0

ኢትዮጵያን አዳኝ ዉይይቶችና እንቅስቃሴዎች ስናደርግ ፣ በዶ/ር ተስፋዬ ደምመላሽ

ኢትዮጵያን አዳኝ ዉይይቶችና እንቅስቃሴዎች ስናደርግ ፣
ዶ/ር  ተስፋዬ ደምመላሽTesfaye Demmelash
በኢትዮጵያ የፖለቲካ መደብና በምሁራን አጋሮቹ ዘንድ የአገር መታደግ ትግል “አማራጮች” ላይ ያተኮሩ የሚመስሉ፣ ግን አማራጮች የተባሉትን ጠጋ ብለዉ አይተዉና ተንትነዉ የጠራ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ሳይሆኑ ብዙዉን ጊዜ የሚያምታቱ አመለካከቶች በገፍ ይሰነዘራሉ። በመገናኛ ብዙሃንና ድረ ገጾች ያለማቋረጥ ይሰራጫሉ።
በዚህ አይነት ሂደት የኢትዮጵያ ነፃነት ትግል የሚይዘዉን መንገድ ወይም የገጠሙትን ዉስብስብ አገራዊ፣ አካባባዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች በሚመለከት በቅጡ የማይደማመጡና የማይገናዘቡ ስብጥር አስተያየቶች፣ ንግግሮችና እሰጥ አገባዎች በየፊናችን ከማዥጐድጐድ ቦዝነን አናዉቅም።
ሰሞኑን የትህዴን (የዴምህት) መሪ ሞላ አስገዶም በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹን ይዞ በሻቢያ ቁጥጥር ሥር በመቋቋም ላይ የነበረን ኢትዮጵያን “አዳኝ” የተባለ የጐሠኛ ጦረኞች “ትብብር” ባልተጠበቀ መንገድ ከድቶ ከኤርትራ መዉጣት በመሃላችን አነጋጋሪ የሆነዉ፣ እንዲሁም በወያኔ/ሻብያ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ክርክሮች ያስከተለዉ በዚሁ መልክ ነዉ።
በጠቅላላ ለመናገር፣ ኢትዮጵያን ከጐሠኛ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ነፃ የማዉጣት ዋና አላማ ላይ የግለሰቦችም ሆነ የስብስቦች ጅምላ ንግግሮችና ክርክሮች፣ እንዲሁም የድርጅቶች ጥቅል አቋሞችና እንቅስቃሴዎች እጥረት የለም። በመሠረቱ ጉድለት ወይም ድክመት ያለዉ የአገር ነፃነት ጥያቄዎችና ገዳዮች አነሳሳችን ላይ ነዉ፤ ተያይዞም በገዳዮቹ ዙሪያ የምናደርገዉን የአስተሳሰብ፣ የዉይይትና የእንቅስቃሴ ጥራት የሚመለከት ነዉ።
ዛሬም ሆነ ትናንት (በአብዮቱ ዘመን) የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ምሁራዊ ሊህቃን የአገር ገዳዮች አመለካከቶችንና ክርክሮችን፣ እንዲሁም ለችግሮች መፍትሔዎች ተብለዉ የቀረቡ የፖለቲካ አማራጮችን ብቁና ተገቢ ናቸዉ ወይም አይደሉም ብለን የምንበይነዉ ከሁለት የተያያዙ መመዘኛዎች አኳያ ነዉ።
አንዱ መስፍርት የጉዳዮችና ችግሮች አተያይ ወይም አቀራረጽ አገራዊ መንፈስና አነሳስ አለዉ ወይ የሚል ነዉ። እዚህ ላይ በዉይይትና በስምምነት መረጋገጥ የሚኖርበት ነገር በእዉንም ሆነ በምናብ የሚታዩ ችግሮች ከአገር ህልዉና፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት፣ ከአገራዊ ሉአላዊነት ዉጭ የሚቀረጹና የሚፈቱ አለመሆናቸዉ ነዉ።
የአገር ዉቃቢ የራቃቸዉ፣ አስልተዉም ሆነ ባለማስተዋል የኢትዮጵያን ህልዉና የሚጠናወቱ “ሥር ነቀል” ለዉጥ አራማጅ ነን ባይ ወገኖች ሁሉ ራሳቸዉን አገራዊ ሥር መሠረት የሚነሱና መጨረሻቸዉ የማያምር መሆኑ በተማሪዉ ንቅናቄ የተጀመረዉ የኢትዮጵያ አብዮት፣ በተለይ የኢሕአፓ ትግል፣ በደረሰበት አሳዛኝ ዉድቀት ያየነዉ ነገር ነዉ።
