0

የግራው ትውልድ ኢትዮጵያዊነትን ቦርቡሮ ለማጥፋት በውጭ ጠላቶቻችን የርእዮተ አለም ቤተ ሙከራ ተፈብርኮ በመሃላችን የተነዛ ጸረ ማንነት ቫይረስ ነው ። ክፍል አንድ:

አሩሲ ነገሌ: ከሰሞኑ ሻቢያ በቅጥረኞቹ በኩል “በአማራ ስም የተደራጁ ቡድኖች የትግል አጀንዳ ተገንጣይነት ነው” በማለት ሽብር በመንዛት ላይ ይገኛል (ይህ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሻቢያ ኤርትራ ውስጥ በአማራው ስም ያቋቋማቸውን ቅጥረኛ ድርጅቶችን ግን አይጨምርም):: የሻቢያ ቅጥረኞች ይህን እጅግ አስገራሚ ለህዝባችን ብሎም ለሚዲያው እንግዳ የሆነ የቅጥፈት ውንጀላቸውን ተዓማኒነት ለማላበስ በተለያዩ የማህበራዊ ድህረገጾች አማራው በሚያካሂደው ትግል ውስጥ “መገንጠልን” እንደ ቀዳሚ ወይም ሁለተኛ አማራጭ መፍትሄ መያዝ እንደሚገባው እየደረሰበት ያለውን የጎሳ ጽዳትና የዘር ማጥፋት ጥቃት እያወሱ ተቆርቋሪ በመምሰል የሚለቀልቁ ግለሰቦችን በስፋት አሰማርተው መልሰው ደግሞ ለዚህ የጸረ አማራ ውንጀላቸው በማስረጃነት እየጠቃቀሷቸው ይገኛሉ:: ይህን መሰሉ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሻቢያ በቅጥረኝነት ያደራጃቸው ቡድኖች ብቸኛ ህዝባዊ ተሰሚነትን ያለተቀናቃኝ እንዲያገኙ በማስቻል በአማራነት የተደራጁትን ጨምሮ በሃቀኛ የአንድነት ሃይሎች ላይ የበላይነትን እንዲቀዳጁ የተወጠኑ ሻቢያ የአማራውን ነገድ ማንሰራራት ለመከላከል ያስችለኛል ብሎ ከሸረባቸው የቆዩና የተለመዱ የማዳከሚያ “እስትራቴጂዎች” ውስጥ አንዱ ነው:: ጸረ አማራ ሃይሎች አማራውን በጽኑ ኢትዮጵያዊ ስሜቱ ምክንያት ለብዙ ዘመናት የጥቃት ኢላማ አድርገውት የቆዩ ሲሆን ዛሬ ይህን ጥቃቱን ለመከላከል እራሱን ማደራጀት በጀመረበት ወቅት ደግሞ በማንነቱ ዙሪያ የሚያደርገውን መሰባሰብ የሚመሩ ቡድኖችን በየሚዲያዎቻቸው በጸረ ኢትዮጵያነት (ተገንጣይነት) በማቅረብ በአማራው ህዝብ መሃል በነዚህ ቡድኖች ላይ ስጋትና ጥርጣሬን በመንዛት እንቅስቃሴውን ለማኮላሸት ይህንኑ ጽኑ ኢትዮጵያዊ እምነቱን ዞረው ደግሞ በደካማ ጎንነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ:: ጠላቶቻችን ያልተረዱት ነገር የአማራው ህዝብ የራሱን ህልውና ለማስጠበቅ የሚያደርገውን የራስ አድን ተጋድሎ ብቸኛው የሃገሪቱ ህልውና ማስጠበቂያ እርምጃ እንደሆነ መግባባት ላይ የደረሰበት መሆኑን ነው:: ስለዚህ ይህን አማራው አንድና አንድ መፍትሄ ብሎ የተያያዘውን መንገድ ጠላቶቻችን እንከን ቢያወጡለትና ጉድለቱን ቢጠቁሙ እንደውም እያረመ በተሻሻለና በተጠናከረ መልኩ እንዲያንጸው ይረዳዋል እንጂ አራግፎ ጥሎ በጠላቶቹ እጅ እንደ በግ እየታረደ ወደሚቀጥልበት የባርነት መስመር እንዲመለስ አይገፋውም:: በስማችን እየማሉ ተገንጣይነትን የሚያናፍሱ ቅጥረኞቻችሁን እያሰማራችሁ የትግል አጀንዳችንን የተሳሳተ ምስል ለማሰጠት ብትሞክሩም ተላላኪ አረሞችን ለይተን አውቀን