸዋላችሁ (ጌታቸው ኃይሌ)

(የላጲሶና የተክሌ ጉዳይ) ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ ፤ ወይ ጣፍጠው ወይ መረው ታገኟቸዋላችሁ ፣በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

Getachew Lapiso and Tekle
ከአንድ ዛፍ ፍሬ ለመልቀም የሚፈልግ ከመልቀሙ በፊት መጀመሪያ ፍሬውን መቅመስ ይኖርበታል። አንዳንድ ዛፍ ዠርገግ ብሎ ሲያዩት ልብ ይማርካል። አበባው በጭለማ ሳይቀር ይታያል፤ ያስደስታል። ለሕይወት የሚሆን ፍሬ ግን ላይኖረው ይችላል። እንደዚያ አምሮ ገምሮ ሳለ የሚጠቀሙበት ትሎች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ።
አንድ ሰው ስሙን ከአካዴሚክ ማዕረጉ (Ph.D) ጋር እየጻፈ ደብዳቤ ይልክልኝ ነበረ። ለማዕረግ ያበቃውን ድርሰት (dissertation) የጻፈው ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ነው። የኋላ ኋላ እንደተረዳሁት፣ አድራሻየን ፈልጎ የጻፈልኝ በችሎታው የሚያገለግልበትን ሥራ በማፈላለግ እንድረዳው ኖሯል። ዛፉ ዲፕሎማው ነው፤ ፍሬው ድርሰቱ ነው። የድርሰቱን ቅጂ በፈቃዱ ላከልኝ። ሳነበው አዘንኩ። እንዴት አንድ ዩኒቨርስቲ ይኸንን ድርሰት ለማዕርግ በቂ አድርዶ ይቀበለዋል? እኔ ብሆን ለPh.D ቀርቶ ለBAም እንኳን አልቀበለውም። እንዴት አንድ መርጦ በያዘው መስኩ የሚመራመር ሰው የአርዮስን ክሕደት ለንስጥሮስ ወይም የንስጥሮስን ክሕደት ለአርዮስ ይሰጣል? መምህሩስ (ምንም ሙስሊም ቢሆን) ይኸንን ስሕተት እንዴት ያሳልፈዋል? የአርዮስንና የንስጥሮስ ዳሕጽ ማማታቱን ለምሳሌ ያህል አነሣሁት እንጂ፥ ድርሰቱስ ስሕተት አልባ ገጾቹ በቍጥር ናቸው።
ይኸን ታሪክ ለምሳሌ እንዳነሣ ያሳሰበኝ አቶ ተክሌ የሻው ዶክተር ላጵሶ ዴሌቦ በኢሳት(ESAT) አማካይነት በሰጠው የኢትዮጵያ ታሪክ ትምህርት ላይ ስሕተት ስለታየው ያንን ለማረም በ10/30/ 2015 በቀረበ ጊዜ በሱና በጋዜጠኛው መካከል በተደረገው ውይይት ላይ የታዘብኩት ትዝብት ነው። ለዶክተር ላጵሶ አክብሮት አለኝ። መጻሕፍቱን ያነበብኩት እሱ ቸሮኝ ነው። የኢሳት ጋዜጠኞችና አቶ ተክሌ ወዳጆቼ ናቸው። ውገናየ ከታሪካችን ጋር ነው።

የጋዜጠኛውና የአቶ ተክሌ የሻው ውይይት አጀማመሩ ግራ የሚያገባ ነበር። ጋዜጠኛው፥ “ስሕተቱ ምንድነው፤ እስቲ ንገረን?” ብሎ በማስጀመር ፈንታ፥ የታሪክ ትምህርት ዲፕሎማ ሳይኖርህ፥ የታሪክ ባለሙያ (ባለ Ph.D) ለመሞገት ምን ችሎታ አለህ? የሚል መንፈስ ያዘሉ ጥያቄዎች አከታተለበት። እርግጥ ማንም ተነሥቶ ማንንም ቢተች አያምርበትም። አንድ ሰው እኩያው ያልሆነን ሰው ልተች ሲል መድረኩን መንሣት ይቻላል፤ የተለመደም ነው። መድረኩን ከሰጡ በኋላ ግን ሲያስፈልግ እንደጋዜጠኛ እየጠየቁ መልሱን በጥሞና ማዳመጥ እንጂ በፖሊስ ምርመራ ዓይነት በተሞጋቹ ስም መከራከር በጋዜጠኝነት ሙያ የተለመደ አይደለም። አዳማጮች የአቶ ተክሌን በመልሱ (በፍሬው) እንጂ በዛፉ (በዲፕሎማው) እንዳልፈረዱት እገምታለሁ። ደሞም እኮ መጽሐፉን ላነበበ አቶ ተክሌ ማንም አይደለም።