ዛሬም ከአነጋገርና ራስ ጠቀም ፖለቲካ ባሻገር በሃቅ ከአገር መንፈስ ጋር ያልታረቁ “አገር አዳኝ” ነን ባይ አገዛዞች የሚጠብቃቸዉ እጣ ፈንታም ይዋል ይደር እንጂ ያዉ ዉድቀት ነዉ። ኢትዮጵያ ግን ትቀጥላለች፤ ከህመሟ አገግማ መልሳ ጤናማ ለመሆን የሚያበቃት ጥልቅ ታሪካዊ መሠረትና እምቅ አቅም አላት።
ሌላዉ የፖለቲካ ምፍትሔዎች (የአማራጮች፣ የእምነቶች፣ የእንቅስቃሴዎች ፣ ወ.ዘ.ተ) መመዘኛ ደግሞ ጽንሰሃሳባዊ ጥራታቸዉ ወይም ይዘታቸዉ ብቻ ሳይሆን ከጠቅላላ ዓለም አቀፍ ትርጉማቸዉ ባሻገር ከብሔራዊ ማንነታችንና ባህላችን ጋር የመጣጣማቸዉ ወይም ያለመጣጣቸዉ ነገር ነዉ። የመፍትሔዎች አገራዊ ይዘትና አገባብ ጉዳዮች በሚገባ ተከራክረን ጽኑ ስምምነት ላይ ልንደርስባቸዉ የሚገባ ቁም ነገሮች ናቸዉ።
ለምሳሌ “ብሔራዊ እርቅ” በደቡብ አፍሪካ እንዲህ ስለተደረገ፣ በሌላ አገር እንዲያ ስለተሠራ እኛም አገር እንዲሁ አማራጭ ሊሆን ይቻላል ወይም አይቻልም ብለን ከመደምደማችን በፊት በሃሳብ ድረጃና በኢትዮጵያ አገባቡ ብሔራዊ እርቅ ምን ትርጉም እንዳለዉ (አለዉ ከተባለ) መገንዘብ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ “እርቁ“ (ከእርቁም በፊት ጠቡ) በማንና በማን ወይም በምንና በምን መካከል እንደሆነ ግልጽ ማድረግ ግድ ይላል።
ለመሆኑ “እንዲታረቁ” የምንፈልገዉ በጣም በመራራቅ ላይ ያሉ፣ በእዉን ወይም በእምቅ የሚጋጩ ጥቅሞች ያሏቸዉ ሃብታምና ሠርቶ ድሃ (ወይም ደህዪ) የኢትዮጵያ ህብረተሰብ መደቦች ናቸዉ? ወይስ በመሠረቱ ጠብ የሌላቸዉ፣ በተጨባጭ ችግሮቻቸዉና ጥቅሞቻቸዉ “አንድ ጀልባ ዉስጥ” ያሉ፣ የአገሪቱ ብዙሃን የባህልና የቋንቋ ማህበረሰቦች?
ይቅር መባባሉ በዜጐችና በብሔሮች ተብዬዎች መካከል ይሆን? እንዲሰፍን የምንፈልገዉ የፖለቲካ ወገኖች ወይም የጐሣ ሊህቃን ሰላም ነዉ? እርቅ ይዉረድ የምንለዉ በዘረኛ ፖለቲካዊ ብሔርተኝነትና በኢትዮጵያዊነት መካከል ይሆን? ወይስ ይቅር መባባሉ እነዚህን ሁሉ ያጠቃልላል? እንደነዝህ አይነት ተቺ ጥያቄዎች ከመጠየቅ ተቆጥበን በረቂቁ ወይም በድፍኑ “ብሔራዊ እርቅ” “ብሔራዊ እርቅ” ማለቱ የአገር ማዳን ትግሉን የትም አያደርሰዉም።
እንግዲህ ዋናዉ ችግራችን ከብሔራዊ እርቅ ጉዳይ ኋላ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ የአገር ማዳን ትግል አማራጮች ተብለዉ በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ተንቀሳሽ ወገኖችና ሚዲያ ለዉይይት ከሚነሱ ጉዳዮች ጀርባ ጉዳዮቹን አጣሪ ጥያቄዎች አናነሳም። የጠራ ግንዛቤ አስጨባጭ ጽንሰሃሳባዊ፣ ስልታዊና ተግባራዊ ትንተናዎች ከማዳበር ወደ ኋላ እንላለን።
ጉዳዮቹን ስናነሳ በድግግም በመባል የተለመዱ የፖለቲካ ቃላትን ማስተጋባት ያለፈ ተጨባጭና ተቺ አቀራረብ አስፈላጊነት እምብዛም አይታየንም፣ ቢታየንም እንኳን በስሌትም ይሁን በዘልማድ በዉይይቶቻችንና በእንቅስቃሴዎቻችን ምንም ያህል ቦታ ወይም ቀደምትነት አንሰጠዉም።
በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ነፃነት ትግል አማራጮች በመባል የሚያነጋግሩን ዋና ዋና ጉዳዮች ባመዛኙ የተድበሰበሱና የተምታቱ ናቸዉ። ለምሳሌ አንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅቶች ደጋፊ ምሁራን ስለሁለገብ ትግል አስፈላጊነት አጥብቀዉ ይከራከራሉ፤ ሆኖም ተከራካሪዎቹ የሁለገብ ንቅናቄ አንድ ዋና አካል የሆነዉ ሰላማዊ ትግል ገና ምኑም ሳይያዝና በቀጣይ ሂደት ሳይሞከር “አይሠራም፣ አልቆለታል” ይሉናል። እንዲህ ሲሉ አወቁትም አላወቁትም የሥነአመክንዮ ፈርጅ ስህተት እየሠሩ ነዉ፣ ምክንያቱም እንደ ጽንሰሃሳባዊ ፈርጅ “ሁለገብ ትግል” የግድ ሰላማዊ ንቅናቄን ያካትታልና።