ከመሃላችን መንጥረን በማውጣት ትግላችንን ከጠላት ጥቃት በመከላከል እንድንጠናከር እረዳን እንጂ ደባው በእንቅስቃሴያችን ላይ ለዘለቄታው የሚያመጣው አንዳችም ተግዳሮት አይኖርም:: በእንቅስቃሴያችን ላይ ጥላ ለማጥላት በመሃላችን የሰገሰጋችኋቸው ተላላኪዎቻችሁ በዚህ ተግባራቸው ትክክለኛ ማንነታቸውን አጋልጠዋልና እናመሰግናለን:: ሌላው አማራው ሃገሬን እወዳለሁ አለ እንጂ እራሴን እጠላለሁ አላለም:: አማራው እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ስም ከፍተኛ መስዋትነት የከፈለውና እየከፈለ ያለው በሰላም፣ በእኩልነትና በብልጽግና የሚኖርባትን የጋራ ሃገር ለመገንባት እንጂ የሚገለልበትን፣ በባርነት የሚማቅቅበትንና የሚፈጅበትን ገሃነም ለመፍጠር አይደለም:: ስለዚህ ኢትዮጵያን እናፈቅራለን ስንል የመጀመሪያውን የጋራ ሃገር እንጂ ሁለተኛውን ገሃነሙን ማለታችን እንዳልሆነ ይታወቅልን:: የአንድነት ፍቅር እንጂ የመገለል ፍቅር የለንም፣ የጋራ ተጠቃሚነት እንጂ የበይ ተመልካችነት ፍቅር የለንም፣ የመኖር እንጂ የመጥፋት ፍቅር የለንም:: ይህን ስንል ሃገሪቷን ለአማራው ገሃነም ያደረጉ ሃይሎችን በመውጋት እንጂ ሃገሪቷን እራሷን በማፈራረስ መፍትሄ እናመጣለን ብለን አናምንም:: ችግሮቻችን ምንም ያህል የተወሳሰቡና ጠንካራ ቢሆኑም ለምፍትሄው ደርሰን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚጨምሩ አመለካከቶች ላይ መንጠልጠል አያስፈልገንም:: እንደ አለመታደል ሆኖ አውቆ አጥፊዎች በፖለቲካችን ውስጥ ተበራክተው እንጂ እንደውም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶቻችን በአየሉ መጠን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የመፍትሄው አካልነታቸው እየጎላ ይመጣል እንጂ በፍጹም የችግሮቻችን ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም:: ከሳሾቻችን በሃሰት እንደሚያናፍሱት እኛ የአማራው ወጣቶች በሌሎች የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ሁሉ እንጠላለን የሚል ቅዠትም የለንም፤ ምንም እንኳን የወያኔ ትግሬ ትልቁ አላማና ድካም አማራውን ከተቀሩት ጎሳዎች ጋር ማናከስ ቢሆንም:: ትላንትም ሆነ ዛሬ የአማራው ህዝብ ጠላቶች የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪ የሆኑ ጥቂት ጸረ ኢትዮጵያዊነት ቡድኖችና ተከታዮቻቸው እንጂ የተቀሩት የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች አይደሉም::

የግራው ትውልድ አዛውንት ተቺዎቻችን በበኩላቸው በአማራነት መደራጀታችንን ሲያወግዙ የጎሳ ፖለቲካን ታራምዳላችሁና ሃገር የማፍረሱ ተግባር ተዋናይ ናችሁ ነው እያሉን ያሉት? በፍጹም አይደለም፤ እኛ የጎሳ ፌደራሊዝምን አጥብቀን የምንቃወምና የምንታገል መሆናችን በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው:: ይህ ካልሆነስ ተገንጣይ አጀንዳ አላችሁ ነው እያሉን ያሉት? ይህንንም አምርረን እንደምናወግዝ ከተቺዎቻችን መሃል የሆኑ እራሳቸው እንደ ኦነግና ሻቢያ ያሉ ገንጣይ አስገንጣይ ቡድኖች ጋር በአንድ ማዕድ በቀረቡ ግዜ ያሰማነው ተቃውሞ ምስክር ነው:: ታዲያ እኝህ ሰዎች ምንድን ነው እያሉን ያሉት? እነሱ በማያወላውል መልኩ እያሉን ያሉት አንድና አንድ ነገር አማራው የማይጨፈጨፍባት፣ የማይፈናቀልባት፣ የማይጎሳቆልባት ኢትዮጵያ ትፈራርሳለችና ተሰብስባችሁ ፍጻሜያችሁን ተጠባበቁ ነው:: ይህን አስተውለን እንደሆነ የወያኔ ትግሬ መንግስት አማራውን ያገለለና የበደለ ያሁኑ ፌደራላዊ ስርአት ከፈረሰ ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች እያለ ዘወትር ከሚደነፋው ጋር ፍጹም ተመሳሳይ ነው:: አማራው እራሴን ከፈጽሞ ጥፋት እታደጋለሁ ብሎ ከተሰባሰበና ከተደራጀ ከኢትዮጵያ እገነጠላለሁ ወይም ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ የሚል የጥላቻ እብደት ውስጥ የገባ የህብረተሰብ ክፍልና ሃይል ካለ መልሳችን መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት ነው:: አንዳንድ ወገኖችም ጥላቻና ጎሰኝነት ምን ያደርግላችኋል ገለመሌ እያላችሁ አታሰልቹን:: እኛ አይደለንም ለጸብ እየተጋበዝን ያለነው:: እኛ ተፈጥሮዓዊ የሆነውን እራሳችንን የመከላከል እርምጃ እንውሰድ ነው የምንለው:: እኛ በሰላምና በእኩልነት የመኖር እንጂ የጎሰኝነት አመል የለብንም:: ይህ ለኛ ዛሬ ቅንጦት ነው:: መጀመሪያ በህልውና እንክረም እስቲ:: ዛሬ የጎሰኝነት ስሜት እንዲህ ጦዞ ጣራ በነካበት ወቅት “የጎሳ ፖለቲካን ከሞተበት አናስነሳው” ሲል በቅርቡ በአማራው መሰባሰብ ዙሪያ የሚመክሩ ግለሰቦችን የተማጠነ ዲያስፖራ “ዶክተር” መኖሩን አንብበናል:: ይታያችሁ እንግዲህ እንዲህ ያሉት ስለ ሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ቅንጣት ታህል እውቀት የሌላቸው ደንቆሮ ዶክተርና ፕሮፌሰር ተብዬዎች ናቸው በሃገሪቱና በህዝቧ እጣ ፋንታ ላይ የሚቆምሩት:: እነዚህ በምእራባዊያን ሃገሮች የተደላደለ ኑሮን የሚገፉ ግለሰቦች የህዝባችን ቁስል የሚሰማቸው አይደሉም እየደረሰብን ያለውም ከፍተኛ በደልም ሆነ በህልውናችን ላይ የተቃጣው አደጋ የሚያሳስባቸውም አይደሉም:: ምክንያቱም አንገታቸው በቆንጨራ እየተቀላ የተጣሉት የነሱ ቅምጥል ልጆች ሳይሆኑ የኛ የአማሮቹ ጨቅላ ህጻናት ናቸው፣ እጆቻቸው የፍጥኝ ወደኋላ እየታሰሩ ከነነብሳቸው በገደል የተወረወሩት የነሱ ሳይሆኑ የኛ እናቶች ናቸው፣ ቤት ንብረታቸውን ተነጥቀው ተሰድደው በየቋጥኙ እንዲወልዱ የተገደዱት የነሱ ሳይሆኑ የኛ ነብሰ ጡር ሚስቶች ናቸው:: የእነሱ ብቸኛ አጀንዳ በዙሪያቸው ከሚያጫፍሩት ዲያስፖራ ነሁላላ የትርፍ ግዜ “ፖለቲከኞች” ዘንድ ስምና ተሰሚነትን ማትረፍ ነው:: እንደዚህ ሰው መስማት የሚፈልገውን “ኢትዮጵያዊነትን” “አንድነትን”፣ “ዴሞክራሲን” ወዘተ የመሳሰሉ የማሞኛ ቃላትን በመደርደር በጀሌዎቻቸው ፊት ሞገስን ማግኘት ትልቁ ግባቸው ነው:: ለህሊናቸው የሚኖሩ ሰዎች ሳይሆኑ የግል ክብራቸውንና ዝናቸውን ከሃገርና ከወገን ጥቅምና ደህንነት በላይ አግዝፈው የሚያዩ ከሃዲዎች ናቸው::
