0

ይቅርታ እጠይቃለሁ ( ሄኖክ የሺጥላ )

ይቅርታ እጠይቃለሁ ( ሄኖክ የሺጥላ )

ሰሞኑን ስለ አማራ እና አማራ ብዙ እና ተከታታይ ጽሑፎቹን ጽፌያለሁ ። ወደፊትም ገና እጽፋለሁ ። እንኳን ስለ አማራ ፣ ሰው ብሎለት ስለ ህውሃት ጅግንነት ይጽፍ የለም እንዴ ? ሚኒሊክ ጡት ቆረጠ ብሎ ሃውልት ይሰራ የለም እንዴ ? በሜንጫ ነው የምንላችው ብሎ በአደባባይ ይናገር የለም እንዴ ? የኢትዮጵያ ታሪክ የአማራ ታሪክ ነው ይል የለ እንዴ ? አይልም እንዴ ?

እንደውም አንድ ጨዋታ ላጫውታችሁ ። ኦቦ በቀለ ገርባ ሰሞኑን አማሪካን ሀገር መጥተው ፎቶ ሊነሱ ሲሉ ፣ ከጀርባም የኢትዮጵያ ባንዲራ ( እንደ የጀርባ መሰረት ) ( ባክ-ግራውንድ ) ሊገባ መሆኑን የተረዱት ኦቦ በቀለ ገርባ ፣ << አይ እኔ ከዚህ ባንዲራ አጠገብ ፎቶ አልነሳም !>> አሉ አሉ ። እንግዲህ ፣ ሰው ተምሮ ፣ ተምሮ ፣ ተምሮ ፣ ተምሮ ( እደግመዋለሁ ፣ ተምሮ ተምሮ ) ፣ እንደዚህ እንደሚያስብስ አስባችሁ ታውቁ ይሆን ? በጣም የገረመኝ ደሞ ፣ እኝህ “ትልቅ ሰው ” ( በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ነው ) ሲታሰሩ፣ እኔን ጨምሮ ፣ ለሳቸው ያልጻፈ ፣ ያልተናገረ ፣ ይኖራል ? ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረ ማሪያም ፣ እስከ ታማኝ በየነ እና ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ መስፍን ወልደ ማርያም እና ወዘተ ።

እና እኔ ስለ አማራ ሥጽፍ ፣ እንደው እመር ብዬ ፣ አማራን የማንገስ ወይም የማሞካሸት አዚም እና አባዜ ይዞኝ ሳይሆን ፣ የምትጠሉት አማራ ፣ እናንተ ሀገሬ ብላችሁ ለምትሏት ሀገር ፣ ከፍተኛ መስዋትነት የከፈለ መሆኑን አትዘንጉት ለማለት ነው ። ሥጽፍ እና ስናገር ፣ አበክሬ ማመልከት የፈለኩት ፣ ዝም ማለት እና ኢትዮጵያ እና ስለ ኢትዮጵያ ብቻ ማውራት ፣ አማራ አለመሆን አይደለም ። <<በፍቅር እና በአንድነት እናምናለን ፣ ግን ይህንን መረዳት ካቃታችሁ ፣ የህልውና ጉዳይ ነውና እኛም ከፈለግን እንደ እናንተ ማሰብም እንችላለን! >> የሚለውን እንድታውቁት ነው ።

ለምሳሌ በቅርቡ ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ << የአማራ ተወላጆች >> ደን ጨፍጫፊዎች ፣ ያለ ሀገራችሁ የመጣችሁ እና-ወዘተ ተብለው መፈናቀላቸውን ሰምተናል ፣ ይህ ጉዳይ የአማራ ጉዳይ ብቻ እስኪመስል ሌላው ዘር ጉዳዩን << ዝም ብሎ >> ለመመልከት ከፈቀደ ፣ እስከሚገባኝ አማራ ቢጮህ ፣ እንደ አማራ ቢጽፍ እና ቢናገር ስህተት አለውን ? እየጠየኩ አይደለም !!!

