0

አንድ ነው ደማችን ( ሄኖክ የሺጥላ )

አንድ ነው ደማችን ( ሄኖክ የሺጥላ )

በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ብዙ ሰብከናል ፣ ኢትዮጵያዊነት የምናምንበት የጋራ ቤታችን ነው ። ከምንም ነገር በላይ ዛሬም ዋጋ የምሰጠው ስለ ኢትዮጵያዊነቴ ነው ። ግን ግን ዋጋ ለመስጠትም ሆነ ዋጋ ለመቀበል በመጀመሪያ እኔ መኖር አለብኝ ፣ የመፈጠሬ ምክንያት የሆኑት ሰዎች ሳይኖሩ ፣ ማንነት የምለው ኢትዮጵያዊነት ሊኖር አይችልም ። ለሌሎች ሊኖር ይችላል ። እኔን ላጠፉት ፣ በዘር ፖለቲካ ፣ በለጠፉብኝ የጨቋኝነት ታርጋ ፣ ማንነቴን ላወደሙ ፣ ለነሱ ፣ ኢትዮጵያዊነት ከኔ ወዲያ ሊኖርላቸው ይችላል ። ለምሳሌ ዛሬ ኢትዮጵያ የማን ነች ? እኔ አለሁ ወይ ? የሌለሁት ኢትዮጵያዊነቴን ስለምጠላ እና ስለምጠየፍ ነውን ? እኔ ከነሱ ያነሰ ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ ነውን ? አይደለም ። እኔ የሌለሁት አማራ ስለሆንኩ ነው ። እኔ ሳልኖር ስለምትኖር ኢትዮጵያ ፣ ልጆቼ ሳይኖሩ ፣ ዘመዶቼ ሳይኖሩ ፣ ወገኖቼ ሳይኖሩባት ስለምትኖር ኢትዮጵያ ማሰብ የሚችል አእምሮ የለኝም ። የጋራ ቤታችን ነው ስንል ፣ በጋራ እስከኖርንበት ብቻ ነው ። ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር ስንል ፣ በአርፍተ ነገር ላይ ብቻ ሕልውናው የተመሰረተ ሀገር በምናብ መገንባትም አይደለም ። የኔ ስል ፣ እኔም የዛ አካል መሆኔን የሚያሳይ ፣ ከዛች ሀገር ላይ የሚገኘው ማንኛውም ጥቅምም ሆነ ፣ የዛች ሀገር ማንኛውም መከራ ተካፍይ መሆን መቻል ነው ።Henok Yeshitela url

ለመሆኑ አማራ ነኝ የሚለው ነገር እንዲህ የሚያስፈራን ለምንድን ነው ? ኮምፒውተር እንኳ ሲሰራ ( ኢንተል ኢንሳይድ ) ይላል ። ይህ አባባል ቁሱን ወይም ነገሩን ኮምፒውተር ከመሆን አያግደውም ። አማራ መሆኔ ኢትዮጵያዊ እናዳልሆን ያረገኛል እንዴ ? እንግዲህ በደንብ እወቁት አማራ ነኝ ። በእስክስታ ያደኩኝ ፣ ጎራው ና የሚለውን እየዘመርኩ ከልጅነት ወደ ወጣትነት የገሰገስኩኝ ። አዎ አማራ ነኝ ፣ የምኮራበት ታሪክ እና ባህል ያለኝ ፣ የጀግና አባቶች ልጅ ። አማራ ነኝ ፣ በጣልያን ቀንበር ስር ሲማቅቁ የነበሩ ባንዳዎችን ሳይቀር የታደኩኝ ፣ በመቅደላ ላይ በአልበገርም ባይነት ፣ ላገሬ በክብር የሞትኩኝ ፣ አርሼ የምበላ ፣ ፈትዬ ሸማ የምሰራ ፣ የቅኔ ቤቱ ባላባት ፣ የዜማ የድጏ መሰረት ፣ የነ ዘራያቆብ ፣ የነ ዳዊት ፣ የነ ሱስንዮስ ፣ የነ ፋሲል ፣ የነ ላሊበላ መፈጠሪያ ለኔም መፈጠሪያ የሆነ ፣ አማራ ነኝ ፣ እኔም መቅኒ መበጠስ ፣ መሃል አገዳ መለየት አሳምሬ የማውቅ ።

አማራ መሆን ያሳፍርም ፣ አማራ ነኝ ማለትም አያሳፍርም ። ይልቅስ እጅግ የሚያሳፍረው ፣ አማራን ከሚያጠፉት ጋ ተሰልፎ ስለ ኢትዮጵያዊነት ማውራት ፣ ይልቅስ እጅግ የሚያሳፍረው ፣ ላለመጥብ እና ላለማነስ በሚል ሰበብ ፣ ወገን ሲገደል ፣ ወገን ሲበደል ፣ ወገን ሲራብ ፣ << ተው አማራ አትበሉ >> እያሉ መኖር ። እሱ ያሳፍራል ፣ ያናዳል ፣ ጥርስ ያስነክሳል ።

ለምሳሌ ፣ በህወሓት ዘመን ብዙ የአማራ ብሔር ተወላጆች ፣ እየታሰሩ ፣ እየተፈናቀሉ ፣ እየተሰደዱ ያሉት ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ነውን ? እነማን ናቸው ሃጋሪቷን ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ በአሁኑ ሰዓት ተቆጣጥረዋት ያሉት ? እነ ማን ናቸው ዛሬ በማዕከላዊ እየተሰቃዩ ያሉት ? የነማን ልጆች ናቸው በየመን ጦርነት ጊዜ ፣ በፍጥነት ከየመን እንዲወጡ የተደረጉት ?

አማራ ነኝ ማለት አያሳፍረኝም ፣ ምክንያቱም አማራ የሚያሳፍር ታሪክ ስለሌለው ፣ አማራ ነኝ ማለት ግራና ቀኝ እንዳስብ አይደርገኝም ፣ ምክንያቱም የሆንኩትን ነገር ነውና ። አሁን እየገባኝ የመጣው ፣ አማራ ነኝ ስል ፣ የደም ግፊታቸው የሚነሳ እንደበዙ ነው ። አማራ መሆኔ እኮ ኢትዮጵያዊ መሆኔን እንደ ሌሎቹ አያስክደኝም ። ወይስ አማራ እየጠፋ ፣ እየተሰደደ ፣ እየተገደለ ፣ ለማይገባቸው ሰዎች ስለ አንድነት ልስበክ ? በወገኖቼ ስቃይ ላይ ፣ አዳራሽ ሕዝብ ሰብስቤ ልጨማለቅ ? ይበቃል ! አማራነቴን ሳትቀበሉ ፣ ኢትዮጵያውነቴን እንድትቀበሉሉኝ አልፈልግም ።
እንዲህ በዘር እና በጎሳ በሽታ የጦዘች ሀገር ፣ እንዲህ በጥላቻ መርዝ የተለከፈች እና የተበከለች ሀገር ፣ ስለ አንድነት መስበክ መጫወቻ መሆን የገባኝ ቆይቶ ነው ። መጀምሪያ ስለ እኔ መኖር ፣ እርግጠኛ መሆን እፈልጋለሁ ። ስለ ኢትዮጵያዊነት ስናገር ደስ ይላቸው የነበሩ ፣ ስለ አማራ ሳወራ የሚቀፋቸው እና የሚከፋቸው ፣ በኢትዮጵያዊነቴ እና በአማራነቴ መሃከል የአስተሳሰብ እና የሀገር ፍቅር ልዩነት ስላዩ ሳይሆን ፣ እነሱ ማጥፋት ለሚያስቡት አማራ ፣ ይሄኛው አካሄደ ህልማቸው ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ስለሚደፋበት እንጂ !

ለምሳሌ የትግራይ ነጻ አውጪ የሚባል ቡድን አለ ፣ አንደኛው አዲስ አበባ ፣ ሌላኛው ደሞ ኤርትራ ። ሁለቱም አላማቸው ትግራይን ነጻ ማውጣት ነው ። በዚህ ላይ ምንም ቀወሜታ የለኝም ። የራሳቸው ጉዳይ ነው ! ግን የነሱ ነጻነት የሚመጣው አማራን በማጥፋት ፣ አማራን በመጨቆን እንዳይሆን ፣ ስለ አማራው እቆማለሁ ፣ እሞታለሁ ፣ ማንኛውንም አይነት መስዋት እከፍላለሁ ። እንደውም አንዳንድ መጻጉ አማራ ነኝ ባይ ሙሁራን ችግር የሚመስለኝ ( የወለደውን ልጅ ሳያሳድግ ፣ ህጻናት ማሳደጊያ ከፍቶ ልጆች ማሳደግ እንደሚፈልግ አይነት ሰው ስለሚመስ ለኝ ነው )። ስለ አማራነቱ እርግጠኛ ሳይሆን ፣ ስለ ኢትዮጵያዊነቱ ማውራት የሚወድ ሕዝብ አማራ ነው ። ያ ሕዝብ መንቃት አለበት ። በይበልጥ << የአማራው ጠላቱ ራሱ አማራው ነው >> የሚለው አባባል ምክንያታዊነት እጅግ ግልጽ ብሎ በሚታይበት ዛሬ !

ስለዚህ አማራ ነኝ ። እነ ጃዋር ሜንጫ ሲስሉ ፣ በአንድነት ስም መታረጃ ሞረዴን የማቀብል አማራ አይደለሁም ፣ ይልቅ እኔን ለማጥፋት ከሆነ ፣ የራሱን ሜንጫ እራሱ አንገት ላይ መሰካት የምችል አማራ እንጂ ! አማራነት በደሜ ውስጥ አለ ። ማንነቴን አክብረው ፣ ለሚኖሩ ከማንም የማላንስ ኢትዮጵያዊ ነኝ ። ማንነቴን ማክበር ላቃታቸው ፣ እኔን ለማጥፋት ቀን ከሌት ሳይተኙ ለሚያድሩት ግን እኔም የማልተኛ አማራ ነኝ ።
ፍርሃት አያውቀኝም ። ልምምጥ አልችልበትም ። ይሉኝታ ፣ የኔ ባህል መሆን ማቆብ እንዳለበት ገብቶኛል ። ለመኖር የምችለው ፣ በሁለት እግሮቼ እኔ ለራሴ መቆም ስችል ነው ። በደካማ እና ተገን አልባ አማሮች የተገነባች ኢትዮጵያን ማየት አልሻም ! ይህ ማንነቴ ነው ። እንዳልናገር የምትፈልጉትን ሁሉ ስለኔ ማንነት ከሆነ ፣ እናገራለሁ ። ኢትዮጵያዊ ነኝ ፣ በዛ ላይ ደሞ የአማራ ልጅ ነኝ ። አንድ ነው ደማችን ለዘፈን እና ዜማ ፈላጊዎች ብቻ እንዳይሆን ፣ መጀመሪያ እኔነቴን ተቀበሉ !

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.