0

የግራው ትውልድ ኢትዮጵያዊነትን ቦርቡሮ ለማጥፋት በውጭ ጠላቶቻችን የርእዮተ አለም ቤተ ሙከራ ተፈብርኮ በመሃላችን የተነዛ ጸረ ማንነት ቫይረስ ነው – ክፍል 2

አሩሲ ነገሌ፦ ለግራው ትውልድ ፖለቲካና አስተዳደር የሚቀረጸው በህብረተሰባዊ ርእዮተ አለም ቀመሮች መሰረት ስለሆነ የአማራው ነገድ በተጨቋኝነት ስም በማንነቱ ዙሪያ መደራጀቱ ነገዱ በግራው ፖለቲካ በገዥና በጨቋኝ መደብነት የተፈረጀበትን ምልከታ በማፋለስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ከአማራ የባህልና የቋንቋ ጭቆና አላቆ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብታቸውን በማጎናጸፍ የሃገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ሊፈታ የሚችልበትን እድል ስለሚያሳጣ ለአማራው ነገድ ጭቆናና መበደል እውቅና መስጠት ኢ-ህብረተሰብአዊነትና ኢ-ተራማጅነት ነው ተብሎ ተይዟል:: የግራው ፖለቲካ የኢትዮጵያን ማህበረሰቦች ትክክለኛ ችግር በተጨባጭ ጥናቶችና መረጃዎች ባገናዘበና ባጤነ መልኩ ሳይሆን አውሮፓውያን ምሁራን የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ አስተዳደራዊ ስርአትና ነባራዊ ሁኔታ የተረዱበትንና ለማጥናት የተጠቀሙበትን የተሳሳተ መንገድ እንዲሁም ፋሺስት ጣሊያኖች የኢትዮጵያዊያን አርበኞችን የነጻነት ትግል ለማዳከም የነዙትን ጸረ አማራና ከፋፋይ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳ ጭምር መነሻ በማድረግ የህብረተሰባዊነት (Socialism) ርእዮተ አለም “የጨቋኝ ተጨቋኝ” ከፋፋይ ቀመርን (formula) በጨቋኝ የአማራ መደብና ተጨቋኝ ብሄር ብሄረሰቦች በቅደም ተከተል በመሙላት በእድገት ጸርነት የተፈረጁትን የሃገሪቱን መልካም ባህሎችና እሴቶች ከጨቋኝ መደቦች ጋር አብሮ በመምታትና በማጥፋት የኢትዮጵያን ችግሮች እፈታለሁ የሚል ነው:: ከዚህ አመለካከትና ቀመር ውጪ ያለ አስተሳሰብ ማርክሳዊ ሌኒናዊ የትግል ዘዴን የሚጻረር አጥፊና አንጃ ነው:: በዚህ መንገድ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የማእዘን ድንጋይ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ባህሎችና እሴቶች ክፉኛ እንዲዳከሙ በመደረጋቸው የሀገሪቱ መሰረታዊ ችግሮች ሊፈቱ ቀርቶ ተጨማሪ አዳዲስና ግዙፍ ችግሮች ተፈጥረውልን የሃገር አንድነትና ሉአላዊነት ታላቅ ፈተና ላይ የወደቁበት አጣብቂኝ ላይ ደርሰናል:: የግራው ትውልድ እንዲህ ያለውን አክራሪና አፍራሽ ፖለቲካ የተቹና የተቃወሙ አርበኞችን በአብዮት እሳት እየበላ እያጠፋ የመጣ እንደመሆኑ መጠን “የአማራው ነገድ መመታት ለሃገሪቱ ችግሮች መፍቻ ወሳኝ ቁልፍ ነው” የሚለውን ህብረተሰባዊ እምነቱን የሚጻረረውን የአሁኑን የአማራውን መደራጀትና ማንሰራራት ሊታገሰውና ችላ ሊለው የማይፈልገው የጥፋት በትሩንም ዳግም ያነሳበት ሂደት ነው:: የግራው ፖለቲከኞች የብሄር ጥያቄና የማንነት ፖለቲካ ፈጣሪነታቸውና ደጋፊነታቸው በዘለለ ለባህልና የቋንቋ ጭቆና የፖለቲካዊ ግንጠላን መፍትሄነት የሚያቀነቅኑ እንደመሆናቸው መጠን የአማራውን መደራጀት በማንነት ፖለቲካ ፈርጀው ለማጣጣል የሚያደርጉት ሙከራ የአማራውን ማንሰራራት የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ ስጋት አድርጎ ከሚሰብክ የቆየ ህብረተሰባዊ (socialist) አመለካከታቸው የመነጨ እንጂ የማንነት ፖለቲካን በመጸየፍ ወይም