0

ኢሳት በአቶ ተክሌ ቃለ መጠይቅ፣ ተጋለጠ

ኢሳት በአቶ ተክሌ ቃለ መጠይቅ፣ ተጋለጠ
የአቶ ፋሲልን ጽሁፍ ካነበብሁ በኋላ ከጥርጣሬ አልፎ  በአማራው ህዝብ ላይ ዘረኝነትና ጥላቻ ምን ያህል ስር የሰደደ፣ በቀላሉ የማይጸዳ፣ ተስፋ የሚያስቆርጥና ወደ መደምደሚያ ውሳኔ የሚወስድ ሆኖ አገኘሁት.
በአቶ ፋሲል ጽሁፍ ጥያቄው በዚህ መልክ ይሁንልኝ ማለት ነውር ነው ሲል፣ አቶ ተክሌ ደግሞ ደጋግመው በቃለ መጠየቁ ከመጀመሪያው ጀምሮ የተናገሩት፣ ዶክተር ላጺሶ የተናገሩት ከጻፉት ጋር ስለሚቃረን፣ ያን ተቃራኒ ነው የምለውን በራሳቸው ጽሁፍ ለማሳዬት ነው ሲሉ ተሰምተዋል. ስለዚህ ምኑ ነው ለአቶ ፋሲል ነውር ሆኖ የተሰማው፣ አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ ካልሆነ በቀር.
ከጀርባው ያለው አይነተኛ ነገር ግን አቶ ፋሲል ነውር ነው ያለው ወይም ለመከላከያ ብሎ ያቀረበው ውሃ የማይቋጥር መከላከያ ምክንያቶች አይደሉም. በቃላ መጠይቁ ጎልቶ የታዬው ነገር የኢሳት ሰራተኞች ሳይቀሩ ምን ያህል በአማራው ህዝብ ጥላቻ የተበከሉ፣ በኢትዮጵያ በትግራይ ብሄረተኞች፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ደግሞ የስልጣን ተጋሪያቸው የነበሩት ነገር ግን የውጩን ክፍል አክራሪ ብሄረተኛ ሆነውና መስለው በመቅረብ የህዝብን አንድነት ለመሸርሸር በእቅድ በወያኔ መንግስት በተላኩ፣ በአክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኞች በሚሰበከው ጸረ አማራ ህዝብ ከመመረዝ አልፈው፣ ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ እንዲሉ፣ በአቶ ፋሲል አማካኝነት ኢሳት ያሳዬን ያንን ዘረኝነት ነው. አቶ ፋሲል ከስራ ጓደኞቻቸው ጋር እንደተነጋገረበት በጽሁፍ ገልጾል፣ ታዲያ ይህን የዘረኝነት አቋም የአቶ ፋሲል አቋም ነው ብሎ ማሰብ አይናችሁን ጨፍኑና ላታላችሁ ማለት ይሆናል.
ውይይቱን በደንብ ላዳመጠው አቶ ተክሌ ስለኢትዮጵያ ህዝብና ሀገር አንድነትና ስለአንድ ኢትዮጵያ ብሄረተኛነት ሲናገሩ፣ የአቶ ፋሲል ሙግት ግን ከብሄረተኞች የባሰ ብሄረተኛ ሆኖ ይደመጣል. ኢትዮጵያዊነት ጨርሶ ተሟጦ የጠፋበት ከመሆን አልፎ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ሆነው የተስማሙበት መሆኑን በራሱ ቃል ሲጽፍልን ደግሞ ብዙዎቻችንን አስደንግጦናል፣ ለኔ ቢጤው በኢሳት ጸረ አማራነት ይደመጥ የነበረውን ሀሜት ከጥርጣሬ አልፎ ከብረት የጠነከረ አውነትነትን ያረጋገጠለት ሆነለት. አቶ ፋሲል እንደ አቶ ጀዋር ከኢሳት ወጦ በአማራውና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ጦር አንሱ ቢል እንግዳ ሊሆን አይችልም፣ ከሁሉ ይበልጥ የኢሳት ደጋፊና ደጋፊ ያልሆኑ ሳይቀሩ በማነኛውም የሶሽያል ሜዲያ በሚዘዋዘሩ ጽሁፎች ማንም ሊታዘበው እንደሚችለው፣ ህዝብን የጎዳው በዚህ ቃለመጠይቅ የተከሰተው ድብቅ መልክ ግልጽ ሆኖ ሲታይ መርዶ የሆነብን በኢሳት የደረሰበት የእምነት ሰለባ ነው.