ትጥቅ ትግልንም በሚመለከት የዛሬዉ ብቸኛ የተባለ “አማራጭ” የአብዮቱን ዘመን ፓራዳይም ወይም ትምሳሌ የተከተለ እንዳልሆነ ብንገነዘብም፣ ካለፈዉ አብዮታዊ ሞዴል ወይም አኪያሄድ እንዴትና ለምን እንደሚለይ መገመት ብንችልም፣ ልዩነቱ በቅጡ ተተንትኖ አለተገለጸም። ግልጽ እንዲሆን የሚፈለግም አይመስልም።
የትጥቅ ትግሉ ከኤርትራ አገዛዝ በሚያገኘዉ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን በዘር ፖለቲካ ክፍፍሉ፣ አወቃቀሩና ይዘቱ ከወያኔ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” የጐሣ ፓርቲዎች “ቅንጅት” አገዛዝ ጋር በመሠረቱ ተመሳሳይ እንደሆነ ብናይም ተመሳሳይነቱ በይፋ ሊረጋገጥ ወይም ሊካድ የሚችል አልሆነም። ነገር ግን ከጅምሩ መፈርከስ ቢደርስበትም፣ ትግርኛ ተናጋሪ ተዋጊዎች ዋና ተንቀሳቃሽ ሃይል የሆኑበትና በሻብያ የበላይ ተቆጣጣሪነት በጐሣ የተደራጁ ጦረኞች “የሚተባበሩበት” ንቅናቄ ለወያኔ ዘረኛ አገዛዝ “አማራጭ” ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እንደ አገር “አዳኝ” ነዉ የተባለ ነዉ።
የአገር ማዳኑ እቅድ እንግዲህ እንደነኝህ አይነት “አማራጮች” ወይም “መፍትሔዎች” ቀርበዉለት ምንስ ችግሮች መወጣት ይኖርበታል!? የኢትዮጵያ ነፃነት ታጋዮች እንደ ወያኔና እንደ ሻብያ ያሉ “ወዳጆች” ወይም ስልታዊና ታክቲካዊ ተባባሪዎች እያሏቸዉ ምን ጠላትስ አስፈለጋቸዉ ወይም አለባቸዉ!?
ግን ነገሩ እንዲህ ነዉ – በፉክክርና በጠብም ይሁን በተጨባጭ ትብብርና ስምምነት ሻቢያና ወያኔ ኢትዮጵያ ላይ አንድ አይነት የፖለቲካ እግር ኳስ እየተጫወቱ ነዉ። እንደ ተወዳዳሪነታቸዉ እርግጥ ሁለቱም ተጋጣሚ “ቡድኖች” ማሸነፍ ይፈልጋሉ። አንዱ (ሰሞኑን እንዳየነዉ ወያኔ) “ግብ” አስቆጣሪ ወይም አትራፊ ሌላዉ ለጊዜዉ ከሳሪ ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ተጋጣሚዎቹ የአጨዋወት ችሎታና ዘዴ ልዩነቶችም ይኖሯቸዉ ይሆናል።
ሆኖም ወያኔና ሻብያ ለየቅልም ሆነ በተወሰነ ጋርዮሽ ሊያስቆጥሩት የሚፈልጉት ዋና “ግብ” ኢትዮጵያ በግዛታዊ ሉአላዊነቷ፣ በሕዝቧ አንድነትና በብሔራዊ ህልዉናዋ ሳትጠናከር በጐሣ ክፍፍል ተዳክማ መቅረቷን ነዉ። ሁለቱም ፈላጭ ቆራጭ አገዛዞች አገሪቱ ተከፋፍላ መዳከሟን የዘረኛ ብሔርተኝነታቸዉ መጠናከር አድርገዉ በማየት “የዜሮ ድምር” ፖለቲካ ጨዋታ የሚጫወቱ ሃይሎች ናቸዉ።
የኢትዮጵያ እዉን ነፃነት ታጋይ ሃይሎች እነዚህን ተፎካካሪም ተባባሪም የብሔራዊ ዉጥረታችን አድራጊ ፈጣሪ አገዛዞች ለመቋቋም ዉይይቶች፣ እንቅስቃሴዎችና ድርድሮች ሲያደርጉ የፖለቲካ ክርክርና እንቅስቃሴ ባህላችእንን ራሱን አዙረዉ አይተዉ የሚለወጠዉን መለወጥ፣ የሚሻሻለዉን ማሻሻል የጐደለዉን መሙላት፣ የሌለዉን መፍጠር ያስፈልጋቸዋል። እዚህ ላይ የሚከናወኑ የለዉጥ፣ የእድሳትና የፈጠራ ሥራዎች በቀላሉ የሚገመቱ ሳይሆኑ የአገር መታደግ ትግሉ ወሳኝ አካልና አራማጅ ክንዉኖች ናቸዉ።

የፖለቲካ ክርክር ባህላችንን ውስንነቶች ለመወጣት

በተለይ በተማሪዉ ንቅናቄ ጊዜ ተጀምሮ በአብዮቱና በድህረ አብዮቱ ዘመን በአገራችን የተስፋፋዉ ተራማጅ የተባለ የፖለቲካ ንግግርና ክርክር ልምድ ሊዘረዘሩ የሚችሉ ብዙ ጉድለቶችና ድክመቶች አሉት። እዚህ በጥቅሉና ባጭሩ ሁለት ዋና ችግሮችን መጠቆም ይበቃል።

አንዱ መሠረታዊ የፖለቲካ ንግግርና ክርክር ልምዳችን ችግር ተራማጅ ከተባለ ፈላጭ ቆራጭ አስተሳሰብና አሠራር ጋር የነበረዉና ዛሬም በቅሪት ያለዉ የተንዛዛ ትስስር ነዉ። ማለትም፣ ልምዱ የዜጐችን፣ የማህበረሰቦችንና የምሁራንን ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና የሃሳቦች ልዉዉጥ በቀጣይነት ለሚያስተናግድ ነፃ ዉይይት ክፍት አለመሆኑ ነዉ።

እዝህ ላይ ማስተዋል ያለብን የዉይይት ክፍትነትና ነፃነት እጦት አይኑን ያፈጠጠ ጥርሱን ያገጠጠ የፖለቲካ ሃይል የፈጠረዉና በቀጣይነት የጫነብን ዉጨኛ ተጽእኖ ብቻ አይደለም። ወያኔ እዉስጣችንም፣ አይምሯችን ዉስጥ፣ መከላከያ ጣቢያዎች አሉት። ተጽእኖዉ ከወያኔ አገዛዝ ርቀንም ሆነ አገዛዙን እየተቃወምን በዘልማድም ይሁን መልሶ ባልታነጸ ተራማጅነት በምንናገረዉ፣ በከፊል ከአብዮታዊ ባህላችን በወረስነዉ የፖለቲካ ቋንቋ አጠቃቀማችን የሚከሰት ነዉ። ዉስጣዊዉ ተጽእኖ በተለይ የኢትዮጵያን አንድ አገርነትና አንድ ህዝብነት ተቃራኒ የሆነ ሽሽግ ትርጉም ባለዉ፣ በማያቆም ድግግም በመባል ብቻ ተለምዶ እንደ እዉነታ ገላጭ በተወሰደዉ አደንዛዥ የ“ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” ፖለቲካዊ አነጋገር ይገለጻል።

ይህ አነጋገር ርዝራዥ ስታልናዊ የርዩተዓለም ፈርጆችን ከማስተጋባት ባሻገር የኢትዮጵያን እውን የነገድና የባህል ማህበረሰቦች ተጨባጭ አካባቢያዊ ገዳዮች፣ ማንነቶች፣ አገራዊ ትስስሮችና ራስን በራስ አተያዮች ምንም ያህል እንደማይወክል ወይም እንደማያንጸባርቅ ለኢትዮጵያ ነፃነት ታጋይ ወገኖች፣ በተለይ ለአገር ወዳድ ምሁራንም፣ ስዉር አይደለም።

የሚገርመዉ ነገር ግን ተራማጅ ተብዬዉ አምባገነናዊ “የብሔሮች” ፖለቲካ ቋንቋ ከናካተታቸዉ ግግር ቀኖናዊ ሃሳቦች ለኢትዮጵያዊነትና ለአገሪቱ ዜጐች መብቶች መሠረታዊ ጠንቅ መሆኑ ቢታወቅም በአገሪቱ ምሁራን በቀጣይ ሥርዓታዊና ሂሳዊ መልክ ምንም ያህል ተፈትሾ፣ ተተንትኖና ተተችቶ አያዉቅም። እንዲያዉም የተማረዉ ክፍል አብዛኛዉን ጊዜ በአገር ጉዳዮች ላይ ሲነጋገር ክርክሮቹንና ዉይይቶቹን በዚሁ የፖለቲካ ሰዋሰዉና ቃላት እየቃኘ ነዉ። ይህን የምናደርግበት ዋና ምክንያት የወልጋዳ ተራማጅነት ልምዳችን ተጽእኖ ቢሆንም በከፊል የራሳችንን ምሁራዊ ስንፍና ወይም ጥግ ያዢነትና ተነሳሽነት እጦት የሚያሳይ ይመስለኛል።