በሃገር አንድነትና በማህበረሰቦች ተቻችሎ የመኖር ባህል ላይ የሚያመጣውን ጠንቅ በመገንዘብ እንደማይሆን የግራውን ፖለቲካ መነሻና መድረሻ ከታሪክ አንብቦ ለተረዳ ሰው የተሰወረ አይደለም(የአማራው ትግል የህልውና እንጂ “የማንነት ጥያቄ” አለመሆኑ ሳይዘነጋ):: ባጭሩ በአምልኮ ህብረተሰባዊነት ርእዮተ አለም የታወረው የግራው ትውልድ ተቆርቋሪነቱና ታማኝነቱ በጥራዝ ነጠቅነት ለሚያመልከው የባእድ ፍልስፍና እንጂ ለሃገርና ለወገን እንዳልሆነ ታሪክ የመሰከረው ሃቅ እንደመሆኑ መጠን ዘንድሮም ከአማራው ሃይሎች ጋር የተያያዘው ግብግብ መነሻ እንዲህ ያለው ጸረ አማራ አመለካከቱ እንጂ ለሃገር አንድነት ያለው ቀናኢነት አይደለም:: ለዚህም ነው ሽብርን፣ ፍጹም አምልኮንና ጭፍን ተከታይነትን በሚያበረታታ እንዲሁም የሰውን ልጅ “እኛና” “እነሱ” በሚል የሚከፋፍል ፈውስ የለሽ የህብረተሰባዊነት ርእዮተ አለም አእምሮው የተበከለ ሰው የርእዮተ አለሙን ከፋፋይና ጸረ ዴሞክራሲያዊ መርሆዎች እንዳቀነቀነ መቃብር ይወርዳል የሚባለው::
ያለፈው የታሪክ አተላ የግራ ትውልድ የቀመመውን የጎሰኝነት፣ የጥላቻና የመበታተን መርዝ የማርከስ፣ ያራከሰውን ኢትዮጵያዊነት ወደተገቢው የክብር ቦታ የመመለስ እንዲሁም በአማራው ህልውና ላይ የለኮሰውን የጥፋት እሳት የማዳፈን ታሪካዊ ሃላፊነት ያረፈው በዚህ ትውልድ ትከሻ ላይ ነው:: ይህ ትውልድ የብዙ ሺህ አመታት እድሜ ባለቤት የሆነችን ጥንታዊት ሃገር ታሪክና ቅርስ እንዳይወድቅ እንዳይነሳ አድርጎ ካዋረደ፣ የህዝቦቿን አንድነትና መፈቃቀድ ከናደ፣ በአባቶች ደም ታፍሮና ተከብሮ የዘለቀውን ሉአላዊነቷን ካስደፈረ የግራው ትቢያ ትውልድ የሚወርሰው መልካም ተሞክሮም ሆነ ለነጻነቱ በሚያደርገው ትግል የሚሻው ትብብር አይኖርም:: ይህ ትውልድ የተዘፈቀበት መከራና ስቃይ ዋነኛ አድራጊና ፈጣሪ የግራው ትውልድ መሆኑ ላፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም:: ሃገራችን ትውልዱ ሃገር አልባ ሆኖ በየበረሃው አካሉ በስለት እየተተለተለ ብልቶቹ በእስራኤል የሆድ እቃ ገበያ የሚቸረቸሩበት አሳዛኝ ሁኔታ ላይ የደረሰችበት መንገድ በግራው ትውልድ መሃንዲስነት የተቀየሰ ነው:: የግራው ትውልድ የኢትዮጵያ የሶስት ሺህ ዘመናት ሃገርነት ተክዶ በብሄር ብሄረሰቦች እስር ቤትነት የተተካበት፣ አማራ የተሰኘ አንድ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ በወራሪነት፣ በጨፍጫፊነትና በቅኝ ገዥነት ተወንጅሎ የጎሳ ብሄርተኞች የጥላቻ ማራገፊያና የተደራራቢ ቅጣት ሰለባ የተደረገበት፣ የኢትዮጵያ አባቶች አኩሪ ታሪክና ገድል በፊውዳል ጉልተኛ ስርዓት የጭቆናና የብዝበዛ ታሪክነት የተለወጠበት፣ የኢትዮጵያዊያን የነጻነት ወዳድነት፣ ጠንካራ በራስ መተማመንና ብሄራዊ ስሜት ተመልሶ ሊታደስ በማይችልበት መልኩ ከስሩ ተነቅሎ እንዲጠፋ የተደረገበት፣ የሃገራችን ምሰሶ የሆኑት ባህል፣ ትውፊት፣ ወግና እምነታችን በአስነዋሪነት፣ በአድሃሪነትና ኋላቀርነት ተፈርጀው እንዲዋረዱና እንዲጠፉ የተዘመተበት፣ ባጠቃላይ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አውዳሚ ፍጻሜ የተለኮሰበት ትውልድ ነው:: እንዲህ ባለው የጥፋት መሃንዲስ ትውልድ ነው እንግዲህ ቁልቁል የምንታየውና በሃገር ስሜት አልባነት፣ በዋልጌነት፣ በሱሰኝነት ወዘተርፈ የምንወነጀለው:: አስገራሚውና አሳዛኙ ነገር ደግሞ እኝህ ለባርነትና ሃገር አልባነት የዳረጉን የእንጨት ላይ ሽበቶች የሆኑ ጠላቶቻችን ዛሬ ተመልሰው እኛ እናውቅልሃለን ማለታቸው ነው:: የትውልዳችን፣ የጀግኖች አባቶቻችንና የሃገር ደመኛ የሆነው የግራው ትውልድ ከሃገራችን ፖለቲካ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ እጁን ሊያነሳ ይገባል:: ወይም የዚህ ትውልድ አባሎች የሆን የግራው ትውልድ በፖለቲካዊና ማህበራዊ ህይወታችን ላይ ያረዘመውን የጥፋት እጁን ልንነሳው ይገባል:: የዚህ ትውልድ አባሎች ትከሻችን ላይ ባረፈው ታሪካዊ ሃላፊነት መሰረት በቋፍ ላይ የቆመውን የሃገርና የህዝባችንን ህልውና ታድገን እንደ አለት በጸና መሰረት ላይ ባኖርን ማግስት በአምልኮ ፈረንጅና በማንነት ቀውስ የሚማቅቀው የግራ ትውልድ በሃገራችን ታሪክ ውስጥ የያዘውን የውድቀትና የጥፋት ጥቁር ታሪክ የሃገር ሻጭነት፣ የክህደትና በታኝ ሚናውን በሚገባ በሚያወሳ መልኩ ዳግም ልንጽፍለት ይገባል:: የግራው ትውልድ የማንነታችን መሰረት በሆኑት በሃገራችን፣ በባህላችንና በእምነታችን ላይ ያደረሰውን የማይጠገን ታላቅ ጉዳት ያደረሰ ሃገር በቀል የሃገርና የህዝብ ጠላት በሃገራችን ረጅም ታሪክ ውስጥ ከቶ አልተስተዋለም:: አህመድ ግራኝና ዮዲት ጉዲት የግራው ትውልድ እንዳደረገው የኢትዮጵያን ሃገርነት፣ የማህበረሰቦቿን ተከባብሮና ተፈቃቅዶ የመኖር ባህልን፣ በራስ ማንነትና ታሪክ የመኩራት መንፈስን ጥያቄ ውስጥ አልጨመሩም:: በዚህ ትውልድ ልብ ውስጥ እንደ እቶን እሳት የሚንቀለቀለው የሃገር ፍቅርና የመጠቃት ስሜት እሩቡ ጀሌዎቻቸውን አስከትለው የስልጣን ጥማቸውን ለማርካትና በህዝብ ጫንቃ ላይ የጭቆና ቀምበራቸውን ለማኖር ሲሯሯጡ ሃገራችንን አጥፍተው የጠፉት መንፈሰ ድሆቹ የግራው ትውልድ አባላት ልብ ውስጥ ከቶ አልነበረም የለምም:: እነዚህን ኢትዮጵያዊነትን የሚወክሉ በብዙ ሺህ አመታት የሃገራችን ታሪክ ውስጥ የገነባናቸውን ማንኛቸውንም ባህሎች፣ እሴቶች፣ እምነቶችና ወጎች በኋላ ቀርነት፣ በእድገት ጸርነት፣ በአሳፋሪነት ፈርጀው ያዋረዱና ያጠፉ እንዲሁም ክፉኛ የሚንቁትንና የሚጸየፉትን የገዛ ህዝባቸውን ባደባባይ አበሻቅጦና አዋርዶ በመሳደብ ለተሳዳቢ አሳልፎ መስጠትን እንደ ተራማጅነት የሚቆጥሩ የግራው ትውልድ ድዊያን ለህዝባችንና ለማንነታችን ክብር፣ ፍቅርና ተቆርቋሪነት ይኖራቸዋል ማለት ዘበት ነው::
የግራው ትውልድ አባላት የማይናወጥ እምነት የሆነው ህዝባችን በነዚህ ጎታች ባህሎችና ልምዶች የተተበተበ ኋላ ቀርና አሳፋሪ ህዝብ ስለሆነ እኛ የተማርን ተራማጆች ስልጣን ይዘን “እስኪዘምንና” “እስኪሰለጥን” (“የዘመናዊነት ጸር” የሆነውን ኢትዮጵያዊ የሆነውን ባህሉን፣ እምነቱንና ልማዱን አራግፎ ጥሎ ወደ ፈረንጅ ባህልና ወግ እስኪገባ ማለት ነው የግራው የስልጣኔና የዘመናዊነት ትርጉም፤ ዘመናዊነት የሃገርበቀል ባህሎችና ልምዶች ተቀጽላ መሆኑን ግን አልተረዱም)ድረስ አብዮታችንን ሳናስደፍር (የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት በመንፈግ) በውድም በግዴታም ልንገዛው ይገባል የሚል ነው (ይህ እምነት የኢህአፓ፣ የኢጭአት፣ የመኢሶን፣ የኢሰፓ፣ ወያኔ፣ ሻቢያ ወዘተ የሁሉም የግራው ትውልድ ግሳንግሶች መሆኑ ይታወቅ) :: ይህ የአውሮፓዊያን ቅኝ ገዢዎች አፍሪካዊ ማንነትን የማንቋሸሽና በስልጣኔ ጸርነት የመፈረጅ ዘረኛ ፍልስፍና በተቀሩት አፍሪካዊያን ላይ በቅኝ ገዢ ጌቶቻቸው፣ በኢትዮጵያውያን የግራው ትውልዶች ላይ ደግሞ በዘመናዊ ትምህርት አማካኝነት የተጫነ የአይምሮ ባርነት ሲሆን ከቅኝ አገዛዝ ማክተም በኋላም የአፍሪካን ህዝብ የራስን ባህል፣ ወግና እምነትን የመጸየፍና ለአፍሪካ ውድቀትና ኋላ ቀርነት በሙሉ ብቸኛ ተጠያቂ አድርጎ የማቅረብ ልምድን የስልጣኔ አይነተኛ መገለጫ አድርገው በሚመለከቱ “ሰለጠን” በሚሉ የገዛ ልጆቹ እጅ እስከ ዛሬው እለት ድረስ በባርነት እንዲማቅቅ አድርጓል:: የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካዊያኖችን በውዴታም በግዴታም በቅኝ ተገዢነት ይዞ ወደ አውሮፓ ባህልና ወግ እንዲገቡ በማድረግ ከኋላቀርነት አውጥቶ ለማሰልጠን የተወጠነ ነው በማለት የቅኝ ግዛት ዘመቻቸውንና አምባገነናዊ አገዛዛቸውን ያስተባበሉበትን ኮሎኒያሊስት ጽንሰ ሃሳብ ተማርን ያሉት የኛዎቹ የግራው ትውልድ አባላትና አፍሪካዊ አቻዎቻቸው ገልብጠው በመውሰድ ህዝባችን እራሱን ለማስተዳደር እስኪበቃ ድረስ ማስተዳደር ያለብን እኛ የአውሮፓ ትምህርት ባለቤት የሆን መደቦች ነን፣ ስልጣንን የምንሻው በፖለቲካው ልንገፋው የምንፈልገው የራሳችን የሆነ የተወሰነ ፍላጎትና አመለካከት ኖሮን ሳይሆን ህዛባችንን ከኋላ ቀርነትና አረመኔነት (savagery) አላቀን ለማሰልጠን ካለን ከግለኝነት የጸዳ ፍጹምና ቅዱስ አላማ የተነሳ ነው በማለት ስልጣንን ያለተቀናቃኝ ለመቆናጠጥና ዘላለማዊ ለማድረግ እንዲሁም አገዛዛቸውን ከግልጽነትና ከተጠያቂነት በላይ ለማድረግ ይረዳቸው ዘንድ በማስጠየቂያነት (Justification) በመጠቀም ህዝቦቻቸውን የውስጣዊ ቅኝ አገዛዝ ሰለባ አድርገዋቸዋል:: “Placide Tempels” የተሰኘ ፈረንሳያዊ ሚሲዮናዊ እኝህን ተማርን የሚሉ አፍሪካውያን ነጭ አምላኪዎች “Bantu Philosophy” በተሰኘ እውቅ መጽሃፉ “évolués” ሲል ከቅኝ ገዢዎቻቸው ከቆዳ ቀለማቸው ውጪ(ይህም አልለወጥ ብሏቸው ነው ይላል) በአመለካከትና(ለአፍሪካዊያን ባህል፣ እምነትና ስልጣኔ ባላቸው ከፍተኛ ንቀትና ጥላቻ) የአገዛዝ ስልት (በአምባገነንናታቸው፣ በጨፍጫፊነታቸው ወዘተ)ፈጽሞ የማይለዩ፣ የቅኝ አገዛዝ ቅርስ የሆነው የአፍሪካውያን በራስ ያለመተማመንና የበታችነት ስሜት አለመቀረፍ ምክንያት የሆኑ የአውሮፓዊያን ምትክ የውስጥ ቅኝ ገዢዎች በማለት ይገልጻቸዋል:: ባጭሩ ህዝባቸውን የእድገት ጸር የሆነ ባህል፣ ትውፊት፣ ወግና እምነት እስረኛ የሆነ ኋላ ቀር ህዝብ በማለት የፈረጁ የግራው ትውልድና አፍሪካዊ አቻዎቻቸው ተልዕኮ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ጀምረው ያልቋጩትን አፍሪካውያንን እንደ ከብት መብትና ነጻነትን በመንፈግ በቅኝ ገዢነት ይዞ “የማሰልጠን” ኮሎኒያሊስት አላማን እዳር ለማድረስ የነጭ ኮሎኒያሊስቶችን የእረኝነት ሚና መተካት እንጂ የአንድ ሃገር መንግስት ሚና የሆነውን በህዝብ የተወከሉበትን አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የመምራት ሃላፊነት መወጣት አይደለም:: በሌላ አነጋገር የግራው ትውልድ የኢትዮጵያን ማህበረሰቦችን እንዲሁም ባህልና እምነታቸውን የሚመለከትበት መንገድና ፖለቲካዊ ፍልስፍናው እራሱን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በሞግዚትነት የሚያጭበት እንጂ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማቋቋም፣ እንደ መንግስት ህዝብን ለማገልገልና ለኢትዮጵያዊነት እሴቶች ማበብና መጠበቅ ያለውን ፍላጎት ጠቋሚ አይደሉም:: የዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ በበኩሉ የሚያሰምርበት ጉዳይ ህዝብ የስልጣን ምንጭ መሆኑንና ገዢዎች ደግሞ የበላይነትን በማግኘት ተግባራዊ እንዲሆን የሚሹት እነሱ በግላቸው የሚያራምዱት አንድ የተወሰነ አመለካከትን ለምርጫ አቅርበው በማሸነፍ በህዝብ የተወከሉ የህዝብ አገልጋዮች መሆናቸውን እንጂ የግራው ፖለቲከኞች ምለው እንደሚገዘቱበት የስልጣንና የአምባገነንነት ማስተባበያቸው “ እነሱ የሚገፉት የራሳቸው የሆነ ፍላጎት የሌላቸውና ስለ ህዝብ ብቻ የሚኖሩ” እንዲሁም የህዝብን መብትና ጥቅም ለጋሾች መሆናቸውን አይደለም:: አንድ ሰው ደግሞ እንዲህ ኋላ ቀርና አሳፋሪ ነው ብሎ ክፉኛ የሚንቀውንና የሚያዋርደውን(መገራት እንዳለበት የዱር እንሰሳ የሚመለከተውን) ህዝብ የስልጣን ባለቤት አድርጎና አክብሮ በፍጹም አይመለከተውም፣ በስልጣን ዘመኑም በታማኝነትና በግልጽነት ሊያገለግለው አይችልም:: ዛሬም ሆነ ትላንት ህዝብ የሚያስፈልገውን እኛ እናውቅለታለን ስለሆነ መፈክራቸው የህዝብን እውነተኛ ፍላጎት ማድመጥ አይፈልጉም፣ የምርጫ ድምጹንም አያከብሩም:: ለዚህም ነው ምንም ያህል የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ተቆርቋሪና ደጋፊ መስለው ቢቀርቡም ህዝብን የስልጣን መቆናጠጫ መሳሪያ ከማድረጋቸው ውጪ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት በኢትዮጵያ ሲያብብ የማናየው:: ለወደፊቱም ተነቅሮ በተተፋው ኢ-ዲሞክራሲያዊ የህብረተሰባዊ ርእዮተ አለም (socialism) አምኖ የተጠመቀ የአይምሮ እስረኛና የህዝብ ጥላቻና ንቀት ያለበት ትውልድ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፈጽሞ እስካልተገለለ ድረስ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ መሰረቱን ሊጥል አይችልም::
የህብረተሰባዊ ርዕዮተ አለም እንደ ቅኝ ገዢዎች ሁሉ አፍሪካውያን ተማሪዎችን ለማንነታቸው ንቀትና ጥላቻን እንዲያዳብሩ ተጽዕኖ ከማድረጉም በላይ አፍሪካዊ የሆነ ባህልና ስልጣኔን በሙሉ ማጥፋትን ለአፍሪካ ኋላ ቀርነትና ድህነት ፍቱን መድሃኒት መሆኑን ይሰብካል:: በሶስተኛው አለም ውስጥ ህዝባቸውን ማስተዳደር የሚገባቸው የአውሮፓ ትምህርት ባለቤት የሆኑ መደቦች(በነጭ የዘረኝነት ርእዮተ አለም የተመረዙትን ማለት ነው)መሆናቸውን በመግለጽ የስልጣኔ እንቅፋት የሆኑትን አፍሪካዊ የሆኑ ማንኛቸውንም ባህልና ወጎች በሙሉ በማጥፋት ህዝቦቻቸውን ያለተቀናቃኝና በአምባገነንነት እየመሩ ከኋላ ቀርነት ሊያወጡ የሚችሉ እነሱ ብቻ መሆናቸውን “ሳይንሳዊ” ባለው መንገድ ያብራራል:: ርዕዮተ አለሙ የሶስተኛው አለም የተማሩ መደቦችን የህዝባቸው ብቸኛ አዳኝ አድርጎ ስለሚያቀርብና በትከሻቸው ላይ አርፏል ያለውን ስልጣንን ህዝብን የማሰልጠኛ መሳሪያ አድርጎ የመጠቀም ተልእኮ ቅዱስና ፍጹም ከማንኛውም አጀንዳ በላይ የሆነ ግብ መሆኑን ስለሚሰብክ ምሁራን በሞያቸው ከሚሰጡት አገልግሎት ባለፈ የስልጣንና የአስተዳደር ሚና ብቸኛባለቤት ጭምር አገዛዛቸውን ከተጠያቂነትና ከግልጽነት ውጪ እንዲሆን ያደርጋል (ባጭሩ የተማሩ መደቦችንና ፖለቲካዊ አገዛዛቸውን መለኮታዊነትን ያላብሳል):: ይህ ርእዮተ አለም ነው እንግዲህ ለግራው ትውልድ እንደ ማስጠየቂያ በማገልገል ኢትዮጵያን መግዛት ያለብንና ለሃገርና ለህዝብ የሚበጀውን የምናውቅ እኛ ብቻ ነን በሚል ለአምባገነንነትና ለጸረ ኢትዮጵያዊ ማንነት አስተሳሰብ ጥርጊያ ያበጀው:: መንግስቱ ሃይለማሪያም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ በራሱ አውቆ ለመምረጥ የሚያስችለው የስልጣኔ ደረጃ ላይ አልደረሰም በማለት ባልተጋራ አፉ የተሳደበበት አጋጣሚ፣ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ሃገር በቀል ትምህርት ባለቤት የሆኑ ምሁራኖችን “ደብተራ” በማለት ያንቋሸሹበት አጋጣሚ እንዲሁም በተደጋጋሚ በሚያወጡት ጽሁፎቻቸው የኢትዮጵያን ህዝብ በአስተሳሰብ ደሃነት፣ በጦርነት ናፋቂ አረመኔነት፣ የእድገት ጸርና ስንፍናን የሚያበረታታ ባህልና እምነት ተከታይነት፣ ወዘተ የሚዘልፉበት ሁኔታና እንደ አምባሳደር ገነት ዘውዴ ባሉ የወያኔ ሎሌዎች የኢትዮጵያ ባህልና እምነት ብቻ ሳይሆን እንደ ግራ አዝማችና በጅሮንድ ያሉ ኢትዮጵያዊ የጦር አበጋዞች የማእረግ ስያሜዎች ሳይቀር አጸያፊና መጥፋት የሚገባቸው “ኢ-ተራማጅነት” መሆናቸው ሲነገረን ያስተዋልንባቸው አጋጣሚዎች የግራው ትውልድ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማንነት ያለውን ጥልቅ ንቀት፣ ጥላቻና መጸየፍ የሚያስገነዝበን ነው:: በዚህ አይነት አፍሪካዊያን በተለይ ኢትዮጵያዊያን የአባቶቻችን አኩሪ ባህል፣ ወግና ልማድ እንዲሁም ታሪካዊ ገድል የፈጠረብንን በራስ መተማመን ተገፍፈን በማንነታችን እንድናፍርና ያደጉ ሃገሮች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የሚያበረታንን የመንፈስ ስንቅ እንድናጣ ተገደን በራሳችን ተስፋ ቆርጠን ለሃገራችን ትንሳኤና ለኑሯችን መሻሻል ወደ ነጭ ሃገራት የምናማትር ብኩን ተመጽዋችና ጥገኛ ዜጎች እንድንሆን ተፈርዶብናል:: የሃገራችን ህልውና መሰረት የሆኑት እነኝህ ባህሎቻችንና እሴቶቻችን ከምንም ግዜ በላይ ተቆርቋሪ መሲህ በሚሹበት ባሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያዊነት (ባህላችንን፣ ወጋችንን፣ታሪካችንን እምነታችንን ይጨምራል) ከፍተኛ ንቀት ብሎም ጥልቅ ጥላቻ ያለበትን ትውልድ ባጨቀየው ፖለቲካ ውስጥ ዳግም እንደልቡ እንዲንቦራጨቅበት መፍቀድ እራስን በራስ እንደማጥፋት የሚቆጠር ነው::
የግራው ትውልድ ኢትዮጵያዊነትን ቦርቡሮ ለማጥፋት በውጭ ጠላቶቻችን የርእዮተ አለም ቤተ ሙከራ ተፈብርኮ በመሃላችን የተነዛ ጸረ ማንነት ቫይረስ ነው:: ኤርትራውያን በኢትዮጵያ በቅኝ ተገዝተዋልና የመገንጠል መብታቸው ሊከበር ይገባል የሚል መፈክር ሲያስተጋባ የነበረ፤ ዋናው “የብሄር ጥያቄ” ተገንጣይ ነው አይደለም የሚለው ሳይሆን ህብረተሰባዊ ነው አይደለም የሚለው ነው በማለት በቅጡ እንኳን ያልተረዳውን የነጭ ህብረተሰባዊ ርእዮተ አለም እንደ መጽሃፍ ቅዱስ ቃል እየጠቀሰ የብሄሮች የመገንጠል ጥያቄ “ህብረተሰባዊ” እስከሆነ ድረስ የኢትዮጵያ ብሄሮች በሙሉ ተገንጥለው መሄድ ይችላሉ የሚል በታኝ መርዝ ማንም ሃገር ወዳድና ለማንነቱ ክብር ያለው ህዝብ በማይሞክረውና በማያልመው መልኩ ቀምሞ በህዝብ መሃል የበተነ፤ “ኢትዮጵያ ሃገር ሳትሆን ሃገር ሊሆኑ የሚችሉ ብሄሮች ስብስብ ናት” በማለት ብዙ የኢትዮጵያ ጎሳዎችና ነገዶችን “ብሄር”(ይህ ቃል ከ “ሃገር” ጋር አቻ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል) ብሎ ከመጥራት አልፎ ለብሄርነት ያልበቁ ያላቸውን ማህበረሰቦችን ደግሞ ለብሄርነት እንዲበቁ ማገዝ ይገባል በማለት ኢትዮጵያን ለቁጥር በሚያዳግቱ ጥቃቅን ሃገሮች ለመተካት እግረ መንገዱንም እነዚህ ማህበረሰቦች ሃገር ሊሆኑ ይችሉ የነበረበትን አጋጣሚ “በነፍጠኞች በሃይል የተነጠቁበት” ያለውን “ታሪካዊ በደል” ለመካስ የደከመ፤ የኢትዮጵያን ሲሶ ግዛት የወረረ የሶማሊያን ጦር ለመውጋት የተንቀሳቀሰን ህዝባዊ ጦር ከአላማው ለማሰናከልና በመርዝ ለመፍጀት ባደረገው ጥረት የደረሰበትን የህይወት ኪሳራ “ሰማዕትነት” ብሎ የሚያፌዝ፤ ዛሬም ከድርጅታዊ ጭፍን አምልኮና ታማኝነት ውጪ ሃገራዊ አላማና ግብ የሌለው ትውልድ ለኢትዮጵያ አንዳች በጎ ነገር ያመጣል ብሎ ተስፋ ማድረግ ከእባብ እንቁላል ጫጩት መጠበቅ ነው:: የሌሎች ማህበረሰቦችን ድጋፍ በማግኘት በአማራ ህዝብ ኪሳራ የስልጣን ባለቤት ለመሆን ያራገቡት “የብሄር ብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል” የሚለው በታኝ ስታሊናዊ ፍልስፍና ኢትዮጵያዊያን በጋራ ለእድገት፣ ለብልጽግናና ለዲሞክራሲ በጋራ እንዳይሰሩና እንዳይታገሉ በማድረግና እንደ ቡና መጣጣት ያሉ ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ሳይቀር ወደ ጎሳ በማጥበብ በጠላትነት ስሜት በአይነቁራኛ እንዲተያዩ በመገፋፋት ለከፋ የጋራ ጥፋትና መከራ ዳርጓቸዋል:: በታሪካችን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ከአማራው ማንነት ጋር ተያይዞ ተነስቶ አያውቅም:: የነዋለልኝ ትውልድ ግን ኢትዮጵያዊነት ማለት አማራነት ነው በማለትና ታሪክን በማፋለስ አማራውንና ማንኛውንም በኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና የሚያምነውን ወገን በትምክህተኝነት ፈርጆ ኢላማ ለማድረግ ተጠቅሞበታል:: በዚህ አይነት ትውልዱ የአንድን ሃገር እጣፈንታ ያልተጠናና በተግባር ያልተፈተሸ የባእድ ርእዮተ አለም ቤተ ሙከራ አደረገው፤ በአክራሪነት ያራገበው እስታሊኒስት-ሌኒኒስት ቀኖናም በመጨረሻ የብሄረሰቦችን ጥያቄ ወደ ቤተሰብ ፖለቲካ አዘቀጠው:: እስቲ የግራው ትውልድ እንደሻማ ነደድኩኩለት የሚለውን በግዜው የተነሳለትን አላማና በአድሃሪነትና በደም መጣጭነት የወነጀለው የአጼው ስርዓት የትውልዱን ያልተገራ ፖለቲካ የተቃወመበትን መከራከሪያና በሃገሪቱ ህልውናና አንድነት ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ በትክክል የተነበየበትን ጽሁፍ አነጻጽረን የሃገር በቀል ልማድና ባህል ውጤት የሆኑት የግዜው አስተዳዳሪዎች የአውሮፓ ትምህርት ምርት ከሆነው የግራው ትውልድ ግሳንግስ እጅግ የላቀ አርቆ አስተዋይነትና የመሪነት ተክለሰውነት እንደነበራቸው እንመልከት(በእውነቱ የኢትዮጵያ ባህላዊ ስርአት ስር ነቀል በሆነ መልኩ ሳይሆን እንደ ጃፓኖች ሁሉ በዝግመተ ለውጥ ተሃድሶ ተደርጎለት ቢሆን ኖሮ የዛሬው የኢትዮጵያ አሳዛኝ ገጽታ በጣም በጎ መልክ በያዘ ነበር)::
“የብሄር ትርጉም ከዚህ ውጪ ምንድን ነው? የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ አለባበስ፣ ታሪክ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አደረጃጀት ያለው ህዝብ ማለት አይደለምን? ይህ ከታወቀ ዘንዳ በኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮሞ ብሄር፣ የትግሬ ብሄር፣ የአማራ ብሄር፣ የጉራጌ ብሄር፣ የሲዳማ ብሄር፣ የወላይታ ብሄር፣ የአደሬ ብሄር፣ እንዲሁም የቱንም ያህል ቢያስከፋችሁ የሶማሌ ብሄር መኖሩን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡ ይህ ነው የኢትዮጵያ እውነተኛ ገጽታ፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያዊነት የተሰኘ በአማራው ገዥ መደብ አማካኝነት በሌሎች ብሄሮች ላይ ያለፍላጎታቸው በሃይል የተጫነ፣ በነዚህ ጭቁን አካላት ሳይቀር በየዋህነት የተገፋ የፈጠራና የውሸት ብሄራዊ ማንነት አለ:: ይህ ኢትዮጵያዊነት የተሰኘ የፈጠራ ብሄራዊ ማንነት ምንድን ነው? በቀላሉ የአማራው የበላይነት ማለት አይደለምን?”