ይህ በኢሳት የተፈጸመብን የእምነት ሰለባ፣ በተለይ የአማራው ህዝብ በማንም ላይ እምነት እንዳይኖረው፣ ተስፋ የቆረጠ፣ የኔ የሚለውና የሚያምነው እንዳይኖረው ለማድረግ በኢሳት የዝግጅት ክፍሎች ታቅዶ፣ በነሱ ፍላጎትና ግንዛቤም ይሁን ወይም ከኋላው ባለ ሀይል የተፈጸመ የስነልቦና ጦርነት ነው.
ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ ሞረሽ በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል አብረው ላልወገኑ ኢትዮጵያኖች በማሰማት የአማራውን ህዝብ እንዳይፈናቀል፣ በገደል እንዳይጣል፣ እንዳይገደል፣ እንዳይዋረድ፣ እንዳይታሰር የሚታገል ሲቪክ ድርጅት ነው. የዚህን ድርጅት መሪ ኢሳት በአመራር ደረጃ መክሮ የሚያጠቃ ከሆነ፣ ያውም ከአማራው ህዝብ ከሆኑ ኢትዮጵያኖች የስራ ማካሄጃ ድጎማ እያገኘ መሆኑ ደግሞ ቢያንስ የኔ ቢጤውን እርም ያስወጣል. በሬ ካራጁ ጋር ይውላል እንደሚሉት እንዳይሆንበትም ይሸሻል.
ኢሳት አማራውን ህዝብ በጀምላ የሚሰድብን፣ የሚከስን፣ የሚያዋርድን አንቱ እያለ ከማስተናገድ አልፎ፣ ገዳይና አስገዳዮቹን እነ ታምራት ላይኔን ክቡርነቶ ብሎ እያስተናገደ፣ ዶክተር ላፒሶ ስለ አማራው ህዝብ የተናገሩት ትክክል አለመሆኑን ከራሳቸው መጽሀፍ ጠቅሸ  ላስረዳ ያለን ቃለ መጠይቁ ሲጀመር ጀምሮ ሞያህ አይደለም ለማለት የታሪክ ተማሪ ነህ ወይ ሲል ጀምሮ በመጨረሻም ግለሰቡን በደርግነት መክሰስ፣ በኢሳት የአመራር ደረጃ ሳይቀር ለአማራ ህዝብ ያላቸው ጥላቻ ምን ያህል ስር የሰደደ መሆኑን የሚጠቁም ብቻ ሳይሆን በግልጽ የሚመሰክር ነው.  ጨው ለራስህ ብትል ጣም እንደሚባለው የኔ ቢጤ አማራ ነኝ የሚል ህዝብ ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል.
በመጨረሻ፣ ምንም እንኳ ከኢሳት አንዳንድ የምወደው ፕሮግራም ቢኖርም፣ ምንም እንኳ እስከዛሬ ስከፍል ብቆይም፣ የወዳጅ ክህደት ቁስሉ የማይደርቅ፣ ይበልጥ የሚያም፣ እያመረቀዘ የሚአነግል ነውና በዚህ ከኢሳት እንለያይ፣ ደንቆሮ አዋቂ ለመምሰል ሲሞክር ድንቁርናው ይከሰታል እንደሚሉት፣ ኢሳትም ብልጣብልጥ ለመሆን ሲሞክር በአቶ ፋሲል ቃለመጠይቅና ጽሁፍ ማንነቱ ተጋልጾ ተለያዬን. ደህንነት የሚባል ነገር ካለ ደህና እንሁን. እግዚአብሄር ያችን ሀገር በቸርነቱ በተአምር ይጠብቃት.
From: abejebelew@gmail.com <abejebelew@gmail.com>

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.