ስለዚህ የአገሪቱ ነገደ ብዙ ምሁራን እስከዛሬ ድረስ ጠባብ የማንነት ፖለቲካን ከሥር መሠረቱ በጋራ ልንገመግም ምንም ያህል አልቻልንም ወይም አልሞከርንም። ለአማራጭ አተረጓጐሞች፣ ለሃሳቦች ልዉዉጥና ለድርድር ዝግ የሆኑ ጠባብ የማንነት ፖለቲካ ቃላትንና ፈርጆችን በተቺ ትንተናና ዉይይት ከመፈተሽና ከማወላለቅ ይልቅ ዝምብለን ስለ አገር ገዳዮች መነጋገሪያና መወያያ አድርገን የመቀብልና የማስተጋባት አዝማሚያ አለን።

ይህን አዝማሚያ ማቆም ለዛሬዉ የፖለቲካ ለዉጥና አገርን ከጥፋት የመታደግ ትግል የመጀመሪያ ወሳኝ እርምጃ ነዉ።
ምክንያቱም ያሉ የክርክር ቃላትን እንዲሁም በጠቅላላ አምባገነናዊና ብቸኛ የሆነ የዘረኝነት ቋንቋን ራሱን ሳይለዉጡ በኢትዮጵያ ሥርዓታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና አሠራር ለዉጥ ማምጣት ወይም ለህዝብ አማራጭ ማቅረብ አይቻልም።

ሌላዉ ዋና የፖለቲካ ንግግርና ዉይይት ባህላችን ውስንነት ድግሞ ሃሳቦችን ባንዳፍታ “ተግባራዊ” በምንለዉ ድርጅታዊ አቀራረብ የመጨበጥና የመጠቀም ሙከራችን ነዉ። ሃሳቦችን በአመዛኙ የተወሰኑ ስብስቦችን ወይም ድርጅቶችን ማንነቶች፣ ዓላማዎች፣ አቋሞችና እንቅስቃሴዎች መቅረጫና መቆጣጠሪያ ብቻ አድርጐ የማየት ልምድ ነዉ። ይህ ልምድ በመሠረቱ ከኢትዮጵያ ተማሪ ንቅናቄና አብዮት የወረስነዉ ቅርስ ነዉ።

እዚህ ላይ ግልጽ ማድረግ የምፈልገዉ ችግሩ ሃሳቦችን የትግል “መሣሪያ” ማድርጉ ራሱ አይደለም። እዉቀት ሃይል ነዉ እንዲሉ የፖለቲካ ሃሳብም የአገር አዳኝ ትግል ትጥቅ ሊሆን ይችላል፤ መሆንም አለበት። ጣጣዉ ያለዉ ሃሳቦችን መሣሪያ አደራረጋችን ላይ ነዉ። በፖለቲካ ትግል እርግጥ ከተወሰኑ ተልዕኮዎችና እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ ቀልጠፍጠፍ ያሉ ታክቲካዊ የሃሳብ አስተጣጠቆችና አፈጻጸሞች አሉ። በዚህ አገባብ የኢትዮጵያ ነፃነት ተዋጊዎች “ነፃነትን” ወይም “እኩልነትን” ከፍተኛ እሴት ሰጥተዉ ብቻ ሳይሆን የትግል ዘዴያቸዉና መሣሪያቸዉ አድርገዉ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ።

ይሁን እንጂ ሃሳቦች ተጠቃለዉ በሆኑ ድርጅቶች ወይም ታክቲኮችና እንቅስቃሴዎች አገልጋይነት የሚዋጡ አይደሉም። በመሠረቱና በዘላቂነት “መሣሪያ” የሚሆኑት በሃሳብነት አንጻራዊ ነፃነታቸዉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ማለትም ሰፊ ይዘታቸዉን ወይም ፍቻቸዉን እንደያዙ ነዉ። ዋናዉ መሣሪያነታቸዉ ሰፊና ጥልቅ ትርጉማቸዉ ራሱ እንጂ በዚህ ወይም በዚያ ወገን በሚደረግባቸዉ ትርፍ ጥምዘዛ አይደለም።