( ዋለልኝ መኮንን ካሳ፤ “Struggle Magazine” ፤ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ፤ ህዳር 9፣ 1961 ዓ ም)
“መገንጠል በራሱ ምንም ችግር የለውም”
(Struggle, V, 2, November 1969.)
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ትውልዱ በምእራባዊያን ቀኖና ሰክሮ ያልታሰበውንና ያልታየውን የብሄር ልዩ ነትና ቅራኔ በምናቡ ፈጥሮ አለ በማለት ወደ እብደት ውስጥ የገባበትን ቅስም ሰባሪ የታሪክ ክስተት የሚያሳዩ ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ ባንጻሩ የአርቆ አሳቢነትና የብስለት ምልከታነታቸውንና ትክክለኛነታቸውን ግዜ የመሰከረላቸው የአጼው መንግስት የተለያዩ መግለጫዎችን እናነባለን:-
“ከጥቂት ዓመቶች ጀምሮ በየትም አለም ተደርጎ በማይታወቅ ልማድ በያመቱ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገና ባልተረዱትና ባላመዛዘኑት ፖለቲካንና አስተዳደርን በሚመለከት ጉዳይ በየጊዜው የሚያደርጉት እንቅስቃሴዎችና ሙከራዎች ሁሉ ለብዙ ዘመን ጸንቶ የኖረውን መሰረተ ባህልና የአንድነታችንንም ኃይል የሚያደክም ከህግና ከሥነ ሥርዓት ውጭ በሆነ መንገድ የተፈጸሙ መሆናቸውን ታውቃላችሁ፡፡ …“
(MoI Files: No.17.2.462.04, Ye’temariwoch Selamawi Self Tiyaqe.)
“እጅግ አስቸጋሪና የተወሳሰቡትን ሶሺያሊና ኢኮኖሚ ፖለቲክም ነክ የሆኑትን ጉዳዮች ትምህርትን ሳይፈጽሙ ባልበሰለ አእምሮ ባልተመዛዘነ እርምጃ ለመፍታት ሙከራ ማድረግ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በራሳቸው ባህል ሲመሩ ኑረው ወደ ዘመናዊ ለሚራመዱ ህዝቦች አደገኛ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል::”
(MoI Files: No.17.2.462.04.)
“በአጉል መንፈስ ተመርተው ህዝቡ አምኖ የተቀበለውን ሥርዓት ለመሻር፣ የቆየውንና የኖረውን ልማድ የሚያኮስስ፣ ኃይማኖትን የሚያቀል፣ አባቶችን የሚያዋርድ፣ ኢትዮጵያን በኃይማኖት በነገድና በጎሳ የሚከፋፍል፣ አንድነቱን የሚያናጋ፣ ሥርዓቱን የሚያቃውስ፣ ባህሉን የሚያራክስ፣ የህዝቡን ጸጥታና ሰላማዊ ኑሮ የሚያደፈርስ ዓላማ ይዘው ተነስተዋል፡፡“ MoI Files: No.17.2.462.04.
እነዚህ በሃምሳዎቹ፣ በስልሳዎቹና በሰባዎቹ መጀመሪያ እድሜ እርከን ውስጥ ያሉ ከርሞ ጥጃ አዛውንት ዘንድሮም ድርጅታዊ አሰራርን(በትውውቅ ብቻ አመራሮች የሚሰየሙበት፣ በጥቂት ግለሰቦች የተፈጠሩ የድርጅት መመሪያና መተዳደሪያዎች ያላንዳች ውይይት ለአባላት የሚጋቱበት ወዘተ.)፣ የሃሳብ ልዩነትን በአንጃነት ኮንኖ የማፈንን፣ ሃገር ወይም ሞት የሚለውን የአርበኞች መፈክር ድርጅቴ ወይም ሞት በሚል የጀሌነትና የተነጅ መንጋነት መፈክር በመተካት የሃገርን ጥቅም በድርጅትና ግለሰብ ፍላጎት የለወጠንና በኢትዮጵያ ለዘርፈ ብዙ የሉአላዊነትና የመልካም አስተዳደር ተግዳሮት መፈጠር መንስኤ የሆነ የግራውን አምባገነናዊ የፖለቲካ ባህል የሙጥኝ ብለው ይዘው እራሳቸውን በመሪነት የሚያጩልን የማርክሲዝም-ሌኒንዝም ምእመናን ለጥፋታችን ምክንያት በሆነው መንገድ መፍትሄ ሊያመጡ አይችሉምና ለሃገር ትንሳኤ የቀረችውን ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል ፈጽሞ ከማጨለማቸው በፊት አፍራሽ የታሪክ ቅርሳቸውን ይዘው እንዲሰበሰቡልን በዚህ ትውልድ ስም የመጠየቅና የማስጠንቀቅ ሃላፊነት አለብን።
የአማራ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ
አምደጺዮን ዘ ተጉለት

 

Source: አውጋን

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.