ዛሬ እኮ በኢትዮጵያ ውስጥ አማራ ነኝ ማለት እጅግ አስፈሪ የመሆኑን ያህል በዲያስፖራው ማህበረሰብ ውስጥም አማራ ነኝ ማለትንም ሆነ ከአማራ ጋር የተያያዘን ነገር እንደ አደገኛ በሽታ አምጪ ቫይረስ የሚሸሹት ጉዳይ ነው:: እንግዲህ ባህር ማዶ ለኛ ለአማሮቹ ምን እየተደገሰልን እንደሆነ ከዚህ ተነስተን መተንበይ የሚያስቸግረን አይሆንም:: ይህ በጣም አስፈሪ ነው:: አንድ ከአማራ ቤተሰቦች የተገኘ ሆኖ ሳለ አማራ አትበሉኝ፣ አማራ አይደለሁም የሚል ዲያስፖራ በአማራው ጉዳይ ገብቶ ለምንስ ያቦካል?አማራነትን የሚጸየፍና የሚጠላ ሰው በአማራው ጉዳይ የሚመለከተው ነገር አይኖርም:: አንድ አማራ ያልሆነ ዜጋ በአማራ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ኢላማ ስለማያደርገው እራሱን ከዘር እና የባህል ጥፋት ለመከላከል ሊወስድ የሚገባው አስገዳጅ እርምጃ አይኖርምና አማራው በማንነቱ ዙሪያ የሚያደርገው አደረጃጀት አካል መሆን ስለማያስፈልገው እነዚህ ዜጎች በአማራነት አንደራጅም ማለታቸው አግባብነት አለው:: እኛም ይህን ለምን አሉ ፣ ሌላው ቢቀር እንደ ዜጋ ወይም ሰብዓዊ ፍጡር እንዴት ከጥቃታችን ሊያስጥሉን አልፈለጉም ብለን ለወቀሳ አንነሳም:: በዚህ በኩል የነጻነት ቀን መጥቶ የአማራው ህዝብ ከእስሩ ሲፈታ እራሱ ጠላት ወዳጁን ስለሚያስታውስ ሌላ ምንም ማለት አንፈልግም:: ከዚህ ባለፈ ግን የአማራውን ትግል ለማደናቀፍ የሚደረግ መሯሯጥ ጠላትነት ነው የሚሆነው ስንል እናስጠነቅቃለን:: እነዚህ የሻቢያ ቡችሎችና ደመኛችን የሆኑት የግራው ትውልድ ርዝራዦች ባደሙት ኢትዮጵያዊነት ስምና ሽፋን ላለፉት 60 አመታት እንዳደረጉት ሁሉ የአማራውን ህዝብ አጎሳቁሎና አመናምኖ ከምድረ ገጽ የማጥፋት የቅጥረኝነት ተልኳቸውን ያለመታከት እየገፉበት ይገኛሉ:: ይህን በህልውናችን ላይ የተቃጣ ሸር የወያኔ ትግሬ ናዚያዊ ስርአትና የአላማ ተጋሪዎቹ ከደቀኑብን አደጋ ለይተን ወይም አሳንሰን አናየውም:: የአማራው ህዝብ የራሱን ህልውና ለመታደግ ለሚያደርገው መሰባሰብና መደራጀት የማንንም መልካም ፈቃድና ቡራኬ አይፈልግም:: ሰብአዊነቱ በገዛ ሃገሩ የተካደውና መድረሻ ያጣው የአማራ ነገድ በህልውናው ላይ የተሰነዘረበትን ግዙፍ አደጋ ዛሬ ነገ ሳይል ተሰባስቦና ተደራጅቶ ለመመከት ያለው ጽኑ ምኞት በይፋ እየታወቀ ፍላጎቱና የድረሱልኝ ጥሪው እንዲታፈን ቢደረግም ጠላቶቻችን ሬት የመጋት ያህል እያንገፈግፋቸውም ቢሆን የአማራው ህዝብ የሚደርስበት የሚዲያ አፈና ሳይገድበው ሃገር ቤት ውስጥ በማንነቱ ዙሪያ የሚያደርገውን መሰባሰብ ከምንግዜውም በላይ በማጠናከር አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ቀጥሎበታል:: በአማራነታችን ዙሪያ ለመደራጀት ያስገደዱንን ጉዳዮች ለኢትዮጵያ ህዝብ ማስረዳት ለቀባሪው ማርዳት ነው:: ነገር ግን እንዲህ አማራነትን መቃብር ሳያወርዱ እንቅልፍ ከማይወስዳቸው ጠላቶቻችን በተደጋጋሚ ያለመታከት በሚሰነዘሩብን የስም ማጥፋት ፕሮፓጋንዳዎች በኩል ሊነዛ የታሰበውን ውዥንብር ማጥራት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለን::
በመጀመሪያ ደረጃ በአሁኑ ወቅት ተገንጣይ አጀንዳ ያላቸው በአማራነት ዙሪያ የተደራጁ ቡድኖችም ሆነ የመገንጠል ሃሳቡን በግለሰብ ደረጃ የሰነዘሩ የአማራ ፖለቲከኞች በፍጹም እንደሌሉ መታወቅ ይኖርበታል:: የአማራው ዋናና ነባር ትግል ተገንጣይነትን መዋጋት ነው:: አማራው በየሄደበት የሚጨፈጨፈውና የሚመነጠረው የረጅምና የቅርብ ግዜ እስትራቴጂክ ግባቸው መገንጠል በሆነ የጎሳ ድርጅቶች ነው:: ሁሉም ዜጋ እንደሚያውቀው የወቅቱ የአማራው ህዝብና የደመኞቹ ዋነኛ ትንቅንቅ አማራው በኢትዮጵያ ያለ ግዛት ሁሉ ሃገሬ ነው፣ በማንኛውም የሃገሪቱ ክፍሎች እንደማንኛውም ዜጋ መብቶቼ ተከብረውልኝ እኖራለሁ የሚል አቋም ሲይዝ የጎሳ ድርጅቶች በበኩላቸው “የለም ሃገርህ አይደለም በታጠረልህ የጎሳ ክልል ተወስነህ ትኖራለህ ከዛ ውጪ በቀድሞ ተስፋፊነትህና ወረራህ የተቆጣጠርከው መሬት ላይ የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳትም ሆነ የዜግነት መብት መጠየቅ አትችልም” የሚል አጥፍቶ የመጥፋትን መንገድ በመከተላቸው የተፈጠረ ነው:: የአማራውን ዘር ማጽዳትና ማጥፋትን ያስከተለው እኮ የጎሳ ልሂቆች ክልላችን የሚሉትን ግዛት በሂደት ለማስገንጠል በቅድሚያ የሃገሪቱ አንድነት ጠበቃ የተባለው ማህበረሰብ ከክልላችን መጽዳትና ሂደቱን መቀልበስ በማይችልበት ደረጃ መዳከም አለበት የሚለው ስሌታቸው ነው:: ይህ ደግሞ እስከ ዛሬ እንደታዘብነው ወያኔና ቡችሎቹን ጨምሮ በተቃዋሚ ጎራ ያሉት እንደ መድረክ ያሉ ብሄርተኛ ድርጅቶች የሚጋሩትና የሚደግፉት አካሄድ ነው:: የወያኔ ትግሬ ስርዓት እንደ ፋሺስት ጣሊያን ሁሉ ሃገሪቱን እንደ ሙጫ አጣብቆ አንድ አድርጎ የያዘውና የሃገሪቱን የተለያዩ ማህበረሰቦች በደምና በስነልቦና ያስተሳሰረው በመላ ሃገሪቱ ተሰራጭቶ የሚኖረው አማራ ነው ብሎ ስለሚያምን ከተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች ጠራርጎ አስወጥቶ አማራ ክልል ብሎ በሰየመው ማጎሪያ (concentration camp) ውስጥ አራግፎ አጉሮ የጎሳ ባንቱስታን ግዛቶችን በመገነጣጠልና አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትኖር በማድረግ ያለተቀናቃኝ ትግራይን የማስገንጠልና የተስፋፊነት ህልሙን እውን ለማድረግ እየሰራ ነው:: ለዚህም ነው አማራው እራሱን በማደራጀት የሚያደርገው የራስ አድን ትግል ከራሱ ህልውና ባሻገር ለሃገሪቱም አንድነት መድህን ነው የምንለው::