ለምሳሌ የኔን ጽሑፍ ስታብጠለጥሉት ወይም ስትኮንኑት የነበራችሁ ሰዎች ፣ ከጽሑፌ ውስጥ ሌላውን ዘር ስለማጥፋት የሚሰብክ ፣ ሌላውን ዘር ስለማፈናቀል የሚሰብክ ፣ አማራ በኦሮሞ ላይ ይነሳ ዘንድ የሚሰብክ አንዲት ሐረግ መዞ ማውጣት ከቻላችሁ ፣ በአደባባይ ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነኝ ።Henok Yeshitela url

ህወሃትን በተመለከተ ፣ የህወሓት ደጀን ሆኖ ይህንን አምባገነናዊ ስርዓት እየደገፈ ያለው በአብላጫው የትግራይ ሕዝብ ነው ። ይሄ አይደለም የምትሉ ከሆነ መረጃ አቅርቡ ። በአመክኖዊ መንገድ ሃሳባችሁን አስረዱ ። አማራ ከኦሮሚያ ሲፈናቀል ፣ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ይህ ነገር አግባብ አይደልም ብለዋል ወይ ? ካሉ መረጃ እና ማስረጃ አቅርቡ ። አሁንም ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነኝ ።

ህወሓት አማራንና ሌላውን ዘር የሚጠላበት ስብእና አንድ አይደልም ። ለአማራ ያለው ጥላቻ በደሙ ውስጥ የሰረጸ ነው ። የስልጣን ብቻም አይደለም ። ሁሉም አማራ የህውሃት ደጋፊ ቢሆን እንኳ ፣ ህውሃት አማራን ከማጥፋት ወደ ሗላ አይልም ። ከሌሎቹ ጋ ያለው ጠብ ግን እኔ የምለውን ስሙ ፣ እኔን ተከተሉ የሚል ነው ። ካማራ ጋ ያለው ሰብ ግን ፣ የዘር ማጥፋት ሰብ ነው ! ይህ አይደልም የምትሉ ካላችሁ ሃሳባችሁን ልስማ ። ከተሳሳትኩ ፣ ይቅርታ መጠየቅ የሚያሳፍረኝ ሰው አይደለሁም ።

ስለ አማራ ሲጻፍ ፣ ህውሃት ብቻ ሳይሆን ፣ በህውሃት እየተጨቆነ ያለም ሌላ ዘር የሚቆጨው ለምንድን ነው ? አማራ ሲባል እንዲህ የሚያንዘፈዝፈን ምክንያቱ ምንድን ነው ? ፍርሃት ! ከመጠን ያለፈ ፍርሃት ። ከመጠን ያለፈ ፣ በልብ ወለድ ላይ መሰረት ያደረገ ጥላቻ ።
እንግዲህ እንድታውቁት የምፈልገው ፣ ስለ ኢትዮጵያዊነቴ ዛሬም ነገም ፣ እሰብካለሁ ። የማምንበትም ምንነቴ ነው፣ ማንነቴ ነው ፣ የማልፍቀው ፣ በክልል ባንዲራ የማልቀይረው ። ሳልፈልግ ተገድጄም ቢሆን ማነስ አልችልም ፣ አንደኛ ኢትዮጵያዊ ነኝ ፣ በዛ ላይ ደሞ አማራ ነኝ ( ይሰማል ወይ ?) ። ታዲያ ያ ማለት ፣ አንድን ትልቅ ዘር ለማጥፋት የሚያደቡ በብዙበት ጊዜ ፣ << ከተንኮለኛ ጋ ተንኮለኛ ፣ ከቅን ጋ ቅን ትሆናለህ >> እንዳለው ዳዊት ፣ እንደዚያ መሆን የግድ ነው ። ኢትዮጵያውነቴን ስለምወድ ፣ አማራ ሲጠፋ ፣ ከኢትዮጵያውነቴ ስለሚያሳንሰኝ ስለ አማራ አላወራም እንድል ይሆን የፈለጋችሁት ? እንደውም ስለ አማራ መጻፌ ፣ መናገሬ ፣ ስለ አማራ መቆጨቴ ፣ የኢትዮጵያውነቴ ተምሳሌት ነው ። ይህ ሊሆን የማይችለው አማራ ኢትዮጵያዊ አይደልም ብሎ ማሳምን ለሚፈልግ ሰው ብቻ ነው ። እሱ ደሞ በጣም ፣ በጣም ከባድ ነገር ስልሆነ ባትሞክሩት እመክራለሁ ።