እርግጥ አንድ ሰው በአንድ ሞያ ላይ ለመዋል፥ ሞያውን ማስመስከር ይጠበቅበታል። Ph.D ሁሉ ተጠርጣሪ ነው አይባልም፤ እኔም አልልም። የፈለግሁት በሙያ ረገድ Ph.Dን ብቸኛ መተማመኛ ማድረግ ስሕተት ነው ለማለት ነው። ለምሳሌ የጋዜጠኝነት ዲግሪ የሌላቸው ታላላቅ ጋዜጠኞች እናውቃለን። ኢሳት ውስጥ አገራቸውን የሚያገለግሉ ሁሉ የጋዜጠኝነት ዲግሪ ያላቸው አይመስለኝም፤ ካላቸው አስተያየቴን በደስታ እለውጣለሁ።

የታሪክ ዕውቀት የሚገኘው የታሪክ ምንጮችን በማንበብ ነው። አቶ ተክሌ አንቱ የሚያስብል የታሪክ መጽሐፍ ደርሷ። በዚያ መጽሐፍ ውስጥ ዶክተር ላጵሶ ያለፋቸው ብዙ ቁም ነገሮችን አስተምሮናል። እኔም ብሆን ማንም የታሪክ አስተማሪ አላስተማረኝም። ታዲያ ከልጅነት ጀምሮ ውሎየ የኢትዮጵያን የታሪክ ሰነዶች ማንበብና መመራመር፣ ማመሳከርም ሆኖ ሳለ፥ ታሪክ አልተማርክምና ስለኢትዮጵያ ታሪክ ለመናገር ብቃት የለህም ብባል ማን እሺ ይላል?

ዶክተር ላጵሶ የመረመረው አቶ ተክሌ ያልመረመረው በሁለቱ ተራኪዎች ማህል ልዩነት የፈጠረው የታሪክ ምንጭ የትኛው ነው? እንዲያውም፥ ፕሮፌሰር ላጵሶ፥ “ዶክተር ስናይደር ነግሮኛል” ሲል ሰምቸዋለሁ። የታሪክ መምህራችን ዶክተር ላጵሶ ዶክተር ስናይደር ያነበበውን ደብተራዎች የጻፉትን አላየውም ማለት ነው። ትምህርት አስኪጨርሱ፥ ከመምህር በታች መሆን ሥርዓት ነው። መምህር ከሆኑ በኋላ ግን፣ ሲሆን መብለጥ አለዚያም እኩል ሆኖ መገኘት ያባት ነው። ለመስማት የፈለግሁት “ይኸንን ለዶክተር ስናይደር አስረድቸዋለሁ” ሲል ነበር።

በውይይቱ ላይ ለአቶ ተክሌ የቀረበለት ሌላው ጥያቄ፥ “ታሪክን መጻፍ የሚችል ማነው?” የሚል ነበር። ጥያቄው ያዘለው ምሥጢር ባይኖረው፥ መልሱ ቀላል ነበር፤ “ታሪክን መጻፍ የሚችል ታሪክ ዐዋቂ” ነው። ታሪክ ዐዋቂ የምለው፥ እንደ ዶክተር ላጵሶ ታሪክ የተማረውን፥ እንደ አቶ ተክሌ የታሪክ ምንጭ የመረመረውን፥ እንደ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ገድላቱንና ታምራቱን የታሪክ ምንጭነታቸውን ያሳየውን፥ እንደ ደብተራዎቹ ድርጊቱ ሲፈጸም በጊዜው የነበረውን (ማን ይናገር? የነበረ፤ ማን ያርዳ? የቀበረ) ነው። ግን ጥያቄው ንጽሕና የጐደለውና ምሥጢር ያዘለ ለመሆኑ፥ በየቀኑ የምንሰማው ትችት ይመሰክራል። “የኢትዮጵያን ታሪክ የጻፉ ደብተራዎች ናቸው፤ አማሮች ናቸው” የሚለውን ዋጋ ቢስ ትችት ያቀፈ ነው።

ትችቱ በውይይቱ ላይም በግላጭ ተነሥቷል። ኢትዮጵያ ታሪካዊ አገር መሆኗን የነገሩንና ዓለምንም ያስረዱልን፣እኛንም ባባቶቻችን ታሪክ እንድንኮራ ያደረጉን “ደብተራዎችና አማሮች” ናቸው፤ ክብርና ምስጋና ይድረሳቸው።

ግን ታሪክ ጸሐፊነታቸው የተነቀፈው፥ደብተራዎችና አማሮች ስለሆኑ ነው ወይስ እንደሚታሙት “ተረት ተረት” ስለጻፉልን ነው? ታሪካችንን ማን እንዲጽፈው ነው የተፈለገው? ማንስ እንዳይጽፍ ማን ከለከለው? ምዕራባውያን ዘንድ ሄደን በታሪክ ዕውቀት የምንመረቀው ደብተራዎቹና አማሮቹ የጻፉትን ምዕራባውያን በየቋንቋቸው የተረጎሙትን አጥንተን አይደለም እንዴ? አውሮፓውያንና ኢትዮጵያውያን (አማሮችና ደብተራዎች) በጻፉት የኢትዮጵያ ታሪክ መካከል ያለው ልዩነት የት ላይ ነው? ምንም ልዩነት ሳይኖርባቸው አንዱ ዶክትሬት ያሰጣል፥ ሌላው ይነቀፋል። ስለ ግራኝ ዐመፅ ዐረብ ፋቂህ በዐረቢኛ የጻፈውንና ደብተራዎቹ የጻፉትን አስተያይታችሁታል? ከዝርዝሩና ከጸሐፊዎቹ የግል አስተያየት (ያላዩትን ከመጻፍ) በቀር እውነቱ ላይ በምንም አይለያይም። አንዱ “እገሌ ሞቶ ነፍሱ ገነት ገባች” ሲል፥ ሌላው ያቺኑ ነፍስ “ገሃነመ እሳት ገባች” ይላል።
አዲስ ማስረጃ ሲገኝ የተሳሳተ ታሪክ ማረም የተለመደ ነው። አሁን ዛሬ የትኛው አዲስ ሰነድ ተገኝቶ የትኛውን ተረት ሊያርም እንደቻለ ማስረጃ ይሰጠን። አብረን እንመረምረዋለን። ደብተራዎቹና አማሮቹ በዘመኑ ተገኝተው በዓይናቸው ያዩትንና በጆሯቸው የሰሙትን ጽፈዋል። ያላየና አዲስ ማስረጃ የሌለው ሰው የነሱን ድርሰት የመንቀፍ መብት እንዴት ይኖረዋል? ማስረጃ ተፈጥሮ እንደሆነ፥ ፍጡር ማስረጃ አንቀበልም።

ለአቶ ተክሌ የቀረበለት አስገራሚ ጥያቄ “አማራ ማነው?” የሚል ነበረ። ነገሩን የቆሰቆሰው ዶክተር ላጵሶ፥ ተጠያቂው አቶ ተክሌ! ሞረሽ ወገኔን ለምን መራህ ለማለት ይሆን? አለቦታው!