አማራው በመላው ሃገሪቱ ተሰራጭቶ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ ከሌሎች የሃገሪቱ ነገዶች ጋር ባመዛኙ የተዋለደና በደም የተሳሰረ ነው:: እንግዲህ አማራው ከማን ነው የሚነጠለው?ከእናቱ? ከአባቱ?ከሚስቱ?ከልጆቹ?የትኛውንስ ግዛት ነው ይዞ የሚገነጠለው?ጎጃምን?ሃረርጌን?ሲዳማን?ሸዋን? ዛሬም ሆነ ወደ ፊት መታወቅ ያለበት የአማራው ህልውና በዋነኝነት የተመሰረተው የሃገሪቱን ህልውና በማስጠበቅ ላይ መሆኑን ነው:: ከምንም በላይ አማራው የሃገሪቱን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት የማስከበር ታሪካዊ ሃላፊነት አለበት::ከዚህ ሚናው በተጻራሪ መቆም ከአማራነት ተፈጥሮ ጋር የሚጣረስ ነው:: “አማራን ሊያስገነጥሉ ነው” የሚል ውንጀላ ማንንም ሊያሳምን የማይችል ውሃ የማይቋጥርና የሚያስገምት የጠላት ውንጀላ ነው:: በአንድ ሃገር ውስጥ ከሃገሪቱ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት እንዲገለል የተደረገ አልፎም ህልውናው የፈተነ ማህበረሰብ የሚደርስበትን መገለልና ጥቃት ተደራጅቶ የመታገል ሙሉ መብት አለው:: የዴሞክራሲያዊ መርሆዎችንም በፍጹም አይጻረርም:: ነገር ግን እነ ኦነግ ለሚዘምሩት ባህላዊ ጭቆና ይቅርና አማራው ለገባበት የህልውና አጣብቂኝ ፖለቲካዊ ግንጠላ መፍትሄ ሊሆን አይችልም:: ለሃገር አንድነትና ሉአላዊነት ጸር የሆነውን የአንድን ታላቅ ማህበረሰብ መገለልና መጥፋት ተደራጅቶ መታገል ገንቢና ጠጋኝ እንጂ በምንም ተአምር በተቃራኒው ከፋፋይና በታኝ ውጤት ሊኖረው አይችልም፣ ኖሮትም አያውቅም:: በአለም ታሪክ ውስጥ በመንግስታቶች በፖሊሲ ተቀርጾ ወይም በስውር አግላይ ስርአታዊ ጫናና በደል የደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በጥላቻና በልሂቃን የስልጣን ጥም እየተገፉ ሳይሆን ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውና ነጻነታቸው መከበር በነበራቸው ቀናኢነት የተነሳ በየሃገራታቸው ያደረጓቸው እልህ አስጨራሽ ትግሎች ፍሬ አፍርተው የሰላምና የእድገት ምንጭ ሆኑ እንጂ የመከፋፈልና የመበታተን መንስኤ ሲሆኑ አልታየም:: እንዲህ ያሉት ዴሞክራሲንና እኩልነትን ያነገቡ የነጻነት ታጋይ ሃይሎች አግላይና ጨቋኝ ፖለቲካዊ ስርአት በሰፈነባቸው ሃገራት ሁሉ የነበሩና ወደፊትም የሚኖሩ በአንድ ሃገር ውስጥ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ማበብና ለሰላም መስፈን መንገድ ጠራጊ የሆኑ ሂደቶች አካል እንደመሆናቸው መጠን የትግል ተነሳሽነታቸውን ለማፈንና ለመቃወም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ለምናደርገው ትግል ብቻ ሳይሆን በቋፍ ላይ ላለው