ለምሳሌ በኢትዮጵያ ራስ ጠቀም የ“ዲሞክራሲ” ጠምዛዣች (ጠባብ ፖለቲከኞች፣ ዘረኞች፣ ተለጣፊዎች ወ.ዘ.ተ) ስለበዙ ዲሞክራሲ በሰፊ ሃሳብነት ወይም መርህነት አገርና ህዝብ አገልጋይነቱ ቀርቶ የህዝብ የበላይ ጌታና ከፋፋይ የሆነ ሌላ አይነት የፖለቲካ መሣሪያ ሆኗል። ሰይፍን ቆልምመዉ ማጭድ ቢያደርጉት እንደ ሰይፍ መሥራቱ እንደሚቀር ማለት ነዉ። በወያኔ አምባገነናዊ አገዛዝ “አብዮታዊ” እና “ልማታዊ” የሚል ቅጽል የተሰጠዉ “ዲሞክራሲ” ከአስመሳይ የአነጋገር ልምድ ያለፈ ለአገዛዙም ሆነ ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ የሚሰጠዉ ምንም አንጻራዊ ነፃነት ያለዉ መርሃዊና ተቋማዊ አገልግሎት የለዉም።

በጠቅላላ ስናየዉ እንግዲህ የፖለቲካ ክርክርና እንቅስቃሴ ባህላችን ችግር የሃሳቦችን ሰፋና ጠለቅ ያሉ ይዘቶች ተወያይተን ለመጨበጥ ወይም በኢትዮጵያ እዉን አገባባቸዉን ለመገንዘብና ለማመቻቸት እምብዛም ሳንጨነቅ፣ በቀጥታ ከዓለም አቀፍ ረቂቅ ትርጉማቸዉ ወይም አባባላቸዉ ተነስተን፣ በተወሰኑ የስብስብ፣ የጐሣና የድርጅት ግቦችና እንቅስቃሴዎች አማካኝነት በአገራችን “ተግባራዊ” የማድረግ ሙከራችን ነዉ።

ሙከራዉ የሃሳቦችን የቃል በቃል ፍቺ ባማረ ንግግር ወይም በሽንገላ የማስተጋባት አቅም ቢኖረዉም በእዉን ትርጉም ይዘቱ በጣም ደካማ ነዉ። ምክንያቱም ይህን የተለመደ የአነጋገር፣ የዉይይትና የእንቅስቃሴ መንገድ ስንይዝ የፖለቲካ ሃሳቦችን ፍቺ በስፋትና በጥልቀት ለመጨበጥ የሚገፋፋን ማበረታቻ የለም።

እንዲያዉም አብዮታዊ የፖለቲካ ባህላችን በዚህ መልክ የሚያበረታታንና ሚያነሳሳን ሳይሆን አስተሳሰባችንን ባንዳፍታ በድርጅታዊ አጀንዳ የሚጠምድና የሚገድብ ነዉ። ይህ አኪያሄድ ደግሞ የፖለቲካ ሃሳባችንን በማጥራት ረገድም ሆነ ሃሳባችንን በቀጣይነት ሃቀኛ ተቋማዊና ተግባራዊ ይዘት ከመስጠት አኳያ ኪሳራ ያመጣብን መሆኑ የሚካድ አይደለም። ሁኔታችን ከሁለት ያጣ ጐመን ነዉ የሆነዉ።

በዛሬዉ የኢትዮጵያ ነፃነት ትግል ከዚህ ሁኔታ ለመላቀቅ የንግግር፣ የዉይይትና የተግባራዊ ጥረት ድርጃዎችን ወይም ረድፎችን ለይቶ ማስቀመጥ፣ ትስስራቸዉንም በሚገባ መገንዘብ ይጠቅማል። የትግል ምህዳሩ የሃሳብ፣ የመርህ፣ የስልትና የእንቅስቃሴ መስኮችን ያካትታል። በነዚህ የትግል መስኮች የሚደረጉ ጥረቶች በሁለት አንጻራዊ ልዩነት ያላቸዉ ግን የተያያዙ እርከኖች ሊታዩ የሚችሉ ናቸዉ።

በመጀመሪያ ደረጃ ሰፋና ጠለቅ ባለ አቀራረብ ስለ ነፃነት ትግሉ (ስለ ዋና ጉዳዮቹና ችግሮቹ፣ ስለ ዕድሎቹ፣ ስለ ሃሳቦቹና እሴቶቹ፣ ስለ አቀራረጹና አነሳሱ፣ ስለ አኪያሄዱ ስልት) መሠረታዊ እዉቀትንና ግንዛቤን ለማፍራትና ለኢትዮጵያ ህዝብ ተደራሽ ለማድረግ የምናኪያሂዳቸዉ ተጨባጭ ምርምር፣ ትንተናና ትችት ላይ ያተኮሩ ዉይይቶችና እንቅስቃሴዎች አሉ። በዚህ እርከን በቅንብር የሚደረግ ሰፊ ንቅናቄ የተወሰኑ ድርጅታዊ ወይም ወገንተኛ አጀንዳዎችን በቀጥታ የሚወክል ወይም በቀላሉ ደማምሮ የሚያካትት ሳይሆን የአገር አዳኝ ትግሉን በጠቅላላ በስልታዊ ራዕይ ያማከለ ነዉ የሚሆነዉ።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከተለዋዋጭ ወይም ከተወሰኑ አካባቢዎች ጉዳዮችና ሁኔታዎችና ጋር የተያያዙ፣ ብዙዉን ጊዜ ወቅታዊና ታክቲካዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ነፃነት ትግል ክርክሮችና ድርጊቶች፣ እንዲሁም ዜጐችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን ማነቃቂያ፣ ማግባቢያ፣ ማስተባበሪያና ማንቀሳቀሻ የሆኑ ንግግሮች፣ ዉይይቶችና ጥረቶች አሉ።