ሌላው የሚናፈሰው ነቀፋ “የኢትዮጵያ ታሪክ የሚባለው የነገሥታት ታሪክ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ አይደለም” የሚል ነው። ይህ መሠረት የሌለው ነቀፋ በውይይቱ ላይ ሰፊ ቦታ ተሰጥቶታል። የዚህ ነቀፋ ምንጭ ሊቃውንቱ በግዕዝ ያቆዩልንን ታሪክ ምዕራባውያን ሲያሳትሙት “Royal Chronicles” የሚል ስም ስለሰጡት ይመስለኛል። ነቀፋውን አንድ ሰው ጫረው፤ ሆድ የባሰው ሁሉ እየተቀባበለ አለኳኰሰው። እኔ እንዳነበብኩት ከሆነ፥ የተነቀፈው ታሪክ የኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ ነው። መንግሥት ደግሞ ንጉሥና ሕዝብ ነው። የሌላው ሁሉ አገር ታሪክም ቢሆን፥ እንደኛው የመንግሥቱ ታሪክ ነው፤ ከዚህ የተለየ የሕዝብ ታሪክ የሚባል ብሔራዊ ታሪክ የትም የለም። ምናልባት “እገሌ እገሊትን አግብቶ እነ እገሌን ወለደ። በዘመነ ሕይወቱ ይህን ይህን ሠርቶ ከዚህ ዓለም በሞት ወይም በምንኵስና ተለየ” የሚል የቤተ ሰብ ታሪክና የጻድቃኑ ገድላትና ተአምራት ቢጠራቀሙ የሕዝብ ታሪክ የሚባል ነገር ይወጣቸው ይሆናል። ዶክተር ላጵሶ ከእነዚህ ገድላትና ተአምራት ውስጥ ብዙዎቹን እንዳላነበባቸው የመጽሐፉ ይዞትና የዘረዘራቸው ዋቢ መጻሕፍት ይመሰክራሉ። ማስረጃዎችን ፈልጎ ያላጣ አላገኘሁም ብሎ አያጕረመርምም።

ለምሳሌ፥ ታሪክ ጸሐፊዎች ኦሮሞዎች ዳዩ ዳባ የሚባል ንጉሥ እንደነበራቸው ያውቃሉ? ደብተራዎቹ የጻፉትን ተአምረ ማርያም ካላነበቡ ከየት አምጥተው ያውቁታል? ተአምሩ እንዲህ ይላል፤
አረሚዎች (= ኦሮሞዎች) የክርስቲያኑን ሀገር (ዋካትን፣ ጠጠራን፣ ምድረ በረሐን፣ መቅደላን) ሊያወድሙ ተመካክረው ከብዙ ቦታ ዋጃ ላይ ከተቱ። ምክንያቱም፣ አረሚዎች፣ (አዲስ ንጉሥ) ሲያንግሡ የነገሠው አገር የማውደም ልምድ አላቸው። በዚያን ጊዜም ዳዩ ዳባ የሚሉት ነግሦ ነበረ። አገር የሚያወድሙበትና ጦር የሚያውጁት በኅዳር ወር በሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል በዐል ዕለት ነበር። . . . እመቤታችን ማርያም አረመኔዎቹ አገሯን ለማጥፋት ጨክነው እንደተነሡ ስታይ፥ሳያስቡት፣ ወደምድረ አዳል መርታ ጠላቶቻቸው (ሙስሊሞቹ) እጅ ላይ ጣለቻቸው። ከ12 ነገሥታት (= የጎሳ መሪዎች) አንድ ንጉሥ ብቻ ተረፈ፤ ከሠራዊቱም አንዳንድ ለወሬ ነጋሪ ተርፎ ይሆናል።
ይህን እዚህ የጠቀስኩት “የአባ ባሕርይ ርድሰቶች” እሚባለው መጽሐፌ ውስጥ ስላልገባ ነው። ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ምዕራባውያን፥ ደብተራዎቹና አማሮቹ የጻፉትን መሠረት ሳያደርግ ተአማኝነት ያለውን የኢትዮጵያን ታሪክ መጻፍ አይችልም። እነሱን (በእነሱነታቸው) የጠላ በምዕራባውያን እጅ አዙር ይጠቅሳቸዋል።

(አባ ባሕርይና አለቃ ታየ ስለ ኦሮሞዎች የጻፉትን የሚተቸውን “የአባ ባሕርይ ርድሰቶች” ለማንበብ የፈለገ ከኢንተርነት ስላለ (The Works of Abba Bahriy – by Dr. Getatchew Haile) በነፃ ቀድቶ ማንበብ ይችላል።)

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.