የሃገሪቱ አንድነት መጠበቅም እንቅፋት የሚሆን አደጋን ስለሚደግኑ የትግል ስልትና እስትራቴጂ አነዳደፍ ላይ ትልቅ ጥንቃቄን ማድረግ እንደሚያስፈልግ እናሳስባለን:: ንቅናቄያችን በፈጠራ የታሪክ ቁርሾዎችና በጥላቻ ላይ ተመስርተው ፖለቲካዊ ግንጠላን ግብ አድርገው የተነሱ ቡድኖችን እንደሚያወግዘው ሁሉ በትግራይ-ትግሪኝ የቅኝ አገዛዝ ስርዓት የተገለሉና የተጨቆኑ ማህበረሰቦች በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር የሚያደርጉትን የነጻነት ትግል በሙሉ ልብ ይደግፋል:: ለአማራው ህዝብ መደራጀትና መሰባሰብ መነሾ የሆኑ አስገዳጅ ምክንያቶችንም ሆነ ሃቀኛ የአማራው ድርጅቶችን ፖለቲካዊ ግብ ከተገንጣይና ጸረ አማራ ከሆኑ የምእራባዊያን ኢምፔሪያሊስቶች ቅጥረኛ ድርጅቶች ጋር ማነጻጸርም ሆነ ባስ ሲልም አክፍቶ ለማቅረብ መሞከር የመነጩበትን የጸረ አማራ ቡድኖች ሰልፍ ከማጋለጥ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም:: በሃገራችን ውስጥ በትግራይ ትግሪኝ የመስፋፋትና የአፓርታይድ ፖሊሲ የጭፍጨፋ፣ ምንጠራና ሌሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሰለባ የተደረጉ እንደ ጋምቤላና የአሰብ አፋሮች ያሉ ሌሎች ማህበረሰቦች የዜግነት መብታቸውንና ኢትዮጵያዊ ነጻነታቸውን ለማስመለስ የሚያደርጉት ትግል እንደ አማራው ህዝብ የህልውና ትግል ሁሉ በኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ ውስጥ ያለና ከኢትዮጵያዊነት ጠላቶች ጋር ያልወገነ እንዲሁም ህዝባዊነትን መሰረት ያደረገ ነው:: እነዚህ ማህበረሰቦች ገፊ በሆኑ አስገዳጅ ምክንያቶች በተናጠልም ሆነ የኢትዮጵያዊነት እምነታቸውን ከሚጋሩ መሰል ድርጅቶች ጋር በትብብር የሚያደርጉትን ትግል ለማፈን መባዘን ከማህበረሰቦቹ ጥቅምና መብት በዘለለ በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚቃጣ ከፍተኛ ጥቃት ነው:: ንቅናቄያችን የአሰብ አፋር ወንድሞቻችን ከሚያድርጉት ጸረ የትግራይ-ትግሪኝ ቅኝ አገዛዝ ትግልም ሆነ ከሌሎች ግፉአን ማህበረሰቦች ሃቀኛ ተወካዮች ጋር ሁሉ አቀፍ ትብብርን መመስረት እንደሚሻ በዚህ አጋጣሚ ማሳወቅ እንፈልጋለን::
ለብዙ ሺህ አመታት በሃገር ምስረታና ደጀንነት አቻ የለሽ ሚና ሲወጣ የኖረውን የአማራ ነገድ ወያኔና ሌሎች መሰል ናዚያዊ የጎሳ ድርጅቶች የከለሉለትን ኩርማን መሬት ይዞ እንዲገነጠል ለማድረግ የሚፈልጉ ወገኖች አሉ ማለት ለነገዱ ትልቅ ሟርት ነው:: ይህን ክህደት ለህዝብ ጆሮ ማላመድም ትልቅ መአትን በነገዳችን እጣ ፈንታ ላይ መጋበዝ ነው:: ይህ ሊሆን የሚችለው በአማራው ህዝብ ግብዓተ መሬት ላይ ብቻ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል:: አማራው በሃገሪቱ ውስጥ “ክልሌ” ብሎ የሚጠራው የራሱ ብቻ የሆነ ተለይቶ የሚታወቅ ግዛት እንደሌለ በሚገባ መታወቅ አለበት:: አማራው በሃገሪቱ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ ያለ መሬት በሙሉ ከመላው የሃገሪቱ ህዝብ ጋር በእኩል ባለቤትነት የሚጋራው ክልሉ ነው:: የአማራውን ህልውና መጋፋት የሚጀመረውም ይህንን ሃቅ በመካድ ነው:: ታዲያ የወቅቱ “አማራን ሊያስገነጥሉ ነው” የምትለዋ ደራሽ አሉባልታ በሃገሪቱ ውስጥ አማራው ባለቤት የሆነበት አንድ የሚታወቅ ውሱን ክልል ብቻ ነው(የወያኔን “አማራ ክልል” ማለት ነው)፣ ከዛ ውጪ ያለው የሃገሪቱ ግዛት ሃገሩ አይደለም የሚለውን የጠላት አቋም በዘዴ እንደ አንድ መግባባት ላይ የተደረሰበት አጀንዳ አስወስዶ ቀጥሎ በሚመጣው “ይገነጠላል” “አይገነጠልም” ንትርክ ውስጥ በመጨመር አማራው በሚሊዮኖች ልጆቹ ደም የተከላከለውን “ግዛቴ ኢትዮጵያ ናት” የሚለውን ጽኑ ሃገራዊ እምነቱን አሳልፎ እንዲሰጥ የታሰበች ስልት አትመስላችሁም? አማራው ባለቤት የሆነበት አንድ ተለይቶ የሚታወቅ ውሱን ክልል አለ የሚል እምነት ከሌላቸው (ሊያሳምኑም ካልፈለጉ) ቅጥረኞች የመገንጠል ፍላጎት አላችሁ ብለው ሲወነጅሉን መቼም አማራው ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ ያስገነጥላል ብለው “ሰግተው” አይሆንም:: ጠላቶቻችን ከኛ ጋር ያላቸው መሰረታዊ ልዩነትም ያለው እዚህ ጋር ነው:: እኛ ዘወትር ሃገራችን ኢትዮጵያ ናት እያልን እንዘምራለን፣ ይህ ያልተዋጠላቸው ጠላቶቻችን በበኩላቸው እንደዚህ አጀንዳችሁ ተገንጣይነት ነው በማለት በጎን ሃገራችን በወያኔ ትግሬ የታጠረልን ክልል ብቻ መሆኑን ሊያስታውሱን ይፈልጋሉ:: እንዲህ ያለው ሸፍጥ ሲሰራ ወዴት ወዴት?መጀመሪያ አማራው የቱን ግዛት ነው የሚያስገነጥለው? አማራው ግዛቱ ኢትዮጵያ ናት፣ አማራው እስከዛሬ የደማለት ወደፊትም የሚሰዋለት እርስቱ ኢትዮጵያ ናት በማለት የጠላትን ድብቅ አላማ ማክሸፍ ተገቢ ነው:: ጠላቶቻችን ስለ “አማራ ክልል” እና “መገንጠል” ሲያናፍሱ የአማራው ወጣት ሃገራዊ ግብና ህልም ከኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች ያለ አግባብ የተነጠቁ ግዛቶችን፣ ወደቦችንና ደሴቶችን መሰብሰብ ነው:: ይህን ደግሞ በማንም ችሮታና መልካም ፈቃድ ሳይሆን ከሌሎች ኩሩ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችን ጋር ደምና አጥንታችንን ገብረን በጠላቶቻችን መቃብር ላይ እውን የምናደርገው ነው የሚሆነው:: እነ “ታጠቅና” “ዳኘው” ዳግም ከህንድ ውቂያኖስና ቀይ ባህር ይጠጣሉ፣ በዳህላክ ደሴቶቻችንም ላይ ይንጎማለላሉ:: ይህ የዚህ ትውልድ ቃል ኪዳን ነው::
ይቀጥላል…………..

የአማራ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ
አምደጺዮን ዘ ተጉለት
22/07/07
አሩሲ ነገሌ

 

Source: አውጋን

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.