እነዚህ ሁለት የዉይይትና የእንቅስቃሴ ረድፎች ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ ናቸዉ፤ ግን ነባሩን የፖለቲካ ልምዳችንን ተከትለን እንዳናምታታቸዉ መጠንቀቅ አለብን። የመጀመሪያዉን ደረጃ አድበስብሰን ወደ ሁለተኛዉ እርከን ከቀነስነዉ ወይም ካወረድነዉ የነፃነት ትግሉን መሠረታዊ የሃሳቦች ትጥቅና መሣሪያ እንነሳዋለን።

ይህ ብቻ አይደለም። በሁለተኛዉ ደረጃ ልናኪያሂዳቸዉ የምንችል ታክቲካዊና ተግባራዊ ዉይይቶችን፣ እንቅስቃሴዎችን፣ ተልዕኮችንና ጥረቶችንም የሃሳብ፣ የአቅጣጫና የስልት ጥራት ምንጫቸዉን እንነፍጋቸዋለን። ይህ እንዳይሆን መጠንቀቅ ግድ ይላል። በቀጣይነት ፈታሽ ጥያቄዎች ማንሳትና በሚገባ መወያየት፣ መመካከር ያስፈልጋል።
የጥያቄዎች ማንሳት መሠረታዊነት

የኢትዮጵያን ነፃነት ትግል በሃሳብ፣ በስልትና በእዉን እንቅስቃሴ ወደ ፊት ለማራመድ የሚረዱ ፍሬያማ የሆኑ መደበኛ ዉይይቶች ለማኪያሄድ አስተዋይና ተቺ ጥያቄዎች በሥርዓት ማንሳቱ ከፍተኛ ቀደምትነት የሚሰጠዉ ነዉ። በማንኛዉም የትግሉ መስክና ደረጃ የጠቃሚ እዉቀትና ግንዛቤ ምንጭ የጥያቄዎችና መልሶች የማያቋርጥ ዳያሌክቲክ ወይም መወላለድና መከፋፈት ነዉ።

ስለ አንድ ሃሳብ ወይም የአገር ጉዳይ ወይም ስለ ሆነ የትግል ስልት ይበልጥ ስናዉቅ፣ ስለ ሃሳቡና አፈጸሙ ይበልጥ ጥያቄዎች ማንሳት እንችላለን። በዚህ አይነት ቀጣይ የጥያቄዎችና መልሶች ዉልልድ የአገር ማዳንና ማጠናከር እዉቀታችንን ያለማቋረት እንገነባለን፣ እናዳብራለን። እንግዲህ ስለ ማንኛዉም ነገር ጥያቄ የምናቀርበዉ ሁልጊዜ ከድንቁርና ወይም የሆነ ነገር ካለማወቅ ሳይሆን ከእዉቀትም ተነስተን ነዉ ማለት ነዉ።

ግን ጥያቄ አነሳሳችን ወሳኝ ነዉ። ጥያቄዎች ብዙዉን ጊዜ በቅድሚያ ዝግጁ የሆኑ መልሶች አዉጪ ወይም አፍሪ ሳይሆኑ ለመልሶች ጥራትና ብቁ አቀራረብ አስተዋጽዎ ሊኖራቸዉ ወይም ላይኖራቸዉ ይችላል። አነሳሳቸዉ ለአገር ነፃ አዉጪዉ ትግል የሚበጅ ወይም የማይበጅ ሊሆን ይችላል።

በበጐ አነሳሳቸዉ ለሃሳብ፣ ለዉይይትና ለትብብር እንቅስቃሴ የጠበቡ የትግል ዕድሎችን፣ መንገዶችንና ሁኔታዎችን ማስፋት፣ የተድበሰበሱ ወይም የጨላለሙ የአገርና የአካባቢ ጉዳዮችን መገላለጥና ብሩህ ማድረግ ያስችሉናል። በዚህ መልክ አገራችንን ከጥፋት ለማዳን የምናደርገዉን ንቅናቄ በማጠናከር ይረዱናል።

ጐጂ ጐናቸዉን ብዙ ትንተና ዉስጥ ሳንገባ በተማሪዉ ንቅናቄ ተነስቶ በአብዮቱ ዘመን በተስፋፋዉ፣ አገራዊ መንፈስ በራቀዉና የፖለቲአ አስተዉሎ በጐደለዉ የኢትዮጵያ ጉዳዮች አነሳስና አቀራረጽ ልምድ በግልጽ ማየት እንችላለን።