ጆን እንዲህ ያለው ትዝ አለኝ
No man is an island,
Entire of itself,
Every man is a piece of the continent,
A part of the main.
If a clod be washed away by the sea,
Europe is the less.
As well as if a promontory were.
As well as if a manor of thy friend’s
Or of thine own were:
Any man’s death diminishes me,
Because I am involved in mankind,
And therefore never send to know for whom the bell tolls;
It tolls for thee.

የማንም ሰው ሞት ያሳንሰኛል ። ስለዚህ ስለ አማራ ፣ በናንተ የዘር ክፍፍል መሰረት ፣ አባቶቼ አጥንታቸውን ከቀበሩበት አፈር ስለተገኙት ፣ በልጅነቴ የመንዝ ጭብጦ ይዘው መጥተው ስለጠየቁኝ ቅን ገበሬዎች ስል ዝም አልልም ፣ ስለ ከለለኝ የጎንደር ገበሬ ስል ዝም አልልም ፣ በጠኑ በቆሎ እና ጤፍ ሸክፎ ስላበላኝ ጎጃሜ አባቴ ስል ዝም አልልም ፣ ስለ ወሎ ሕዝብ ፍቅር ብዙ ስለነገረችን አያቴ ስል ዝም አልልም ! ወደድክም ጠላህም !

አንድ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ፣ ወይም በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ኦሮሞ ፣ ስለ ኦሮሞ ህዝቦች በደል ቢጽፍ ስህተት ነው ብዬ አላስብም ። ምክንያቱም በኢትዮጵያዊነቱ እስካመነ ድረስ ፣ በኢትዮጵያ ዙሪያ ስላለው መንፈስ ያለው ግንዛቤ ወደ ዘር መጥፋት የሚመራው ስላልሆነ ፣ ስለ በደሉ ሲናገር ፣ ምክንያቱ መፍትሄ ፍለጋ ይሆናል እንጂ ፣ የዘር ማጥፋት ራእይ አይሆንምና ። አንድ በኢትዮጵያዊነቱ የማያምን ኦሮሞ ፣ ተበድያለሁ ሲል ግን አልሰማውም ። ምክንያቱም በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ውስጥ ያለውን የጋራ መግባባት ፣ የአንድነት ስሜት ፣ የአብሮ መኖር ስሜት ስለማይቀበል ፣ ለሱ እና እወክለዋለው ላለው ብሄሩ ብቻ የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ፣ እራሱን ወይም ብሄሩን በጉልበት እና በኢኮኖሚ የዳበረ ለማድረግ ፣ ሌሎቹን ሙሉ በሙሉ እስከማጥፋት ሊያስብ ይችላልና ። ይህንን በህወሀት እያየነው ነው ። ይህ የኔ ሀገር አይደለም የሚል ክልላም መንፈስ ፣ ባለሃገሩን ማፈናቀል ፣ ማሳደድ ፣ መግደል እና መጨቆን ሁነኛ ባህሪው ነውና ። እና እኔም ስለ አማራ ስጽፍ ፣ እነዚህ በኢትዮጵያዊነታቸው የማያምኑ ፣ ዘመነኛ ሀገረኞች እያደረሱበት ያለውን በደል ከመረዳት እና ከመቆርቆርም ጭምር ነው !

መቆርቆሬ የሚቀፋችሁ ፣ የሚከፋችሁ ካላችሁ ፣ ደግሞ ደጋግሞ ይከርፋችሁ እንጂ ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ለሚያምን ማንኛውም አካል ፣ እቆረቆራለሁ ! ስለዚህም ላማራም !

ቸር እንሰንብት

Filed in: Amharic News, eMedia, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.