0

ኢህአዲግ እንዲያሸንፍ ሰማያዊን ምረጡ ( ሄኖክ የሺጥላ )

ኢህአዲግ እንዲያሸንፍ ሰማያዊን ምረጡ ( ሄኖክ የሺጥላ )

ማስታወቂያ ማለት አዲስ ነገሮችን የተለመዱ ፣ የተለመዱ ነገሮች አዲስ አምድረግ ነው ይላል ቴድ የሚባል እንግሊዛዊ የወሬ ቋት ። በሰወየው ቋንቋ ሲገለጽ ሃሳቡ ይህንን ይመስላል (advertisement is making the familiar new and the new familiar )። ስለ መጪው ምርጫ ሳስብ ፣ የመንግስታችንን ጥረት አሰብኩ ። ምርጫው ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ ይሆን ዘንድ ያደረጋቸውን ጥረተቶች አሰብኩ ። ለምሳሌ ፣ ምርጫው ፍትሃዊ ይሆን ዘንድ የነጻ ሚዲያዎችን ጥርቅም አርጎ ዘግቷል ፣ የመናገር እና የመጻፍ መብታችን በምርጫ ሰሞን ይከበር ዘንድ ጋዜጠኞችን አስሯል ( እኔ ተመስገን ደስለኝ ምሳሌዬ ናቸው )፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻ ይንቀሳቀሱ ዘንድ መኢአድን እና አንድነትን የግል ንብረቱ አድርጏል ፣ በሕገ መንግሱስቱ መሰረት ፣ ሰማያዊ ፖርቲ የጠራውን የምርጫ ስብሰባ እና ሰላማዊ ሰልፍ ለምርጫው ማማር ሲል ከልክሏል ፣ ብሎም የሰማያዊ ፣ የአንድነት ፣ የመኢአድ አባላትን በምርጫ ሰሞን ከተባራሪ ጥይት ለመጠበቅ ሲል አስቀድሞ አስሯል ፣ የውጭ ሀገር ታዛቢዎች ሀገር አቋርጠው ( አሳብረው ) የምርጫውን ሂደት ለመከታተል ከሚደክሙ ፣ ተውት አትድከሙ ብሎ መንግስት ብቻ ሳይሆን ባለ እናት አንጀት ስርዓት መሆኑን አሳይቷል ፣ ከዛ በተጨማሪ በቅርቡ ወገኖቻችን በሊቢያ ሲታረዱ ፣ በደቡብ አፍሪካ በእሳት ሲቃጠሉ ፣ በየመን በሞርታር የኮንክሪት ክምር ውስጥ ሲቀበሩ ፣ ከልቡ በማዘኑ ፣ የዜጎቹ ሞት ከልማቱ እንደማያደናቅፈው ተናግሯል ።

በይበልጥ ከሁሉም በላይ ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የ 6 ደቂቃ የአየር ሰዓት በመፍቀድ ፣ ቸርና ዲሞክራቲክ መንግስት መሆኑን ብቻ ሳይሆን በዛ በረጅም ስድስት ደቂቃ ውስጥ ለሀገራቸው ምን መስራት እንዳሰቡ ለሚመርጣቸው ሕዝብ ማንነታቸውን ያስተዋውቁ ዘንድ የፈቀደ መንግስት ነው ። ለምሳሌ ኣንዳንድ የሰማያዊ ፖርቲ ሰዎች ( ኣባሎች )በተሰጣቸው የ ፮ ደቂቃ የኣየር ጊዜ የረኩ ኣይመስለም ። ያልገባቸው ኣብዛኛው የኢኣዲግ ሰዎች የመጽሃፍ ቅዱስን ኦሪት ዘ ፍጥረት ጋ እያሉ ነው ኣቁመው ጫካ የገቡት ። በዚህም ጥልቅ እውቀታቸው እግዚያብሄር ሰማይና ምድርን ለመፍጠር ፯ ቀን ኢንደፈጀበት ያውቃሉ ። ታዲያ ሰማይና ምድርን ለመፍጠር ሰባት ቀን ከፈጀ ፣ ለምርጫ ማስተቃወቂያ ፮ ደቂቃ የዘላለም ያህል ረጅም ነው ብለው ኣስበው እና ተጨንቀው ያደረጉት ነገር ነው ። በደርግ ጊዜ ቢሆን ስድስት ደቂቃ አይደለም ስድስት ሴኮንድ ማን ይሰጥሃል ። አንድ ነገር ልናገር ብትል ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ነው የምትሄደው ። እንዴ በደርግ ጊዜ እኮ ወጣቱ በውትድርና ነበር የሚያልቀው ፣ እና ውትድርና የፈራ ወጣት በአብዛኛው አልጋ ስር እና ቁም ሳጥን ውስጥ ነበር መዋያ ማደሪያው ። በኢህአዲግ ጊዜ ግን ውትድርና ብሎ ነገር የለም ። በአምስት ዓመት የልማት መርሃ ግብሩ መሰረት መንግስታችን ውትድርናን በግርድና ቀይሮልናል ። ቁም ሳጥን ውስጥ ከመደበቅ ፣ አልጋ ስር ከመግባት ወጥተን ዛሬ ባህር ውስጥ ነው የምንገባው ። የመንግሥታችን ውለታ ብዙ ነው ። እኛንም ታዲያ ውለታ መላሽ ያድርገን ።

አዎ በደርግ ጊዜ እድገት በህብረት ዘመቻ ተብሎ ፣ የተማሩ ወጣቶች ወገኖቻቸውን ለማስተማር በአራቱም አቅጣጫ ተገደው ተመው ነበር ። ዛሬ ግን ከአራቱ አቅጣጫ ዘርህን ፈልገህ ባንዱም በኩል መውጣት እስከምያቅትህ ሀገርህ በራሽ ላይ ተደፍናለች ። ይህ ደሞ የልማታዊ መንግስታችን ብሔር ተኮር ፣ ገጠር መር እና ሕዝብ መረር ሥራ ውጤት ነው ። በእርግጥም መንግስታችን ባለውለታችን ነው ።

ኢህአዲግ ባይኖር ኖሮ እንዲህ እንደፈለግን ይርበን ነበር ? ልማታዊ መንግሳትችን በዋለልልን ውለታ እና ኢኮኖሚው በዓመት 11% ለ 24 ዓመት በማደጉ አይደለም እንዴ ዛሬ አንድ በግ 4000 ብር የሚሸጠው ። በአምባገነኖችና ፍውዳሎቹ ዘመን ( ለምሳሌ በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ሰሜን አንድ በግ 7 ብር ይሸጥ ነበር አሉ ) እንግዲህ እግዜር ያሳያችሁ በግን የሚያል ነገር ዋጋውን እንደዚህ አርክሰው በስጋው ሲጫወቱ የነበሩት እነዚህ አማሮች ናቸው ። ለዚህ እኮ ነው አማራ ተመልሶ ስልጣን ላይ አይወጣም ፣ ምክንያቱም የበጎችን ውድ ሆኖ የመኖር አደራ ተቀብለን ለማስፈጸም ቃል ስለገባን ።

በምድር ላይ እንደ ኢሃዲግ ለቆዳችን የሚጨነቅ ፤ ላይናችንን የሚሳሳ መንግስት ይኖር ይሆን ፧ ይህንንም ስል ለምሳሌ ውሃን በማጥፋት በወር ኣንዴ ገላችን እንድንታጠብ ያደረገ መንግስት ነው ። የኣምፖል ብርሃን ኣይናችንን እንዳያጠፋው ኤሌትሪክ ኢንዳይኖር በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ የትራኮማ በሽታን ያጠፋ መንግስት ነው ። ከሁሉም በላይ በኣምስት ኣመቱ መርሃ ግብር መሰረት ፣ ሳንባችንን ንጹህ ኣየር ኣሸክመን ከምናስጨንቀው ሺሻ በማጨስ የተለየ ኢና ልማታዊ ኣየር ኢንዲስብ ያድረገ መንግስት ማን ነው ? ለምሳሌ በቅርቡ ወገኖቻችን በሊቢያ ሲታረዱ ወደ ሃዘን ዘለን ኢንዳንገባ የተፈለገው ፣ ያኔ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያረፉ ሰሞን ደረታችንን እንደዚያ ስንደቃ ስላየ ኢጅግ ኣዝኖ ፣ ይህ ነገር ቢደገም ብዙ ሰው ደረቱን ሊያጣ ኢንደሚችል ኣስቦ ነው ።

አሁን ኢህአዲግ ለኛ የዋለልን ውለታ ተቆጥሮ ይጨረሳል ? ለምሳሌ የባህር በር እንዳይኖረን ያደረገው ፣ የወባ በሽታ እንዳያጠቃን አስቦ ስለመሆኑ ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን ? በምትኩ አሰብን አንፈልግም ብሎ ፣ በየሰፈሩ ውሃ ማቆር የሚል ፕሮጀክት ነድፎ ህብረተሰቡ ለባህር በር ያለውን ፍቅር በጉድጏድ ውሃ ይቀይር ዘንድ እጅግ ዘናጭ በሆነ መንገድ ታች ድረስ ወርዶ ያስረዳ ስርዓት ነው ። ለምሳሌ አደገኛ ቦዘኔዎች ወደ ልማታዊነት እንዴት እንደሚቀየሩ አስቦና ሃሳቡን ወደ ተግባር ቀርጾ መንገዶችን በኮብል ስቶን ለመደልደል በሚደረግ ዘመቻ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ፣ ከዚህም ተሳትፎ ትምህርት በመቅሰም ከትላልቅ የትምህርት ተቋማት የተመረቁት ሳይቀር በድንጋይ ፈላጭነት እንዲሰሩ ፣ እጅግ ያማረ የስራ ዕድል በመፍጠር ፣ የወጣቱን ጥያቄ ያሟላ ስርዓት ነው ።

አሁንም ቀጣዩ ምርጫ እጅግ ፍትሃዊና ፣ ሚዛናዊ ይሆን ዘንድ ፣ እያጣረ ይገኛል ። ምናልባት እስካሁን የተደረጉት እና ከላይ የገለጽኳቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው የኢህአዲግ የመጨረሻ ሰዓት የምርጫ ቅስቀሳ ” ኢህአዲግ እንዲያሸንፍ ሰማያዊን ምረጡ” የሚል እንደሆነ ስገልጽ ፣ በአብዮታዊ ድሞክራሲ እና በአምስት ለአንድ ደስታ ውስጥ ሆኘ ነው ።

ቸር እንሰንብት ( ሄኖክ የሺጥላ )

Source: Henok Yeshitla fb

Filed in: Amharic News, eMedia, News, Politics & Openion

Recent Posts

Leave a Reply

You must be Logged in to post comment.

© 2019 Moresh Information Center. All rights reserved.