እዚህ ላይ “የብሔሮች ጥያቄ” የተባለዉ ጉዳይ ዋና ምሳሌ ነዉ። ይህ “ጥያቄ” ከጽንሱ ራሱ ተወዛግቦ አገር አወዛጋቢ የሆነ ነዉ። አቀራረጹና ከተማሪዉ ንቅናቄ ጊዜ ጀምሮ ያስከተላቸዉ ክርክሮች የወገንተኝነትን ሙቀት ከፍ ከማድረግ በቀር የፖለቲካ ብርሃን ምንም ያህል እንዳላፈለቁ የምናዉቀዉ ነገር ነዉ።

እንዲሁም ጥያቄዉ በመንፈሱና በአነሳሱ ህዝብ ከፋፋይ የጐሣ ሊህቃን ጠቦች የጫረ፣ አገር ለብላቢ የዘረኝነት እሳት የለኮሰ ነዉ። ከጽንሱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ህልዉና የራቀ ብቻ ሳይሆኑ የተጠናወተ እንደነበር ከብዘዎቻችን ስዉር አይደለም። ዛሬም በተቀናቃኝ የገዢና የተቃዋሚ የማንነት ፖለቲካ ቅሪቶቹ ይከሰታል። በተለይ በወያኔ አገዛዝ አገር ከፋፋይና አሰናካይ ዘረኛ አወቃቀር በግልጽ ይታያል።

ከዚህ ምሳሌ የምንጨብጠዉ ጠቅላላ ግንዛቤ የኢትዮጵያን ጉዳዮችና ጥያቄዎች አነሳስ ልምዳችን አካቶ የአገርን አድማስ የለቀቀ ሊሆን እንደሚችልና እንደሆነ፣ ለህዝብ ነፃ ሰሚነትና ተቀባይነት ወይም መልስ ሰጪነትና ተወያይነትም ምንም ያህል ቦታ እንደሌለዉ ነዉ። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጉዳዮች አቀራረባችን ባህል ራሳችንን (እንደ ፖለቲከኞች፣ እንደ ምሁራን ወ.ዘ.ተ) የጠያቂም የመላሽም፣ የአድራጊም የፈጣሪም የበላይነት ሰጥቶ አገርና ህዝብ ጨቋኝ ሊያደርገን እንደሚችል ነዉ።

የዚህን የፖለቲካ ጥያቄዎች አነሳስ ልምድና አብሮት የሚሄድ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ክርክርና እንቅስቃሴ ባህል መሠረታዊ ብልሽት በሚገባ መረዳት ማለት እንግዲህ ዛሬ ለምናደርገዉ ኢትዮጵያን ከጥፋት የመታደግና ነፃ የማዉጣት ንቅናቄ ወሳኝ ግንዛቤ መጨበጥ ማለት ነዉ።

ለማጠቃለል፣ በአገር ነፃነት ትግሉ ጥሩ፣ ዉጤታማ ዉይይቶችና እንቅስቃሴዎች ዝምብለዉ በግብታዊ መንገድ የሚፈጠሩ አይደሉም። ነፃ የሆኑ ግን ለትግሉ አላማ የማያወላዉል ቃል ግባት ያላቸዉና የትግሉን አቅጣጫ የጠበቁ ብርቱ አይምሯዊና ተግባራዊ ጥረቶች ይጠይቃሉ። የሥርዓታዊ ቅንብርና አመራር ዉጤቶች ናቸዉ።

ፈታሽ፣ ባንዴ ሂሳዊም ገንቢም የሆኑ ጥያቄዎች በቀጣይነት የማንሳት ችሎታችን ደግሞ ጥራት ላላቸዉና አቅጣጫቸዉን ለጠበቁ አገር ነፃ አዉጪ ዉይይቶችና እንቅስቃሴዎች ወሳኝ አስተዋጽዎ አለዉ። ችሎታዉ በተለያዩ ደረጃዎችና ሁኔታዎች የሚኪያሄዱ የአገር ማዳን ትግል ጥረቶችን ተገናዛቢ፣ ተመጋጋቢና ተጠነካካሪ ለማድረግ ይረዳል።

ጥያቄዎችን ቀደምትነት የሰጡና መሠረታዊ ያደረጉ የዕዉቂያ ስሜቶች፣ ፍላጐቶችና ድርጊቶች ዝምብለዉ ተፈጥሯዊ ስጦታዎች ወይም በጠባቡ አካዳሚያዊና ምሁራዊ አዝማሚያዎች አይደሉም። በተለያዩ የኑሮ፣ የሥራ፣ የልምድና የትግል ሁኔታዎች በትብብር ኮትኩተን ልናዳብራቸዉ የምንችል የአይምሮ ንቃት፣ ተነሳሽነትና ተንቀሳቃሽነት መገለጫዎች ናቸዉ።

tdemmellash@comcast.net

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.